ሜክሲኮ ከፍተኛ የሞት ቁጥር በማስመዝገብ ሦስተኛዋ አገር ሆነች
ሜክሲኮ በዓለማችን ላይ ከአሜሪካ እና ብራዚል በመቀጠል በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ ሞት በማስመዝገብ ሦስተኛዋ አገር ሆነች።
እስካሁን በአጠቃላይ 46 ሺህ 688 ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን፤ 424 ሺህ 637 ደግሞ በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።
ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ኪንግደም ነበረች ሦስተኛውን ቦታ ይዛ የነበረው። እስከ አርብ ድረስ የነበረው ቁጥርም 46 ሺህ 204 ነው።
የሜክሲኮ ባለስልጣናት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከተዘገበውም በላይ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ፕሬዝደንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ደግሞ እየተዳከመ የመጣውን ምጣኔ ሀብት እንዲያንሰራራ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ይፈልጋሉ።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ በዓለማችን ላይ እስካሁን 17.5 ሚሊየን ሰዎች በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሲሆን፤ 679 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አሜሪካ እስካሁን 153 ሺህ 415 ሞት ስታስመዘግብ ብራዚል ደግሞ 92 ሺህ 475 ሞት ማስተናገዷን አስታውቃለች።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የወረርሽኙ ጉዳት እስከ መጪዎቹ ዓሥርት ዓመታት ድረስ የሚስተዋል ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።