በኢትዮጵያ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

በኢትዮጵያ በየቀኑ በሚደረገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በሽታው የሚገኝባቸው ሰዎችና ከህመሙ የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እጨመረ ነው። በዚህም መሰረት የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዕሁድ ዕለት ባወጡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት እስካሁን 289,550 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ 7766 ሲገኝ 4550 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። የባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረግ እራስን ከቫይረሱ መከላከል እንደሚቻል ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ተመጋቢዎች 50 በመቶ ቅናሽ ሊሰጣቸው ነው

    በሬስቶራንቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩናይትድ ኪንግደም ነሀሴ ላይ ምግብ ቤቶች ለደንበኞቻቸው የ50 በመቶ ቅናሽ ሊያደርጉ ነው።

    ቅናሹን ይፋ ያደረጉት ቻንስለር ሪሺ ሱናክ እንዳሉት፤ ኮቪድ-19 ያስከተለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የተለያዩ ዘዴዎች ያስፈልጋሉ።

    በውሳኔው መሠረት፤ ነሀሴ ላይ ከሰኞ እስከ እሮብ ባሉት ቀናት በሬስቶራንቶች የሚመገቡ ሰዎች ቅናሽ ይደረግላቸዋል።

    ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች ከሦስት ወራት በኋላ ተከፍተዋል። ውሳኔው ዘርፉን ያነቃቃል ተብሎም ይጠበቃል።

    ቅናሹ መጠጥን ባይጨምርም፤ ለስላሳና ምግብ እስከ 10 ፓውንድ ይሸጣሉ።

  2. የኬንያ ትምህርት ቤቶች ለወላጆች ገንዘብ እንዲመልሱ ታዘዙ

    የኬንያ ትምህርት ሚኒስትር ጆርጅ ማጎሃ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኬንያ ትምህርት ሚኒስትር ት/ቤቶች ወላጆች የከፈሉትን ክፍያ እንዲመልሱ አልያም ደግሞ ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን እንዲያስተላልፉ አዘዋል።

    ሚኒስትር ጆርጅ ማጎሃ ማክሰኞ ዕለት ት/ቤቶች እስከሚቀጥለው ዓመት [ጥር] ድረስ ላይከፈቱ ይችላሉ ማለታቸውን ተከትሎ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው ይህን ያሳወቁት።

    ሚኒስትሩ፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኬንያ እየተስፋፋ እንጂ እየቀነሰ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።

    ሚኒስትሩ ሁሉም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካቋረጡበት እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል። አክለውም በዚህ ዓመት አገር አቀፍ ፈተናዎች እንደማይኖሩም ይፋ አድርገዋል።

    ወላጆች ክፍያን አስመልክቶ ያቀረቡትን ጥያቄ የመለሱት ሚኒስትሩ፤ ተማሪዎች ሁለት ወራት ብቻ ስለተማሩ ትምህርት ቤቶች ክፍያውን ይመልሱ አልያም ለሚቀጥለው ዓመት ያስተላልፉ ብለዋል።

    አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በበይነ-መረብ አማካይነት ስለተማሩ ክፍያ እየፈፀሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

    የኬንያ የተማሪ ወላጆች ማሕበር የበይነ-መረብ ትምህርት ቤት ለሚውሉ ተማሪዎች ጠቀሜው የጎላ ነው ይላል።

  3. በአሜሪካ በአንድ ቀን 60 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአገራትን ኦፊሴላዊ የኮሮናቫይረስ አሃዝ የሚያሳውቀው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በአሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ይፋ አድርጓል።

    በዓለም በአንድ ቀን ብቻ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል። ከዚህ በፊት በአንድ ቀን የተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር 55 ሺህ ነበር።

    ከሰዓታት በፊት አሜሪካ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 45 ሺህ ነበር። ነገር ግን ካሊፎርኒያና ቴክሳስ ግዛቶች እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ሰው ካስመዘገቡ በኋላ ነው ቁጥሩ የናረው።

