በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ ደረሰ- የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

ሰባተኛ ሳምንቱን በያዘው የጋዛው ጦርነት በእስራኤል የተቀናጁ ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከነዚህም ውስጥ 70 በመቶዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የእስራኤል መከላከያ በሆስፒታሉ ስር አሉ ያላቸውን "ዋሻዎች" ምስል አሳየ

    እስራኤል የሐማስ ናቸው ያለቻቸው ዋሻዎች

    የፎቶው ባለመብት, IDF

    የእስራኤል መከላከያ በጋዛው ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ስር የሐማስ ናቸው ያላቸውን 'ዋሻዎች' ምስል በኤክስ ገጹ አውጥቷል።

    ቢቢሲ የእነዚህን ምስሎች ትክክለኛነት ገና አላረጋገጠም። "በአልሺፋ ሆስፒታል ቅጽር ግቢ ውስጥ የአሸባሪው ሐማስ ዋሻ ተገኝቷል" ሲል መከላከያው በትዊተር ገጹ ለጥፏል።

    በተጨማሪም በሆስፒታል ግቢ ውስጥ በመሬት ስር ያለ መተላለፊያ መግቢያንም ያሳያል ያለውንም ቪዲዮ አውጥቷል።

    መከላከያው በጋዛ የህጻናት ሆስፒታል አል ራንቲሲ ውስጠኛው ክፍል "ሌላ የአሸባሪ ዋሻ" ነው በሚልም ሌሎች ምስሎችን አጋርቷል።

    ጦሩ በዚሁ ሆስፒታል ውስጥ ተገኝተዋል ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች እና ፈንጂዎችም ቪዲዮ በቅርቡ ማውጣቱ ይታወሳል።

    በተጨማሪም በአልቁድስ ሆስፒታል "ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ እና ጥይቶች" ተገኝተዋል ሲልም ፎቶ አጋርቷል።

    እስራኤል ሐማስ ሆስፒታሎቹን ለወታደራዊ ዓላማ ይጠቀምበታል በማለት የምታቀርበውን ክስ አሜሪካ ትደግፈዋለች። ሐማስም ሆነ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች የእስራኤል ውንጀላ ፍጹም ሀሰት ነው ሲሉ አይቀበሉትም።

  2. ኔታንያሁ የእስራኤል ታጋቾች በአልሺፋ ሆስፒታል እንደነበሩ 'ጠንካራ ፍንጮች እንዳሉ' ተናገሩ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, CBS

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወደ ጋዛ የተወሰዱ ታጋቾች በአልሺፋ ሆስፒታል እንደነበሩ የሚጠቁሙ 'ጠንካራ ፍንጮች' እንዳሉ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካው ሚዲያ ሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጦሩ ወደ "ሆስፒታሉ ከገባበትም ምክንያቶች አንዱ ነው" ብለዋል።

    ኔታንያሁ ወታደሮቻቸው ረቡዕ ዕለት ወደ ሆስፒታሉ ሲገቡ ታጋቾቹ አልነበሩም ብለዋል። " [ታጋቾቹ] ካሉም ወደውጭ ተወስደዋል" ሲሉም ገልጸዋል።

    እስራኤል ስለታሰሩት ሰዎች ተጨማሪ መረጃ አለኝ ብትልም ኔታንያሁ ግን "ስለ ጉዳዩ ትንሽ መረጃ መስጠቴ የተሻለ ነው" ብለዋል።

    እስራኤል በጋዛ በሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ሐማስ ወታደራዊ ጣቢያ ስትል በተደጋጋሚ የምትከስ ሲሆን ሐማስም ሆነ የሆስፒታሉ ኃላፊዎች ይህንን ፍጹም ሐሰት ነው ሲሉ አይቀበሉትም። ኔታንያሁ አገራቸው በአልሺፋ ታጋቾች እንደነበሩ አለኝ ስለምትለው መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

  3. የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ በሚገኝ ሆስፒታል ወረራ ማካሄዱ ተነገረ

    ጄኒን የስደተኞች መጠለያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ውስጥ በምትገኘው ጄኒን የስደተኞች መጠለያ ወረራ በማካሄድ ኢብን ሲና በተሰኘው ሆስፒታል ውስጥ መግባታቸው ተነገረ።

