በኢትዮጵያ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

በኢትዮጵያ በየቀኑ በሚደረገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በሽታው የሚገኝባቸው ሰዎችና ከህመሙ የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እጨመረ ነው። በዚህም መሰረት የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዕሁድ ዕለት ባወጡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት እስካሁን 289,550 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ 7766 ሲገኝ 4550 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። የባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረግ እራስን ከቫይረሱ መከላከል እንደሚቻል ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ቤልጂየም ሌይስተርን የረገጡ ተጓዦች ተለይተው እንዲቆዩ አዘዘች

    ቤልጂዬም

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የቤልጂየም መንግሥት በቅርቡ የእንግሊዟን ሌይስተር ከተማን የረገጡ ተጓዦች ወደ የግዳጅ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

    በምሥራቅ ሚድላንድስ ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደ አዲስ ማገርሸቱን ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።

    የቤልጂየም መንግሥት ጥቂት ከተሞችን 'ቀይ ቀጣና' ብሎ ሰይሟቸዋል። እነዚህ ከተሞች ወረርሽኙ እንደ አዲስ ያገረሸባቸው ናቸው።

    በዚህ ቀጣና ውስጥም የተወሰኑ የፖርቹጋልና የሰሜን ስፔን ከተሞች ይገኙበታል።

    በብራሰልስ አውሮፕላን ማረፊያ ከሌይስተር ከተማ ለሚመጡ መንገደኞች የግዳጅ ለይቶ ማቆያ እንደተዘጋጀ የሚያሳይ መልዕክት ይለጠፋል ተብሎ ይጠበቃል።

    የእንግሊዟ የሌይስተር ከተማ ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋባት በመሆኑ ባለስልጣናት በሽታውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።

  2. ኤምሬትስ በኮቪድ-19 ሰበብ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን ሊቀንስ ነው

    የኤምሬት አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኤምሬትስ አየር መንገድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ተጽእኖ ምክንያት ዘጠኝ ሺህ የሚደርሱ ሠራተኞቹን ሊቀንስ መሆኑን ፕሬዝዳንት ተናገሩ።

    የረጅም ርቀት ጉዞዎችን በማድረግ በዓለማችን ግዙፍ ከሚባሉት አየር መንገዶች አንዱ የሆነው ኤምሬትስ ይህን ያህል ሠራተኞችን ሊቀንስ መሆኑን ሲያስታውቅ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።

    እስካሁን ኤምሬትስ ካሉት 4,500 አብራሪዎች ውስጥ ቢያንስ 700 ለሚሆኑት ቅጥራቸው እንደሚቋረጥ በዚህ ሳምንት አሳውቋል። ይህም የኮሮናቫይረስ ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ቢያንስ 1,200 የሚደርሱት ከሥራ እንደሚቀነሱ ተነግሯቸዋል ማለት ነው።

    በአብራሪዎቹ ላይ የተደረገው ከሥራ የመቀነስ ውሳኔ ያተኮረው ከቦይንግ አውሮፕላኖች ይልቅ በዋነኝነት ኤርባስ የተባሉትን አውሮፕላኖች በሚያበሩ ፓይለቶች ላይ ነው ተብሏል።

    ከአብራሪዎቹ በተጨማሪ ኤምሬትስ በሺህዎች የሚቆጠሩ የበረራ ሠራተኞችንም እንደቀነሰ ተነግሯል።

  3. የዕለተ ቅዳሜ ሐምሌ 04/2012 የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምንአደራችሁ?

    ዕለተ ቅዳሜ ሐምሌ 04/2012 ዓ.ም

    ከቢቢሲ አማርኛ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በየደቂቃው የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን በተለይ በዚህ ገጽ ላይ በቀጥታ እናቀርባለን።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የተመለከቱ ጠቃሚና ትኩስ መረጃዎችን ለማግኘት አመቺ በሚሆንላችሁ ጊዜ ሁሉ ይህንን የቀጥታ ዘገባ ገጽ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

    በዚሁ አጋጣሚ በባለሙያዎች የሚመከሩ የበሽታውን የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በመድረግ እራሳችሁንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንድትጠብቁ እያስታወስን መልካም ዕለት እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።

    ቢቢሲ አማርኛ
  4. በዓለም በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 228,102 ደረሰ

    ሸማች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው፤ ባለፉት 24 ሰዓታት በመላው ዓለም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 228,102 ደርሷል። ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው።

    ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን የተመዘገቡት በአሜሪካ ነው። በቀጣይነትም በብራዚል፣ በሕንድ እና በደቡብ አፍሪካ በርካታ ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዋል።

    ከዚህ ቀደም በአንድ ቀን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር 212,326 ነበር።

    የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 12.1 ሚሊዮን ናቸው ብሏል። ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ግን ቁጥሩ 12.3 ሚሊዮን ነው ይላል።

  5. ካዛኪስታን 'ያልታወቀ የሳንባ ምች ወረርሽኝ' አልተከሰተብኝም ስትል አስተባበለች

    ካዛኪስታን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ካዛኪስታን 'አዲስ የሳንባ ምች በሽታ ወረርሽኝ ታይቶባታል' ሲሉ የቻይና ባለሥልጣናት ያወጡት መረጃ ሐሰት ነው ስትል አስተባበለች።

    በካዛኪስታን የቻይና ኤምባሲ አዲስ ምንነቱ ያልታወቀና ገዳይነቱ ከኮቪድ-19 በላይ የሆነ የሳንባ ምች በሽታ ተከስቷልና ተጠንቀቁ የሚል መልዕክት ለዜጎቹ አስተላልፏል።

    የካዛኪስታን ጤና ሚኒስትር ዘገባው 'ሐሰት' ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

    ካዛኪስታን ከቅርብ ጊዘኤ ወዲህ ኮሮናቫይረስ እንደ አዲስ ማገርሸቱን ተከትሎ አገር አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ ለሁለተኛ ጊዜ ጥላለች።

    እንደ ጤና ሚኒስቴር ዘገባ ከሆነ አገሪቱ እስካሁን ድረስ 55 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ስታረጋግጥ 264 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሞተዋል።

  6. በሩስያ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች እየጨመሩ ነው

    በሩስያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየናረ መጥቷል። ባለፉት 24 ሰዓታት በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 6,635 ደርሷል።

    ባጠቃላይ በበሽታው የተያዙት 713,936 ሰዎች ናቸው።

    በአንድ ቀን የሞቱት 174 ሰዎች ሲሆኑ እስካሁን በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች 11,017 ደርሰዋል።

    የሩስያ የስታትስቲክስ ተቋም እንዳለው፤ በዚህ ዓመት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ18,375 የጨመረ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል 7,444 የሚሆኑት ያለፉት በኮቪድ-19 ሳቢያ ነው።

  7. "የአፍሪካ የጤና ባለሙያዎች መገልገያ ሊሟላላቸው ይገባል"

    ሀኪሞች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኬንያ በኮሮናቫይረስ የመጀመሪያው ዶክተር መሞታቸውን ተከትሎ፤ የህክምና ባለሙያዎች ለአደጋ የመጋለጣቸው ጉዳይ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጓል።

    አሁን ላይ በኬንያ ወደ 300 የሚደርሱ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

    በኬንያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የሀኪሞች መገልገያ ቁሳቁስ (ፒፒኢ) እጥረት የጤና ባለሙያዎች እሮሮ ከሆነ ሰነባብቷል።

    በአህጉሪቷ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ማህበራት አባሎቻቸው ከበሽታው ራሳቸውን የሚከላከሉበት ግብአት ባለመሟላቱ በበሽታው የሚያዙ ባለሙያዎች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል።

    በዚምባብዌ 21 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

    የአህጉሪቱ የጤና ባለሙያዎች በተሻለ ሁኔታ መገልገያ ሊሟላላቸው እንደሚገባም የተለያዩ የሙያ ማህበራት እየጠየቁ ነው።

  8. በኢትዮጵያ ከ8 እና ከ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጪ ወደ ቀጣይ ክፍል እንዲያልፉ ተወሰነ

    ትምህርት ቤት

    የፎቶው ባለመብት, SEAN GALLUP

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የትምህርት ሂደት ላይ ባስከተለው መስተጓጎል ሳቢያ ክልላዊና አገር አቀፍ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች በስተቀር ሁሉም ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲያልፉ የትምህርት ሚኒስቴር ወሰነ።

    በዚህም መሰረት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ያለምንም ፈተና ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲዘዋወሩ ቢወሰንም የማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጣቸውም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    ከዚህ ውጪ የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ክልላዊና አገር አቀፍ ፈተና ለሚወስዱት ተማሪዎች የ45 ቀናት የማካካሻ ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ ለፈተናዎቹ እንደሚቀመጡ ተገልጿል።

