በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ ደረሰ- የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

ሰባተኛ ሳምንቱን በያዘው የጋዛው ጦርነት በእስራኤል የተቀናጁ ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከነዚህም ውስጥ 70 በመቶዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል እግረኛ ጦሯን በጋዛ ካሰማራች ጀምሮ የሞቱ ወታደሮቿ ቁጥር 44 መድረሱን አስታወቀች

    በሰሜን ጋዛ በሚካሄደው ጦርነት ከተገደሉ የእስራኤል ወታደሮች መካከል የአንዱ ጓደኞች እና ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ሲገልጹ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል መከላከያ ሰኞ ዕለት ሁለት ተጨማሪ ወታደሮቹ በሰሜን ጋዛ ጦርነት ምክንያት እንደሞቱበት አስታወቀ።

    እንደ እስራኤል ሚዲያ ዘገባ ከሆነ እስራኤል ጦሯን ወደ ጋዛ ካሰማራች ጀምሮ የሞቱት ወታደሮቿ ቁጥር 44 ደርሷል።

    የእስራኤል ጦር ኃይል በምዕራብ ጋዛ ከተማ በሚገኘው አል ሻቲ የስደተኞች መጠለያ አካባቢ የሚያካሄደውን ማጥቃት እንደቀጠለ ተናግሯል።

    እስራኤል በጋዛ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው ሐማስ መስከረም 26 በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ200 በላይ ታግተው መወሰዳቸውን ተከትሎ ነው።

    በሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስትር እንዳስታወቀው በጋዛ እስካሁን ድረስ 11 ሺህ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም 4ሺህ 500ዎቹ ሕጻናት ናቸው።

  2. ቱርክ ከራፋ ድንበር አቅራብያ ስምንት የመስክ ሆስፒታሎች ልትገነባ ነው

    ጄኔሬተሮች፣ አምቡላንሶች፣ እንዲሁም የሕክምና ቁሳቁሶች የጫነች መርከብ ሰኞ ዕለት በግብጹ አል አሪሽ ወደብ መድረሷ ተሰምቷል።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለመስክ ሆስፒታል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን የጫነች የቱርክ መርከብ ለራፋ ድንበር አቅራብያ በሚገኝ የግብጽ ወደብ ላይ መድረሷ ተሰማ።

    መርከቧ ላይ ጄኔሬተሮች፣ አምቡላንሶች፣ እንዲሁም የሕክምና ቁሳቁሶች የሚገኙ ሲሆን ዕቅዱ ስምንት የመስክ ሆስፒታሎችን መገንባት መሆኑን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

    መስከረም 26 በሐማስ እና እስራኤል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ እንዲህ ዓይነት እርዳታ ግብጽ ሲደርስ የመጀመርያው ነው።

    የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ ከተማ የሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል “አገልግሎት መስጠት አቁሟል” ሲል መናገሩ ይታወሳል።

    ሌሎች የሕክምና ተቋማትም በተመሳሳይ ነዳጅ እና የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ እንዲሁም በዙሪያቸው የሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ለደህንነታቸው አስጊ በመሆኑ ስራ ያቆሙ መሆናቸው በተለያዩ አካላት ተገልጧል።

    የቱርክ የጤና ባለሥልጣን ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት አናካራ ከግብጽ ባለስልጣናት በአል አሪሽ የመስክ ሆስፒታሎች ለመገንባት ይሁንታን አግኝታለች።

    የሚገነቡት ሆስፒታሎች ከራፋህ ድንበር 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ይሆናል።

  3. በሰሜን ጋዛ በሚገኙ ቁልፍ የሕክምና ተቋማት የተከሰተው ምንድን ነው?

    እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ 22 ሆስፒታሎችን ጨምሮ፣ 36 የሕክምና ተቋማት ወድመዋል

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎች እና የሕከምና ተቋማት እስራኤል ሐማስ ላይ በከፈተችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የተነሳ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል።

    የበርካቶች ዋናው ትኩረት በትልቅነቱ ቀዳሚ በሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል ነው።

    በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ከ2ሺህ 300 በላይ ሰዎች በሆስፒታሉ አቅራብያ በሚካሄዱ ግጭቶች የተነሳ መላወስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

    በሌሎች የሕክምና ተቋማት ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።

    የኃይል አቅርቦት እና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት በሆስፒታሎቹ ሕክምና ለማግኘት የሚጠባበቁ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎታል።

    እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ 22 ሆስፒታሎችን ጨምሮ፣ 36 የሕክምና ተቋማት ወድመዋል።

    በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው በስራ ላይ ያሉት።

    እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መግለጫ ከሆነ በጋዛ ከተማ የሚገኘው እና 700 አልጋዎች ያሉት ትልቁ ሆስፒታል አል-ሺፋ አገልግሎት መስጠት አቋርጧል።

    ጤና ድርጅቱ አክሎም በሆስፒታሉ ውስጥ ያለውን ሁኔታ “ አሰቃቂ እና አደገኛ” ሲል ጠርቶታል።

    በሆስፒታሉ ዙርያ የሚገኙ መንገዶች በሐማስ እና በእስራኤል ኃይሎች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች እየተናጡ ነው።

    እንደ ተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ ወሳኝ የሚባሉ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።

    የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሞትን አልያም ጉዳትን ሳይጋፈጡ ከሆስፒታሉ መውጣት የሚታሰብ አይደለም።

    እንደ ፍልስጤም ቀይ ጨረቃ መረጃ ከሆነ በጋዛ ሰርጥ የሚገኘው እና ከአል -ሺፋ በመቀጠል ሁለተኛ የሆነው አል-ቁድስ ሆስፒታል ስራውን አቋርጧል።

    የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ቅዳሜ ዕለት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የሆስፒታሉ ሰራተኞች ከ500 ሕሙማን እና ከ14 ሺህ ተፈናቃዮች ጋር መላወሻ አጥተው ይገኛሉ።

    ቅዳሜ ዕለት ሆስፒታሉ በነዳጅ አቅርቦት አለመኖር እና የኤሌትሪክ ኃይል በመቋረጡ የተነሳ አገልግሎት መስጠት ማቋረጡ ይፋ ተደርጓል።

    ድንበር የለሽ የሐኪሞች ማህበር ቅዳሜ ዕለት፣ በሆስፒታሉ የሚሰራ እና ከእነ ቤተሰቡ የተጠለለ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡን እና አሁን ስላለበት ሁኔታ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቆ ነበር።

    በሰሜን ጋዛ ከተማ የሚገኙት ለሕጻናት ሕክምና የሚሰጠው ራንቲሲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በአቅራብያው የሚገኘው አል-ናስር ሆስፒታል ያሏቸውን ሕሙማን እና ሠራተኞቻቸውን ለማትረፍ ለቅቀው እንዲወጡ የተደረገው አርብ ዕለት ነበር።

    ራንቲሲ በጋዛ ከተማ የሕጻናት ካንሰር ሕክምና የሚሰጥ ብቸኛው ተቋም ነበር።

    የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ ቅዳሜ ዕለት በምዕራብ ጋዛ የሚገኘው የስዊዲሽ ክሊኒክ “በአየር ድብደባ መመታቱን እና መውደሙን” ይፋ አድርጓል።

    በክሊኒኩ 500 ሰዎች የተጠለሉ መሆናቸውን እና ስለደረሰው ጉዳት ይፋዊ መረጃ አለመኖሩንም በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

  4. የአውሮጳ ሕብረት በጋዛ 'ተጨባጭ የሆነ' የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቀ

    የአውሮጳ ኮሚሽን ከፍተኛ ባለስልጣን ዣኔዝ ሌናርሲስ

    የፎቶው ባለመብት, OLIVIER HOSLET/EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የአውሮጳ ሕብረት በጋዛ የሚካሄደው ውግያ 'ተጨባጭ የሆነ" የተኩስ አቁም ተደርጎ ሆስፒታሎች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የነዳጅ አቅርቦት መዳረስ እንዳለበት ገለጸ።