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት [ማክሰኞ] አሜሪካ ቫይረሱን በተመለከተ "የተሻለ ሁኔታ" ላይ ነን ብለው ነበር።

    የአሜሪካ ተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ኃላፊና የትራምፕ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ፤ አገራቸው አሁንም ከወረርሽኙ 'ማጥ' አለመውጣቷን ይናገራሉ።

    አሜሪካ በኮቪድ-19 በተያዙ እና በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አንደኛ ናት።

    ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ፤ 131 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል።

  4. የኡጋንዳ ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች መንግሥትን ከሰሱ

    ሞተርሳይክሉ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኡጋንዳ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ተጨማሪ ሰው እንዳይጭኑ በመከልከላቸው መንግሥትን ከሰሱ።

    የሞተር ሳይክል ማህበሩ መንግሥት ሌሎች ቢዝነሶችን በተወሰነ ገደብ እንዲሰሩ ሲያደርግ እኛን በመከልከል አድሎ ፈጽሞብናል ብሏል።

    አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ሲባል የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሞሰቬኒ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪዎች በግማሽ አቅማቸው እንዲጭኑ አዟል።

    ነገር ግን የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎችን ፈቃድ ለመስጠት ጊዜው አይደለም ብለዋል፤ ምክንያቱም በአሽከርካሪውና በተሳፋሪው መካለከል ያለው ርቀት አነስተኛ በመሆኑ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎቹ እቃዎችን ብቻ እንዲያመላልሱ ነው ፈቃድ የሰጧቸው ነገር ግን የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ውሳኔውን ባለመቀበል እየተቃወሙ ነው፤ ክሳቸውም መንግስት ይህንን ውሳኔ ሲያስተላልፍ ሰው ባለመጫናችን ልናጣው የምንችለውን ገንዘብ የሚያካክስ ካሳ አልሰጠንም ብለዋል።

  5. በኢትዮጵያ ሰሞኑን በነበሩ አለመረጋጋቶች የተነሳ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገለፀ

    ኮቪድ-19

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ባለፈው ሳምንት ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የታየው መዘናጋት በቀጣይ ወራት በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋት መኖሩ ተገለፀ።

    በተለያዩ ምክንያቶች የሚታዩ መዘናጋቶች አሳሳቢ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ትናንት በነበራቸው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

    በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር ከ15 ቀን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት ገልፀዋል።

    ባለፈው ሳምንት በነበረው አለመረጋጋትና የተለያዩ ሁኔታዎች በሚፈለገው መጠን የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ አልተቻለም ነበር ያሉት ሚኒስትሯ በዚህም የተነሳ የምርመራው ቁጥር በከፍተኛ ሁናቴ ቀንሷል ብለዋል።

    ሚንስትሯ አክለውም በተደረጉ ሰልፎችም ሆኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎች የኮሮና መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃ ባለመወሰዱ በቀጣይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል።

    ዶ/ር ሊያ ታደሰ ቸልተኝነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ጠቅሰው “ከጥቂት ወራት በኋላ ወደኋላ የማንመለስበት ዋጋ ሊያስከፍለን ስለሚችል” በማለት ወጣቶች ጥንቃቀ እንደያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

    ወጣቶች የተጓዳኝ ሕመሞችና ላለባቸውና ለአረጋውያን ቫይረሱን አስተላልፈው ከባድ ችግር ሊከሰት ይችላል በማለት የጥንቃቄ መልእክቶች እነዲተገበሩ ሲሉ ተናግረዋል።

    ሰሞኑን አለመረጋጋት ተስተውሎባቸው በነበሩ አካባቢዎችም በትኩረት ምርመራ እንደሚደረግ ዶ/ር ሊያ ጨምረው ገልፀዋል።

  6. በመላ ኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከሰተ

  7. በአውስትራሊያ ሜልቦርን የአንድ ህንጻ ነዋሪዎች መግባት መውጣት ተከለከሉ

    ሜልቦርን

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    በአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ለሁለተኛ ጊዜ በተከሰተ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሙሉ ከተማዋ ለስድስት ሳምንት የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባታል።

