የማክሰኞ ሰኔ 30/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ
እንደምን አደራችሁ?
ቢቢሲ አማርኛ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ ዜናና መረጃዎችን በተለይ በዚህ ገጽ ላይ በቀጥታ እናቀርባለን።
ስለወረርሽኙ ጠቃሚ ትኩስ መረጃዎችን ለማግኘት በአመቻችሁ አጋጣሚ ሁሉ ይህንን የቀጥታ ዘገባ ገጽ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።
መልካም ዕለት ይሁንላችሁ!
ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሰሞኑ የድምፃዊ ሃጫሉ መኪና ውስጥ መገደል ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት ምክንያት የላብራቶሪ ናሙናዎችን መሰብሰብ ችግር አጋጥሞ እንደነበር የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።በዛሬው ዕለት በ1ሺህ 929 ናሙናዎች ላይ ምርመራ መደረጉን ሚኒስቴሩ ያሳወቀ ሲሆን በዚህም 108 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።በዚህም መሰረት በሃገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 774 ደርሷል። ከነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት 3ሺህ 301 ከህመሙ ማገገማቸውም ተገልጿል።የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በአግባቡ መከተል ራስንም ሆነ ሌሎችን ለመከላከል ሁነኛ መላ መሆኑን ባለሙያዎችና መንግሥት ዘወትር ይመክራሉ። በመሆኑም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፈንጫን መሸፈን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
እንደምን አደራችሁ?
ቢቢሲ አማርኛ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ ዜናና መረጃዎችን በተለይ በዚህ ገጽ ላይ በቀጥታ እናቀርባለን።
ስለወረርሽኙ ጠቃሚ ትኩስ መረጃዎችን ለማግኘት በአመቻችሁ አጋጣሚ ሁሉ ይህንን የቀጥታ ዘገባ ገጽ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።
መልካም ዕለት ይሁንላችሁ!
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በ2426 ናሙናዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎ ተጨማሪ 102 ሰዎች ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት ዕለታዊ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው በቫይረሱ ከተያዙት ሌላ 65 ሰዎች ከበሽታው ሲያገግሙ የአንድ ሰው ሕይወት ደግሞ ማለፉ ተገልጿል።
በሽታው በአገሪቱ መኖሩ ከታወቀ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ 266 ሺህ 323 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ በ6 ሺህ 666 ሰዎች ላይ የወረርሽኙ ቫይረስ የተገኘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 3 ሺህ 199 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
ከአስር ካናዳውያን ስምንቱ አገራቸውን ከአሜሪካ ጋር የሚያዋስነው ድንበር ተዘግቶ እንዲቆይ ይፈልጋሉ ተባለ። እጅግ አስፈላጊ ለሆነ ጉዳይ ወደ ካናዳ የሚገቡ ሰዎች ብቻ እንዲፈቀድላቸው ነው ካናዳውያኑ የሚፈልጉት።
ጎረቤታቸው አሜሪካ ውስጥ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨቱን ቀጥሏል።
በርካታ ካናዳውያን ድንበሩ እንዲከፈት እንደማይፈልጉ የታወቀው ግሎብ ኤንድ ሜል የተሰኘው ጋዜጣ በሠራው የዳሰሳ ጥናት ነው።
የአሜሪካና የካናዳ እንዲሁም የአሜሪካና የሜክሲኮ ድንበር የተዘጋው መጋቢት ላይ ነበር። በዳሰሳ ጥናቱ መሠረት፤ 81 በመቶ የሚሆኑ ካናዳውያን ድንበሩ ላልተወሰነ ጊዜ እንደተዘጋ እንዲቆይ ይሻሉ።
14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የበሽታው ስርጭት ሲቀንስ ድንበሩ ይከፈት ብለዋል።