    በርካታ ወታደሮች በከተማዋ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ወረራ መፈጸማቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    እስራኤል በፈጸመችው የድሮን ጥቃትም ሶስት ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ሮይተርስ የፍልስጤም አምቡላንስ አገልግሎት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

    የእስራኤል ወታደሮች ወደ ከተማዋ ኢብን ሲና ሆስፒታል ሲገቡም አምቡላንሶችን እንዲቆሙ እና የህክምና ሰራተኞችም ለቀው እንዲወጡ ማስገደዳቸውንም በርካታ የፍልስጤም የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

    ቀይ መለዮ የለበሱ ሰራተኞች እጃቸውን ወደላይ አድርገው የሚያሳዩ ቪዲዮ የተጋራ ሲሆን ቢቢሲ ቪዲዮውን ማረጋገጥ አልቻለም።

    የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ በሆስፒታሉ የሚገኙ ሰራተኞቻቹ መታሰራቸውን ማስታወቁንም እነዚህ የዜና ማዕከላት ዘግበዋል።

    እስራኤል በጄኒን የስደተኞች ጣቢያ ላይ ተደጋጋሚ ወረራዎችን ፈጽማለች። ባለፈው ሳምንት ብቻ በእስራኤል ወረራ 14 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በጣቢያው በቅርብ ጊዜ ከተከሰቱትም የከፋው ነው ተብሏል።

  4. እስራኤል ከታጋቾቹ መካከል የአንዷን አስከሬን በጋዛ ማግኘቷን አስታወቀች

    ይሁዲት ዌይስ

    የፎቶው ባለመብት, FAMILY HANDOUT

    የእስራኤል ጦር ከታጋቾቹ መካከል ይሁዲት ዌይስ የተሰኘችውን አስክሬን በጋዛ አልሺፋ ሆስፒታል አጠገብ በሚገኝ ስፍራ ውስጥ ማግኘቱን አስታወቀ።

    የ65 አመቷ ይሁዲት ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ከተወሰዱ 200 ታጋቾች መካከል አንዷ ነበረች።

    ግለሰቧ በታገተችበት ወቅት ከጡት ካንሰር ህመም እያገገመች የነበረች ሲሆን የምትወስደውን መድኃኒትም ይዛ እንዳልነበር ብሪንግ ዜም ሆም ናው የተባለው ቡድን አስታውቋል።

    ባለቤቷ ሻሙዔል በሐማስ ታጣቂዎች መገደሉንም የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

  5. በአልሺፋ ሆስፒታል ውሃ እና ኦክስጅን አለመኖሩን ዳይሬክተሩ ገለጹ

  6. 41ኛው ቀኑን የያዘው የጋዛ ጦርነት የቅርብ ክስተቶች

    የአልሺፋ ሆስፒታል
    • የእስራኤል ጦር ባለፉት ቀናት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በመሬት ስር የሚገኙ ሁለት ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የከፋ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል። ጥቃቱ ያነጣጠረው ተደብቀው ባሉ ከፍተኛ የሐማስ አመራሮች ላይ መሆኑንም ገልጿል። ከነዚህም መካከል የሐማስ የሮኬት ብርጌድ መሪ እና የሰሜን ጋዛ ብርጌድ መሪ ተጠቅሰዋል።
    • በጋዛ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ታግተው ከነበሩት መካከል ይሁዲት ዌይስ የተባለችውን አስከሬን ከሺፋ አጠገብ በሚገኝ ስፍራ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ጦሩ በገባበት የጋዛው ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የዋሻ መተላለፊያ እንዲሁም የተጠመደ መኪና ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
    • የእስራኤል ጦር የተቆጣጠረው የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ዳይሬክተር በመቶዎች የሚቆጠሩ ታማሚዎች በስፍራው እንደሚገኙ ገልጸዋል። ሆስፒታሉ መብራት፣ ውሃ ተቋርጦበታል እንዲሁም ኦክስጅንን ጨምሮ የህክምና ግብዓቶች የሉትም። በርካታ ህሙማንንም "በውሃ ጥም" እያቃሰቱ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
    • እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ነዳጅ እንዳይገባ በመከልከሉ በመላው ጋዛ የሞባይል ስልክ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን የፍልስጤም የቴሌኮም ኩባንያዎች አስታውቀዋል።
    • በጋዛ ደቡባዊ ክፍል በአራት ከተሞች ነዋሪ የሆኑ ፍልስጤማውያን ከቤታቸው ወጥተው ወደ መጠለያዎች እንዲገቡ የሚያስጠነቅቁ በራሪ ወረቀቶች በእስራኤል ጦር ተበትኗል። ጦሩ በራሪ ወረቀቶቹን የበተነው በኻን ዪኒስ ከተማ መሆኑም ተነግሯል።
    • የእስራኤል ጦር ከዌስት ባንክ ወደ እየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኝ የፍተሻ ኬላ ላይ ተኩስ ከፍተዋል ባላቸው ሶስት ታጣቂዎችን መግደሉን አስታውቋል። የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ በሚገኘው የጄኒን የስደተኞች መጠለያ ላይ ወረራ መፈጸሙንም ዘገባዎች አመልክተዋል።
  7. በጋዛ የቴሌኮም ግንኙነት አማራጮች በሙሉ ተቋረጡ

