በኢትዮጵያ 3 ሺህ 301 ሰዎች ሲያገገግሙ የሟቾች ቁጥር 120 ደረሰ

ከሰሞኑ የድምፃዊ ሃጫሉ መኪና ውስጥ መገደል ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት ምክንያት የላብራቶሪ ናሙናዎችን መሰብሰብ ችግር አጋጥሞ እንደነበር የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።በዛሬው ዕለት በ1ሺህ 929 ናሙናዎች ላይ ምርመራ መደረጉን ሚኒስቴሩ ያሳወቀ ሲሆን በዚህም 108 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።በዚህም መሰረት በሃገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 774 ደርሷል። ከነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት 3ሺህ 301 ከህመሙ ማገገማቸውም ተገልጿል።የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በአግባቡ መከተል ራስንም ሆነ ሌሎችን ለመከላከል ሁነኛ መላ መሆኑን ባለሙያዎችና መንግሥት ዘወትር ይመክራሉ። በመሆኑም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፈንጫን መሸፈን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፈተና ውስጥ የገባው የሕንድ ሻይ ቸርቻሪዎች ሕይወት

  2. በሜክሲኮ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሺህ አለፈ

    በቫይረሱ ክፉኛ በተመታችው በላቲን አሜሪካዋ ሜክሲኮ፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ አንስቶ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሺህ በላይ መድረሱ ተገለፀ።

    የጤና ሚኒስቴር እንዳለው የሟቾቹ ቁጥር ቅዳሜ ዕለት በ523 የጨመረ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 30 ሺህ 366 አድርሶታል።

    በዚህም አገሪቷ በሟቾች ቁጥር ከ29 ሺህ በላይ ሰዎችን ካጣችው ፈረንሳይ ቀድማ በ5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

    በሜክሲኮ በአንድ ቀን 6 ሺህ 914 አዲስ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 252 ሺህ 165 መድረሱን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    ይሁን እንጅ በቂ ምርመራ ቢደረግ በቫይረሱ የሞቱም ሆነ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይታሰባል።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ ሜክሲኮ በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ አገራት፤ ከብራዚል ቀጥላ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበባት ሁለተኛዋ አገር ናት።

    በብራዚል ከ1.5 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 64 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  3. በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል ግማሽ የሚጠጉት አገገሙ

    ከሰሞኑ የድምፃዊ ሃጫሉ መኪና ውስጥ መገደል ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት ምክንያት የላብራቶሪ ናሙናዎችን መሰብሰብ ችግር አጋጥሞ እንደነበር የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በትናንትናው ዕለት በ2ሺህ 192 ናሙናዎች ላይ ምርመራ መደረጉን ሚኒስቴሩ ያሳወቀ ሲሆን በዚሀም 169 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በዚህም መሰረት በሃገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 6386 ደርሷል።ከነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት 3018ቱ ከህመሙ ማገገማቸውም ተገልጿል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስም 260 ሺህ 582 ሰዎች ላይ የላብራቶሪ ምርመራዎችም ተከናውነዋል።

    በትናንትናው ዕለትም የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉም ተገልጿል። ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች፣ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ መፅናናትን ይመኛል። የኮሮናቫይረስን በተመለከተ አዳዲስ መረጃዎችን እዚህ በቀጥታ ዘገባችን ታገኛላችሁ

  4. በኢትዮጵያ ተጨማሪ 169 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ሲገኝ 185 ሰዎች አገገሙ

    ባለፉት 24 ሰዓታት በኢትዮጵያ በ2 ሺህ 192 ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 169 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ተገለጸ።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠው 169 ህሙማን መካከል 148ቱ ከአዲስ አበባ የተገኙ ናቸው።

    በበሽታው ተይዘው የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከልም 185 ሰዎች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 3018 ደርሷል።

    ዕለታዊው ሪፖርት ጨምሮም ምርመራ ከተደረገባቸው መካከል 40ዎቹ በአስከሬን ላይ ሲሆን ሁለቱ ላይ በሽታው እንደተገኘ ተገልጿል።

    በህክምና ላይ ከሚገኙት ህሙማን መካከልም 28ቱ በጽኑ የህክምና ክትትል ላይ የሚገኙ መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

    እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገባቸው አጠቃላይ ናሙናዎች ብዛት 260 ሺህ 582 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በሽታው የተገኘው ደግሞ 6386 ሰዎች ላይ ነው።

    በዚህም መሰረት አስካሁን በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ከወረርሽኙ ማገገማቸው የወጣው አሃዝ ያመለክታል።

