በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ ደረሰ- የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

ሰባተኛ ሳምንቱን በያዘው የጋዛው ጦርነት በእስራኤል የተቀናጁ ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከነዚህም ውስጥ 70 በመቶዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ‘ሆስፒታሎች የጦር ሜዳዎች አይደሉም’ የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን

    ማርቲን ግሪፊትስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ማርቲን ግሪፊትስ

    የእስራኤል ወታደሮች ጋዛ ውስጥ ወደሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል አል-ሺፋ መግባታቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ተቃውሟቸውን አሰሙ።

    “በጋዛው አል-ሺፋ ሆስፒታል ውስጥ የተካሄደውን ወታደራዊ ወረራን በተመለከተ እየወጡ ባሉት ዘገባዎች አዝኛለሁ” ሲሉ ግሪፊትስ በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ጨምረውም “የጨቅላ ሕጻናትን፣ የህሙማንን፣ የሕክምና ባለሙያዎችን እንዲሁም የሲቪሎችን ደኅንነት መጠበቅ ከምንም በላይ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሆስፒታሎች የጦር ሜዳዎች አይደሉም” ብለዋል።

    ቀደም ሲል እንደተዘገበው የእስራኤል ጦር ኃይል አባላት ወደ ሆስፒታሉ የገቡ ሲሆን፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ላገኗቸው ሰዎች ጥያቄ እያቀረቡ ምርመራ እያካሄዱ ነው። በተጨማሪም በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ወንዶችን በአንድ ቦታ ላይ እያሰባሰቧቸው መሆኑ ተነግሯል።

    የእስራኤል ጦር ሠራዊት ሐማስ ከሆስፒታሉ ስር የዕዝ ማዕከል እንዳለው በመግለጽ ቢከስም ሐማስ ግን ይህንን ያስተባብላል።

    ሠራዊቱ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት በአል-ሺፋ ሆስፒታሉ ውስጥ “የተመረጡ ዘመቻዎችን” እያከሄደ ነው።

  2. እስራኤል የተወሰኑ የተባበሩት መንግሥታት መኪኖች ዛሬ ነዳጅ እንደሚሞሉ ገለፀች

    የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ወደ ጋዛ እርዳታ የሚያጓጉዙ የተወሰኑ የተባበሩት መንግሥታት ከባድ መኪኖች ዛሬ ነዳጅ እንደሚሞላላቸው ገለፀ።

    በግዛቲቱ የመንግሥታቱን እንቅስቃሴ የሚያስተባብሩት እና በፍልስጤማውያን ሲቪል ጉዳዮችን የሚከታተለው የእስራኤል ሚኒስትር መሥሪኣ ቤት፣ መኪኖቹ ነዳጅ የሚሞላላቸው በአሜሪካ መንግሥት ጥያቄ መሰረት መሆኑን ገልጾ በግብጻውያን ድንበር ራፋ አካባቢ ነዳጅ እንደሚሞሉ ተናግሯል።

    ሚኒስትር መሥርያ ቤቱ አክሎም “ከአስፈላጊ የደህንነት ተቋማት ጋር በጥምረት በመሆን” እንደሚሰራ ተናግሯል።

    ማክሰኞ ማለዳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መኪኖቹ በነዳጅ እጥረት ምክንያት እርዳታ ማመላለስ አለመቻላቸውን ገልጾ ነበር።

    ጁሊዬቴ ቶኡማ፣ በተባበሩት መንግሥታት በፍልስጤም ስደተኞች ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ነዳጅ ገና ሊቀበሉ መሆኑን ገልጸው “እንቅስቃሴያችንን በከፍተኛ ሁኔታ ልንቀንስ የምንችልበት ጫፍ ላይ ደርሰናል” ሲሉ ተናግረዋል።

    እስራኤል በሐማስ ሊሰረቅ ይችላል በሚል ምክንያት ወደጋዛ የሚገባ ነዳጅን ካገደች ሳምንታት ያለፉ ሲሆን፣ ሆስፒታሎች፣ ዳቦ መጋገርያዎች፣ ለኤሌትሪክ ጄነረተሮች እና ውሃ ፓምፖች ስራቸውን ማከናወን መቸገራቸው ሲነገር ቆይቷል።

    የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ ከባድ መኪኖች በራፋ ድንብ ላይ ረዥም ሰልፍ ይዘው ይታያሉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  3. 'ሕይወቷ በማስታገሻ መድኃኒት ላይ ተንጠልጥሏል'- የጋዛ ህጻናት አሰቃቂ ታሪክ

  4. ሐማስ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ላይ 'የተፈጸመው ወረራ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው' አለ

    አል-ሻፊ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሐማስ መንግሥት መገናኛ ብዙኀን እስራኤል በጋዛ በሚገኘው አል-ሻፊ ሆስፒታል የፈጸመችው “የጦር ወንጀል” ነው ሲል በመግለጫው ላይ ኮንኖታል።

    መግለጫው አክሎም የእስራኤልን ወረራ “ከግብረ ገብ ያፈነገጠ" እንዲሁም "በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል” ሲል ጠርቶታል።

    ሐማስ በሆስፒታሉ ወረራ በተፈጸመ ወቅት 9000 ሕሙማን፣ የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎች እንደሚገኙ አስታውቋል።

    በቀድሞው ትዊተር፣ ኤክስ፣ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የፍልስ=ጤማውያን መረጃ ማዕከል መሪ ኢዛት አል-ሪሺቅ፣ እስራኤል ወታደራዊ ማዕከል ሳይሆን የሰለማዊ ዜጎች ተቋምን ነው ያጠቃችው ሲሉ ተናግረዋል።

    ሐማስ ከዚህ ቀደም ብሎ ዋሺንግተንን እና ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ለተፈጸመው ወረራ ተጠያቂ አድርጓል።

    እስራኤል እና አሜሪካ ከአል-ሻፊ ሆስፒታል ስር የሐማስ ማዘዣ ጣብያ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

  5. አሜሪካ ሐማስ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ስር ማዘዣ ጣብያ አለው ስትል ገለጸች

  6. ‘ቢያንስ ሆስፒታሉ ጥቃት አይደርስበትም ብለን አስበን ነበር’፡ ከሆስፒታል የሸሹ የጋዛ ነዋሪዎች

  7. የእስራኤል ጦር ኃይል ወደ አል-ሺፋ ሆስፒታል ዘልቆ መግባቱ ተሰማ

    አል-ሺፋ ሆስፒታል
    የምስሉ መግለጫ, አል-ሺፋ ሆስፒታል

    የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ትልቅ ወደ ሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል መግባቱ ተሰምቷል።

    ወታደራዊ ኃይሉ ወደ ሆስፒታሉ መግባቱ የተሰማው አሜሪካ ለመጀመርያ ጊዜ ሐማስ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ስር ማዘዣ ጣብያ እንዳለው የሚያሳይ መረጃ አለኝ ካለች በኋላ ነው።

    ምንም እንኳ እስራኤል በተደጋጋሚ ይህንን ብትልም ሐማስ ግን በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደረግ ቆይቷል።

    ቢቢሲ በሆስፒታሉ የሚገኝ የዓይን እማኝ አናግሮ መረዳት አንደቻለው ታንኮች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አል-ሺ ሆስፒታል ገብተዋል።

    “ስድስት ታንኮችን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮማንዶ ወታደሮችን በሆስፒታሉ ውስጥ ተመልክቻለሁ። በዋናው ድንገተኛ ክፍል በኩል ነው የገቡት። የተወሰኑት ፊታቸውን የሸፈኑ ሲሆን በአረብኛ ’እንዳነትንቀሳቀሱ እንዳትንቀሳቀሱ’ እያሉ ይጮሃሉ” ሲል ተናግሯል።

    ይህ የአይን እማኝ የእስራኤል ወታደሮች አስለቃሽ ጋዛ መተኮሳቸውን እና ሰዎች መተንፈስ ተቸግረው አንደነበር’ ገልጿል።

    አክሎም ወታደሮቹ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ሲገቡ መመልከቱን ተናግሯል።

    ቢቢሲ የአይን እማኙን ምስክርነት ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳነት ጆ ባይደን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔተንያሁ ጋር የስልክ ልውውጥ አድርገዋል።

    ኋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ መሪዎች “በሐማስ እገታ ስር የሚገኙ ሕጻናትን እና አሜሪያውያንን ጨምሮ ስለሚለቀቁበት ሁኔታ ረዥም ጊዜ ወስደው ተነጋግረዋል”

    ሐማስ እስራኤል በሆስፒታሉ ላይ ለፈጸመችው ወረራ አሜሪካ ሙሉ ኃላፊነት ትወስዳለች ሲል ተናግሯል።

    ሐማስ የአሜሪካ መግለጫ ለእስራኤል ወረራ “ይሁንታን” የሰጠ ነው ሲል ይከስሳል።

  8. ከአል-ሺፋ ለመውጣት የሚሞክሩ በጥይት እየተመቱ ነው ተባለ

    በእስራኤል ጦር ከበባ ስር ከሚገኘው ከጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ለመውጣት ሙከራ የሚያደርጉ ከወገባቸው በታች በጥይት እየተመቱ ነው ተባለ።

    የቢቢሲው ጋዜጠኛ ቁስም ሆነ ሰው ላለፉት 48 ሰዓታት ወደ ሆስፒታሉ እንዳይገባም ሆነ እንዳይወጣ የእስራኤል ጦር መከልከሉን በስፍራው ከሚገኙ ምንጮቹ ሰምቷል።

    በሆስፒታሉ ከሚገኘው ጋዜጠኛ እንደሰማው ከአል-ሺፋ ሆስፒታል ለመውጣት የሞከሩ አራት ሰዎች እግራቸው ላይ ተመትተው ደም እየፈሰሳቸው እርዳታ ጥበቃ እስከ ሁለት ሰዓታት በመንገድ ላይ ውድቀው ነበር።

    የሆስፒታሉ ጤና ባለሙያዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው አራቱን ሰዎች ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ መልሰው አስገብተዋል።

    እስራኤል ሐማስ ከአል-ሺፋ ሆስፒታል ስር የማዘዣ ጣቢያ አለው ትላለች። ይህን ግን ሐማስም ሆነ የጤና ተቋሙ ሐሰት ነው ይላሉ።

  9. እውቅ ፖለቲከኞች ኔታኒያሁ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ምርመራ እንዲከፈተ ጠየቁ

    ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትኒያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትኒያሁ

    በአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ፖለቲከኞች የእስራኤል መንግሥት የዘር ማጥፋት ወንጀል ምርመራ እንዲከፈትበት ጠየቁ።

    60 የሚሆኑት ግራ ዘመም ፖለቲከኞች እስራኤል በጋዛ እያካሄድ ባለችው ወታደራዊ ዘመቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመፈጸሟ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምርመራ እንዲያደርግ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል።

    የስፔን የማኅበራዊ መብቶች ሚንስትሯ አዮን ቤላራ እንዲሁም የዬኬው ሌበር ፓርቲ አመራር እና የፓርላማ አባል ጄሬሚ ኮርቤይ ጥያቄውን ካቀረቡት ፖለቲከኞች መካከል ይገኙበታል።

    ፖለቲከኞቹ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትኒያሁን፣ መከላከያ ሚንስትሩ ዮአቭ ጋላንትን እንዲሁም የፋይናንስ ሚንስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪችን በዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል ከሰዋቸዋል።

  10. ባለፉት ጥቂት ሰዓታት በጋዛ ያጋጠሙ ዋና ዋና ክስተቶች

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    እስራኤል በሐማስ ላይ የምትወስደውን የአጸፋ እርምጃ አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን ባለፉት ቀናት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ የቆየው የእስራኤል ጦር በዋነኛ ሆስፒታሎች ዙሪያ የሚያደርገው ዘመቻ ነው።

    የቢቢሲው ዘጋቢ በጋዛ ካሉት ምጮቹ እንደሰማው በጋዛ ትልቁ በሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል 170 አስክሬኖችን ለመቅበር የጅምላ መቃብር እየተቆፈረ ነው።

    እስራኤል በተለይ አል-ሺፋ ሆስፒታልን ዒላማ አላደረጉም በትልም ሐማስ የማዘዣ ጣቢያ ከሆስፒታሉ ስር ስለገነባ በሆስፒታሉ ዙሪያ ዘመቻ እያካሄድኩ ነው ትላለች።

