በኢትዮጵያ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው
በኢትዮጵያ በየቀኑ በሚደረገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በሽታው የሚገኝባቸው ሰዎችና ከህመሙ የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እጨመረ ነው። በዚህም መሰረት የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዕሁድ ዕለት ባወጡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት እስካሁን 289,550 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ 7766 ሲገኝ 4550 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። የባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረግ እራስን ከቫይረሱ መከላከል እንደሚቻል ይመክራሉ።
የቀጥታ ሽፋን
እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ወዳጆች!
ባለፈው ሳምንት ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የታየው መዘናጋት በቀጣይ ወራት በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋት መኖሩ የተገለፀው በዚህ ሳምንት ነው።
ባለፈው ሳምንት በነበረው አለመረጋጋትና የተለያዩ ሁኔታዎች በሚፈለገው መጠን የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ አልተቻለም ነበር ያሉት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ በዚህም የተነሳ የምርመራው ቁጥር በከፍተኛ ሁናቴ ቀንሷል ብለው ነበር።
በወቅቱ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ቸልተኝነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ጠቅሰው "ከጥቂት ወራት በኋላ ወደኋላ የማንመለስበት ዋጋ ሊያስከፍለን ስለሚችል" በማለት ወጣቶች ጥንቃቄ እንደያደርጉ ጥሪ አቅርበው ነበር።
መደረግ ካለባቸው ጥንቃቄዎች መካከል ደግሞ እጅን በሚገባ መታጠብ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ናቸው።
እናንተ የቢቢሲ ቤተሰቦች የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር እየተከታተላችሁ ራሳችሁንም ጤና፣ ወዳጆቻችሁም ደህና ሆነው እንዲቆዩ ታደርጋላችሁ የሚል እምነት አለን።
ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ከአገር ውስጥና ከዓለም ዙሪያ ከኮሮናቫይረስ ጋር ያሉ አበይት ዜናዎችን እናቀርባለን።
መልክም ቀን!

የፎቶው ባለመብት, West Gonder Zone
በደቡብ አፍሪካ ለኮሮናቫይረስ ህሙማን 1.5 ሚሊዮን መቃብር ይዘጋጅ መባሉ ፍርሃትን አነገሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የደቡብ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት ማዕከል የሆነችውጋውተንግ ግዛት የጤና ኃላፊ ባንዲሌ ማሱኩ ለኮሮናቫይረስ ህሙማን 1.5 ሚሊዮን መቃብር ይዘጋጅ ማለታቸው ፍራቻን አንግሷል።
የጤና ኃላፊው ይህንን ያሉት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ሲሆን ፤ ግዛቲቷ ይህን ያህል የመቃብር ቦታዎች ማዘጋጀት ብትችልም እስካሁን እየተቆፈሩ ያሉ መቃብሮች በቁጥር ትንሽ መሆናቸውንም ተገልጿል።
የጤና ቢሮው ቃለ አቀባይ ክዋራ ኬካና ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ምንም እንኳን ስለ ሞት ማውራት ባለው ባህል ለህዝቡ እንደ ነውር የሚታይና ምቾት የሚነሳ ቢሆንም ካለው እውነታ ጋር ተያይዞ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ስለሚሞቱ ሰዎች መወያየት አለብን" ብለዋል።
ቃለ አቀባዩ አክለውም በግዛቲቷ ውስጥ ያሉ ቦታዎች ለሚሞቱ ሰዎች ቅድመ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ቢያስፈልግ በሚልም እየተለዩ ነው። ከዚህም ጋር ጎን ለጎንም ህይወት የማዳኑ ተግባርም ይቀጥላል ብለዋል።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኮሮና ክፉኛ የተጠቃችው የጆሃንስበርግ ከተማን የምታጠቃልለው የጋውተንግ ግዛት ናት።