    NetBlocks

    የፎቶው ባለመብት, NetBlocks

    በጋዛ የሞባይል ስልክ፣ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት፣ ዋይፋይ እንዲሁም መደበኛ የስልክ መስመሮች መቋረጣቸው ተገለጸ።

    የፍልስጤም ኮሚኒኬሽን ኩባንያ የሆነው ጃዋል በጋዛ ሁሉም የቴሌኮም አማራጮች መቋረጣቸውን አስታውቋል።

    “በጋዛ የቴሌኮም አግልግሎቶችን የሚያንቀሳቀሱ የኃይል ምንጮች ተሟጠው በማለቃቸው ሁሉም የቴሌኮም አማራጮች ተቋረጠዋል” ብሏል ኩባንያው።

    በመላው ዓለም የኔትዎርክ ግንኙነትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ የተሰኘው ድርጅትም ይህንኑ ያረጋገጠ ሲሆን ጋዛ የጠቅላላ የኢንተርኔት መቋረጥ ውስጥ ትገኛለች ብሏል።

  8. የእስራኤል ጦር አል-ሺፋ ሆስፒታልን ፈትሾ ለመጨረስ ሳምንታት ሊወስድብኝ ይችላል አለ

    ከሆስፒታሉ ተገኘ የተባለ የሐማስ ወታደራዊ ርዕዮተ ዓለም
    የምስሉ መግለጫ, ከሆስፒታሉ ተገኘ የተባለ የሐማስ ወታደራዊ ርዕዮተ ዓለም

    የእስራኤል ጦር በጋዛ ትልቁ የሆነውን ሆስፒታል ፈትሾ ለመጨረስ ጥቂት ሳምንታት ሊወስዱበት እንደሚችል አስታወቀ።

    የጦሩ ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሌኔል ጆናታን ኮንሪከስ ለቢቢሲ ሲናገሩ ሐማስ ከሆስፒታሉ ስር የሰራውን ግንባታ ስፋት መጠን ለማሳየት ጥቂት ሳምንታት ሊወስድብን ይችላል ብለዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ ሐማስ ከሆስፒታሉ ስር ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እና ዋሻ ግንብቷል ይላሉ።

    ሐማስ እና የጤና ተቋሙ ግን ይህን ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።

    የእስራኤል ጦር ባለፉት ሁለት ቀናት ሆስፒታሉን ተቆጣጥሮ ብርበራዎችን እያደረገ ሲሆን እስካሁን ድረስ ጥቂት ክላሺንኮቭ መሳሪያዎችን እና ወታደራዊ የደንብ ልብሶችን አግኝቻላሁ ከማለቱ ወጪ የተገነባ ዋሻ አላሳየም።

    “ሁሉንም የሆስፒታለ ክፍል ፈትሸን አልጨረስንም- ገና አልተጀመረም ማለት ይቀላል” ብለዋል ቃል አቀባዩ ኮንሪከስ።

  9. ጀርመን ለሄዝቦላ ድጋፍ በመስጠት በጠረጠረችው ማዕከል ላይ ድንገተኛ ፍተሻ አደረገች

    የጀርመን ፖሊስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የጀርመን ፖሊስ በሰባት ግዛቶች ውስጥ ለሄዝቦላ ድጋፍ ያደርጋል ብሎ በጠረጠረው እስላማዊ ማዕከል ላይ ድንገተኛ ፍተሻ አደረገ።

    የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳለው የሃምቡርግ እስላማዊ ማዕከል ለታጣቂው ቡድን ሄዝቦላ ድጋፍ ያደርጋል በሚል ፍተሻ ተደርጎበታል።