    ከዚህ በተጨማሪም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግቢያ ፈተናን በበይነ መረብ ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የቀጣይ ዓመት የሁሉም ትምህርት ቤቶች ምዝገባ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የሚጀመር ሲሆን ትምህርት ቤቶችም በተማሪዎች ክፍያ ላይ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

  9. በኢትዮጵያ ተጨማሪ 282 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ሲገኝ 239 ሰዎች አገገሙ

    የኮሮና መግለጫ

    ባለፉት 24 ሰዓታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተሰባሰቡ 5 ሺህ 139ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 282 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ተገለጸ።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸውከዚህ በፊት በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ተጨማሪ 239 ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 4152አድርሶታል።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 179ኙ ከአዲስ አበባ፣ 75ቱ ከድሬዳዋ፣ 15ቱ ከጋምቤላ፣ 7ቱ ከትግራይ፣ 2ቱ ከኦሮሚያ፣ 2ቱ ከአፋር፣ 1 ከቤኒሻንጉልና 1 ከሲዳማ ክልሎች ናቸው።

    ዕለታዊው መግለጫ ከዚህ በተጨማሪም በዛሬው ዕለት ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሞት አለመመዝገቡን አመልክቷል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን 281 ሺህ 069 ናሙናዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ በአጠቃላይ 7 ሺህ 402 ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ተገኝተዋል።

  10. ጀርሲ ለነዋሪቿ 100 ዶላር በነፍስ ወከፍ ልታድል ነው

    ጀርሲ

    የጀርሲ ምጣኔ ሀብት እንዲነቃቃ ለእያንዳንዱ ነዋሪ 100 ዶላር እንደሚሰጥ የደሴቷ መሪ ተናገሩ።

    ኮሮናቫይረስ ካሳደረው ተጽዕኖ ለመላቀቅ 150 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን፤ በነፍስ ወከፍ የሚሰጠው 100 ዶላር ደግሞ መንግሥት ለማገገሚያ የበጀተው 11 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ይካተታል።

    ገንዘቡ ለነዋሪዎች የሚሰጠው መስከረም ላይ ነው። የሁለት ወራት ጊዜ ገደብም አለው።

    ገንዘቡ በድረ ገጽ ለመገበያየት፣ ለቁጠባ ወይም ለቁማርም ሊውል ይችላል።

    የሕዝብ ተወካዩ ጆን ፎንዴ እንዳሉት፤ ገንዘቡ ድጎማ ሳይሆን ደሴቷ ላይ የሚፈስ ኢንቨስትመንት ነው።

    በጀርሲ በበሽታው ሳቢያ 15 ሰዎች ሞተዋል።

  11. በእንግሊዝ ውስጥ የቤት ለቤት ምርመራ ሊጀመር ነው

    ምርመራ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    እንግሊዝ ውስጥ ቤት ለቤት እየተሄደ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።

    በአገሪቱ የመጀመሪያው ነው በተባለው ይህ የምርመራ ዘመቻ በእንግሊዟ ከተማ ሌስተር እንደሚካሄድ ተነግሯል።

    የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ቡድን አባላትና በጎ ፈቃደኞች የህመሙ ምልክት ያልታየባቸው ሰዎችን ጨምሮ ለመመርመር የሚያስችሉ የመመርመሪያ መሳሪያዎች እያቀረቡ ነው።

    በሌስተር ከተማ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በድንገት በመጨመሩ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው ከሳምንት በፊት ነበር።

    የከተማዋ ከንቲባ ሰር ፒተር ሶልስቢ እንደተናገሩት የሚደረገውን የምርመራ ቁጥር መጨመር በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለመቀነስ ብቸኛው መንገድ ነው።

  12. በዚምባብዌ 21 የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ተያዙ

    ዚምባብዌ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ዚምባብዌ ውስጥ ቡላዋዮ በተባለች ከተማ 21 የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 እንደተያዙ የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር አስታወቀ።

    ባለሙያዎቹ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲሆን፤ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል።

    ከጥቂት ቀናት በፊት የአገሪቱ የነርሶች ማኅበር ሐኪሞች የሚለብሷቸው የመከላከያ መገልገያዎች (ፒፒኢ) እጥረትና አነስተኛ ደሞዝን በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ ጠርተው ነበር።

