በኢትዮጵያ 3 ሺህ 301 ሰዎች ሲያገገግሙ የሟቾች ቁጥር 120 ደረሰ

ከሰሞኑ የድምፃዊ ሃጫሉ መኪና ውስጥ መገደል ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት ምክንያት የላብራቶሪ ናሙናዎችን መሰብሰብ ችግር አጋጥሞ እንደነበር የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።በዛሬው ዕለት በ1ሺህ 929 ናሙናዎች ላይ ምርመራ መደረጉን ሚኒስቴሩ ያሳወቀ ሲሆን በዚህም 108 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።በዚህም መሰረት በሃገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 774 ደርሷል። ከነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት 3ሺህ 301 ከህመሙ ማገገማቸውም ተገልጿል።የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በአግባቡ መከተል ራስንም ሆነ ሌሎችን ለመከላከል ሁነኛ መላ መሆኑን ባለሙያዎችና መንግሥት ዘወትር ይመክራሉ። በመሆኑም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፈንጫን መሸፈን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በጀርመን በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ቡና ቤቶች ይከፈቱ ብለው ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ

    ጥቂት የማይባሉ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች ቡና ቤቶች ይከፈቱልን በማለት በጀርመኗ ዋና ከተማ በርሊን ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ያደረጉት ሰልፈኞቹ ከጀርመን ፌደራል ምክር ቤት በር ላይ ነው ጥያቄያቸውን ያቀረቡት።

    ‘’በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ሥራቸው ይወደድም ይጠላ ሊከበሩ ይገባል’’ የሚል መፈክር ሰልፈኞቹ ይዘው የታዩ ሲሆን፤ አንዲት ሴት ደግሞ ቡና ቤቶቹ የማይከፈቱ ከሆን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሥራቸውን ለመስራት እንደሚገደዱ መልዕክቷን አስተላልፋለች።

    ምንም እንኳን ጀርመን እንቅስቃሴ ገደቡን ማላለት ብትጀምርም በኮሮረናቫይረስ ምክንያት የወሲብ ንግድ ዘርፉ አሁንም በእጅጉ ተጎድቷል ተብሏል።

    ነገር ግን እንደ ስዊትዘርላንድ፣ ኦስትሪያ እና ኔዘርላንድስ ያሉ ጎረቤት አገራት ቡና ቤቶች እንዲከፈቱ ፈቅደዋል።

  2. የሕንዷ መዲና ዴልሂ የመጀመሪያውን የፕላዝማ ባንክ ከፈተች

    የሕንዷ ዋና መዲና ዴልሂ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን ለማከም የሚውል ፕላዝማ እየሰበሰበች ሲሆን ሐሙስ ዕለት ከተማዋ የመጀመሪያ የሆነውን የፕላዝማ ባንክ ከፍታለች።

    ይህም ህሙማኑ ፕላዝማን በቀላሉ ለማግኘት ያስችላቸዋል ተብሏል።

    አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ሲያዝ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ ሥርዓቱ ተህዋስያን የመከላከያ ዘዴን (አንቲቦዲ) ያዘጋጃል፤ ይህም ቫይረሱን በማጥቃት ወደ በሽታ እንዳይሸጋገር ያደርጋል።

    ይህም ፕላዝማ በተባለውና በደም ውስጥ ባለው ፈሳሽ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ነው።

    ፕላዝማን በኮቪድ-19 በጠና ለታመሙ ሰዎች በመስጠት ከቫይረሱ ጋር ፍልሚያ የገጠመውን የእራሳቸውን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ ሥርዓት በማጠናከር ከበሽታው እንዲያገግሙ ለማገዝ የሚያስችል ነው።

    ሚኒስተር አርቪድ ኬጂሪዋም "በዴልሂ ያለው ሁኔታ በጣም የተጨናነቀ ሲሆን ፕላዝማ ማግኘት አዳጋች ነው። የፕላዝማ ባንኩ የተቋቋመውም ይህንን ችግር ለማቃለል ነው። ባንኩ ውጤታማ የሚሆነው ደግሞ ሰዎች ፕላዝማ የሚለግሱ ከሆነ ነው።" በማለት ፕላዝማ መለገስ የሚችሉ ሰዎች እንዲለግሱ አሳስበዋል።

    በዴልሂ የፕላዝማ ህክምና በሙከራ ደረጃ ያለ ሲሆን ከኮቪድ-19 ካገገመ ታማሚ የሚወሰደው ፕላዝማ ሌሎች ታማሚዎችን ለማከም ይረዳል የሚል ተስፋ አለ።

    በዴልሂ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ከ2ሺህ በላይ ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላዩን ቁጥር ከ90 ሺህ በላይ አድርሶታል።

    በሕንድ እስካሁን ከ625 ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ይህም ከዓለም አገራት በአራተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