  5. በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ ሲደርስ ግማሹ አገገሙ

  6. ሁለት ጊዜ ባለቤታቸውን የቀበሩት ደቡብ አፍሪካዊት

    አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት ሴት በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸው ላለፈው ባለቤታቸው ሁለት የቀብር ሥነ ሥርዓት ማካሄዳቸው ተሰምቷል።

    ይህ ሁለት ጊዜ የተደረገው ቀብር እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው የባለቤቷ አስክሬን በሌላ ሰው በመቀየሩ ነው ተብሏል።

    ኒውስ 24 የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ጡረተኛዋ ነርስ ኖምሳ ኖዳ በምሥራቃዊ ኬፕ ታውን ነዋሪ ሲሆኑ ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ ነበር ባለቤታቸው የቀበሩት።

    ነገር ግን ከሦስት ቀናት በኋላ አንድ የሐይማኖት አባት ወደ ቤታቸው በመምጣት ስህተት መፈጠሩንና የቀበሩት ሰው ባለቤታው እንዳልሆኑ በመግለጽ የተፈጠረውን ስህተት ገልጸውላቸዋል።

    ይህንንም ተከትሎ ለባለቤታቸው ሁለተኛውን የቀብር ሥነ ሥርዓት ከቀናት በኀወላ ሐሙስ ዕለት መፈጸማቸው ታውቋል።

    ኖምሳ ኖዳ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ሲናገሩ ምናልባት የባለቤታቸው አስክሬን ላይ የነበረው መለያ በስህተት ወደ ሌላ አስክሬን ሳይቀየር እንዳልቀረ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

    በጀመሪያው ቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት ወረርሽኙን በመፍራት በተደረገ ጥንቃቄ አስክሬኑን እንዲያዩ አልተፈቀደላቸውም ነበር።

    ሌላሰው አስከሬን እንደቀበሩ ሲነገራቸው የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ "እስካሁን ድረስ ድንጋጤው አልቀቀኝም’’ ብለዋል ጡረተኛዋ ነርስ ኖምሳ።

  7. እንግሊዛዊያን ጸጉራቸውን ለመቆረጥ በየጸጉር ቤቱ ደጃፍ ተሰልፈዋል

    በበርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ ሚሊዮኖች ለወራት በቤታቸው ውስጥ ለመቀመጥ ተገደዋል።

    በዚህ ጊዜ ከቤት መውጣት የሚቻለው መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለመሸመትና የጤና አገልግሎት ለማግኘት ብቻ በመሆኑ በርካታ ወንዶች ጺማቸው ጎፍሮ ጸጉራቸው ተንጨባሮ ማየት የተለመደ ሆኗል፤ ሴቶችም ቢሆኑ ወደ ውበት ሳሎኖች ሄደው ጸጉራቸውን ለመስራት ሳይችሉ ቆይተዋል።

    እንግሊዝ ውስጥ ለሦስት ወራት በዘለቀው የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ ተዘግተው የነበሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ሥራቸውን እንዲጀምሩ በመፈቀዱ ሰዎች ከቤታቸው እየወጡ ነው።

    በተለይ መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችና የወንዶችና የሴቶች ጸጉር ቤቶች ዛሬ ሥራ ጀምረዋል።

    በተለይ ጸጉራቸውንና ጺማቸውን ወደ ጸጉር ቤት ሄደው ለመስተካከል ቀን ሲቆጥሩ የነበሩ ወንዶች ደንበኞቻቸውን ከጠዋት ጀምሮ እየጎበኙ ነው።

    በዚህም ሳቢያ በበርካታ ጸጉር ቤቶች ደጃፍ ላይ ጸጉር ለመቆረጥ የሚጠባበቁ ወንዶች እንደተመከሩት አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ሰልፍ በመያዝ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ከተለያዩ የዜና ምንጮች ያገኘናቸው ፎቶዎች ያሳያሉ።

  8. የስፔኗ ካታሎኒያ በ200 ሺህ ሕዝብ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

    በሰሜናዊ ምሥራቅ የምትገኘው የካታሎኒያ ግዛት ባለስልጣናት 200 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች ያሉበትን ሴግሪያ የሚባለው አካባቢ ላይ በድጋሚ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣሉ።

    ባለስልጣናቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በአካባቢው እየቀነሰ የነበረው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በድጋሚ እየጨመረ በመምጣቱ ነው ተብሏል።