ህዝቡ ጥቅጥቅ ባለ ሁኔታ ከመኖሩም አንፃር ወረርሽኙ ከዚህ በከፋ ሊሰራጭም ይችላል እየተባለ ነው።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 225 ሺህ ሲሆን ከነዚህም መካከል 107 ሺህ አገግመዋል፤ 3 ሺህ 600 ዜጎቿም ህይወታቸውን አጥተዋል።
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ7 ሺህ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ 147 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገለፀ።
እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 7120 ደርሷል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ለ3 ሺህ 476 ናሙናዎች ምርመራ መደረጉንም የጤና ሚኒስቴር እና በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት ያሳያል።
ከዚህም በተጨማሪ በዛሬው ዕለት 473 ሰዎች ማገገማቸውን ተከትሎም ቁጥሩን 3 ሺህ 913 አድርሶታል።
ባለፉት 24 ሰአታት ከአስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ አራት ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለ275 ሺህ 930 ናሙናዎች ምርመራ አድርጋለች።
ደቡብ ሱዳን አየር ማረፊያዋን ከፈተች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ ሱዳን የኮሮናቫይረሰን ስርጭት ለመግታት አቋርጣው የነበረውን በረራ መጀመሯን እንዲሁም አየር ማረፊያዋን መክፈቷን የአገሪቷ የአቪየሽን ባለስልጣን አስታውቋል።
የጁባ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዋና ዳይሬክተር ኩር ኮል በትናንትናው ዕለት ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት ከአለም አቀፍ በረራዎች ውስጥ በማረፍ ቀዳሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆኗል። አየር መንገዱም በየቀኑ በረራዎችን እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
የሱዳኑ ባድር እንዲሁም የግብፅ አየር መንገዶችም እንዲሁ ወደ ጁባ የሚያደርጓቸውን በረራዎችን ጀምረዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፍላይ ዱባይም ወደ ጁባ የሚያደርገውን በረራ በነገው እለት እንደሚጀምርም አስታውቋል። በአየር ማረፊያው የሚያርፉ መንገደኞች በሙሉ ራሳቸውን ለአስራ ቀናት ማግለልና እንዲሁም ሌሎች መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
"የአየር ማረፊያችን ካሁን በኋላ ያለምንም ገደብ ክፍት ነው። ነገር ግን የትኛውም ወደ አገራችን የሚገባ መንገደኛ፣ የደቡብ ሱዳን ዜጋም ይሁን የውጭ አገር የጤና ሰርቲፊኬት ማምጣት እንዲሁም ለአስራ ቀናት ያህል ራሳቸውን ማግለል ይጠበቅባቸዋል" በማለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ደቡብ አፍሪካዊቷ ንግሥት በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, @SAgovnews
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንጉሣውያን ቤተሰብ እንዳሰወቀው ንግሥት ኖሎይሶ ሳንዲሌ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው ማለፉን ነው።
ንግሥቲቷ በአሁኑ ሰዓት የዙሉ ሕዝብ ንጉሥ የሆኑት ጉድዊል ዚዌልቲኒ እህት ሲሆኑ አማርሃርህቤ የተባለውንም ስርወ መንግሥትንም በመወከል አገረ ገዢ ሆነው ሲያገለግሉም ነበር ተብሏል።
ንግሥቲቷ የአማርሃርህቤ ንጉሥ የሆኑትን ማክሆባ ሳንዲሌም ጋር ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በጋብቻ የቆዩ ሲሆን፤ ንጉሡም ህይወታቸው ያለፈው በጎርጎሳውያኑ 2011 ነው።
ስልጣኑን መረከብ የነበረበት ልዑል ጆንጉክሶሎ ሳንዲሌ ቢሆንም አልጋ ወራሹ እድሜው ባለመድረሱ ንግሥቲቱ ቦታውን ተረክበው ነበር ተብሏል።
የአምሳ ስድስት አመቷ ንግሥት በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደነበሩም የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤስኤቢሲ ዘግቧል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በንግሥቲቷ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀው "አባታዊ ሥርዓት እንዲቀየርና፣ ኢ-ፍትሃዊ የሥርዓተ- ፆታ አወቃቀርን የታገለች እንዲሁም በአስተዳደሯ በርካታ ሥራዎችን የሰራች ናት" በማለት አሞካሽተዋቸዋል።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እውቅና የተሰጣቸውና የተለያዩ ጎሳዎችን የሚወክሉ ሰባት ስርወ መንግሥታት አሉ።