    የአውሮጳ ኮሚሽን ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት፣ ዣኔዝ ሌናርሲስ፣ ሰኞ ዕለት በብራሰልስ በተካሄደ ስብሰባ ላይ "በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሆስፒታሎች በዋናነት በነዳጅ አቅርቦት አለመኖር ምክንያት ስራ አቁመዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

    "የተኩስ አቁሙ ተጨባጭ መሆን አለበት" በማለት አክለዋል ሌናርሲስ።

    " በመጀመርያ ድርጅቶች በአግባቡ ስራቸውን እንዲያቅዱ በቅድሚያ መነገር አለበት። በመቀጠል ደግሞ ከጊዜ አንጻር በሚገባ መቀመጥ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

    ሐማስ ጥቃት ከከፈተበት መስከረም 26 ጀምሮ ነዳጅ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዳይገባ ታግዷል።

    የአውሮጳ ሕብረት አባል አገር የሆኑ 27 አገራት እሁድ እለት "አስቸኳይ የሰብዓዊ ተኩስ አቋም" አንዲደረግ የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን ሐማስ የሕክምና ተቋማትን እና ሰላማዊ ሰዎችን "እንደ ሰብዓዊ መከላከያ" መጠቀሙንም አውግዘዋል።

    ባለፈው ሳምንት አሜሪካ፣ እስራኤል በየዕለቱ ለአራት ሰዓታት ያህል ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን አንድታቋርጥ ጠይቃ ነበር።

  5. የተባበሩት መንግሥታት ከ100 በላይ ሰራተኞቹ በጋዛ እንደተገደሉበት አስታወቀ

    የተባበሩት መንግሥታት ሰንደቅ ዓላማ

    የፎቶው ባለመብት, UN

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ100 በላይ ሰራተኞቹ በጋዛ እንደተገደሉበት አስታወቀ። ህይወታቸውን የተነጠቁትን ሰራተኞቹን ለማስታወስ እና "ክብሩንም ለመግለጽ" በዛሬው ዕለት ሰንደቅ ዓላማው ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ብሏል።

    እስራኤል በጋዛ ላይ የቦምብ ጥቃት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የተገደሉ ሰራተኞች ከመቶ በላይ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች የእርዳታ ኤጀንሲ አስታውቋል።

    በየትኛውም ጦርነት የዚህን ያህል ቁጥር ያለው የተቋሙ ሰራተኞች ተገድለው እንደማያውቁም ተገልጿል። የሰራተኞቹ ሞት በተባበሩት መንግሥታት ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

    የተገደሉት የተመድ ሰራተኞች በጋዛ ውስጥ ከሚሰሩት 13 ሺህ ሰራተኞች መካከል ሲሆን ብዙዎቹም የተገደሉት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መሆኑን ተመድ ገልጿል።

    ከተገደሉት መካከል መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የማህጸን ሐኪም፣ መሐንዲሶች፣ የስነ ልቦና ባለሙያ እና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችም ይገኙበታል።

    ተቋሙ በጋዛ ሰርጥ ዙሪያ ከ150 በላይ ባሉ ማዕከላቱ ከ780 ሺህ ህዝብ በላይ እያስተናገደ ይገኛል።

    እነዚህ መጠለያዎችም በጋዛ በሚደረገው ጦርነት ጉዳት ደርሶባቸዋል። እስካሁን ድረስ 60ዎቹ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አስሩ በቀጥታ ጥቃት የተፈጸመባቸው መሆኑንም ተመድ ገልጿል።

  6. የእስራኤል መከላከያ በአል ሻቲ የስደተኞች መጠለያ ወረራ መፈጸሙን አስታወቀ

    የእስራኤል ጦር ከጋዛ ከተማ በስተምዕራብ በምትገኘው አልሻቲ የስደተኞች መጠለያ ላይ ድንገተኛ ወረራዎች ማካሄድ መቀጠሉን አስታውቋል።