    ሐማስ እና የሕክምና ተቋሙ ግን ይህ ሐሰት ነው ይላሉ።

    በሌላ ዜና የእስራኤል ጦር መስከረም 26 በሐማስ ከታገቱት መካከል አንዲት የ19 ዓመት እስራኤላዊት መገደሏን አረጋግጫለሁ ብሏል። ጦሩ የወጣቷ ሞት መንስዔ ምን እንደሆነ ያለው ነገር የለም።

  11. የዓለም ጤና ድርጅት ከግማሽ በላይ የጋዛ ሆስፒታሎች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል አለ

    አልሺፋ ሆስፒታል አቅራቢያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ ከሚገኙ 36 ሆስፒታሎች መካከል 22 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን አስታወቀ።

    ድርጅቱ ሆስፒታሎቹ ሥራ ለማቆም የተገደዱት በነዳጅ እጥረት፣ በደኅንነት ስጋት ወይም ውድመት አጋጥሟቸው ነው ብሏል።

    በሥራ ላይ የሚገኙ 14 ሆስፒታሎችም ቢሆኑ ከፍተኛ የሕክምና ቁሳ ቁስ እጥረት እንዳለባቸው የገለጸው ተቋሙ፤ በጋዛ አስቸኳይ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ዳግም ጠይቋል።

  12. የጋዛ ጉዳይ ወታደራዊ መፍትሄ የለውም- የዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላህ

    የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል የተወሰነውን የጋዛ ክፍል ለመቆጣጠር ወይም በግዛቲቱ ውስጥ የጸጥታ ቀጠና ለመመስረት ያቀደችውን እቅድ እንደማይቀበሉ የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ ተናገሩ።

    በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ላለው ግጭት "ወታደራዊም ሆነ የጸጥታ መፍትሄ" እንደማይኖሩ ንጉሱ ለከፍተኛ ፖለቲከኞች መናገራቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የቀውሱ መንስኤ እስራኤል የፍልስጤማውያንን "ህጋዊ መብት መካዷ" እንደሆነም ተናግረዋል። "መፍትሔው ከዚህ ይጀምራል። የትኛውም ሌላ መንገድ የማይሳካ እና የበለጠ የብጥብጥ እና ውድመት አዙሪት የሚያስከትል ነው" ብለዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላልተወሰነ ጊዜ "አጠቃላይ የጸጥታ ኃላፊነት" እንደሚኖራት ባለፈው ሳምንት በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።

    ዮርዳኖስ በርካታ የፍልስጤም ስደተኞች መኖሪያ ነች።

  13. ባይደን አል-ሺፋ ሆስፒታል ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

    የፎቶው ባለመብት, Al Drago/POOL/EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እስራኤል የጋዛ ትልቁን ሆስፒታል አል ሺፋን እንድትጠብቅ አሳሰቡ።

    ፕሬዚዳንቱ ትናንት በሰጡት መግለጫ መንግሥታቸው ከእስራኤል ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ እና በሆስፒታሉ ላይ የምትወስደው እርምጃ "ተገቢ" በሆነ መልኩ እንደሚሆንም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

    "ሆስፒታሉ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል" ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ትልቁ የጋዛ ሆስፒታል አል ሺፋ ወደ መቃብርነት ስፍራ እየተቀየረ እንደሆነ ማሳሰቡን ተከትሎም ነው ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት።

    በሆስፒታሉ አቅራቢያ ጦርነት እየተፋፋመ ሲሆን እስራኤል ሆስፒታሉን ከበባ ውስጥ አስገብታዋለች ተብሏል።

    በርካታ አገራት ዕርዳታ እንዲገባ እና ነዋሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ እና እንዲወጡ ለማስቻል ጦርነቱ እንዲገታ ሲጠይቁ ሌሎች ደግሞ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየጠየቁ ይገኛሉ።

    እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጥቃት በተቀናጀ ሁኔታ የቀጠለች ሲሆን በየቀኑ ለአራት ሰዓታት የሚቆይ የእፎይታ ጊዜ እንደሚኖርም ተናግራለች።