በካናዳ በበሽታው የተያዙ ሰዎች 105,000 ሲሆኑ፤ በአሜሪካ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
እስራኤል የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር በድጋሚ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጣለች።
የምሽት ክበቦች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያዎችና የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾች ከዛሬ ጀምሮ ይዘጋሉ ተብሏል።
በእምነት ተቋምና በምግብ ቤቶች መገኘት የሚችሉ ሰዎች ቁጥርም ተገድቧል።
ከግንቦት ወዲህ በየቀኑ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 1,000 ከፍ ብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ወረርሽኙ እየተሰራጨ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። በርካቶች ክፉኛ እየታመሙ ነው” ብለዋል።
እስራኤል አገር አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣሏ በፊት ከዚህ ቀደም የወሰደቻቸውን እርምጃዎች መመለስ እንዳለባትም አክለዋል።
ሕንድ- የሕንድ ሳይንቲስቶች ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ለነሀሴ ቀነ ገደብ መቀመጡ የተጋነነ ነው አሉ። ቀነ ገደቡን ያስቀመጠው የሕንድ የጤና ባለሙያዎች ካውንስል ነው።
በሕንድ ባለፉት 24 ሰዓታት 24,000 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም በበሽታው በተያዙ ሰዎች ብዛት ከዓለም ሦስተኛ አድርጓታል።
አሜሪካ- በሌላ በኩል የአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ተቋም ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ዓመት ክትባት ይገኛል ማለታቸው ላይ ጥያቄ እንስቷል።
አውስትራሊያ- ኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ከቪክቶሪያ ጋር የሚያዋስናት ድንበሯን ዘግታለች።
ቦሊቪያ- የጤና ሚንስትር ኤዲ ሮካ ኮቪድ-19 ተገኝቶባቸዋል። ከአገሪቱ የካቢኔ አባላት በቫይረሱ የተያዙ ሦስተኛው ሰው ናቸው።
ፈረንሳይ- በፓሪስ ዝነኛው ሉቭሬ ሙዝየም ተከፍቷል። ለአራት ወራት ተዘግቶ ነበር። የጎብኚዎች ቁጥር ተወስኖ፣ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ይሆናል ተብሏል።
ስፔን- ጋሊሲያ እና ካታሎኒያ በተባሉ ግዛቶች ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።
ባጠቃላይ በዓለም በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከ11,470,000 በላይ ሲሆኑ፤ 534,000 ሰዎች ሞተዋል።
ማዳጋስካር መዲናዋ አንታናናሪቮን የሚጠቀልለውንና ከዋነኛ ግዛቶቿ አንዱ የሆነውን ክፍል ከእንቅስቃሴ ውጪ አደረገች። ከዚህ ቀደምም በግዛቱ እንቅስቃሴ ታግዶ ነበረ። በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች መጨመራቸውን ተከትሎም በድጋሚ እገዳ ተጥሏል።
ከሐምሌ 20 በኋላ ወደ ግዛቱ መውጣትም ሆነ መግባት አይቻልም። ሰዓት እላፊ ገደብም ይታወጃል።
ከጠዋት እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከአንድ ቤት አንድ ሰው ብቻ ነው መውጣት የሚችለው።
ለ24,000 ምርመራ ተደርጎ እስካሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች 2,941 ሲሆኑ 32 ሰዎች ሞተዋል።
ግንቦት ላይ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት አንድሪ ራጆሊና ከቅጠላቅጠል የሚሠራ፣ ኮሮናቫይረስን የሚከላከልና የሚያድን መድኃኒት አለን በማለታቸው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
