ማክሮን እስራኤል ሕጻናት እና ሴቶችን በቦምብ ከመደብደብ ትቆጠብ አሉ

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እስራኤል በጋዛ ያሉ ሕጻናት እና ሴቶችን በቦምብ ከመደብደብ መቆጠብ አለባት አሉ። ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ አስካሁን የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 11,078 ከፍ ማለቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት ፍልስጤማውያን መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሂዩማን ራይትስ ዎች በአምቡላንስ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ እንደ ጦር ወንጀል ሊመረመር ይገባል አለ

    ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች እስራኤል በጋዛ በአምቡላንስ ላይ ጥቃት መሰንዘሯ እንደ ጦር ወንጀል መመርመር አለበት አለ።

    ከጥቂት ቀናት በፊት የእስራኤል ጦር በጋዛ አል-ሺፋ ሆስፒታል አቅራቢያ አምቡላንስ መምታቱ ይታወሳል።

    እስራኤል በአምቡላንሱ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ያመነች ሲሆን ተሸከርካሪውን ዒላማ ያደረገችው የሐማስ አባላት እየተጠቀሙበት እንደነበረ መረጃው ስለነበረኝ ነው ብላለች።

    ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን ከጥቃቱ በኋላ የተነሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መመልከቱን እንዲሁም የዓይን እማኞችን ማነጋገሩን ጠቅሶ በጥቃቱ 5 ሕጻናትን ጨምሮ 21 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

    ሂዩማን ራይትስ ዎች ጨምሮም አምቡላንሱ ወታደራዊ ዓላማን ለማስፈጸም ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ምንም አይነት ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል።

  2. ሱናክ አገራቸው የአይሁድ ማህበረሰብን ለመጠበቅ የተቻላትን ሁሉ ታደርጋለች አሉ

    በዩናይትድ ኪንግደም የጸረ-ሴማዊነት ሰሜት መበራከቱን ተከትሎ የአይሁድን ማህበረሰብ ደኅንነትን ለመጠበቅ መንግሥት “አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ገለጹ።

    ከአገሪቱ ንጉሱ ቀጥለው በፓርላማ ፊት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሪታንያ አይሁዶች “በዚህች አገር በስጋት እየኖሩ ነው” ብሎ ማሰቡ እንዳሳመማቸው ተናግረዋል።

    ሱናክ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መነጋገራቸውን እና ከ100 በላይ የእንግሊዝ ዜጎች በራፋ ማቋረጫ በኩል ጋዛን ለቀው መውጣታቸውን አረጋግጠዋል።

  3. እስራኤል ጋዛን በድጋሚ መያዟን እንደምትቃወም አሜሪካ ገለጸች

    እስራኤል የጋዛ ሰርጥ በአዲስ መልክ ለረዥም ጊዜ ተቆጣጥራ ለመቆየት ማቀዷን ዩናይትድ ስቴትስ እንደምትቃወም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታወቁ።

    ቬዳንት ፓቴል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ዩናይትድ ስቴትስ ከጋዛ ውጭ ፍልስጤማውያንን በግዳጅ ማስፈርን አትደግፍም።

    "በእኛ እምነት ፍልስጤማውያን ለዚህ ውሳኔ ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው። ጋዛ የፍልስጤም መሬት ነች፤ የፍልስጤም መሬት ሆናም ትቀጥላለች" ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እስራኤል ለጋዛ "የደህንነት ሃላፊነት" እንደሚኖራት መናገራቸውን ተከትሎ ነው ቃል አቀባዩ ሃሳባቸውን የሰነዘሩት።

    እስራኤል ከ38 ዓመታት በኋላ እአአ በ2005 ነበር ወታደሮቿን ከጋዛ ያስወጣችው።

  4. ሐማስ በእስራኤል ጦር ላይ ከባድ ኪሳራ እያደረስኩ ነው አለ

    የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ በእስራኤል ጦር ላይ ከባድ ኪሳራ እያደረስኩ ነው አለ።