    ፖሊስ ከ300 ያላሱ አባላቱን አሰማርቶ ከማዕከሉ ጋር ግንኙነት አላቻው በተባሉ 50 ቦታዎች ብርበራ ማድረጉ ተሰምቷል።

    የባለስልጣናት ትኩረት ተቋሙ ለሄዝቦላ ድጋፍ እንደሚሰጠ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማግኘት ስለነበረ ብርበራውን ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋለ የለም ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    በጀርመን ከእአአ 2020 ጀምሮ የሄዝቦላ ንብረቶች ተወርሰው እንቅስቃሴዎቹ በሙሉ ታግደዋል።

  10. ኔታኒያሁ ስልጣን እንዲለቁ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጠየቁ

    የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ላፒድ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ላፒድ

    የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ያይራ ላፒድ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ስልጣን መልቀቅ አለባቸው አሉ።

    ላፒድ የእስራኤል መንግሥት ከሐማስ ጋር የተገባውን ግጭት በአግባቡ መያዝ ባለመቻሉ ኔታኒያሁ በአስቸኳይ ስልጣን መልቀቅ አለባቸው ብለዋል።

    ቻናል 12 ለተባለ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ፤ “ኔታኒያሁ አሁን መሰናበት አለባቸው። መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም። . . . ሕዝብ አመኔታ ባጣበት መሪ ልንመራ አንችልም” ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚንስርት የነበሩት ላፒድ ፓርቲያቸው ዬሽ አቲድ ከገዢው ሊኩድ ፓርቲ ጋር በመጣመር ግዚያዊ መንግሥት ለማቋቋም ዝግጁ መሆኑን ተናግረው ኔታኒያሁ ግን መሪ ሆነው መቀጠል አይችሉም ብለዋል።

  11. የእስራኤል ጦር ከአል-ሺፋ ሆስፒታል የተገኘ ነው ያለውን ወታደራዊ ቁስ አሳየ

    ክላሽንኮቭ

    የእስራኤል ጦር ለሁለት ቀናት ተቆጣጥሮ በያዘው የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል የተገኙ ናቸው ያላቸውን ወታደራዊ ቁሳቁሶች አሳየ።

    ጦሩ ሐማስ ከአል-ሺፋ ሆስፒታል ስር የጦር ማዘዣ እና ወታደራዊ መሳሪያዎችን የሚያከማችበት ዋሻ ገንብቷል ሲል ቆይቷል።

    ባለፉት ሁለት ቀናትም የእስራኤል ጦር በአስተርጓሚዎች ታጅቦ እያንዳንዱን የሆስፒታል ክፍሎች እየበረበረ፤ ሐኪሞችን እና ታካሚዎችን ጥያቄ ሲጠይቅ ቆይቷል።

    የእስራኤል ጦር የቢቢሲን ጋዜጠኛ ይዞ ወደ ሆስፒታሉ የገባ ሲሆን የሐማስ የሆኑ እና ከሆስፒታሉ የተገኙ ናቸው የተባሉ ጦር መሳሪያዎችን አሳይቷል።

    ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከኤምአርአይ ማሽን ጀርባ ተደብቆ መገኘቱን እንዲሁም የሐማስን ወታደራዊ የደንብ ልብሶች እና ወታደራዊ ርዮአተ ዓለም የሚገልጹ ጽሑፎች መገኘቱን የጦር አባላቱ ገልጸዋል።

  12. ደቡብ አፍሪካ በጋዛ ጥቃት እስራኤልን ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ወሰደች

    ራማፎሳ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ባለችው እርምጃ አገሪቱን ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ወሰደች።

    ፕሬዝዳንት ራማፎሳ የእስራኤል መንግሥት በጋዛ እየፈጸመ ያለው ተግባር በዓለም አቀፉ የወንጀለ ፍርድ ቤት መዳኘት እንዳለበት ከሌሎች በርካታ አገራት ጋር ተግባብተናል በለዋል።

    ራማፎሳ የእስራኤል እርምጃ በፍርድ ቤቱ መታየት አለበት ያሉት ቀሪ አገራት የትኞቹ እንደሆኑ ያሉት ነገር ባይኖርም፤ በጋዛ “የጦር ወንጀለኞች እየተፈጸሙ እንደሆነ እናምናል” ብለዋል።