    እስራኤል የምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ አል ቁድስ ዩኒቨርስቲ እና አቡበከር መስጊድን ያጠቃልላል።

    እነዚህ ስፍራዎች ሐማስ የሚንቀሳቀስባቸው ናቸው በማለት እንደሆነም ተገልጿል። በነዚህ ወረራዎች የተያዙ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ወታደራዊ ቁሶችን ፎቶዎች ለቢቢሲ አጋርቷል።

    በተጨማሪም ስሙ ያልተገለጸ የእስላሚክ ጂሃድ ታጣቂ አባል መኖሪያ ቤትም በተፈጸመው ድንገተኛ ወረራ የጦር መሳሪያ ተይዟል ተብሏል።

    እስራኤል የጋዛ ከተማ ከምትገኝበት ሰሜናዊ ጋዛ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ከምትፈጽመው የማያባራ የአየር ጥቃት በተጨማሪ እግረኛ ጦሯን ካስገባች ሳምንት አልፏል።

  7. የአል ሺፋ ሆስፒታል ሶስት ነርሶች መገደላቸውን ተመድ አስታወቀ

    የአል ሺፋ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አል ሺፋ አቅራቢያ የማያባሩ የአየር ጥቃቶች እና ውጊያዎች ተከትሎ ሶስት ነርሶች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

    የሆስፒታሉ ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች መጎዳታቸውን ያስታወቀው ተመድ የኦክስጂን ማመንጫ፣ የውሃ ማጠራቀሚያ እና ጉድጓድ፣ የልብ እና የእናቶች ማቆያ ክፍል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

    እስራኤል በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ መሬት ውስጥ ሐማስ እንደ ማዕከል ይጠቀምበታል በማለት የምትከስ ሲሆን ሐማስ ይህንን ውንጀላ አይቀበለውም።

    የሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ኃላፊ ዶክተር ማርዋን አቡ ሳዳ ሐማስ አል ሺፋን እየተጠቀመበት እንደሆነ ተጠይቀው ውንጀላውም "ፍጹም ሐሰት ነው" ብለዋል።

    "እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን። እኔ የቀዶ ሐኪም ነኝ። ሐኪሞች የስራ ባልደረቦች አሉን። ታማሚዎች እንዲሁም ተፈናቃዮች የተጠለሉ አሉ። ሌላ ምንም የለም" ሲሉም ተናግረዋል።

    በቅርብ ቀናት በሰሜን ጋዛ የሚገኘው አል ሺፋ አቅራቢያ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን እስራኤል ሆስፒታሉ ላይ ጥቃት ፈጽማለች ተብሏል።

    የእስራኤል ጦር በሆስፒታሉ አካባቢ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ቢገልጽም በተቋሙ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስተባብሏል።

  8. ኔታንያሁ የእስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቀ 'ስምምነት ሊኖር እንደሚችል' ተናገሩ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በመስከረም 26ቱ ጥቃት የተወሰዱ 240 የሚገመቱ የእስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቅ ስምምነት ሊኖር ይችል እንደሆነ ተጠይቀዋል።

    "ስምምነት ሊኖር ይችላል" ሲሉም ለአሜሪካ የቴሌቪዥን ኔትወርክ ኤንቢሲ ተናግረዋል።

    "ስለ ጉዳዩ ትንሽ ነገር በተናገርኩ ቁጥር የመፈጸሙን እድል የበለጠ እጨምራለሁ" ብለዋል። ኔታንያሁ ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ቢቆጠቡም ስምምነቱን ሊያስገድድ የሚችለውን አንድ ነገር "የመከላከያ ሰራዊቱ በሐማስ ላይ እያሳደረ ያለው ወታደራዊ ጫና ነው" ብለዋል።

    ነገር ግን አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ ባለስልጣን ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ግጭቱ መገታት እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ሁሉም ታጋቾች እስካልተለቀቁ ድረስ የተኩስ አቁም እንደማይኖር በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል።