    18 ሺህ 213 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  3. ማዳጋስካር 'ኮቪድ-19ን ይፈውሳል' ያለችውን መድሃኒት ናይጀሪያ እየመረመረች ነው

    የናይጄሪያ ጤና ሚኒስተር በማዳጋስካር ከዕፅዋት የተዘጋጀውንና 'ኮቪድ-19ን ይፈውሳል' የተባለው ባህላዊ መድሃኒት የወባ በሽታን ለማከም የሚያስችል ይዘት ያለው መሆኑን ገልፀው፤ ለኮሮናቫይረስ ህክምና ውጤታማ መሆን አለመሆኑን አሁንም እየመረመረ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ሚኒስትሩ ኦሳጌ ኢሃንሬ እንዳሉት በብሔራዊ የመድሃኒት ምርምር ተቋም በመጀመሪያ ደረጃ የምርምር ውጤት መድሃኒቱ ለወባ በሽታ ሕክምና የሚውል አርቲ የተባለ ዕፅዋት እንዳለው አሳይቷል።

    ሚኒስተሩ አክለውም ለምርምሩ የሚውል ገንዘብ ከተፈቀደ በኋላ የመድሃኒቱ ውጤታማነት ላይ ተጨማሪ ምርምር እንደሚደረግ መናገራቸውን የናይጄሪያው ፕሪሚየም ታይምስ ዘግቧል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ከኮሮናቫይረስ ይፈውሳል በሚል ያልተፈተኑና ያልተረጋገጡ መድሃኒቶችን መጠቀም አደገኛ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

    ይሁን እንጅ የማዳጋስካሩ ፕሬዚደንት አንድሪይ ራሆሊና መድሃኒቱን በአህጉሪቱ በሙሉ እያስተዋወቁ ነው።

    'መድኃኒቱን' ካዘዙት መካከልም ወደ ደሴቷ አገር አውሮፕላን የላኩት የታንዛኒያው ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ ይገኙበታል፡፡

    ከዚህም በተጨማሪ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ኮንጎ ፣ ጋቦን እና ኮሞሮስ መድሃኒቱን ወደ አገራቸው የማስገባት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

    ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ ቢሳውም የተወሰኑ መድኃኒቶችን ለማምጣት አውሮፕላን መላካቸው ይታወሳል።

  4. 40 የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች በኮቪድ መያዛቸው ተገለፀ

    የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ኃይል 40 የሚሆኑ ኦፊሰሮቹ በኮሮናቫይረስ መያዛችን ገለፀ።

    "ልክ እንደ ሌሎቹ ኮሮናን በመከላከል ከፊት እንዳሉ ባለሙያዎች ሁሉ ወታደሮቻችን ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ናቸው፣ ከመደበኛው ዜጋ በተለየ" ብሏል የመከላከያ ኃይሉ መግለጫ።

    ወታደሮቹ በኬፕታዎን የነበሩ ሲሆኑ አለመግባበት ወዳለበት የዚምቧቤ እና ደቡብ አፍሪካ ድንበር፣ ሌፋሌሌ፣ ለግዳጅ መሰማራታቸው ተገልጿል።

    መከላከያ ኃይሉ ወታደሮቹ ወደ ተመደቡበት ሌፋሌሌ ቀጠና ከመሄዳቸው በፊት አስፈላጊውን የጤና ቅድመ ጥንቃቄ ሁሉ እንዳደረገ ገልጿል።

    ሌፋሌሌ እንደደረሱ ወዲያውኑ ምርመራ የተደረገላቸው ወታደሮቹ የሕመም ምልክት ስለነበራቸው ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን መግለጫው ያስረዳል።

    ምርመራ ሲደረግላቸው የተወሰኑት ወታደሮች ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው መታወቁን መግለጫው አክሎ ገልጿል።

    "ቫይረሱ የተገኘባቸው በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለይቶ ማቆያ ተዘጋጅቶ እዚያ እንዲቀመጡ ተደርጓል" ብለዋል።

  5. "አገሪቷ ስለተረጋጋች ኢንተርኔቱ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚከፈት ተስፋ አደርጋለሁ"-ቢልለኔ ስዩም

  6. በኢትዮጵያ 3 ሺህ 301 ሰዎች ሲያገገግሙ የሟቾች ቁጥር 120 ደረሰ

  7. በሴራሊዮን የዶክተሮች የሥራ ማቆም አድማ የኮቪድ-19 ሕሙማንን ያለተንከባካቢ አስቀረ

    በሴራሊዮን ዶክተሮች ቃል የተገባልንን ጥቅማጥቅም አልተሰጠንም በሚል የሥራ ማቆም አድማ በመምታታቸው በአንዳንድ የእንክብካቤ ማዕከል የሚገኙ የኮቪድ-19 ሕሙማን ሕክምና እያገኙ እንዳልሆነ ተገለፀ።