    በዚህም የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ከባርሴሎና በስተምዕራብ ወደምትገኘው ሴግሪያ ማንም ሰው መግባትም ሆነ መውጣት አይችልም። ገደብ የተጣለበት አካባቢ ላይዳ የተባለችውን ከተማም የሚጨምር መሆኑ ተገልጿል።

    የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማስፈጸምም የፖሊስ የመቆጣጠሪያ ኬላዎች ተቋቁመዋል። በአካባቢው በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ ከአስር ሰዎች በላይ በአንድ ላይ መሰብሰብ እንደማይችሉም ተገልጿል።

    በአውሮፓ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከመታቸው አገራት መካከል ስፔን አንዷ ስትሆን፤ ካታሎኒያ ደግሞ በስፔን ውስጥ በሽታው በከፋ ሁኔታ ካጠቃቸው ግዛቶች መመካል አንዷ ናት ተብሏል።

  9. በእንግሊዝ የአገራት ዝርዝር ውስጥ ፖርቱጋል ባለመካተቷ ቅሬታ አሰማች

    እንግሊዝ ከየትኞቹ አገራት የሚመጡ ሰዎች ተለይተው መቆየት አያስፈልጋቸውም ከሚለው ዝርዝር ውስጥ ፖርቱጋል ባለመካተቷ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግራ መጋባታቸውን ገለጹ።

    ሚኒስትሩ አውጉስቶስ ሳንቶስ ሲልቫ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እንግሊዝ ከአገራት ዝርዝሩ ውስጥ ፖርቱጋልን አለማካተቷ “የማያሳምንና ፍትሃዊነት የጎደለው” ነው።

    እንግሊዝ ወደ ግዛቷ ሲገቡ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ተለይተው መቆየት አያስፈልጋቸውም ያለቻቸውን አገራት ዝርዝር ትናንት አርብ ነበር ይፋ ያደረገችው።

    የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንደተናገሩት የኮሮናቫይረስ በቁጥጥር ሰር ካልዋለባቸው አገራት የሚመጡ ሰዎች ለ14 ቀናት ተለይተው የመቆየት ግዴታ ተግባራዊ ሆኖ ይቀጥላል።

    ከፖርቱጋል በተጨማሪ በዝርዝሩ ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩ ሌሎች ትልልቅ አገራት ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አሜሪካ፣ ቻይና፣ ማልዲቭስና ስዊዲን ይገኙባቸዋል።

  10. በአውስትራሊያ የህሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው ተባለ

    የአውስትራሊያዋ ቪክቶሪያ ግዛት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ተባለውን የኮሮናቫይረስ ህሙማን ማግኘቷን አስታወቀች።

    በተደረገው ምርመራ 108 አዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህም በሽታው መኖሩ ከታወቀ በኋላ በቪክቶሪያ ግዛት ውስጥ እስካሁን በአንድ ቀን ከተመዘገበው ከፍተኛ የህሙማን ቁጥር ውስጥ ሁለተኛው እንደሆነ ተነግሯል።

    ምንም እንኳን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ችላልች ቢባልም በሜልበርን ውስጥ በሽታው የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ላይ ድንገተኛ ማሻቀብ ተስተውሏል።

    ሜልበርን ውስጥ በታየው የበሽታው ክስተት ሳቢያ በከተማዋ ዳርቻዎች ከሚገኙ 36 አካባቢዎች በተጨማሪ ከተማዋ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለ ሰንበትበት ብሏል።

    ከዚህ ባሻገርም ደግሞ በበሽታው ክፉኛ ተጠቅተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ዘጠኝ የመኖሪያ አካባቢዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ተነግሯል።

    እስካሁን አውስትራሊያ ውስጥ 8,200 የሚደርሱ የኮሮናቫይረስ ህሙማን መገኘታቸው የተመዘገበ ሲሆን 104 ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

  11. የፈረንሳይ መንግሥት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ስለወሰደው እርምጃ ምርመራ ተጀመረ

    አንድ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት መንግሥት የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በወሰደው እርምጃና በሰጠው ምላሽ ዙሪያ ምርመራ ጀምሯል።

    የአገሪቱ ሕግ ፍርድ ቤት በሚኒስትሮች ደረጃ የሚፈጸሙ ስህተቶችና ያልተገቡ ሥራዎችን የሚመረምር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሦስት ከፍተኛ ባላስልጣናት ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

    ከእነዚህ ሰዎች መካካል ደግሞ ከሐኪሞችና ከማኅበራት ከፍተኛ ቅሬታ የቀረበባቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤድዋርዶ ፊሊፔ ይገኙበታል።