  14. አል ሺፋ ሆስፒታል በታንክ ተከቧል

    አል ሺፋ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጋዛው ትልቁ ሆስፒታል አል ሺፋ በታንክ መከበቡን በሆስፒታሉ ውስጥ ካለ ሰው ቢቢሲ ሰምቷል።

    በሆስፒታሉ አካባቢ ያለው ውጥረት አሁንም ተፋፍሞ እንደቀጠለ እና በትናንትናው ሌሊትም የፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ መስማታቸውን እኚሁ ግለሰብ ተናግረዋል።

    በተጨማሪም ታንኮች ሆስፒታሉን ከየአቅጣጫው እንደከበቡትና ወደ ሆስፒታሉ መግባትም ሆነ መውጣት እንደማይቻል ገልጸዋል።

    በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢም ቢሆን ከአንዱ ህንጻ ወደ ሌላው መንቀሳቀስ ከፍተኛ አደጋ እንደጋረጠም ተናግረዋል። በሆስፒታሉ መብራት፣ ውሃ እና በቂ መድኃኒት ባለመኖሩ በርካቶች ለሞት ተዳርገዋል ብለዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ሆስፒታሉ ወደ መቃብር ስፍራነት እየተቀየረ እንደሆነ እና በርካታ አስከሬኖችም በሆስፒታሉ ውስጥ እና ቅጽር በአሰቃቂ ሁኔታ ተከምረዋል ብሏል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፍተኛ አማካሪ ማርክ ሬጅቭ መንግሥታቸው እሁድ እለት 300 ሊትር ነዳጅ ለሆስፒታሉ ለማድረስ ያደረገው ሙከራ ሐማስ ሊቀበለው ባለመቻሉ ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል።ሐማስ ይህንን ሐሰት ነው ብሏል።

    እኚሁ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉት ግለሰብ አልሺፋ ያለው ነዳጅ ለግማሽ ሰዓት ብቻ የሚያቆይ ነው ብለዋል። ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ለማከናወን በየቀኑ ቢያንስ 10 ሺህ ሊትር እንደሚያስፈልገው ገልጸው መፍትሄ እንዲፈለግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

    እስራኤል በአልሺፋ መሬት ስር የሐማስ ማዘዣ እና የቁጥጥር ማዕከል አለ ትላለች። ሐማስ ይህንን ውንጀላ አይቀበለውም። እንዲሁም የሆስፒታሉ ዶክተሮችም ፍጹም ሐሰት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    "በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት ወደዚህ ሆስፒታል መጥቼያለሁ። እዚሁ ነው የተወለድኩት። ልጄ የተወለደው በእዚህ ሆስፒታል ውስጥ ነው። እናቴ ከመሞቷ በፊት በመጨረሻዎቹ ሁለት ወራት በኩላሊት የእጥበት ማዕከል ተኝታ ትታከም ነበር። በየቀኑም እጎበኛት ነበር"

    "ከሆስፒታሉ ስር ያለውን አላውቅም። በሆስፒታሉ ህንጻዎች ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአይኔ አይቼ አላውቅም"