በኮቪድ-19 ሳቢያ በኢንግላንድ የታቀዱ ህክምናዎች 82 በመቶ ቀንሰዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢንግላንድ ግንቦት ላይ መደበኛ ህክምና ከ295,881 ወደ 54,550 ማለትም 82 በመቶ መቀነሱ ተነገረ።
ህክምና ለማግኘት ከ18 ሳምንታት በላይ የቆዩ ታካሚዎች ቁጥር ደግሞ 1.45 ሚሊዮን ደርሷል። ይህም እአአ ከ2007 ወዲህ ከፍተኛው ነው።
በ18 ሳምንት ህክምና ማግኘት የቻሉት 62.2% ሰዎች ብቻ ናቸው። ታቅዶ የነበረው ግን 95% ታካሚዎችን ለማዳረስ ነበር።
ግንቦት ላይ 52 ሳምንታት ለህክምና የጠበቁ ሰዎች 26,029 ሰዎች ደርሰዋል። አምና ግን1,032 ህሙማን ብቻ ነበሩ።
የካንሰር ህክምናም 69.9 በመቶ ቀንሷል። ይህም ከ2009 ወዲህ እጅግ አነስተኛው ነው።
አጣዳፊ የጡት ካንሰር ህክምናዎች ካለፈው ዓመት 15,802 ወደ 5,371 ማለትም 66% ቀንሰዋል።
በተጨማሪም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኢንግላንድ ነዋሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ምርመራ ለማግኘት ከስድስት ሳምንት በላይ ለመጠበቅ ተገደዋል።
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ብዛት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሆነ
በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።
በዚህም መሰረት አስካሁን በወረርሽኙ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ከ12 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በየሰዓቱ በዓለም ዙሪያ የተገኙ መረጃዎችን በመጠቀም በሚያወጣው መረጃ መሰረት የህሙማኑ ቁጥር 12 ሚሊዮን 51 ሺህ 561 ደርሷል።
ከዚህ አሃዝ ውስጥ ከፍተኛው በበሽታ የተያዙ ሰዎች ያሉባት አገር አሜሪካ ስትሆን እስካሁን 3 ሚሊዮን 055 ሺህ 144 ሰዎች በሽታው እንዳለባቸው ሲረጋገጥ በደቡብ አሜሪካ የምትገኘው ብራዚል 1 ሚሊዮን 713 ሺህ 160 ሰዎች በበሽታው ተይዘውባት ሁለተኛ ሆናለች።
በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ሕንድ ስትሆን 767 ሺህ 296 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ተረጋግጧል። ከሕንድ ቀጥላ ሩሲያ 706 ሺህ 179 ሰዎች ላይ ቫይረሱን እንዳገኘች በመግለጽ አራተኛ ሆናለች።
በኢትዮጵያ በጠቅላላው 6973 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
ናይጄሪያ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የነበራትን ዕቅድ ሰረዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ መንግሥት በመላዋ አገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ያሳለፈውን ውሳኔ ቀለበሰ።
የትምህርት ሚኒስትሩ አዳሙ አዳሙ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱት በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የማይጨምር ከሆነና መከፈታቸው ምንም ስጋት የማይኖረው ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በናይጄሪያ ያሉ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማጠናቀቂያ ፈተናዎችን የሚወስዱ ተማሪዎችን ለማዘጋጀት እንደሚከፈቱ ተነግሮ ነበር።
ነገር ግን ባለው የበሽታው መስፋፋት ስጋት የተነሳ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው አይመለሱም ሲሉ ሚኒስትሩ አሳውቀዋል።
ጨምረውም ትምህርት ቤቶች በቅርቡ የመከፈት እድላቸው ጠባብ ነው ብለዋል። በዚህም ሳቢያ በዚህ ዓመት ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች አይኖሩም ማለት ነው ብለዋል።