    የፈረንሳይ መንግሥት በኮቪድ-19 ወረርሽን ወቅት ባጋጠመው የሕክምና አገልግሎት መስጫ መገልገያዎች እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት ነበር።

    ፈረንሳይ እስካሁን 202 ሺህ 673 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የገለጸች ሲሆን 29 ሺህ 875 ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

    ኤድዋርዶ ፊሊፔ በትናንትናው ዕለት ከስልጣናቸውን መልቀቃቸው የሚታወስ ነው።

    የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን ካስታወቁ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው ፍርድ ቤቱ መንግሥት በወቅቱ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በወሰደው እርምጃ ዙሪያ ምርመራውን እንደሚጀምር ያስታወቀው።

  12. በእንግሊዝ ምግብ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችና ጸጉር ቤቶች ሥራ ጀመሩ

    ለሦሰት ወራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተለያዩ እገዳዎች ውስጥ ለቆዩት እንግሊዛውያን ዛሬ ታላቅ ቀን ነው።

    ተሰባስበው የሚዝናኑባቸው መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም ጸጉር ቤቶች ተከፍተው ሥራ ጀምረዋል።

    ቢሆንም ግን እነዚህ እንዲከፈቱ የተፈቀደላቸው ንግድ ቤቶች ሥራቸውን ሲያከናውኑ ጥብቅ የሆነ አካላዊ ርቀት አጠባበቅ መመሪያን እንዲከተሉ የታዘዙ ሲሆን ተገልጋዮችም በእነዚህ ስፍራዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በኃላፊነት መንፈስ እንዲፈጽሙ ተጠይቀዋል።

    አንዲት የለንደን ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ወደ ውበት ሳሎን ጸጉሯን ልትሰራ ስትሄድ “እፎይታ” እንደተሰማትና ጸጉር ቤት ሄዳ ጸጉሯን መሰራት በመቻሏ “ወደ መደበኛው ሕይወት” እንደተመለሰች እንዲሰማት እንዳደረጋት ገልጻለች።

    ሽርጡን ለብሶ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርጎ ሥራውን የጀመረ አንድ ጸጉር አስተካካይም “መቀሴን ለሥራ ደግሜ በማንሳቴ ደስ ብሎኛል” ሲል ስሜቱን ገልጿል።

  13. የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ሕንድ ውስጥ ተጀመረ

    በምርምር ላይ የቆየ የመጀመሪያ ክትባት ፍቃደኛ በሆኑ ሰዎች ላይ ሕንድ ውስጥ መሞከር ተጀመረ።

    ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆኑ ያልተገለጹት እኒህ ሕንዳዊያን ክትባቱ የሚሰጣቸው በሐይድራባድ በሚገኝ ባራት ባዮቴክ በተሰኘ የጥናት ድርጅት ነው።

    ክትባቱ በእንሰሳት ላይ በተደረገ ሙከራ ምንም የጎንዮሽ ጉዳት ያላስከተሉ ከመሆኑ በላይ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ ኃይል ቫይረሱን የሚከላከሉ ህዋሶችን እንዲያመርት አስችሎታል።

    በመላው ዓለም በቤተ ሙከራ ደረጃ ያሉ 120 የክትባት ምርምሮች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ በሕንድ ነው እየተካሄዱ የሚገኙት።

    ይህ ክትባት የሚመረተው ከራሱ ከኮቪድ-19 ሲሆን ቫይረሱ በቤተ ሙከራ ውስጥ ተዳክሞና መጠኑ ቀንሶ ነው ወደ ክትባትነት የሚለወጠው። ዝርዝሩን ከዚህ ያንብቡ ሕንድ አዲስ የኮሮና ክትባትን በሰው ላይ ልትሞክር ነው

  14. በኡጋንዳ "ጉቦ የተጠየቀ" የሞተር ሳይክል አሽከረካሪ ራሱን አጠፋ

  15. ከ11 ሚሊዮን በላይ በቫይረሱ ሲያዙ ከግማሽ የሚበልጡት አገግመዋል

    በዓለም ዙሪያ በፍጥነት እየተስፋፋ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ ደረሰ።

    አስከ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ ያለው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሃዝ እንደሚያመለክተው 11 ሚሊዮን 074 ሺህ 878 ሰዎች በዓለም ዙሪያ በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በዓለማችን በበሽታው መያዛቸው ከታወቁት ከ11 ሚሊዮን ከሚበልጡት ሰዎች መካከል ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው ህሙማን የሚገኙት አሜሪካ ውስጥ ሲሆን ቁጥራቸውም 2 ሚሊዮን 794 ሺህ 153 ነው።