    ቡድኑ በእስራኤል ወታደሮች እና ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሱን ይገልጻል።

    ባለፉት ቀናት በምዕራብ ጋዛ ቢች ከተሰኘ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ጋዛ ቤይት ሃኑን አቅራቢያ በርካታ የእስራኤል ወታደራዊ ተሸከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማውደሙን አስታውቋል።

    ቡድኑ ይህን ያለው የእስራኤል ጦር መሃል ጋዛ ከተማ መግባቱን ይፋ ባደረገበት ዕለት ነው።

  5. እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የትኞቹ አገራት ተቃወሙ? የትኞቹስ ደገፉ?

  6. ባይደን የጋዛ ጥቃት በጊዜያዊነት እንዲቆም ኔታንያሁን ጠየቁ

    የጋዛ ጥቃት በጊዜያዊነት እንዲቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን መጠየቃቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።

    የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ የአሜሪካ እና የእስራኤል መሪዎች ሰኞ ዕለት ባደረጉት ውይይት እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጥቃት ለሰብዓዊ ድጋፍ እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ “ለአፍታ ስለማቆም” መወያየታቸውን አስታውቀዋል።

    ባይደን ጥቃቱ ለሦስት ቀናት እንዲቆም ሃሳብ አቅርቧል ወይ በሚል ከጋዜጠኛ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

    ባይደን ለጥያቄው ምላሽ ሲሰጡ ስለ ርዝማኔው ግን ምንም አስተያየት አልሰጡም።

    ዋሽንግተንን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት እስራኤል የተኩስ አቁም ካደረገች ለሐማስ እገዛ ያደርጋል የሚለውን አቋም ይደግፋሉ።

  7. የእስራኤል ጦር መሃል ጋዛ ከተማ መግባቱን አስታወቀ

    የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ጦራቸው "በጋዛ ከተማ እምብርት እንደሚገኝ" ገለጹ።

    የእስራኤል ጦር ጋዛ ከተማ የገባው ሐማስ ወደ እስራኤል ተሻግሮ ጥቃት ካደረሰ ከአንድ ወር በኋላ ነው።

    የእስራኤል ጦር "የምድር፣ የአየር እና የባህር ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ በማስተባበር ማንቀሳቀሱን" ገልጸዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ወታደሮቻቸው ጋዛ ከተማን ከበው “ዘመቻውን ከውስጥ እያከናወኑ” መሆኑን አስታውቀው ነበር።

    የጋዛን ሕዝብ "እባካችሁ ወደ ደቡብ ሂዱ" ሲሉም ኔታንያሁ ጥሪ አቅርበዋል።

    እስራኤል ከጦርነቱ በኋላ የጋዛ አጠቃላይ የፀጥታ ኃላፊነት እንደምትወስድ ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት የሰጡትን አስተያየት አስመልክቶ የጦር ካቢኔያቸው አባል ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

    የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሚኒስትር ሮን ዴርመር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጋዛ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ውጪ መሆኗን እስራኤል ከማረጋገጥ ባለፈ ወታደሮቿ ማንኛውንም አይነት አዲስ የሽብር ስጋት ለመዋጋት የጸጥታ ሥራዎችን ያከናውናል ሲሉ የኔታንያሁን ሃሳብ አብራርተዋል።

    እስራኤል ዳግም ጋዛን የማስተዳደር ሃሳብ እንደሌላት ተናግረዋል።

    በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ4,100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ10,300 በላይ ሰዎች በጋዛ ተገድለዋል ብሏል።

    በእስራኤል ወገን 1,400 ሰዎች ሲገደሉ ከ240 በላይ ሰዎች ታግተው ተወስደዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳ፣ የዓለም ጤና ድርጅት በእስራኤል እና በጋዛ ግጭት እየደረሰ ያለው “የሞት እና የስቃይ ደረጃ ለመረዳት የሚከብድ ነው” ብሏል።

