እስራኤል እና ሐማስ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን እየገለጹ ነው
ዛሬ ጠዋት እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከ10 ሰዓታት ከባድ ውጊያ በኋላ “የሐማስ ጠንካራ ይዞታ ነው” የተባለ ስፍራን ሠራዊቷ መቆጣጠሩን አስታውቃለች።
በተመሳሳይ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው አል-ቃሳም ብርጌድ ውጊያውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በእስራኤል ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጉዳት ዘርዝሯል።
በዚህም አል-ሻቲ ከተባለው ካምፕ አቅራቢያ ሦስት የእስራኤል ተሽክርካሪዎች እና አንድ ቡልዶዘር፣ ጋዛ ከተማ ውስጥ ሼክ ራድዋን ከተባለው ስፍራ በስተሰሜን አንድ ታንክ፣ ጋዛ ከተማ አል-ታዋም ውስጥ አንድ ታንክ ተዋጊዎቹ ማውደማቸውን አሳውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ቡድን አካል የሆነው አል-ቁዱስ ብርጌድ በጋዛ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንሳር በሚባል ስፍራ የእስራኤል ወታደራዊ ተሽክርካሪዎችን በቦምብ ማጥቃቱን ገልጿል።
ቡድኑ በተጨማሪም የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወል በተሰማባት የእስራኤሏ አሽዶድ ከተማ ላይ ሮኬቶችን መተኮሱን አሳውቋል።
ቢቢሲ በጦርነቱ ውስጥ ስለተፈጸሙት ጥቃቶች ወዲያውኑ ለማረጋገጥ አልቻለም።