እስካሁን በሳይንስ ፍቱንነቱ ባይረጋገጥም የአፍሪካ አገራት ለመሞከር ፍላጎት አሳይተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ስለመድኃኒቱ ፍቱንነት እና ለጉዳት እንደማያጋልጥ ሳይንሳዊ መረጃ እፈልጋለሁ ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት ሙከራ ያልተደረገባቸው መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
'ኮቪድ-19 ፖለቲካዊ ጨዋታ ነው' የተፈጠረውም በአሜሪካ ነው ሲል አንድ የሴራ ፅንሰ-ሐሳብ የሚተነትን ቪድዮ በፌስቡከኞች ዘንድ አምስት ሚሊዮን ጊዜ ሲታይ፤ 100 ሺህ ሰዎች ተጋርተውታል።
ምንም እንኳ ቪድዮው አሁንም በፌስቡክ ድር ላይ የሚገኝ ቢሆንም "የሐሰት" የሚል ታርጋ ተለጥፎበታል። ይህን ያደረጉት የፌስቡክ ሰዎች ናቸው።
ዩትዩብ የተሰኘው የተንቀሳቃሽ ምስሎች ድር ላይ ደግሞ 'ያልተገባ ወይም ጎጂ ሐሳብ የያዘ' የሚል ርዕስ ሰፍሮበታል።
ፊልሙ ማሕበራዊ ድር-አምባዎች ላይ የተለጠፈው 'የሴራ ፖለቲካ እንተነትናለን' በሚል ግለሰብ ሲሆን፤ ለጣፊው 'ፕሬዝንደንት ትራምፕ በሙስናና በሕፃናት ብዝበዛ ወንጀል የተዘፈቁ የዓለም ፖለቲከኞችን እየተፋለሙ ነው' ሲል ያምናል።
ፊልሙ በርካታ ያልተረጋገጡ ፅንሰ-ሐሳቦችን ይተነትናል። ዴሞክራት ፖለቲከኞች በአሜሪካ ምርጫ ዘመን ሆነ ብለው ነው ወረርሽኙን የፈበረኩት ሲል ይወነጅላል።
ፈረንሳይ ውስጥ አንድ የ59 ዓመት የሕዝብ ትራንስፖርት ሹፌር መንግሥት የጣለውን ሕግ አስከብራለሁ በማለታቸው ክፉኛ ደብደባ ደርሶባቸዋል።
ሹፌሩ ወደ አውቶብሳቸው የሚገቡ ሰዎች ጭምብል እንዲያጠልቁ ያስገድዳሉ። ነገር ግን አራት ሰዎች ይህን ችላ ብለው ሊገቡ ሲሉ የከለከሉት ሹፌር ሕግ በማስከበራቸው ምስጋና ሳይሆን ክፉኛ ድብደባ ነው የደረሰባቸው።
ፖሊስ ከአራቱ ሰዎች አንድ ሰው በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ማለቱን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሹፌሩ ግን ከደብደባው የተነሳ አእምሯቸው ሥራውን አቁሟል ሲሉ ዶክተሮች አሳውቀዋል። የመትረፋቸውም ነገር የማይታሰብ ነው ተብሏል።
ፈረንሳይ ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያጠልቁ የሕዝብ ትራንስፖርት መሳፈር አይቻልም።
የሥራ አጋራቸው ላይ የደረሰውን ጥቃት ተክትሎ በርካታ የባስ ሹፌሮች የሥራ ማቆም አድማ መተዋል።
የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ተጥሎ የነበሩ ማዕቀቦችን ማንሳት ጀምረዋል።
ምንም እንኳ ፕሬዝደንቱ ማዕቀቦችን ያንሱ እንጂ በሃገሪቱ አሁንም በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም።
ከመዲናዋ ናይሮቢ፤ እንዲሁም ከሞምባሳና ማንዴራ ከተሞች መግባትና መውጣት ተከልክሎ ነበር። ፕሬዝደንቱ ይህን የእንቅስቃሴ ገደብ አንስተዋል።
ነገር ግን ከምሽት 3 ሰዓት እስከ ንጋት 10 ሰዓት የተጣለው ሰዓት እላፊ ለሚቀጥሉት 30 ቀናት ይቆያል።
ፕሬዝደንቱ ቤተ-አምልኮዎች ከዛሬ ጀምሮ እንዲከፈቱ ወስነዋል። ቢሆንም ቤተ-አምልኮዎቹ ተከፍተው የሚቆዩት ለአንድ ሰዓት ሲሆን ከ100 ሰው በላይ መሳተፍ አይችልም።
ፕሬዝደንቱ አክለው የሃገር ውስጥ በረራ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደሚከፈት ይፋ አድርገዋል።
ዓለም አቀፍ በረራ ደግሞ ከፈረንጆቹ ወርሃ ነሃሴ ጀምሮ ሊከፈት እንደሚችል ነገር ግን ወረርሽኙን ለመግታት አስፈላጊው እርምጃ ተግባራዊ እንደሚደረግ አሳውቀዋል።
ፕሬዝደንቱ ወረርሽኙ የሚያገረሽ ከሆነ ሃገሪቱ ወደ እንቅስቃሴ ገደብ ልትመለስ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።
ኬንያ እስካሁን 7886 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ስታረጋግጥ 160 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
ቀደም ሲል ህንድ ውስጥ ክትባት ለማግኘት እየተደረገ ያለው ሙከራ ነሐሴ አጋማሽ ላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል መባሉ ተጨባጭ አይደለም ሲል የሕንድ የሳይንቲስቶች ቡድን ገለጸ።
ታዲያ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ምን ተስፋ አለ?