    የድርጅቱ ቃል አቀባይ ክርስቲያን ሊንድሜየር ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በጤና ተቋማት ላይ ከ100 በላይ ጥቃቶች ደርሰዋል ብለዋል።

  8. አል-ሲሲ ከሲአይኤ ኃላፊ ጋር በካይሮ ተወያዩ

    የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ከአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ኃላፊ ዊሊያም በርንስ ጋር ተገናኝተው በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መከሩ።

    ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ከሲአይኤው ኃላፊ ጋር በተገናኙ ወቅት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

    ሁለቱ ባለሥልጣናት ትኩረታቸውን እስራኤል በጋዛ ሰርጥ አጠናክራ ስለቀጠለችው ወደታደራዊ ዘመቻ ላይ ያድርጉ እንጂ ዓለም አቀፍ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ወይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

    የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ አል-ሲሲ ሰላማዊ ሰዎች ለመጠበቅ እና የሰብዓዊ እርዳታ ሥርጭትን ለማስተባበር የተኩስ አቁም ማድረግ እጅግ ቁልፍ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸውን ገልጸዋል።

    የሲአይኤው ኃላፊ በርንስ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት እያደጉ ሲሆን፣ በጉዟቸው ከደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎች እና መሪዎች ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።

    በርንስ ሰኞ ዕለት እስራኤል እንደነበሩ ተዘግቧል።

  9. ፍልስጤማዊው ጋዜጠኛ ከ42 የቤተሰቡ አባላት ጋር ተገደለ

    ፍልስጤማዊው ጋዜጠኛ ሞሐመድ አቡ ሐሲር ከ42 የቤተሰቡ አባላት ጋር መገደሉን የሚሠራበት ተቋም አስታወቀ።

    የፍልስጤም ዜና ወኪል የሆነው ዋፋ ጋዜጠኛው ከቤሰብ አባላቱ ጋር የተገደለው የእስራኤል የአየር ኃይል መኖሪያ ቤቱን በመምታቱ ነው።

    ከሟች የቤተሰብ አባላት መካከል የጋዜጠኛው ልጆች እና ወንድሞች እንደሚገኙበት የዜና ወኪሉ ጨምሮ አስታውቋል።

    ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ እንደሚለው ከሆነ ሐማስ በእስራኤል ላይ መስከረም 26̀/2016 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በጋዛ እና እስራኤል 36 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች ተገድለዋል ብሏል።

  10. የእስራኤል ጦር የሐማስን ጠንካራ ይዞታ ተቆጣጠርኩ አለ

    የእስራኤል ጦር ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ በጋዛ ሰርጥ የሐማስ ጠንካራ ይዞታን መቆጣጠሩን አስታወቀ።

    በመግለጫው ጦሩ በሰሜናዊ ጋዛ የሐማስን ጠንካራ ይዞታ ከተቆጣጠረ በኋላ ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን፣ ላውንቸሮችን፣ መሳሪያዎችን እና መረጃ ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን መያዙን ይፋ አድርጓል።

    የእስራኤል ባሕር ኃይልም የቴክኖሎጂ ውጤት የሚገኙባቸው የሐማስ ወታደራዊ የመመልከቻ ቦታዎችን ስለመምታቱም ተገልጿል።

    ጦሩ ሐማስ ያከማቻቸው ተቀጣጣይ ነገሮች ፍንዳታ ፈጥረዋል ያለ ሲሆን፣ ይህም ቡድኑ በሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ አካባቢ መሳሪያ እንደሚያከማች ማሳያ ነው ብሏል።

  11. እስራኤል ከወር በፊት በሐማስ ጥቃት የተገደሉትን ሻማ በማብራት አሰበች

    እስራኤል ከአንድ ወር በፊት በሐማስ ጥቃት የተገደሉትን 1 ሺህ 400 በተለያዩ ዝግጅቶች አሰበች። በጥንታዊቷ ኢየሩሳሌም ከተማም በርካቶች ሻማ በማብራት አስበዋቸዋል።