    በእስራኤል-ጋዛ ጦርነት እስራኤልን አጥብቆ በመተቸት እና ለፍልስጤማውያን ግልጽ ድጋፍ እየሰጡ ካሉ ጥቂት አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ነች።

    ሐማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ያለወገዙት ራማፎሳ፤ እስራኤል በጋዛ እያደረገች ያለችው ወታደራዊ ዘመቻ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንድትታይ ያደርጋታል ብለዋል።

    አይሲሲ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሲሆን እንደ ጦር ወንጀል እና ዘር ማጥፋት ባሉ ክሶች የተከሰሱ ግለቦችን ይዳኛል።

  13. ባይደን የጋዛ ታጋቾች እንደሚለቀቁ ተስፋ እንዳላቸው ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ጋዛ የተወሰዱ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ "ተስፋ አለኝ" አሉ።

    ቀደም ሲል በካሊፎርኒያ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሁኔታው ሳይበስል ያለጊዜው መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸው ነገር ግን አገራቸው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተጀመረውን ድርድር ስትመራ ከነበረችው ኳታር "ታላቅ ትብብር" አይታለች ብለዋል።

    እስራኤል በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ያደረገችውንም ወታደራዊ ዘመቻ ደግፈው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ሐማስ ስፍራውን ለወታደራዊ ዓላማ በመጠቀም "የጦር ወንጀል" ፈጽሟል ብለዋል።

    እስራኤል ከሆስፒታሉ ውስጥ ተገኙ ያለቻቸውን የሐማስ የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ ቁሶች ምስሎች እና ቪዲዮዎች አሳይታለች።

    ሐማስ የህክምና ተቋማትን በሽፋንነት እንደማይጠቀም ተናግሯል። ፕሬዚዳንቱ እስራኤል የሐማስ ምሽጎችን ለመፈለግ በምትታደርገው ጥረት ሰላማዊ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበዋል።

  14. እስራኤል በኳታር ተቀማጭነታቸውን ያደረጉትን የሐማስ መሪ የጋዛ ቤታቸውን እንደመታች አስታወቀች

    የሐማስ ከፍተኛ አመራር እስማኤል ሐኒዬህ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጦር በኳታር ተቀማጭነታቸውን ያደረጉትን የሐማስ ከፍተኛ አመራር እስማኤል ሐኒዬህ የጋዛ መኖሪያ ቤታቸውን እንደመታ አስታወቀ።

    የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊን መኖሪያ ቤት ለምምታት ተዋጊ ጄቶች መጠቀማቸውንም የእስራኤል መከላከያ ኃይል በኤክስ ገጹ አስፍሯል።

    የእስራኤል ጦር የአመራሩ መኖሪያ ቤት "ለሽብር መሰረተ ልማትነት " እንዲሁ "ለድርጅቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሰብሰቢያ ቦታ ነበር" ብሏል። ቢቢሲ የእስራኤል ጦር ያቀረባቸውን ክሶች በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።

    እስማኤል ሐኒዬህ ማን ናቸው?

    ሃኒዬህ በአውሮፓውያኑ 2017 የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ቢመረጡም ኑሯቸውን በኳታር ካደረጉ ዓመታት አስቆጠሩ።

    በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ከሐማስ ስመ ጥር አመራሮች አንዱ የነበሩ ሲሆን እስራኤልም ለሶስት ዓመታት አስራቸዋለች። ከእስር ተፈትተው ለግዞት የታደረጉ ሲሆን ከዚያም ወደ ጋዛ ተመልሰዋል።

    በአውሮፓውያኑ 1997 የሐማስ መንፈሳዊ ጽህፈት ሐላፊ ሆነው ተሾሙ። ሃኒዬህ በአውሮፓውያኑ 2006 የፍልስጤም ጠቅላይ ሚነስትር ሆነው በፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ሆነው ቢሾሙም ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ከስልጣን ተባረዋል።

    ሐማስ የፕሬዚዳንት አባስ ፓርቲ የሆነውን ፋታህን ከጋዛ ሰርጥ እንዲወጣ ካደረገ በኋላም ነው ከኃላፊነታቸው የተነሱት።

    ሃኒዬህ ከስልጣን የተባረሩበትን መንገድ ህገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት ውድቅ ያደረጉ ሲሆን መንግሥታቸው "ለፍልስጤም ህዝብ ያለውን አገራዊ ኃላፊነት አይተውም"