    በሁለተኝነት ደግሞ ብራዚል 1 ሚሊዮን 539 ሺህ 081 በበሽታው የተያዙ ሰዎች እንዳገኘች ያረጋገጠች ሲሆን ሩሲያ ደግሞ በ666 ሺህ 941 ህሙማን ሦስተኛዋ አገር ሆናለች።

    የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ እንደሚያመለክተውም እስካሁን በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡት ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ማገገማቸውን ያመለክታል።

    በዚህም መሰረት እስከ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ 5 ሚሊዮን 863 ሺህ 847 ሰዎች በዓለም ዙሪያ ከወረርሽኙ ያገገሙ ሲሆን ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበባት አገር ደግሞ ብራዚል ናት።

    በብራዚል 984 ሺህ 615 ሰዎች፣ በአሜሪካ 790 ሺህ 404 ሰዎች እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ ሩሲያ ውስጥ 437 ሺህ 115 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ አገግመዋል።

    በተጨማሪም በበሽታው ሰበብ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 525 ሺህ 121 ሰዎች በዓለም ዙሪያ ህይዋታቸውን ሲያጡ፤ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገቡባት አገር አሜሪካ ናት።

    በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ ሰበብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 129 ሺህ 434 ሆኖ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ስትገኝ በሁለተኛዋ ብራዚል ውስጥ ደግሞ 61 ሺህ 884 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ሦስተኛዋ አገር ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም ስትሆን የሟቾች ቁጥር 44 ሺህ 216 ነው።

  16. የቅዳሜ ሰኔ 27/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምን አደራችሁ?

    ዕለተ ቅዳሜ ሰኔ 27/2012 ዓ.ም

    ቢቢሲ አማርኛ ትኩስ ዜና፣ መረጃና ታሪኮችን ከኢትዮጵያና ከተለያዩ የዓለም ከፍሎች በማሰባሰብ በድረገጽ፣ በፌስቡክና በሬዲዮ ያቀርባል።

    ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በአሳሳቢው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ በየደቂቃው የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን በድረገጹ ላይ በሚገኘው የቀጥታ ዘገባ ገጽ ያቀርባል።

    በዚህ አጋጣሚ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከዕለት ዕለት እየተስፋፋ መሆኑን በመገንዘብ በሽታውን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችን ዋነኛ ምክር የሆኑትን እጅን በአግባቡና በተደጋጋሚ መታጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምና በርካታ ሰው በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች አካላዊ ርቀት መጠበቅን ተግባራዊ በማድረግ እራሳችንንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንጠብቅ።

    የመልካም ነገሮችን የምንሰማበት ዕለት እንዲሆን እንመኛለን!

  17. በኮሮናቫይረስ በእጅጉ የተጎዳው የናይጄሪያ ፊልም ዘርፍ

    በተለምዶ ኖሊዉድ ተብሎ የሚታወቀው የናይጄሪያው የፊልም ኢንዱስትሪ በኮሮናቫይረስ በእጅጉ ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች አንዱ እንደሆነ ተነግሯል።

    በርካታ የፊልም ቀረጻዎች በመቆማቸው ቀላል የማይባል ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

    የናይጄሪያ የፊልም ኢንዱስትሪ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች የሚያሳትፍ ትልቅ ዘርፍ ሲሆን በሳምንት እስከ 50 ፊልሞችን ይሰራል።

    ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘም በርካታ ተዋናዮች የገቢ ምንጫቸው ተቋርጦ ሕይወታቸውን የሚገፉበት መንገድ እንደጠፋቸው ገልጸዋል።

    ተዋናይት ኬሚ ላላ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ወረርሽኙ ቢቆም እንኳን የገቢ ምንጫቸው በመቋረጡ በትንሽ ገንዘብም ቢሆን ሥራዎችን ለመቀበል እንደሚገደዱ ገልጻለች።

    የፊልም ዳይሬክተሯ ሚልድሬድ ኦክዎ በበኩሏ ከወረርሽኙ በፊት የጀመረቻቸው የፊልም ታሪኮች ከዚህ በኋላ ይወደዱ አይወደዱ ማወቅ ከባድ መሆኑን ገልጻለች።

    በዚህም ምክንያት የአንዳንድ ፊልሞችን ታሪክ፣ ይዘትና አቀራረብ የቫይረሱን ማግስት ከግምት ውስጥ በማስገባት መቀየር ግድ እንደሚል አክላለች።