    በርካቶች አንድ ሺህ 400 ሻማዎችን በማብራት እና 240 የሚሆኑትን ታጋቾች ፎቶ በግንቡ ላይ በፕሮጀክተር እንዲታይ ተደርጓል።

    በሌላ ስፍራም በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች ባዘጋጁት ዝግጅትም ጥቁር ሸሚዝ ለብሰው ብሔራዊ መዝሙር ዘምረዋል።

    በትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሰቲዎች የመታሰቢያ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው። በጋዛ ታግተው የሚገኙ 240 የሚጠጉ ቤተሰቦቻቸውም እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

  12. በጋዛ የሚገኙ የተመድ መጠለያዎች በመጨናነቃቸው ተፈናቃዮችን መቀበል ተስኗቸዋል ተባለ

    በጋዛ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያዎች በከፋ ሁኔታዎች በመጨናነቃቸው ተፈናቃዮችን መቀበል እንደተሳናቸው ተገለጸ። በርካታ ተፈናቃዮችም በተቋሙ አቅራቢያ በሚገኙ ጎዳናዎች ለመተኛት መገደዳቸውንም አስታውቋል።

    እስራኤል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰሜን ጋዛውያን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቷን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ወደ ደቡብ ጋዛ ሸሽተዋል።

    "የኛ መጠለያዎች በሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጨናንቀዋል" የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ትምህርት ቤቶች ወደ መጠለያዎች የተቀየሩ ሲሆን መያዝ ከሚችሉት በላይ በአራት እጥፍ እንደያዙም ጁሊየት ቱማ ተናግረዋል።

    ከሰሜን ጋዛ ከተፈናቀሉት 1.5 ሚሊዮን መካከል 717 ፍልስጤማውያን በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ ብሏል።

    የተባበሩት መንግሥታት መጠለያዎች ክፉኛ ተጨናንቀዋል። በደቡብ ጋዛ የሚገኙትም ጣቢያዎች አዳዲስ ተፈናቃዮች መቀበል አቁመዋል።

  13. እስራኤል በጋዛዎቹ ኻን ዩኒስ እና ራፋህ ባደረሰቻቸው ጥቃቶች በርካቶች ተገደሉ

    እስራኤል በደቡብ ጋዛዎቹ ኻን ዩኒስ እና ራፋህ ባደረሰቻቸው የአየር ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

    በሁለቱ የተለያዩ ጥቃቶች 23 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለውን የጋዛ ጤና ሚኒስትርን ዋቢ አድርጓል ኤኤፍፒ የእስራኤል መከላከያ ጥቃቶቹን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

    ከጥቃቶቹ ያገኘናቸው ምስሎች፦

  14. በኢራቅ እና በሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች 38 ጊዜ ተመትተዋል- ፔንታገን

    በኢራቅ እና በሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ከጥቅምት 6/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ 38 ጊዜ መመታታቸውን ፔንታገን አስታወቀ።

    አብዛኛዎቹ ጥቃቶች በሮኬቶች እና በድሮኖች እንደተፈጸሙ እና አድራሾቹም ከኢራን ጋር ግንኙነት ባላቸው ቡድኖች ነው ተብሎ እንደሚታመን የፔንታገን ቃለ አቀባይ ብሪክ ጄነራል ፓት ራይደር ተናግረዋል።

    ኢራን የጋዛን አስተዳዳሪ ሐማስ እና የሊባኖሱን ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህን ትደግፋለች። በነዚህ ጥቃቶች 24 አሰቃቂ የአዕምሮ ጉዳቶችን ጨምሮ ቢያንስ 45 የአሜሪካ ሰራተኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