    በቡላዋዮ ከተማ ረቡዕ ብቻ 51 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በዚምባብዌ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 926 ደርሰዋል። ከፊል የእንቅስቃሴ ገደቡ አልተነሳም።

    አሁኑ ያለው ቀዝቃዛ ወቅት የበሽታውን ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምረው ይችላል ተብሎም ተሰግቷል።

  13. ሩዋንዳ ከኮቪድ-19 ህክምና መስጫ ያመለጡ ሰዎችን አሰረች

    የሩዋንዳ ፖሊስ ከኮቪድ-19 ህክምና መስጫ ያመለጡ አራት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

    ግለሰቦቹ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ከሚገኝ ህክምና መስጫ ባለፈው ረቡዕ ካመለጡ በኋላ በማግስቱ ተይዘዋል።

    ሰዎቹ ማምለጣቸው እንደተሰማ የጸጥታ ኃይሎች በመተባበር እንደያዟቸው የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። የሰዎቹ ማንነት ይፋ ከተደረገ በኋላ በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ሊያዙ ችለዋል።

    የጤና ባለሙያዎችና ፖሊሶች ከአራቱ ግለሰቦች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ቫይረሱን እንዳያሰራጩ እያፈላለጓቸው ይገኛሉ።

    በሩዋንዳ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1,210 ሲሆን፤ እስካሁን ሁለት ሰዎች በበሽታው ሞተዋል።

  14. ኬንያ በኮቪድ-19 የመጀመሪያዋን የሕክምና ባለሙያ አጣች

    የኬንያ ዶክተሮች ባልደረባቸው ኮሮናቫይረስ ከተያዘች በኋላ በመሞቷ ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው።

    ዶክተሯ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት እንደነበረችና በደንበኞቿ ተወዳጅ እንደነበረች ተገልጿል።

    ባልደረቦቿም "ወጣትና በርካታ ነገር ልታበረክት የምትችል" በሚልም አሞካሽተዋታል።

    የኬንያ ጤና ሚኒስትር ከአስር ቀን በፊት 186 የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን አስታውቆ የነበረ ሲሆን በወቅቱ አንድም የሞተ ባለሙያ እንደሌለ ተገልጾ ነበር።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  15. የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ደህና መሆናቸውን ገለፁ

    የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ

    የፎቶው ባለመብት, facebook.com/jairmessias.bolsonaro

    የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ በፌስቡክ ሰሌዳቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በኮሮናቫይረስ ቢያዙም "ደህና መሆናቸውን" ተናገሩ።

    ማክሰኞ እለት ከፍተኛ ትኩሳትና ሳል ስለነበራቸው ሲመረመሩ በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋገግጦ ነበር።

    ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ምንም እንኳ ፈዋሽነቱ ባይረጋገጥም፣ እርሳቸውና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፐ የሚያደናነቁትን የወባ መድሃኒት፣ ሃይድሮክሎሮክዊንን ስላለው ጥቅም ተናግረዋል።

    ቦልሶናሮ በተደጋጋሚ የኮሮናቫይረስ ያለውን ጉዳት በማጣጣልና በአገራቸው የተለያዩ ክልሎች የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደብ ሲያጣጥሉ ነበር።

    • አፍሪካ የኮቪድ-19 ክትባት ሙከራ ላይ በትብብር መስራት ጀመረች

      መርፌ ሊወጋ የተቀመጠ አፍሪካዊ

      የፎቶው ባለመብት, Reuters

      የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኮቪድ-19 ክትባት ምርምር ላይ በትብብር መስራት ጀመረ።

      ኮሚሽኑ የኮሮናቫይረስ ክትባት የሚደረግ ሙከራ በተቻለ ፍጥነት አስር ያህል የምርምር ሙከራዎችን ለማድረግ ማቀዱ ተሰምቷል።

      ይሀ አዲሱ ትብብር የሚመራው በአፍሪካ የበሽታ መቆጣጣርና መከላከል ነው ተብሏል።

      ይህ የኮሚሽኑ ጥምረት የዓለም አቀፉን የክትባት አምራቾች፣ በገንዘብ የሚደግፉ አካላት እና የአፍሪካ ድርጅቶችን ወደ አንድ በማምጣት አፍሪካ ውስጥ የሚደረገው የኮሮናቫይረስ ምርምርና ሙከራ ውጤታማ እና በቂ መረጃ እንዲገኝ ይሰራል ተብሏል።

      የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ክትባት መገኘቱ ያለውን ጠቀሜታ ሲናገር " ስርጭቱን ለመቀነስ፣ ሞትን ለመከላከል እና የአፍሪካን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁናቴ መልሶ እንዲያገግም መሰረት በመጣል" ያግዛል ብሏል።

      ኮሚሽኑ ክትባቱን ለማግኘት "ፈጠራ እና ትብብር" መታከል እንዲሁም አፍረካ ውስጥ ማምረት መቻል ወሳኝ መሆኑን አስቀምጧል።

      የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አክሎም የአፍሪካ ሳይንቲስቶች እና የጤና ባለሙያዎች ድጋፍና አስተዋጽኦ እንደሚፈልግ ጠቅሶ፣ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት አለብን ብሏል።

      ደቡብ አፍሪካና ግብጽ ክትባቱን በሰው ላይ ሙከራ እየተካሄደባቸው ከሚገኙ አገራት መካከል ናቸው።

    • በአሜሪካ በኮቪድ-19 በአንድ ቀን ብቻ ከ60ሺህ በላይ ሰዎች ተይዘዋል

      በአሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ ቢያንስ 60 ሺህ 565 አዳዲስ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ማግኘቷን አሳወቀች።

      ሮይተርስ በአሜሪካ በቫይረሱ አዳዲስ በሚያዙ ሰዎችም ሆነ በሟቾች ቁጥር ለተከታታይ ሁለት ቀናት ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን ዘግቧል።

      ለተከታታይ ሶስት ቀናት ደግሞ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ800 በላይ ሆኗል።

      ከሰኔ ወዲህ ከፍተኛው ነው የተባለው ይህ የሟቾች ቁጥር በፍሎሪዳ 120፣ ካሊፎርኒያ 136 ሞቶች ተመዝግበዋል።

      ካሊፎርኒያ ፍሎሪዳ እና ቴክሳስ በቅርቡ የቫይረሱ ስርጭት ከፍ እያለባቸው ከሚገኙ ግዛቶች መካከል ናቸው።

      በአሜሪካ እስካሁን ድረስ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ቫይረሱ ከመቀነስ ይልቅ መጨመር እያሳየ ነው።

      ባለፉት ሶስት ቀናት በአማካኝ በ900 ሰዎች በላይ በቫይረሱ መያዛቸው ሲገለፅ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ለቁጥሩ መጨመር የሚደረጉ ምርመራዎች መጨመርን በምክንያትነነት አስቀምጠዋል።

      የ X ይዘትን ይለፉት
      ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

      ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

      ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

      የ X ይዘት መጨረሻ

    • ሲንጋፖር ምርጫ እያካሄደች ነው

      የሲንጋፖር ምርጫ

      የፎቶው ባለመብት, Reuters

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአለም ስጋት ሆኖ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ሲንጋፖር አጠቃላይ ምርጫ እያካሄደች ነው።

      ወረርሽኙን ተከትሎ የተለያዩ አገራት በእቅድ ይዘውት የነበረውን ምርጫ ቢያራዝሙም ሲንጋፖር ምርጫ ለማካሄድ ከወሰኑት ጥቂት አገራት አንደኛዋ ሆናለች።

      መራጮች የፊት ጭምብልና ጓንት ማድረግ አስገዳጅ ሲሆን የሚመርጡበትም ሰዓት ተወስኖላቸዋል። አገሪቷም ጥብቅ ከሚባሉ መመሪያዎች ጋር ነው ምርጫውን እያካሄድኩ ያለሁት ብላለች።

      በእስያ ካሉ ሃገራት በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጠቃችው ሲንጋፖር 45 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

      ሲንጋፖር ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃነቷን ካገኘችበት እለት ጀምሮ ፒፕልስ አክሽን ፓርቲ በሚባለው ፓርቲ እየተመራች ሲሆን አሁንም ቢሆን ፓርቲው ያሸንፋል ተብሎ ይጠበቃል።

    • በቫይረሱ ምክንያት በቤት እስር የቆየው የቀድሞ የትራምፕ ጠበቃ እስር ቤት ተመለሰ

    • በሶሪያ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ይጨምራል የሚል ስጋት ተፈጥሯል