  15. በእስራኤል-ጋዛ የተከሰቱ የቅርብ ጉዳዮች

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት የጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። እስራኤል በሆስፒታሎቹ ላይ የምትወስደው እርምጃ "ተገቢ" በሆነ መልኩ እንደሚሆንም ተስፋቸውን ገልጸዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ትልቁ የጋዛ ሆስፒታል አል ሺፋ ወደ መቃብርነት ስፍራ እየተቀየረ እንደሆነ ማሳሰቡን ተከትሎም ነው ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት።
    • እስራኤል ሐማስ አል ሺፋ ሆስፒታልን እንደ ወታደራዊ ማዕከል እየተጠቀመበት ነው ስትል እየወነጀለች ትገኛለች። የእስራኤል ጦር ቃለ አቀባይ ዳንኤል ሐጋሪ ሐማስ በጋዛ የሚገኘውን የህጻናት ሆስፒታል ለጦር መሳሪያ ማከማቻነት እየተጠቀመበት ነው ሲሉ ማስረጃ ለቢቢሲ አቅርበዋል። ቢቢሲ ይህንን ማስረጃ ማረጋገጥ አልቻለም። ሐማስ ሆስፒታሎችን ለወታደራዊ አገልግሎት ይጠቀምበታል የሚለውን ክስ አይቀበለውም።
    • እስራኤል በጋዛ እየፈጸመቻቸው ባለው የተቀናጀ የአየር፣ የመሬት እና የባህር ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 11 ሺህ 240 መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ 4 ሺህ 630 ህጻናት መሆናቸው ተገልጿል። በተጨማሪም በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት 3 ሺህ 130 ሴቶች መሆናቸውን ሐማስ የሚቆጣጠረው የመንግሥት የሚዲያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በጥቃቱ የቆሰሉ ፍልስጤማውያን ከ28 ሺህ በላይ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። ሐማስ መስከረም 26 በፈጸመው ጥቃት 1 200 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ200 በላይ ታጋቾችም ተወስደዋል።
    • የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ዩኤን ኦቻ) 200 ሺህ የሚገመቱ ፍልስጤማውያን በቅርቡ ከሰሜን ጋዛ ወደ ደቡብ መሸሻቸውን ገልጿል። በደቡባዊ ጋዛ የመጠለያ፣ የምግብ እና የውሃ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ውስን እንደሆነ እና አሳሳቢ መሆኑንም አስጠንቅቋል።
    • የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እስራኤል ራሷን ለመከላከል እና ታጋቾቿን ለማስለቀቅ የምታደርገው ጥረት አለም አቀፉን ህግ የተከተለ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ንጹሃን ዜጎችን ለመጠበቅ ሁሉንም እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባት ያሳሰቡት ሱናክ ከነዚህም ውስጥ በሆስፒታሎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም እንዲሁም በዌስት ባንክ ግዛት አክራሪ ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ እየፈጸሙት ያሉትን ጥቃት ማስቆም አለባት ብለዋል። እንዲሁ ጦርነቱ በተጨባጭ መንገድ እንዲገታም ጠይቀዋል።
  16. የጋዛው ትልቁ ሆስፒታል በአስከሬኖች እንደተጨናነቀ ተገለጸ

  17. አሜሪካ ሶሪያ በሚገኙ በኢራን በሚደገፉ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ማድረሷን ቀጥላለች

  18. በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 11 ሺህ 240 ደረሰ- የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

    በጋዛ ቤተሰቡን ያጣ ሰው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል በጋዛ እየፈጸመቻቸው ባለው የተቀናጀ የአየር፣ የመሬት እና የባህር ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 11 ሺህ 240 መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ 4 ሺህ 630 ህጻናት መሆናቸው ተገልጿል። በተጨማሪም በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት 3 ሺህ 130 ሴቶች መሆናቸውን ሐማስ የሚቆጣጠረው የመንግሥት የሚዲያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

    በጥቃቱ የቆሰሉ ፍልስጤማውያን ከ28 ሺህ በላይ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ሐማስ የሚመራው ባለስልጣናት በሚያቀርቡት የተገደሉ ፍልስጤማውያን አኃዝ ላይ እምነት እንዳለው ገልጿል።

  19. የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ በጋዛ የሚገኝ የነዳጅ ዴፖውን አሟጦ መጠቀሙን ገለጸ

    የፍልስጤማውያንን ስደተኞች የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ በነዳጅ ማከማቻው የሚገኘው ነዳጅ ተሟጦ ማለቁን ተናገረ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፍልስጤማውያንን ስደተኞች የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ በነዳጅ ማከማቻው የሚገኘው ነዳጅ ተሟጦ ማለቁን ተናገረ።

    ይህ በጋዛ የሚገኙ በርካታ አገልግሎቶችን የሚደግፈው ኤጀንሲ በነዳጅ ዴፖዬ እንጥፍጣፊ ነዳጅ የለም ማለቱን የዘገበው ሮይተርስ ነው።

    የስደተኞች ኤጀንሲው ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ ለለጋሾች እንደገለጹት፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ኤጀንሲው ለሆስፒታሎችን የሚያስለፍገውን ማቅረብ፣ ፍሳሾችን ማስወገድ እንዲሁም የመጠጥ ውሃ ማቅረብ አይችልም።