    ቃለ አቀባዩ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ አራት ዋና አላማዎች አሏት ሲሉም ተናግረዋል።

    እነዚህም "በቀጣናው ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ኃይል አባላትን መጠበቅ፣ እስራኤል ከሐማስ ጋር ለምታደርገው ውጊያ ወሳኝ የደህንንት እርዳታ መስጠት፣ ታጋቾች እንዲለቀቁ ለእስራኤል አርዳታ መለገስ እንዲሁም ቀውሱ ከጋዛ አልፎ እንዳይዘመት ለመከላከል በአካባቢው ያለውን የኃይል ዝግጁነት ማጠናከር ነው" ብለዋል

  15. በጋዛ- እስራኤል የተከሰቱ የቅርብ ጉዳዮች

    የእስራኤል የማያባራ ጥቃቶች የቀጠሉባት ጋዛ ወደ ህጻናት የመቃብር ስፍራነት እየተቀየረች ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አሳስበዋል።

    ወር ባስቆጠረው የጋዛ- እስራኤል ቀውስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተፈናቅለዋል የከተማ ህንጻዎች ወደ አመድነት ተቀይረዋል።

    በቅርብ የተከሰቱ ጉዳዮችን እንዳስ፦

    • ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በጋዛ ሰርጥ ላይ አጠቃላይ የጸጥታ ኃላፊነቱ ላልተወሰነ ጊዜ የእስራኤል እንደሚሆን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከአሜሪካው ኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።
    • በተጨማሪም መስከረም 26 ከ1 ሺህ 400 በላይ ሰዎች በተገደሉበት የሐማስ ጥቃት የተወሰዱ ከ200 በላይ ታጋቾች ሳይፈቱ የተኩስ አቁም ጥሪ መደረጉንም ውድቅ አድርገዋል። ሆኖም ለሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ወይም ታቀቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ "በጊዜያዊነት ሊገታ" እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል።
    • የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጋዛ ያለውን ሁኔታ "የሰብዓዊነት ቀውስ" ሲሉ የጠሩት ሲሆን በማያባራ የእስራኤል ጥቃት ውስጥ ያለችውንም ጋዛ ወደ "ህጻናት የመቃብር ስፍራነት" እየተቀየረች ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
    • እስራኤል እየፈጸመቻቸው ባለቻቸው ጥቃቶች ከ4 ሺህ 100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ10 ሺህ በላይ ህጻናት መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ባለፉት ቀናት ጥቃቶቹ ክፉኛ ተጠናክረው ቀጥለዋል ተብሏል።
  16. ሐማስ በእስራኤሉ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን አልገደልኩም አለ

  17. ጋዛ ወደ ህጻናት የመቃብር ስፍራነት እየተቀየረች ነው- ተመድ

    የእስራኤል የማያባራ ጥቃቶች የቀጠሉባት ጋዛ ወደ ህጻናት የመቃብር ስፍራነት እየተቀየረች ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አሳሰቡ።

    ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጋዛ ሰርጥ ያለው ሁኔታ "ከሰብዓዊ ቀውስነት" አልፏል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

    "በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳጊ ሴቶች እና ወንዶች እየተገደሉ ነው እንዲሁም እየቆሰሉ መሆናቸው ሪፖርት እየተደረገ ነው" ሲሉም ነው ዋና ጸሐፊው የተናገሩት።

    የጋዛው ጦርነት "ዓለምን እያናወጠ" እና "የብዙኃን ንጹሓንን ህይወት እየቀጠፈ ነው" ሲሉም አክለዋል።

    እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከ4 ሺህ በላይ ህጻናት መሆናቸውን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

    አንድ ወር ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲያከትምም የተኩስ አቁም ይደረግ ሲሉም በድጋሜ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

