በስፋት የሚደረግ የኮቪድ-19 ምርመራ የበሽታው ምልክት የማያሳዩትንም ማካተት አለበት-ቶኒ ብሌር
የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚነስትር ቶኒ ብሌር በጅምላ የሚደረጉ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ምልክቱን የማያሳዩ ሰዎችንም ቢያካትት ሌላ የእንቅስቃሴ ገደብ ላለመጣል እንደሚያግዝ ተናገሩ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታይምስ ከተሰኘ የሬዲዮ ጣብያ ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ " 70 በመቶ ያህል ቫይረሱ ያለባው ሰዎች ምልክት አያሳዩም የሚል ግምት አለ፤ ስለዚህ ምልክት የሚያሳዩትን ብቻ የምንመረምር ከሆነ የምርመራ ስልቱ አብዛኛውን ህዝብ ያላማከለ ነው የሚሆነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ቶኒ ብሌር አክለውም ክትባት ወይንም ውጤታማ የሆነ ህክምና እስኪገኝ ድረስ የቫይረሱን ስርጭት በቁጥጥር ስር ለማዋል ያለው መፍትሄ ሰፊ ምርመራ ማድረግ ነው ብለዋል።
አክለውም በብዛት ምርመራ ማድረግ ዳግም የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣል እንደሚታደግና ምጣኔ ሃብቱንም ቫይረሱን እየተቆጣጠሩ ማስቀጠል ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ቶኒ ብሌር ቫይረሱ ጥሎን ስለማይሄድ እንዴት አብረን መኖር እንዳለብን ልንማር ይገባል ብለው ነበር።