ባለሙያዎች እንደሚሉት የአንድ በሽታን ክትባት ለማግኘት አስርታት ባይሆን እንኳን ዓመታትን ይፈልጋል። ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ያሉ ተመራማሪዎች ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በፍጥነት ለማግኘት እየሰሩ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አገራት ውስጥ 120 የሚደርሱ ክትባቶችን የማዘጋጀት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና የለንደኑ ኢምፔሪያል ኮሌጅ በሰው ላይ ሙከራ ማድረግ ጀምረዋል።
ክትባቱ መቼ ለአገልግሎት ይውላል ለሚለው አንዳንድ የጤና ባለስልጣናት ክትባቱ በሚቀጥለው ታህሳስ ወር መጨረሻ ወይም ጥር መጀመሪያ ላይ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ። አንዳንዶች ግን ጥርጣሬ አላቸው።
ከሰሞኑ የመተንፈሻ ቀዳዳ ወይም ቫልቭ የተገጠመላቸው (በተለምዶ N95) የሚባሉ ማስኮች በሽታ ለመከላከል የሚውሉ እንዳልሆኑ የመድሃኒትና ምግብ ባለሥልጣን አስታውቋል።
በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብደላ ካሶ እነዚህ የአፍና የአፍንጫ ማሸፈኛዎች በተለይ ይህንን በሽታ የሚያባብሱ እንጂ ጥቅም የሚሰጡ እንዳልሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህ ማስኮች የሚጠቀመውን ሰው የሚጠብቁና ሌላውን ሰው ግን የሚያጋልጡ "ራስ ወዳድ ማስኮች ናቸው" ሲሉም ይገልጿቸዋል።
በመሆኑም ይህንን በሽታ ለመከላከል የሚውሉ የመተንፈሻ ቀዳዳ (ቫልቭ) የሌላቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች በመሥሪያ ቤቱ ተመዝግበውና ተገምግመው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግም ያስረዳሉ።
አቶ አብደላ እንደሚሉት ከሆነ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎቹ ባክቴሪያ ወይም ቫይረስን ከውጭም ሆነ ከውስጥ የማላሳለፍ ብቃታቸው እንዲሁም በአተነፋፈስ ላይ የሚያመጣው ችግር መኖር አለመኖሩን በተመለከተም የጥራት ፍተሻ ይደረግላቸዋል።
የመተንፈሻ ቀዳዳ የተገጠመላቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች ለሌሎች አላማ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በኢንዱስትሪዎች፣ በማዕድን ማውጣትና በመድሃኒት ርጭት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲሁም ስፖርተኞች እንደሚጠቀሟቸው ይገልጻሉ፡፡ ማድረግ ያለብን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ምን ዓይነት ነው?
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ሪፖርት ባለፉት 24 ሰዓታት በኢትዮጵያ በ3 ሺህ 315 ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 178 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ይህም አጠቃላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 6 ሺህ 564 አድርሶታል።
የወረርሽኙ ዕለታዊ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው ከዚህ ቀደም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከልም 116 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ134 ደርሷል።
ከበሽታው ጋር በተያያዘ የ2 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን በአጠቃላይ በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 118 ደርሷል።
እስካሁን በአገሪቱ 263 ሺህ 897 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
የእስያዊቷ አገር ሲሪላንካ ባለሥልጣናት በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስክሬን እንዲቃጠል ጫና እያደረጉ ነው።
አስክሬን ማቃጠል በሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ ክልክል ቢሆንም፤ በአገሪቷ የሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሙስሊም ማህበረሰቦች ግን ወረርሽኙን በማስታከክ መገለል እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው የ44 ዓመቷ ፋጢማ ሪኖዛ፤ በኮቪድ-19 ተጠርጥራ ሆስፒታል የገባችው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።
በዋና መዲናዋ ኮሎምቦ ትኖር የነበረችው ፋጢማ፤ በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ የመተንፈሻ አካል ህመም የነበራት ሲሆን ባለሥልጣናት በኮሮና ሳትያዝ እንዳልቀረች ሰግተው ነበር።
ሆስፒታል በገባችበት በዚያኑ ዕለት ታዲያ ቤተቦቿ በባለሥልጣናት ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው ባለቤቷ ሞሃመድ ሻፌክ ይናገራል።