  15. በእስራኤል-ጋዛ የተከሰቱ የቅርብ ጉዳዮች

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኘው አልሺፋ ሆስፒታል በታንክ ታግዞ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዱን አስታውቋል። ሐማስ ሆስፒታሉን ለወታደራዊ ትዕዛዝ ማዕከልነት እየተጠቀመበት ነው ስትል እስራኤል ትከሳለች። ሐማስም ሆነ የሆስፒታሉ ሐላፊዎች ይህንን ፍጹም ሐሰት ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
    • በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኝ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው የእስራኤል ወታደሮች ሆስፒታሉን ለቀው መውጣታቸውን የጠቀሰ ሲሆን ነገር ግን ቢቢሲ ይህንን በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።
    • የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ወደ ሆስፒታሉ ዋና ድንገተኛ ክፍል ገብተው ታካሚዎችን መመርመራቸውም ይኸው ጋዜጠኛ ተናግሯል።
    • ጦሩ በአል ሺፋ ውስጥ የሐማስ ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች እና ወታደራዊ ቁሶች የሚያሳዩ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችንም አውጥቷል።
    • በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ኻን ዩኒስ ከባድ ዝናብ እየዘነበ ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ 25 ሺህ ሊትር ነዳጅ በግብጽ በኩል ባለችው የድንበር ማቋረጫ ራፋህ በኩል ገብቷል።
    • የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የጋዛው ጦርነት 'የተራዘመ ሰብዓዊ ፋታ' እንዲሰጠው ውሳኔ አሳልፏል። ተመድ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ያሳለፈው ውሳኔ በሙሉ ከበባ ውስጥ ባለችው ጋዛ እርዳታ እንዲገባ ለማድረግ 'ለበቂ ቀናት' የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል።
    • በዩናይትድ ኪንግደም በጋዛ የተኩስ አቁም ጥሪን በመቃወም የተወካዮች ምክር ቤት ድምጽ ሰጥተዋል። ጥሪው በ293 ተቃውሞ እና በ125 ድጋፍ ውድቅ ተደርጓል። የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኬይር ስታርመን የፓርላማ አባላት ድምጸ ተዓቅቦ እንዲያካሂዱ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
  16. ከእስራኤል ወረራ በኋላ የአልሺፋ ሆስፒታል ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል- የሆስፒታሉ ኃላፊ

    የአልሺፋ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, IDF

    የእስራኤል ጦር በታንክ ታግዞ የወረረው የጋዛው ትልቁ ሆስፒታል የከፋ ውድመት እንደደረሰበት የሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ኃላፊ ዶ/ር ማርዋን አቡ ሳዳ ተናገሩ።

    በተለይም የራዲዮሎጂ (የራጅ) ክፍሉ የከፋ እንደሆነም ነው የገለጹት። 'የእስራኤል ጦር በልዩ የቀዶ ህክምና ውስጥ የሚገኘው የራጅ ክፍሉ ላይ ወረራ ፈጽሟል" ሲሉም ለቢቢሲ በላኩት መልዕክት ልከዋል።

    "ወንዶቹን እጃቸውን አስረው በአንድ ክፍል ለዩዋቸዋው። በሲቲ ስካነር፣ በኤምአርአይ ማሺን እና በበርካታ የአልትራ ሳውንድ የህክምና መሳሪያዎች እና እቃዎች ላይ የከፋ ውድመት አድርሰዋል" ብለዋል።

    "የጥገና ቡድን አባላት የሆኑ ሁለት ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም" አክለው ገልጸዋል።

  17. ተመድ የጋዛው ጦርነት 'ሰብዓዊ ፋታ' እንዲሰጠው ውሳኔ አሳለፈ

    የአልሺፋ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የጋዛው ጦርነት 'የተራዘመ ሰብዓዊ ፋታ' እንዲሰጠው ውሳኔ አሳለፈ።

    ተመድ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ያሳለፈው ውሳኔ በሙሉ ከበባ ውስጥ ባለችው ጋዛ እርዳታ እንዲገባ ለማድረግ 'ለበቂ ቀናት' የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል።

    በማልታ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብም 12 አገራት ሲደግፉት የምከር ቤቱ ሶስቱ ቋሚ አባላት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሩሲያ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