በናይጄሪያ ውስጥ እስካሁን 30,249 ሰዎች ላይ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 684 ሰዎች በበሽታው ሰበብ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በሚሲሲፒ ከ26 በላይ የምክር ቤት አባላት በኮሮናቫይረስ ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, የሚሲሲፒ አገረ ገዢ ቴት ሪቭስ በአሜሪካዋ ግዛት ሚሲሲፒ ውስጥ ቢያንስ 26 የምክር ቤት አባላትና 10 ምክር ቤቱ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።
የግዛቲቱ ምክር ቤት 174 እንደራሴዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል በበሽታው የተያዙት ከ26 እንደ ሚበልጡ ነው የተነገረው።
ይህንንም ተከትሎ የሚሲሲፒ ገዢ ቴት ሪቭስ በሽታው ከተገኘባቸው የምክር ቤት አባላት ጋር በየትኛውም መንገድ ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል የምትገኘው ሚሲሲፒ ውስጥ የተከሰተው ወረርሽኝ የግዛቲቱ ባለስልጣናት ለሳምንታት ሲያላሉት የነበሩትን የእገዳ እርምጃዎች መልሰው እንዲያጤኑት አስገድዷቸዋል።
አገረ ገዢው እንዳሉት አካላዊ ርቀትና ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የመጠቀም ግዴታ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ገልጸዋል።
"የፈራነው ነገር ተከስቷል" ሲሉ አገረ ገዢው በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የወረርሽኙን አሳሳቢነት አመልክተው "እባካችሁ እራሳችሁን ጠብቁ። እባካችሁ የምትወዷቸውን ጠብቁ። እባካችሁ ጭምብል አድርጉ። በተቻላችሁ አቅም ከቤታችሁ አትውጡ” ሲሉ የግዛታቸውን ነዋሪዎች ተማጽነዋል።
የሚሲሲፒ ግዛት እስካሁን ድረስ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የ1,188 ሰዎች ሞት ያጋጠማት ሲሆን ከ32,800 ሰዎች በላይ ደግሞ ወረርሽኙ ተገኝቶባቸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በወረርሽኙ ሰበብ በርካታ ሰዎች በረሀብ ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Save the Children
በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ በሚከሰት ረሀብ ሳቢያ በቀን 12ሺህ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ ኦክስፋም አስጠነቀቀ።
ይህም በወረርሽኙ ሳቢያ ሊሞቱ ከሚችሉ ሰዎች ቁጥር ይበልጣል።
የተራድኦ ድርጅቱ እንዳለው፤ ሥራ አጥነት፣ ምግብ አምራቾች በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት መሥራት አለመቻላቸው እንዲሁም እርዳታ ለማከፋፈል አዳጋች መሆኑ ረሀቡን ያባብሰዋል።
ኦክስፋም ያወጣው ሪፖርት በከፍተኛ ሁኔታ ረሀብ የተጋረጠባቸውን አስር አገሮችን ይዟል።
እነዚህም የመን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዝዊላ፣ ሳኸል፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶሪያ እና ሄይቲ ናቸው። ዝርዝሩን ከዚህ ያንብቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገራት ከኮቪድ-19 በባሰ በረሃብ በርካቶች ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የሞት ፍርድን ማስፈጸም በቴክሳስ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአሜሪካዋ የቴክሳስ ግዛት ውስጥ ለአምስት ወራት ያህል በፍርድ ቤት ሞት በተበየነባቸው ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙ ቆሞ ነበር።
ነገር ግን ከትናንት ረቡዕ ጀምሮ የቴክሳስ ግዛት ፍርደኞችን በሞት መቅጣት ጀምራለች። ይህም የተፈጸመው በአንድ የ45 ዓመት ሞት ቅጣት የተወሰነበት ግለሰብ ላይ ሲሆን ከአምስት ወራት በኋላ ተግባራዊ የሆነ ቅጣት ሆኗል።
ጆ ዋርድሎው የተባለው ይህ ግለሰብ ከ17 ዓመታት በፊት የ82 ዓመት አዛውንትን ገድሎ በፈጸመው ዘረፋ ነው ሞት የተፈረደበት። ውሳኔውም በመርዝ መርፌ ተወግቶ ትናንት ተግባራዊ ሆኗል።
ግለሰቡ ላይ የሞት ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን በሚያዚያ መጨረሻ ላይ ቀነ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከሁለት ወራት በላይ በህይወት የመቆየት እድል አግኝቶ ነበር።
የግለሰቡ ጠበቆች ፍርደኛው ወንጀሉን የፈጸመው ገና የ18 ዓመት ለጋ ወጣት ሳለ በመሆኑ የተላላፈበተ የሞት ፍርድ እንዲነሳ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የሞት ፍርድ ማስፈጸም መልሶ በመጀመር የቴክሳስ ግዛት የመጀመሪያዋ አይደለችም።
