ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠጋ
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የማህበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠግቷል። ይህንንም ተከትሎ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር "ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ" በትናንትናው ዕለት የብሄራዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በይፋ አስጀምረዋል።ዘመቻው አገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በሃላፊነትና በንቃት እንዲተገብር የሚያስችል እና ሰፊ ምርመራ በማድረግ የወረርሽኙን ሁኔታ ይበልጥ በማወቅ ቀጣይ ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል። "ማንም" የሚል ስያሜ የተስጠው ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዟል። አገሪቷ እስካሁን ድረስ 444 ሺህ 226 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።
የቀጥታ ሽፋን
በኤርትራ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 279 ደረሰ
ኤርትራ 14 ሰዎችን በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ ማረጋገጧን ገለፀች።
ይህም በአገሪቱ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥርን 279 ያደረሰው መሆኑን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያሳያል።
በተያያዘ ዜና በሆስፒታሎች ህክምና እየተከታተሉ የነበሩ 34 የኮሮናቫይረስ ህሙማን ሙሉ በሙሉ አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸው ተገልጿል።
በኤርትራ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ከታወቀበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 225 ደርሷል።
አፍሪካውያን የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደብ እንዳያነሱ ዓለም ጤና ድርጅት አሳሰበ
የዓለም ጤና ድርጅት አፍሪካውያን በኮቪድ-19 ምክንያት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ማላላታቸው ስርጭቱን እንደሚያሰፋው በመጥቀስ ምርመራ እና ንክኪ መለየት ላይ አጠናክረው እንዲሰሩ ለመንግሥታቱ ጥሪ አቀረበ።
የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺድሶ ሞይቲ "ሁላችንም ደህንነታችን ካልተጠበቀ ማንም ደህነቱ እንደማይጠበቅ" የአፍሪካ አገራት ማወቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በአህጉሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 800,000 የደረሰ ሲሆን አንዳንድ አገራት የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደብ ማላላት ጀምረዋል።
እንደ ሞሮኮ ያሉ አገራት ደግሞ ወረርሽኙ ዳግም መስፋፋት በመጀመሩ አላልተውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ዳግም አጥብቀዋል።
"እንደ አፍሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን እየተጠጋን ነው፣ አህጉሪቷ በወሳኝ ጊዜ ላይ ትገኛለች" ሲሉ የተናገሩት ዶ/ር ሞይቲ ናቸው።
አክለውም ''አምስት የአፍሪካ አገራት በመላው አፍሪካ አገራት በወረርሽኙ ከተያዙት ሰዎች 75 በመቶ ያህሉን አስመዝግበዋል'' ብለዋል።
እንደ አፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ከሆነ በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙና በዚሁ ምከንያት የተከሰቱ ሞቶችን ካስመዘገቡ አገራት መካከል ከአራቱ ሶስቱ ከደቡብ አፍሪካ፣ግብጽ፣ ናይጄሪያ አልያም ሱዳን የተመዘገቡ ናቸው ተብሏል።
ከኮሮናቫይረስ በእጅጉ እያተረፉ ያሉት ትልልቅ ድርጅቶች
350 ህሙማንን ከኮሮናቫይረስ ፈወስኩ የምትለው አወዛጋቢዋ ዶክተር
እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች!
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 413 ሺህ 397 የላብራቶሪምርመራተካሂዶ 16 ሺህ 615ሰዎች ኮቪድ-19 እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ከእነዚህም መካከል 263ያህሉ ህይወታቸውን አጥተዋል።
እስካሁን ድረስ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ያገገሙ 6763 ሰዎች ቢኖሩም የቫይረሱ ስርጭት ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ ነው። በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ስርጭቱ ከየትኛውም ስፍራ ልቆ ይታያል። የህክምና ባለሙያዎችም ሆኑ መንግሥት በነዋሪዎች ዘንድ አሁን የሚታየው ቸልተኝነት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል አዘውትረው ይናገራሉ። ስለዚህ የኮሮናቫይረስን ስርጭትን ለመከላከልና ባለበት ለማቆም እጃችንን በየጊዜው በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዲሁም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ተገቢ መሆኑን ሁሌም ማስታወስ ተገቢ ነው።
እናም ከዚህ ሰኣት ጀምሮ ከመላው ዓለም ከኮሮና ጋር የተገናኙ ዘገባዎችን በመሰብሰብ ወደ እናንተ እናደርሳለን።
መልካም ቀን!