    ዶክተሮቹ የሚሉት መንግሥት ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ለመክፈል ቃል ገብቶ የነበረውን ጥቅማ ጥቅም አልሰጣቸውም።

    የሥራ ማቆም አድማው በሐኪሞቹና በመንግሥት መካከል አዲስ ፍጥጫን የቀሰቀሰ ሲሆን ዶክተሮቹ ለኮሮናቫይረስ መከላከል የመጣ ፈንድ ተመዝብሯል እንዲሁም በቂ የመከላከያ ቁሳቁስ አለመኖርን በማንሳት መንግሥትን ይከስሳሉ።

    "የሚያስፈልገንን ድጋፍ እስክናገኝ ድረስ አንድም የኮቪድ-19 ምልክት የሚያሳይ ታማሚ ህክምና አያገኝም" ያሉት በአገሪቱ ትልቅ በሆነው የለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚሰሩት ዶ/ር ኤስ ኬ ዩሱ ናቸው።

    ሴራሊዮን እስካሁን ድረስ 1 ሺህ 500 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ 60 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። ከእነዚህም መካከል 160ዎቹ የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው ተብሏል።

    ከዚህ በፊት ሴራሊዮን በኢቦላ ተጠቅታ የነበረ ሲሆን በዚያም ወቅት 4 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 250ዎቹ የሕክምና ባለሙያዎች ነበሩ።

  8. የአፍሪካ አየር መንገዶች ሰራ መጀመራቸውን ተከትሎ የአለም ጤና ድርጅት እንዲጠነቀቁ ጠየቀ

    በኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አየር መንገዶች ስራ መጀመራቸውን ተከትሎ ጥንቃቄን እንዲያስቀድሙ የአለም ጤና ድርጅት መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ድርጅቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይዛመት አየር መንገዶቹ ጥብቅ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ብሏል።

    መንግሥታት የመንገደኞችን መረጃ እንዲሁም በየሃገራቱ በሚቆዩበት ወቅትም ክትትል የሚያደርጉበት መንገድ አየር መንገዶቹ እንዲቀይሱም ጥሪ አስተላልፈዋል።

    የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ማትሺዲሶ ሞየቲ እንዳሉት የአየር ጉዞ ለኢኮኖሚው ጠቃሚ ቢሆንም "ወደቀደመው መመለስ ስለማይቻል ሃገራት ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ የደህንነት መመሪያዎችን ሊያጠብቁ ይገባል" ብለዋል።

    የአየር ማረፊያ ባለስልጣናቱም አካላዊ ርቀት መጠበቅን፣ እጅ መታጠብና ሳኒታይዝ ማድረግን እንዲቆጣጠሩም ድርጅቱ ጠይቋል።

    በአሁኑ ወቅት ካሜሮን፣ ኢኳተሪያል ጊኒ፣ ታንዛንያ፣ ዛምቢያ በረራ መጀመራቸውን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

    ቱኒዝያም ከሳምንት በፊት በረራዎችን ጀምራለች።

    በረራዎች መጀመራቸውን ተከትሎ በባለፈው ሳምንት 66 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንም ድርጅቱ ጠቁሟል።

  9. የሰሜን ኮሪያው መሪ አገራቸው በኮሮናቫይረስ ላይ "አንፀባራቂ ድል" ማስመዝገቧን ተናገሩ

  10. "ከዚህ በኋላ በየትኛውም ሚዲያ፤ . . . ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የጥላቻ፤ የፕሮፖጋንዳ ሥራ አንታገስም" ታከለ ኡማ

  11. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች!

    በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ የዓለማችን ሕዝቦች 10 ሚሊዮን 800 ሺህ መሻገሩን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያሳያል።

    ይህ ወረርሽኝ በብዛት በአሜሪካና አውሮጳ ተስፋፍቶ ቢገኝም በአሁኑ ሰዓት ግን በአሜሪካ ከምን ግዜውም በላይ ስርጭቱ ጨምሯል።

    በአፍሪካና በምዕራብ እስያ ይህ ቁጥር መጨመር እያሳየ ነው ተብሏል።

    በኢትዮጵያም ቢሆን በዚህ ሳምንት በነበረው አለመረጋጋት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግም ሆነ መረጃ መሰብሰብ አዳጋች ቢሆንም የኮቪድ-19 በፍጥነት እየጨመረ መሆኑ ግን የማይካድ ሃቅ ነው።

    የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በአግባቡ መከተል ራስንም ሆነ ሌሎችን ለመከላከል ሁነኛ መላ መሆኑን ባለሙያዎችና መንግሥት ዘወትር ይመክራሉ።

    በመሆኑም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፈንጫን መሸፈን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

    ከመላው ዓለም የምንሰበስባችንና ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኙ አበይት ዘገባዎችን እዚህ እናቀርብላችኋለን።

    መልካም ቀን!