    የተመዱ ዋና ጸሐፊ በዚሁ ንግግራቸው ሐማስ መስከረም 26 "በእስራኤል ሰላማዊ ዜጎች" ላይ ያደረሰውን "የሽብር ጥቃት" ኮንነዋል። "ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደልም ሆነ ለማሰቃየት ምንም ምክንያት ሊቀርብበት አይገባም" ሲሉም ነው የተናገሩት

  18. ደቡብ አፍሪካ ሁሉንም ዲፕሎማቶቿን ከእስራኤል ጠራች

  19. በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ10ሺህ አለፈ

    እስራኤል ጋዛ ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት በቀጠለበት ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ ማለፉን በጋዛ ያለው የሐማስ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

    የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ ቀን ከሌት ጥቃት ማካሄድ ከጀመረች ዛሬ አንድ ወር የደፈነ ሲሆን እስካሁን 10,022 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል::

    ትላንት እሁድ ምሽት እስራኤል ከፍተኛ ጥቃት በጋዛ ከፈጸመች በኋላ ነው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ይፋ የተደረገው።

    እስራኤል የሐማስ ወታደራዊ ቅጥር ጊቢን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዒላማዎች መምታቷን ገልጻለች።

    በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ዳይሬክተር ለቢቢሲ እንደገለጹት በቅርቡ ወደ 200 ሰዎች ናቸው የተገደሉት።

    የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ ተቋማትና እርዳታ ሰጭዎች በጋዛ በንጹኃን ዜጎች የደረሰውን “አሰቃቂ ግድያ” ሲሉ ገልጸዋል።

    ከሞቱት መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት ሕጻናት ናቸው።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ውስን ፖለቲከኞች የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ያወጣው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ስለቁጥሩ ተጠይቆ እንደገለጸው ከሆነ ግን የተጠቀሰው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ተአማኒነት ያለው ነው።

    እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት የሰነዘረችው በሐማስ ጥቃት 1,400 ሰዎች በእስራኤል ከተገደሉና ከ240 በላይ ሰዎች ከታገቱ በኋላ ነው።

  20. ብሊንከን ከመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት በኋላ ምን አሉ?

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የመካከለኛው ምሥራቅ ጎብኝታቸውን አጠናቀው ከቱርክ ወጥተዋል።

    በቀጠናው ስላለው ሁኔታ ያደረጉት ውይይት በሦስት ነጥቦች ላይ ያጠነጠነ እንደሆነ ተናገረዋል።

    እነዚህም እንዴት ሰብአዊ እርዳታ ማስፋፋት ይቻላል፣ እንዴት ግጭቱ እንዳይሰፋ ማድረግ ይቻላል እና ለእስራኤላውያን እና ፍልስጥኤማውያን ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ምን ማድረግ ይቻላል የሚሉት ናቸው ተብሏል።

    ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊደን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ቀጣዮቹን ነጥቦች ብሊንከን አንስተዋል።

    እርዳታ- አሜሪካ ተጨማሪ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ “በከፍተኛ ሁኔታ” እና “በተጨባጭ መንገድ” እየሠራች ነው ብለዋል።እርዳታ ለመጨመር ተስፋ ሰጭ ሥራዎች እንደተሠሩና “በቀጣይ ቀናት” ለውጥ እንደሚኖር ተናግረዋል። በጋዛ ፍልስጥኤማውያን የደረሰባቸውን “አስከፊ ጫና” አሜሪካ እንደምትረዳ ገልጸዋል።

    ታጋቾች- በሐማስ የታገቱ ሰዎችን “በሰላም ወደ ቤታቸው ለመመለስ” እየሠሩ እንደሆነና “ትኩረት የሚሰጡት” ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

    በጋዛ ያለው ሞት- እስራኤል “ሰብአዊ ቀውስን መቀነስ በምትችልበት መንገድ ላይ” እንደተነጋገሩ ገልጸዋል።

    ብሊንከን ግባቸውን አሳክተው ከሆነ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሁሉም ሂደት ላይ ያለ ነው” ብለዋል።