  9. አሜሪካ በሶሪያ በሚገኙ የኢራን ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃቶች ፈጸመች

    አሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    አሜሪካ በደቡብ ምስራቅ ሶሪያ በሚገኙ ሁለት የኢራን ጦር ሰፈሮች ላይ የአየር ጥቃቶች መፈጸሟን አስታወቀች።

    አሜሪካ በቅርቡ በሶሪያ እና ኢራቅ ባሉ ወታደሮቿ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎም እነዚህን ጥቃቶች መፈጸሟን ገልጸላች።

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ጥቃቶቹ የተፈጸሙት "የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ እና ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች በሚጠቀሙባቸው ስፍራዎች ላይ ነው" ብለዋል።

    "ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በአቡ ከማል እና ማያዲን ከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ የስልጠና ተቋም እና ማዕከል መሆኑንም" ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

    "ፕሬዚዳንቱ ከአሜሪካ ሰራተኞች ደህንነት የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር የለም። አሜሪካ ራሷን ለመከላከል፤ የሰራተኞቿን እና ጥቅሞቿን ለማስከበር ግልጽ ለማድረግም የዛሬው እርምጃ እንዲከናወን ትዕዛዝ ሰጥተዋል" ብለዋል።

    ረቡዕ ዕለት አሜሪካ በምስራቅ ሶሪያ በሚገኘው ማይሱሉን ግዛት በኢራን እና የኢራን አጋሮች ናቸው ባለቻቸው ቡድኖች የሚጠቀሙበት የጦር መሳሪያ ማከማቻ እንደሆነ በገለጸችው ስፍራ "ራስን የመከላከል ጥቃት" ጀምራለች ተብሏል።

  10. በአል ሺፋ ሆስፒታል ከ2 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን አሉ- የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

    የጋዛ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    መብራት እና ውሃ በተቋረጠበት የጋዛው ትልቁ ሆስፒታል አል ሺፋ ቢያንስ ከ2 ሺህ 300 በላይ ፍልስጤማውያን እንዳሉ የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የዓለም የጤና ድርጅት በሐማስ የሚመራውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ዋቢ በማድረግ አኃዙን በኤክስ ገጹ አስፍሯል።

    በሆስፒታሉ ውስጥ ከ600- 650 የሚደርሱ ታማሚዎች፣ ከ200- 500 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች እና 1 ሺህ 500 የሚሆኑ መጠለያ የሚሹ ተፈናቃዮች እንዳሉም ተገልጿል።

    በሆስፒታሉ መብራት እና ውሃ በመቋረጡ እንዲሁም ምግብ ባለመኖሩ "የበርካቶችን ህይወት በአደጋ ላይ ጥሏል" ብሏል።

    የዓለም ጤና ድርጅት በሆስፒታሉ ያለው ሁኔታ አስከፊ መሆኑን ገልጸ 'አስቸኳይ የተኩስ አቁም' እንዲደረግ እና ሰላማዊ ነዋሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስቧል።

  11. በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ያለው ሁኔታ አስከፊ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ገለጹ

    ጨቅላ ህጻናት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    መብራት እና ውሃ የተቋረጠበት የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ሁኔታ አስከፊ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ።

    ከመብራት በተጨማሪ ምግብ፣ እና መድኃኒት እየተመናመነ ሲሆን በጨቅላ ማሞቂያ ያሉ ህጻናትም በሞት አፋፍ ላይ ናቸው ተብሏል። እስካሁንም ሶስት ህጻናት ሞተዋል።

    በሆስፒታሉ አቅራቢያ "የማያባራ ተኩስ እና የአየር ጥቃት እየተፈጸመ" ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያለውን ሁኔታ የበለጠ እንዳከፋውም ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል።

    አልሺፋ እንደ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠትም አቁሟል ብለዋል። የእስራኤል ጦር ሆስፒታሉን በከበባ ውስጥ አስገብቷል መባሉን ያስተባበለ ሲሆን በማሞቂያ ውስጥ ያሉ ጨቅላዎችን ወደ ሌላ ሆስፒታል ለማዛወርም እገዛ አደርጋለሁ ብሏል።