  18. የአውሮፓ ኮሚሽን ሬምደስቪር የተባለው መድሀኒት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደ

    የአውሮፓ ኮሚሽን ሬምደስቪር የተባለው መድሀኒት በአውሮፓ ህብረት አገራት በኮቪድ-19 የተጠቁ ህሙማንን ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቅዷል።

    የቫይረስ በሽታዎችን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው መድሀኒት በዋነኛነት ኢቦላን ለማከም የሚያገለግል ሲሆን በኮሮረናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገግሙ ያደርጋል ተብሏል።

    ሬምደስቪር በበርካታ አገራት የኮሮረናቫይረስ ህሙማን እንዲወስዱት የተፈቀደ ሲሆን አሜሪካም ከነዚህ አገራት መካካል አንዷ ናት።

    አሜሪካ ጊሊድ ከሚባለው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ያለውን ሁሉ አቅርቦት በሚባል ደረጃ ሬምደስቪር መግዛቷን አስታውቃለች።

    ሬምደስቪር በመላው ዓለም በሚገኙ ሆስፒታሎች በተደረገበት ክሊኒካል ሙከራ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን የማገገም ሂደት ከ15 ቀናት ወደ 11 ቀናት ዝቅ እንደሚያደርግ ተነግሮለታል።

  19. በኮሮናቫይረስ ተይዘው ደንብ የጣሱት ሚኒስትር ስልጣናቸውን እንዲለቁ ተገደዱ

    የጋና ንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚያዘውን ሕግ በመጣሳቸው ሥራቸውን እንዲለቁ ተገደዋል።

    የፓርላማ አባል የሆኑት ካርሎስ አሄንኮራህ፤ ራሳቸውን ለይተው የሚቆዩበትን ጊዜ ሳያጠናቅቁ በቴማ ከተማ ወደሚገኘው የምርጫ ምዝገባ ማዕከል በመሄድ ጉብኝት አድርገው ነበር ተብሏል።

    ሚኒስትሩ በበኩላቸው የበሽታው ምልክት እንደማይታይባቸው በመግለፅ፤ አካላዊ ርቀታቸውንም ጠብቀው እንደነበር ተናግረዋል።

    አንዳንድ ጋናዊያን ሚኒስትሩ የጥንቃቄ ሕጉን በመጣሳቸውና በርካታ ሰዎችን አደጋ ላይ በመጣላቸው ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ እየጠየቁ ነው።

    በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና፤ እስካሁን ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

    አገሪቷ ከባለፈው ወር ጀምራ የጣለቻቸውን ገደቦች ማላላት በመጀመሯም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

    ጋና በመጭው ታህሳስ ወር ለሚካሄደው ምርጫ ምዝገባ እያካሄደች ነው።

  20. ሶማሊያ የአገር ውስጥ በረራ እንዲጀመር ፈቀደች

    የሶማሊያ ካቢኔ ከእሁድ ጀምሮ የአገር ውስጥ በረራ እንዲጀመርና ወደ ክልሎች በቀን አንድ ጊዜ የመንገደኞች በረራ እንዲደረግ ፈቀደ።

    የአገሪቱ የአየር ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሞሐመድ አብዱላሂ ኦማር ለቢቢሲ እንደገለፁት አየር ማረፊያዎቹ ወደ ሥራ የተመለሱት ጥንቃቄ የተሞላባቸውን ሒደቶች ተከትሎ ነው።

    ምንም እንኳን በአገሪቱ ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር ባይውልም፤ የመንገደኞችን ቁጥር በመቀነስ በረራዎችን ለመጀመር አሁን ትክክለኛ ሰዓት መሆኑን የካቢኔ አባላቱ ተስማምተዋል።

    በዚህም ወደፊት በአንድ ቀን 6 የአገር ውስጥ በረራዎች ይኖራሉ ተብሏል።

    ከዚህም በተጨማሪ መንገደኞቹ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ፣ የእጅ ማፅጃ ፀረ ተህዋስ እንዲጠቀሙ በማድረግ እንዲሁም በአውሮፕላን ውስጥ ማድረግ የሚገባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመከተል እንዲጠነቀቁ ይደረጋል ብለዋል።

    ሶማሊያ ከሦስት ወራት በፊት ቫይረሱ ወደ አገሪቱ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ሁሉንም በረራዎችን ሰርዛ ነበር።

    አገሪቱ እስካሁን 2 ሺህ 944 በቫይረሱ ተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን፤ 90 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።