    ውሳኔው በሐማስ እና በሌሎች ቡድኖች የተወሰዱ ታጋቾች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቁም ጠይቋል።

    በተጨማሪም ሁሉም አካላት በአለም አቀፍ ህግ የተጣለባቸውን ግዴታዎች እንዲወጡ የሚጠይቅ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ሁኔታውን እየተከታተሉ አፈጻጸሙን ሪፖርት እንዲያደርጉም ወስኗል።

    የጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በጋዛ የተኩስ አቁም ወይም የሰብዓዊነት ፋታ እንዲሰጥ የሚጠይቁ ውሳኔዎችን ለአራት ጊዜ ያህል ማሳለፍ ተስኖት ነበር።

  18. ኳታር ለሦስት ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ እያደራደረች ነው ተባለ

    እስራኤል ለሦስት ቀናት ያክል በጋዛ የተኩስ አቁም አድርጋ በምላሹ 50 ታጋቾች እንዲላቀቁላት ኳታር እያደራደረች ነው ተባለ።

    በውይይት ላይ የሚገኘውን ስምምነት የአሜሪካ መንግሥት እያስተባበረው ሲሆን የእስራኤል ጦር ለሦስት ቀናት በጋዛ የሚያደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ካቆመ መስከረም 26 በሐማስ ከታገቱት መካከል 50 የሚሆኑት ይለቀቃሉ ተብሏል።

    ስምምነቱ ተፈጻሚ ከሆነ እስራኤል ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ የምትፈቅድ ሲሆን በእስራኤል እስር ቤቶች ተይዘው የሚገኙ ሴቶች እና ሕጻናትም ነጻ ይወጣሉ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ለድርድሩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው ሐማስ በድርድሩ የተስማማ ሲሆን እስራኤል ግን ገና እንዳልተስማማች እና በዝርዝር ጉዳዮች ላይ እየተደራደረች ነው።

  19. የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር እስራኤል “የዘፈቀደ ግድያን” ታቁም አሉ

    የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ

    የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ያለችውን የዘፈቀደ ግድያ ማቆም አለባት አሉ።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ እስራኤል ዓለም አቀፍ “የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመጣስ ፍልስጤማውያንን በጋዘ በዘፈቀደ እየገደለች ነው” ስለማለታቸው የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ዓለም አቀፍ ሕግጋቶች እንዲከበሩ ጠይቀዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እስራኤል እራሷን የመከላከል መብት እንዳላት እናምናል፤ ሐማስም አግቶ የያዛቸውን በአስቸኳይ መልቀቅ አለበት የሉ ሲሆን የዘፈቀ ግድያዎችን ግን መንግሥታቸው እንደሚቃወም አስታውቀዋል።

    ከጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር በኋላ የስፔን የማኅበራዊ መብቶች ሚንስትሯ አዮን ቤላራ አገራቸው ስፔን ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድታቋርጥ እና እስራኤል ላይ ምጣኔ ሃብታዊ ማዕቀብ እንድትጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።

  20. የእስራኤል ወታደሮች በሺፋ ሆስፒታል ብርበራ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ

    የእስራኤል ጦር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ እያደረገ ያለውን ዘመቻ በተመለተ በሰጠው መግለጫ በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ፍተሻ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

    ጦሩ በአስተርጓሚዎች ታጅቦ እያንዳንዱን የሆስፒታል ክፍሎች እየበረበረ፤ ሐኪሞችን እና ታካሚዎችን ጥያቄ እየጠየቀ እንደሆነ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በስፍራው ከሚገኙ ምንጮች ሰምቷል።

    ጦሩም ባወጣው መግለጫ በሺፋ ሆስፒታል ውስጥ ሐማስን ዒላማ ያደረገ ዘመቻ እየተካሄደ ነው ብሏል። ጦሩ ጨምሮ እንደገለጸው ወደ ሆስፒታሉ ሲገባ የሕጻናት ምግብ እና የሕጻናት ማሞቂያ ማሽኖችን ይዞ ነው።

    እስራኤል እና አሜሪካ ታጣቂ ቡድኑ የጦር ማዘዣ ጣቢያ እና መጋዘን ከሆስፒታሉ ስር ገንብቶ ይገኛል የሚሉ ሲሆን ሐማስ እና የጤና ተቋሙ ግን ይህ ሐሰት ነው ይላሉ።