    ለሆስፒታሉ የኤሌክትሪክ አግልግሎት በፍጥነት ካልተለቀቀ ሁሉም ሊሞቱ እንደሚችሉ የአል ሺፋ ቀዶ ህክምና ኃላፊ ዶ/ር ማርዋን አቡ ሳዳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ የሐማስ ዋና ጽህፈት ቤት በአል ሺፋ ሆስፒታል ስር ነው የሚለውን ውንጀላ ደግመው ተናግረዋል። ሐማስ በበኩሉ ሆስፒታሉን ለወታደራዊ አገልግሎት እየተጠቀመበት ነው የሚለውን ክስ አልተቀበለውም።

    ዶክተር አቡም የእስራኤልን ውንጀላ "ፍጹም ሐሰት" ነው ያሉ ሆን በአቅራቢያው ያሉት ሐይሎች መጥተው ፍተሻ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    በሆስፒታሉ ውስጥ ህመምተኞችና የተጠለሉትን ጨምሮ 2 ሺህ 300 ፍልስጤማውያን እንዳሉ የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

  12. የጋዛ ታሪኮች፡ “ስንሞት ማንም አያውቅም”

  13. በእስራኤል ጋዛ የተከሰቱ የቅርብ ጉዳዮች

    አል ሺፋ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    • የእስራኤል ጦር በጋዛ ትልቁ የሆነውን የአል ሺፋ ሆስፒታሉ ከበባ ውስጥ አስገብቶታል መባሉን ያስተባበለ ሲሆን በአቅራቢያው ግን የተፋፋመ ውጊያ መኖሩን አምኗል። በሆስፒታሉ ምስራቃዊ ክፍል በኩልም ታማሚዎችና የተጠለሉ ፍልስጤማውያን መውጣት ይችላሉ ብሏል። ጦሩ በአል ሺፋ ላይ ጥቃት ፈጽሟል ቢባልም ይህንንም አልተቀበለውም። አል ሺፋ ሆስፒታል ውሃ እና መብራት በመቋረጡ እንዲሁም የህክምና ግብዓት እጦት ምክንያት ሆስፒታሉ ተዘግቷል።
    • እስራኤል ሐማስ በሆስፒታሉ ስር ያሉ ዋሻዎችን እንደ ማዘዣ ማዕከል ይጠቀማል ስትል የምትከስ ሲሆን ሐማስ ይህንን አይቀበለውም።
    • ዓለም አቀፍ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች የማያባራ የቦምብ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል አስጠንቅቋል።
    • በአል ሺፋ ሆስፒታል በጨቅላ ማሞቂያ ውስጥ የነበሩ ሁለት ህጻናት መሞታቸውን ተከትሎ ለሆስፒታሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በፍጥነት ካልተለቀቀ ሁሉም ሊሞቱ እንደሚችሉ በዚያ የሚገኙ ሐኪሞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
    • ቢቢሲ 20 የሚሆኑ ጨቅላ ሕጻናት ምስሎች ደርሰውታል። በማሞቂያ ውስጥ መሆን የሚገባቸው ህጻናት በአዋቂዎች አልጋዎች ላይ ይታያሉ።
    • እስራኤል ጨቅላዎቹን እንዲወጡ ለማድረግ አግዛለሁ ብትልም ለአልሺፋ ሆስፒታል ሰራተኞች የሰጠችው ዝርዝር መረጃ የለም።
    • በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በሰሜናዊ ጋዛ ከቀጠለው የእስራኤል የተቀናጀ ጥቃት ለማምለጥ ከሰሜን ጋዛ ወደ ደቡብ ጋዛ መሸሻቸውን ቀጥለዋል።
    • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ጥሪን ውድቅ በማድረግ ሐማስ እስኪጠፋ እና ታጋቾቹ እስኪለቀቁ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ብለዋል።
  14. በአልሺፋ ሆስፒታል ጨቅላ ማሞቂያ ውስጥ ያሉ ሕጻናት በሞት አፋፍ ላይ ናቸው ተባለ