"ፖሊስና ወታደሮች ከባለሥልጣናት ጋር ወደ ቤት መጥተው እንድንወጣ ከተደረግን በኋላ ቤቱ በፀረ ተህዋስ ተረጨ። ሁላችንም በጣም ተጨንቀን ነበር፤ ምንም የነገሩን ነገር አልነበረም። የሦስት ወር ህፃን ሳይቀር የተመረመረ ሲሆን እንደ ውሻ አንጠልጥለው ነበር ወደ ለይቶ ማቆያ የወሰዱት" ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስረዳል።
ሞሃመድ እንደሚለው ቤተሰቦቹ ምሽቱን በቁጥጥር ሥር አሳልፈው፤ በሚቀጥለው ቀን ተለቀቁ። ለሁለት ሳምንታትም እራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ተነገራቸው። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ባለቤቱ ሆስፒታል እያለች መሞቷ ተነገራቸው።
ከዚያም የፋጢማ ትልቁ ልጅ ሆስፒታል በመሄድ የእናቱን አስክሬን እንዲለይ ተነገረው። ወደዚያው አቀና። የሞተችው በኮቪድ-19 በመሆኑ አስክሬኗን መውሰድ እንደማይችሉ ተገለፀለት።
ቤተሰቡ እንደሚለው ምንም እንኳን በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ አስክሬን ማቃጠል የተከለከለ ቢሆንም አስክሬኗ እንዲቃጠል እንዲፈርም አስገድደውት ነበር።
በሲሪላንካ አስክሬን ማቃጠልን የሚፈቅደውን ሕግ በመቃወም የተሰባሰበው ፊርማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መድረሱ ታውቋል።
በህንዷ መዲና ደልሂ አስር ሺህ አልጋዎች ያሉት የኮሮናቫይረስ ህክምና ማዕከል በዛሬው ዕለት ባለሥልጣናቱ መርቀው ከፍተዋል።
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ህሙማንን እንዲሁም መካከለኛ ምልክቶችን የሚያሳዩትን የሚያክም ሲሆን የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ለማያሳዩት ግን ህክምና አይሰጥም ተብሏል።
የማዕከሉ ስፋትም 20 የእግር ኳስ ሜዳዎችን ያክላል የተባለ ሲሆን የሃገሪቱም ሚዲያዎች በአለም ትልቁ መሆኑንን እየዘገቡ ነው።
ደልሂ በወረርሽኙ በሃገሪቱ ክፉኛ ከተጠቁ ከተሞች አንዷ ናት።
በሃገሪቱ በትናንትናው ዕለት 24 ሺህ 800 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከፍተኛውም ቁጥር ነው ተብሏል። ሃገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 19 ሺህ መድረሱ ተገልጿል።
በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ባለባት የቦሊቪያዋ ትልቋ ከተማ ኮቻባምባ በርካታ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመቅበር ቀናት መጠበቅ ግዴታ ሆኖባቸዋል።
አንዳንዶቹም በቤታቸው ውስጥ አስከሬኖችን ለቀናት ማስቀመጣቸው ለበለጠ ጭንቀት ዳርጓቸዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ተገደዋል። በባለፈው ሳምንት እሁድ የሞተው የ62 አመቱ ግለሰብ ዘመዶች አስከሬኑን በጎዳናው ላይ ለሰዓታትም አስቀምጠዋል።
በማዕከላዊ ከተማዋ 600 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ያሉ ሲሆን ባለስልጣናቱም አስራ ሰባት አስከሬኖችን በቀን እየሰበሰቡ እንደሆነም አስታውቀዋል።
በከተማዋ ዋና መካነ መቃብርም መጨናነቅ ተፈጥሯል ተብሏል። የከንቲባው ፅህፈት ቤት በርካታ የመቃብር ስፍራዎችን እየቆፈረ እንደሆነ የገለፀ ሲሆን ይህ ግን ባለው ተቃውሞ እንደተፈለገው ሊሳለጥ አልቻለም።
የተቃውሞው መነሻም አስከሬን ያስቀመጡ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንጠቃለን በሚል ስጋት ነው።
መቃብር ቆፋሪዎች በበኩላቸው በኮሮናቫይረስ ለሚሞቱ ሰዎች የተለየ መካነ መቃብር እንዲዘጋጅ መንግሥትን ጠይቀዋል።
የደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቦሊቪያ ማዕድን ሚኒስትር ጆርጅ ፈርናንዶ ኦሮፔዛ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገለፀ።
ሚኒስትሩ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁለተኛው የካቢኔ አባል ናቸው።
ሌላኛው የካቢኔ አባል የርኮ ኑኔዝ፤ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ካወቁ በኋላ በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው እንደሚገኙ ያስታወቁት ሐሙስ ዕለት ነበር።
በቦሊቪያ እስካሁን 37 ሺህ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከሌሎች ጎረቤት አገራት፤ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙባት ብራዚልና በቫይረሱ የተያዙ 300 ሺህ ሰዎች ከመዘገበችው ፔሩጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ አነስተኛ ነው።
ለዚህም የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ተነግሯል።
ይሁን እንጅ ቅዳሜ ዕለት በኮቻባማ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ገደቦቹን በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።
በወቅቱም በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አራት ፖሊሶች የተጎዱ ሲሆን፤ 15 ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።