    ነገር ግን 3000 ሰዎች የሚኖሩበት የመንግሥት አፓርትመንት ከሁሉም ጥብቅ የተባለው የእንቅስቃሴ ገደብ ከቅዳሜ ጀምሮ ተጥሎበታል።

    ከሌሎች የሜልቦርን ከተማ ነዋሪዎች በተለየ በዚህ አፓርትመንት ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች ለምንም ዓይነት ነገር መውጣት እንደማይችሉ ተገልጾ በፖሊስ ቀንና ለሊት እየተጠበቁ ይገኛሉ።

    በእነዚህ መኖሪያ ሕንጻዎች ላይ መንግሥት ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ ያደረገው ህንጻው ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል በቫይረሱ የተያዙ በርከት ብለው በመገኘታቸው ነው ተብሏል።

    መንግሥት በህንጻዎቹ መግባትና መውጣት መከልከሉን እንዳሳወቀ ፖሊስ አካባቢውን የከበበ ሲሆን፣ በርካታ ነዋሪዎች ምን እየተከናወነ እንደነበር ማወቅ አለመቻላቸውን ተናግረዋል። ከቤታቸው ለመውጣት ሲሞክሩም እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።

    መንግሥት በሕንጻዎቹ ውስጥ ለሚኖሩት ሰዎች የላከው ደብዳቤ እንደሚያሳየው የእንቅስቃሴ ገደቡ ከአምስት እስከ 14 ቀን የሚቆይ ይሆናል።

    በተጨማሪም በሕንጻው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው፣ እንግሊዘኛ ከማይነገርባቸው አገራት የመጡ ስደተኞች መሆናቸውም ተገልጿል።

    አንዳንዶቹ ከአፍሪካ፣ ከቬትናም እና ከቻይና የመጡ ስደተኞች ሲሆኑ በርካታ ወጣቶችና ጡረተኞች የሚኖርበትም መሆኑ ተገልጿል።

  8. የሕንዷ ሙምባይ ለነዋሪዎቿ በሙሉ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ይችላሉ አለች

    ሙምባይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሕንድ ትልቋ ከተማ ሙምባይ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጠቃች ስትሆን የከተማዋ ነዋሪዎች በአጠቃላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ እንደሚችሉ ገልፃለች።

    እስካሁን ድረስ ምርመራ ማድረግ የሚችሉት የበሽታውን ምልክት ያሳዩ ብቻ ሲሆኑ የሃኪም ማዘዣ ማምጣት ይጠበቅባቸው ነበር።

    86 ሺህ 500 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት ሙምባይ ግን ከአሁን በኋላ በዚህ መመሪያ ስር አትቆይም።

    በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም ላብራቶሪዎች፣ የግሎቹን ጨምሮ፣ ምርመራ ማከናወን እንደሚችሉ ተገልጿል።

    መንግሥት ለምርመራ የሚያስፈልገውን ዋጋ ተምኖ ማስቀመጡም ተነግሯል።

    ይህ የከተማዋ ውሳኔ የተሰማው ሕንድ የኮሮናቫይረስን የመመርመር አቅሟን ማሳደግ በመጀመሯና ያንንም ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች በቫይሱ መያዛቸው በመታወቁ ነው።

    በአሁኑ ሰአት በሕንድ ከ740 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲታወቅ ይህም በአለም ሶስተኛዋ ያደርጋለታል።

  9. 49 ሚሊዮን አፍሪካውያን ለከፋ ድህነት ይጋለጣሉ-የአፍሪካ ልማት ባንክ

    የአፍሪካ ልማት ባንክ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የአፍሪካ ልማት ባንክ 49 ሚሊዮን አፍሪካውያን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለከፋ ድህነት እንደሚጋለጡ አስታወቀ።