    በአልሺፋ ሆስፒታል ጨቅላ ማሞቂያ ውስጥ ያሉ ሕጻናት

    በጋዛ የሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል አል ሺፋ ሆስፒታል መብራት በመቋረጡ ጨቅላ ማሞቂያ ውስጥ ያሉ ህጻናት በሞት አፋፍ ላይ ናቸው ተብሏል።

    እስራኤል በአየር እና በመሬት አቀናጅታ በቀጠለችበት ጋዛ የሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል ውሃ እና መብራት በመቋረጡ እንዲሁም የህክምና ግብዓት እጦት ምክንያት ሆስፒታሉ ተዘግቷል። መብራት በሆስፒታሉ በመቋረጡ በማሞቂያ ውስጥ ያሉ ሁለት ህጻናት ሞተዋል።

    37 ሌሎች ጨቅላዎችም በሞት አፋፍ ላይ እንደሆኑም ተነግሯል። እስራኤል በበኩሏ በአል ሺፋ ሆስፒታል የሚገኙ ሕጻናት ወደ ሌላ ሆስፒታል ቢወሰዱ መልካም ነው ስትል መክራለች።

    እስራኤል ጨቅላዎቹን እንዲወጡ ለማድረግ አግዛለሁ ብትልም ለአልሺፋ ሆስፒታል ሰራተኞች የሰጠችው ዝርዝር መረጃ የለም።

    የሆስፒታሉ ቀዶ ጥገና ኃላፊ በበኩላቸው መብራት ከመቋረጡ በፊት በጋዛ ያሉ ሌሎች ሆስፒታሎች ጨቅላዎችን ለመንከባብ የሚያስችል መሳሪያም ሆነ ሙያተኞች የሉም ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ቢቢሲ 20 የሚሆኑ ጨቅላ ሕጻናት ምስሎች ደርሰውታል።

    ጨቅላዎቹ የሚገኙት በአል ሺፋ የቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ እንደሆነና ለሆስፒታሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በፍጥነት ካልተለቀቀ ሁሉም ሊሞቱ እንደሚችሉ በዚያ የሚገኙ ሐኪሞች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከሆስፒታሉ የሚወጡ መረጃዎች አስጨናቂና የሚያውኩ ሆነዋል።

    በተለይ በቅርብ ጊዜ ቀዶ ጥገና አድርገው ያልዳኑ ታማሚዎችና ሕጻናት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።በሆስፒታሉ ታማሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ጦርነትን ሸሽተው የተጠለሉ በርካታ ፍልስጤማዊያን ይገኙበታል።

  15. ተመድ በጋዛ የሚገኘው ቢሮው ጥቃት እንደደረሰበት አስታወቀ

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ ከተማ ከሚገኙት ቢሮዎች አንዱ ትናንት ምሽት በነበረው ውጊያ ጥቃት እንደደረሰበት አስታወቀ።

    በስፍራው ተጠልለው የነበሩ ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ እና የተጎዱም እንዳለ አስታውቋል።

    “ይህ በየትኛውም መንገድ ፍጹም ስህተት ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) አስተዳዳሪ አቺም ስቴይነር በትዊተር ገጻቸው አስታውቋል።

    “ሰላማዊ ዜጎች፣ የነዋሪዎች መሰረተ ልማቶች እና እና የተባባሩት ተቋማት የማይጣሱ መሆን አለባቸው። ሁልጊዜም ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል።

    እስራኤል በአየር እና በመሬት አቀናጅታ በቀጠለችው የጋዛ ጥቃት በርካታ ሆስፒታሎች እንደተጠቁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ። በጋዛ ከተማ ከሚገኘው ሺፋ ሆስፒታል ለመሸሽ የሞከሩ ነዋሪዎች፣ ህመምተኞች እና ሰራተኞችም እንደተተኮሰባቸውም ሪፖርት መድረሱንም ተመድ ገልጿል።