ሌላኛዋ ግዛት ሚዙሪ ለተወሰነ ጊዜ አቋርጣው የነበረውን ሞት የተፈረደባቸውን ሰዎች የመቅጣት ተግባር በግንቦት ወር አጋማሽ ላይ መጀመሯ ይታዋሳል።
ቶክዮ በአንድ ቀን ከፍተኛውን የህሙማን ቁጥር መዘገበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጃፓኗ ዋና ከተማ ቶክዮ ባለፉት 24 ሰዓታት ከፍተኛውን የኮሮናቫይረስ የህሙማን ቁጥር መዝግባለች።
ከዚህ ቀደም በአንድ ቀን ኮቪድ-19 እንዳለባቸው የተረጋገጡት ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር 206 ነበረ። አሁን ግን ቁጥሩ ጨምሮ 224 ደርሷል።
ባለፉት ሰባት ቀናት በየ24 ሰዓቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል። ሆኖም የአገሪቱ ባለስልጣናት በድጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣል አያስፈልግም ብለዋል።
በቶክዮ ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ ይታወሳል። በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ቀንሶ ነበር።
የኒው ዚላንድ ፖሊስ ለይቶ ማቆያ የገቡ ሰዎችን መጠበቅ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒው ዚላንድ ፖሊሶች ለይቶ ማቆያ የገቡ ሰዎችን መጠበቅ እንደሚጀምሩ ተገለጸ። ውሳኔው የተላለፈው ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ የ32 ዓመት ግለሰብ ተደብቆ ከወጣ በኋላ ነው።
ግለሰቡ ከማቆያው ወጥቶ ገበያ መሄዱ ተደርሶበታል።
ከዚህ ቀደምም አንዲት ሴት በአጥር ዘላ ከለይቶ ማቆያ መውጣቷና ከሁለት ሰዓት ቆይታ በኋላ መያዟ ይታወሳል።
የለይቶ ማቆያዎች ኃላፊ ሜጋን ውድስ “ከለይቶ ማቆያ የሚያመልጥ ሰው ራስ ወዳድ ነው። በሕግ እንፋረደዋለን” ብለዋል።
በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን አለፈ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
በአሜሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ከሦስት ሚሊዮን በላይ እንደሆኑ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያሳያል። ከ131,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
ሆኖም ግን ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎችም ዘርፎች ወደ ሥራ መመለስ እንዳለባቸው ከዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
ምክትል ፕሬዘዳንት እና የኮቪድ-19 መከላከል ግብረ ኃይል መሪ ማይክ ፔንስ፤ ሕጎች “ከመጠን በላይ መጥበቅ” የለባቸውም ብለዋል።
እሳቸውም ይሁን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ያለችው “ጥሩ ሁኔታ ውስጥ” ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ማክሰኞ ዕለት 60,000 ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም ከዚህ ቀደም በአንድ ቀን በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር የአሜሪካ ከፍተኛው ነው።
ካሊፎርንያ እና ቴክሳስ በአንድ ቀን ከ10,000 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውን አስታውቀዋል።
የተላላፊ በሽታዎች ሙያተኛና የዋይት ሐውስ አማካሪው ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፤ አገሪቱ በመጀመሪያው የወረርሽኙ የስርጭት ወቅት ላይ ብትሆንም፤ በበሽታው ማዕበል ተውጣለች ብለዋል።
የሐሙስ ሐምሌ 02/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ
እንደምንአደራችሁ?
ዕለተ ሐሙስ ሐምሌ 02/2012 ዓ.ም
ቢቢሲ አማርኛ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በማሰባሰብ የሚያቀርባቸው ዜናና ታሪኮች በእዚህ የቀጥታ ዘገባ ገጽ ላይ ይቀርባል።
ስለወረርሽኙ በየሰዓቱ የሚወጡትን ትኩስ መረጃዎችን ለማግኘት በአመቻችሁ አጋጣሚ ሁሉ ይህንን የቀጥታ ዘገባ ገጽ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።
መልካም ዕለት ይሁንላችሁ!

በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊየን ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 500 ሺህ ማለፉን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
ባለፉት አምስት ወራት በአፍሪካ 11 ሺህ 959 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸውን ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ ያትታል።
በ22 የአህጉሪቱ አገራት የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር በእጥፍ የጨመረው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው።
አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር እየናረባቸው እንደሆነ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ፣ ጋምቢያ፣ ማሊ፣ ሲሼልስና ቶጎ የበሽታው መስፋፋት ፍጥነት ከሌሎች አገራት ሲነፃፀር ቀርፋፋ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ 88 በመቶ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ዕድሜያቸው 60ና ከዚያ በታች ነው። የሟቾች ዕድሜ ግን 60ና ከዚያ በላይ ነው ይላል መግለጫው።
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ272 ሺህ ባላይ ሰዎች መርምራ 6973 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ አረጋግጣለች።
ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛውን የህሙማን ቁጥር አስመዘገበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ አፍሪካ በዓለም በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር 14ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በሽታው በእጥፍ እየተሰራጨ መምጣቱ የአገሪቱን መሪዎች አሳስቧል።
አገሪቱ ቀዝቃዛ ወቅት ላይ መሆኗ ደግሞ ነገሮችን አባብሷል።
ባለፉት 24 ሰዓታት 192 ሰዎች በወርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ሲሆን፤ 10,000 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።
በዌስተርን ኬፕ እስካሁን በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች 72,000 ደርሰዋል። የምጣኔ ሀብት ማዕከል በሆነችው ጉዋቴንግ በቀጣይ ቀናት በርካታ ሰዎች በበሽታዎች እንደሚያዙም ተሰግቷል።
ማዕከሏ የአገር ውስጥና የውጪ ሠራተኞችም የሚዘዋወሩባት፣ በሰው የተጨናነቀችም መሆኗ ለወረርሽኙ ተጋላጭ አድርጓታል።
በደቡብ አፍሪካ ቢያንስ 3,470 ሰዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ሞተዋል።
ዓለም እንዴት ዋለች?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ- ባለፉት 24 ሰዓታት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ነው። ካሊፎርንያ እና ቴክሳስ ከ10,000 በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች መዝግበዋል።
በሌላ በኩል ከተለያዩ አገራት ወደ አሜሪካ የሄዱ ተማሪዎች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚያስገድደውን ሕግ በመቃወም ሀርቫርድ እና ኤምአይቲ መንግሥትን ከሰዋል። በሕጉ መሠረት ተማሪዎቹ ክፍል ገብተው መማር ካልጀመሩ አሜሪካን ይለቃሉ።
ዩናይትድ ኪንግደም- ቻንስለር ሪሺ ሱናክ ቫይረሱ ካደረሰው የምጣኔ ኃብት ጫና ለማገገም የሚረዱ እርምጃዎች ይፋ አድርገዋል። ይህም ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመቀነስ፣ ለተመጋቢዎች ቅናሽ ለማድረግ የተመደበውን 2.52 ቢሊዮን ዶላር ያካትታል።
ብራዚል- በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ፕሬዘዳንት ዣቪር ቦልሶናሮ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሚኒስትሮች እየተመረመሩ ነው። ፕሬዘዳንቱ “ደህና ነኝ” ብለው፤ ሀይድሮክሲክሎሮክዊን ሲወስዱ የሚያሳይ ቪድዮ ለቀዋል።
ፈረንሳይ-አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዣን ካስቴክስ በአገሪቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቢጨምሩም አገር አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ አይጣልም ብለዋል።
አውስትራሊያ- ሜልቦርን ውስጥ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍ ስላለ በከተማዋ እንቅስቃሴ ቆሟል።
ኒው ዚላንድ- ኮሮናቫይረስ ያለበት የ32 ዓመት ግለሰብ ከለይቶ ማቆያ አምልጦ ገበያ በመውጣቱ ተከሷል።
ቻይና- አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት መውጣቷ ታዳጊ አገሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ስትል ወቅሳለች።
ሕንድ- ሙምባይ የኮቪድ-19 ምርመራ ለሁሉም ሰው ክፍት በማድረግ ቀዳሚዋ የሕንድ ግዛት ሆናለች። እስካሁን 86,500 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።
ባጠቃላይ በመላው ዓለም 11.8 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ሲያዙ፤ 545,000 መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያሳያል።
በኢትዮጵያ 199 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ

በኢትዮጵያ 199 ተጨማሪ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቁ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት 24 ሰዓታት 4162 ሰዎች ምርመራ እንደተደረገላቸው ይፋ አድርጓል።
77 ሰዎች ከድሬዳዋ፣ 71 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 21 ሰዎች ከጋምቤላ እና 15 ሰዎች ከትግራይ ክልል ነው የተገኙት ይላል መግለጫው። ሌሎች 15 ሰዎች ደግሞ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንደተገኙ መግለጫው አትቷል።
በሌላ በኩል 139 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
በኢትዮጵያ በጠቅላላው 6973 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል። ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 3440 ደርሷል።