    የአፍሪካ ልማት ባንክ ማክሰኞ እለት እንዳለው ምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ በምጣኔ ሃብት ድቀቱ ክፉኛ ከሚመቱት የአህጉሪቱ ክፍሎች መካከል ናቸው።

    ባንኩ የአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት ከተንኮታኮተበት በመጪው 2021 ያገግማል ሲል ተንብይዋል።

    የአፍሪካ ባንክ አህጉሪቱ በ2020 በ3.4 በመቶ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ እንደሚቀንስ ገልጿል።

    በአፍሪካ በምጣኔ ሃብታቸው ጥንካሬ የሚጠቀሱት ደቡብ አፍሪካ፣ ነዳጅ ላኪዋ ናይጄሪያ፣ አንጎላ እና አልጄሪያ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጠቁ አገራት ናቸው።

    በተለያዩ አገራት የተጣሉት የእንቅስቃሴ ገደቦች ምጣኔ ሃብቱን በማሽመድመድ በርካቶችን ሥራ አጥ አድርገዋል።

    የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤም ኤፍ እንዳለው የአለም ምጣኔ ሃብትም በ4.9 በመቶ እንደሚቀንስ አስታውቋል።

  10. በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን አለፈ

    በአሜሪካ ጭምብል ያጠለቀች ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን ማለፉን ከኒውዮርክ ታይምስና ኤንቢሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

    በትናንትናውም ዕለት 46 ሺህ 500 አዲስ ሰዎች መያዛቸውንም ኤንቢሲ ዘግቧል።

    አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ ስትሆን በአለምም ቀዳሚዋ ናት።

  11. በበይነ መረብ የሚማሩ የውጭ አገር ተማሪዎች ከአሜሪካ እንዲወጡ መወሰኑ ቁጣን ቀሰቀሰ

  12. የዚምባብዌ ጤና ሚንስትር ከኃላፊነታቸው ተነሱ

    የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የጤና ሚኒስትሩን ኦባዲሃ ሞዮን "ያልተገባ ጠባይ አሳይተዋል" በሚል ከኃላፊነታቸው አነሱ።

    ሞዮ ከስልጣን መነሳታቸውን የሚገልፀው ደብዳቤ " ከመንግሥት ሚኒስትር የማይጠበቅ ያልተገባ ባህሪ በማሳየታቸው ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ካላቸው የመንግሥት ኃላፊነት ተነስተዋል" ይላል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    ባለፈው ወር፣ የጤና ሚኒስትሩ ከኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ግዢ ጋር በተገናኘ ሙስና ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል በቁጥጥር ስር ውለው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ወጥተዋል።

    የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለመግዛት በወጣው ጨረታ ለወደቁ ሶሰት ድርጅቶች ግዢውን እንዲያከናውኑ ፈቅደዋል ተብለው ነበር ክስ የቀረበባቸው።

  13. የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስ በአየር ወለድ ብናኞች ሊተላለፍ እንደሚችል ተናገረ

  14. የኮሮናቫይረስ ሐሰተኛ ዜና በሕንድ ያስከተለው ጉዳት

  15. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ወዳጆች!

    በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ከ260 ሺህ በላይ ናሙናዎች ተመርምረው 6 ሺህ 774 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ይህ የምርመራ ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ የነበረ ሲሆን የመመርመሪያ ላቦራቶሪዎችም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፉ ነበር። ባለፈው ሳምንት ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በምርመራ፣ ውጤት በማሳወቅ እንዲሁም የቫይረሱን መከላከል ትምህርቶችን እንደ ከዚህ ቀደሙ በስፋት ማድረስ ላይ ክፍተት ታይቷል።

    ቢሆንም አሁንም ድረስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

    እኛም ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ከመላው ዓለም የምንሰበስባቸውን የኮሮናቫይረስ አበይት ዜናዎችን ወደ እናንተ ማድረስ እንጀምራለን።

    አብረን እንቆይ!