    ከጥቂት ሰዓታት በፊት በጋዛ የስደቶች ኤጀንሲው ዳይሬክተር የሆኑት፣ ቶም ዋይት፣ በኤክስ ገጻቸው ላይ “በጋዛ የሚካሄደው ሰብዓዊ እርዳታ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ጋዛ ነዳጅ እንዳይገባ በመደረጉ ምክንያት ይቆማል” ሲሉ አስፍረዋል።

    ዳይሬክተሩ አክለውም ዛሬ ማለዳ ሁለት የኤጀንሲው መጠጥ ውሃ አከፋፋዮችስራቸውን አቁመዋል ሲሉ ተናግረዋል።

    ይህም ለ200ሺህ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ እንዳይቀርብ አድርጓል።

    ውሃ አከፋፋዮቹ “ነዳጅ ጨረሰዋል” ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

    እስራኤል ሐማስ ጥቃት ከፈጸመበት ከመስከረም 26 ጀምሮ የሐማስን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ያግዛል በሚል ወደ ጋዛ ነዳጅ እንዳይገባ ከልክላለች።

    እስራኤል አክላም በጋዛ በቂ ነዳጅ እንዳለ እና ሐማስ እያከማቸ ነው ስትል ትወነጅላለች።

    እስራኤል ለአል-ሺፋ ሆስፒታል 300 ሊትር ነዳጅ ማቅረቧን ተናግራ ነበር።

    ከሳምንታት በፊት የአሜሪካ ባለሥልጣናት በፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ በግዛቱ የሚገኝ የነዳጅ መጠባበቅያን መጠቀም አለመቻሉን ገልጸው ነበር።

    በፍልስጤም የስደተኞች ጉዳይን የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ቀስ በቀስ በጋዛ እና እስራኤል ድንበር አካባቢ ያለውን የነዳጅ ዲፖ አሟጦ እየተጠቀመ መሆኑን በመግለጽ፣ እንዲሞላለት ለእስራኤል መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ሰሚ ጆሮ ማጣቱን ሮይተርስ ላዛሪኒን ጠቅሶ ዘግቧል።

  20. የእስራኤል ጦር በአል-ሺፋ ሆስፒታል ነዳጅ ላለመኖሩ ሐማስን ተጠያቂ አደረገ

    የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ፣ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ሠራተኞች ደህንነት አደጋ ላይ ለመውደቁ ሐማስን ተጠያቂ አደረጉ

    የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ከጊዜያቸው ቀድመው የተወለዱ ሕጻናት ሕይወትን ለመታደግ በአስቸኳይ የሚያስፍለገው ነዳጅ እንዳይደርስ ያደረገው ሐማስ ነው ሲሉ ወነጀሉ።

    “ድጋፍ አቅርበናል፣ ለሆስፒታሉ የሚያስፈልገው ነዳጅን አቅርበናል። ነዳጁ ያልተወሰደው በሐማስ ትዕዛዝ መሰረት ነው” ሲሉ ተናግረዋል ሌተናንት ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ።

    ኮርኒከስ የሆስፒታሉ ሰራተኞች እስራኤል ያቀረበችውን 300 ሊትር ነዳጅ ለመቀበል ከሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውጪ ከወጡ በእስራኤል ጦር ጥቃት ይደርስብናል ሲሉ መግለጻቸውን “ሙሉ በሙሉ ውድቅ” አድርገውታል።

    “ይህ ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው። ደህንነታቸው አስተማማኝ ባይሆን እንኳ በእስራኤል ጦር የተነሳ ሳይሆን በሐማስ ምክንያት ነው የሚሆነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ኮንሪከስ ሐማስ ለአል-ሺፋ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ “ነዳጁን እንዳይወስዱ” መናገሩን አስረድተዋል። አክለውም “ምናልባት በሆስፒታሉ የሚገኙ ሠራተኞች ላይ እየተኮሰ ሕይወታቸውነ አደጋ ላይ የጣለው ይኸው ሐማስ ይሆናል” ብለዋል።

    የእሰራኤል ጦር ለሆስፒታሉ የሚያስፈልግ ያለውን 300 ሊትር ነዳጅ ቢያቀርብም፣ አል-ሺፋ ሆስፒታል ግን በሰዓት ለመንቀሳቀስ 500 ሊትር ነዳጅ እንደሚያስፈልገው ይገልጻል።