የአውስትራሊያዋ ግዛት ቪክቶሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጅ ያወጣች ሲሆን አዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሏ ተገለፀ።
የቪክቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ዳንኤል አንድሪው እንዳሉት የተጣሉት ገደቦች ከእሁድ ምሽት 2
ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ።
በዚህ አዲስ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብም የግዛቷ ዋና ከተማ ሜልቦርን ነዋሪዎች በምሽት
መንቀሳቀስ አይችሉም ተብሏል።
ከዚህም ባሻገር ነዋሪዎች ቤት ውስጥ መቆየት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ነገር ግን በተወሰነ መልኩ ከቤታቸው
እንዲወጡ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።
በመሆኑም ነዋሪዎች ከቤታቸው ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው መጓዝ የማይፈቀድላቸው ሲሆን አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችሉትም በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይሆናል።
ለዕለት ተዕለት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመግዛትም በአንድ ጊዜ ወደ ገበያ ማዕከላት የሚሄደውም
ከአንድ ቤት አንድ ሰው ነው ተብሏል።
አውስትራሊያ ቀደም ብላ በወሰደችው እርምጃ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር በቫይረሱ የተያዙባት
ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው።
እስካሁን በአገሪቷ 17 ሺህ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 200 ሰዎች ደግሞ
በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ይሁን አንጂ በቪክቶሪያ ግዛት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ከቅርብ ሳምንታት
ወዲህ በአገሪቷ የተመዘገቡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም በዚሁ ግዛት የተገኙ ናቸው።
በመሆኑም ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ተጥለው የነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦች በድጋሚ ተጠናክረው እንዲመለሱ
ሆኗል።
እሁድ ዕለት በግዛቷ 671 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ሰባት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው
አልፏል።
ይህም በአጠቃላይ በግዛቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 11 ሺህ 557 ያደረሰው ሲሆን የሟቾቹ ቁጥርም 123 ሆኗል።
አስተዳዳሪው "በርካታ ሕዝብ በሚኖርባት ቪክቶሪያ ግዛት የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ውጤታማ
የነበረ ቢሆንም ውጤቱ ግን ዘገምተኛ ነው" በማለት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
አዲስ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብም ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ እንደሚቆይ አስተዳዳሪው
ገልፀዋል።