  16. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር በለንደን ሰልፍ ላይ የተከሰተውን ነውጥ አወገዙ

  17. የእስራኤል መከላከያ ቤይሩት የጋዛ እጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል ሲል ሄዝቦላህን አስጠነቀቀ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የሊባኖሷ መዲና ቤይሩት የጋዛ እጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል ሲሉ ሄዝቦላህን አስጠነቀቁ።

    የእስራኤል አየር ኃይል በእስራኤል ሊባኖስ ድንበር ላይ እያንዣበበ መሆኑን ገልጸው ጦርነቱን ለሚያባብስ ማንኛውም ተግባር ጦሩም ተዘጋጅቷል ብለዋል።

    "የሊባኖስ ዜጎች የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ ስህተት ከፈጸመ የቤይሩት እጣ ፈንታ እንደ ጋዛ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አለባቸው" ሲሉም ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ሄዝቦላህን ያስጠነቀቁ ሲሆን "ጦርነት በመጀመር ስህተት አትፈጽሙ" ብለዋል።

    ሄዝቦላህ ጦርነት ከከፈተ "የሊባኖስን እጣ ፈንታ የሚወስን ነው" ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

  18. በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ሥራ ለማቆም ተቃርቧል

  19. በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከሰሜን ጋዛ መሸሻቸውን ቀጥለዋል

    የጋዛ ሰርጥ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል ከማያባራ የአየር ጥቃት በተጨማሪ የእግረኛ ጦሯን በጋዛ ሰርጥ ውስጥ አስገብታለች።

    ጦሩ ከመግባቱም በፊት ቢሆን በሰሜን ጋዛ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሸሽተው እንዲወጡ ማስጠንቀቋን ተከትሎም በርካቶች ተፈናቅለዋል።

    አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ጥቃቱን በመፍራት ወደ ደቡባዊ ጋዛ እየሸሹ ይገኛሉ።

    የጋዛ ሰርጥ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የጋዛ ሰርጥ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የጋዛ ሰርጥ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  20. እስራኤል በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ላይ ጥቃት ፈጽማለች መባሏን አስተባበለች

    የጋዛ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ ሰርጥ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ላይ ጥቃት ፈጽሟል መባሉን አስተባበለ። ነገር ግን በአካባቢው ከሐማስ ተዋጊዎች ጋር "ውጊያ" እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

    የሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ሐኪም ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጽኑ ህክምና ክፍሉ በጥቃቱ እንደተመታ እንዲሁም ኤሌክትሪክ መቋረጡንና እና ውሃ እና ምግብ አልቋል ብለዋል።

    የህክምና ባለሙያዎች ሁለት ህጻናት መሞታቸውን እንዲሁም 37 ለጉዳት መጋለጣቸውን መናገራቸውን ተከትሎ እስራኤል ህጻናቱን "ደህንነቱ ወደተጠበቀ ሆስፒታል" ለማስወጣት እንደምታግዝ ገልጻለች።

    እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን የስደተኞች መጠለያ ላይ በፈጸመችው ወረራ የተገደሉ 11 ፍልስጤማውያን የቀብር ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

    የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለውን በቤይሩት ልትደግመው እንደምትችል ለሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ አስጠንቅቋል።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ሊባኖስን ወደ ጦርነት ሊጎትታት ይችላል ሲሉ ዮአቭ ጋላንት ተናግረዋል።

    ከ36 ቀናት በፊት ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ተገድለዋል። እስራኤል ከአየር ጥቃት በተጨማሪ የእግረኛ ጦሯን በጋዛ ሰርጥ ውስጥ አስገብታለች።

    በአየር እና በመሬት ጥቃቶች እንዲሁም ከባሕር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን በማቀናጀት ጋዛን እያጠቃች እንደሆነ ጦሯ አስታውቋል። በእነዚህም ጥቃቶች ከ11 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም 4 ሺህ 500 በላይ ህጻናት መሆናቸውን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።