በኢትዮጵያ 3 ሺህ 301 ሰዎች ሲያገገግሙ የሟቾች ቁጥር 120 ደረሰ

ከሰሞኑ የድምፃዊ ሃጫሉ መኪና ውስጥ መገደል ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት ምክንያት የላብራቶሪ ናሙናዎችን መሰብሰብ ችግር አጋጥሞ እንደነበር የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።በዛሬው ዕለት በ1ሺህ 929 ናሙናዎች ላይ ምርመራ መደረጉን ሚኒስቴሩ ያሳወቀ ሲሆን በዚህም 108 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።በዚህም መሰረት በሃገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 774 ደርሷል። ከነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት 3ሺህ 301 ከህመሙ ማገገማቸውም ተገልጿል።የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በአግባቡ መከተል ራስንም ሆነ ሌሎችን ለመከላከል ሁነኛ መላ መሆኑን ባለሙያዎችና መንግሥት ዘወትር ይመክራሉ። በመሆኑም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፈንጫን መሸፈን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በብራዚል የአሜሪካ አምባሳደር ከፕሬዝዳንት ቦልሳናሮ ጋር ግብዣ ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ ኮሮና ሊመረመሩ ነው

    በብራዚል የአሜሪካ አምባሳደር፣ በአሜሪካ የነጻነትን ቀንን አስመልክቶ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮን ጋብዘው ነበር።

    በዚህም የተነሳ የፕሬዝዳንቱ በኮቪድ-19 መያዝን አስመልክቶ ምርመራ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

    ቅዳሜ እለት ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጋር የአሜሪካውን አምባሳደር ቶድ ቻፕማንንን አቅፈው የአሜሪካ የነጻነት በዓልን ሲያከብሩ የተነሱት ምሰል በትዊትር ላይ ታይቷል።

    ፕሬዝዳንቱ በቫይረሱ መያዛቸው እንደተሰማ ኤምባሲው በትዊትር ላይ አምባሳደሩ “ምልክት አልታየባቸውም ነገር ግን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ያደርጋሉ” የሚል መልእክት አስፍሯል።

    የአሜሪካ ኤምባሲ መልእክት አክሎም ምርመራ እንደሚያደርጉ ገልጾ” የምርመራ አሰራሮችን ይከተላሉ” ብሏል።

  2. አሜሪካ እስካሁን ድረስ ለኮሮናቫይረስ ክትባት ምርመር ከፍተኛውን ገንዘብ ማፍሰሷ ተገለፀ

    የአሜሪካ መንግሥት 100 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ መድሃኒት ለማምረት ለግዙፉ የመድሃኒት አምራች ኖቫቫክስ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚከፍል ተገለፀ።

    ይህ ክፍያ እስካሁን ድረስ የአሜሪካ መንግሥት ከከፈለው ከፍተኛው ነው የተባለ ሲሆን ለመድሃኒት አምራቹ ደግሞ አራተኛው ነው ተብሏል።

    የአሜሪካ መንግሥት ከግል የምርምር ተቋማት ጋር ጥምረት ፈጥሮ የክትባት ምርምር ስራው በፍጥነት እንዲካሄድ እየሰራ ይገኛል።

    ኖቫቫክስ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ምርት አለማምረቱ ተገልጿል።

    የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ስታንሊ ኤሪክ ለሲኤንኤን ሰኞ እለት እንደተናገሩት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የገቡት ይህ ስምምነት "ክትባቱን ለመስራት በኛ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

    አክለውም 100 ሚሊየን ክትባቶችን በመጪው ዓመት የካቲት ወር ላይ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ገልፀዋል።

  3. የብራዚሉ ፕሬዝዳንት በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

  4. በአንድ መጠጥ ቤት አንድ ግለሰብ በኮሮና በመያዙ 90 ሰዎች ጋር የደወለችው ባለቤት

    በእንግሊዝ በሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት አንድ ግለሰብ በኮሮናቫይረስ መያዙን ተከትሎ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ያላቸውን ዘጠና ደንበኞች ጋር ባለቤቷ መደወል ነበረባት። "ይህ ሁኔታ አስጨናቂ ነው" ትላለች።

    ላይትሃውስ ኪችን የተባለ መጠጥ ቤት ባለቤት የሆነችው ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገረችው እንግሊዝ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን ማላሏቷን ተከትሎ ቅዳሜ እለት መጠጥ ቤቷን ከፍታ ነበር። መጠጥ ቤቱም ከመጡ ሰዎች መካከልም አንዱ ግለሰብ በኮሮናቫይረስ መያዙ ታወቀ። እናም ባለቤቲቱ መጠጥ ቤቱ የመጡ ደንበኞችን ማፈላለግ ነበረባት።

    "ዋናው ነገር ሁሉም ደህንነታቸውን ማረጋገጥ ነበረብን። ስለዚህ ደንበኞቻችን ጋር ደውለን ማረጋገጥ ነበረብን" ብላለች

    "ደንበኞቻችን ጋር ደውለን ለመጨረስ ሙሉ ቀን ፈጅቶብናል። ምንም እንኳን በርካታ ሰዎች በመጠጥ ቤቱ የነበሩ ቢሆንም የዘጠና ደንበኞቻችን ስምና ስልክ ቁጥር ነበረን ስለዚህ እነሱ ጋር ደውለን የሆነውን ነገር መንገር ነበረብን" በማለት አስረድታለች።

    • በኢትዮጵያ 108 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል

      ዛሬ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሰጡት መግለጫ ባለፉት 24 ሰዓታት 1 ሺህ 969 ናሙናቸውን መመርመሩን ገልፀዋል።

      ባለፉት 24 ሰዓታት ከተወሰዱት ናሙናዎች 108 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ሲረጋገጥ ይህም በአገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 6 ሺህ 774 አድርሶታል።

      በመግለጫው ላይ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ሲጠቀስ ይህም የሟቾችን ቁጥር 120 እንዲሆን አድርጓል።

      በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በተመለከተም በአዲስ አበባ 52፣ በሶማሊያ 28፣ በትግራይ ሶስት፣ በኦሮሚያ አራት፣ በቤንሻንጉል አንድ፣ በአፋር አራት፣ በጋምቤላ 13 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

      3 ሺህ 301 ሰዎች ማገገማቸው ሲገለጽ ከእነዚህ መካከል 102 ሰዎች አዲስ ያገገሙ መሆናቸው በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

      በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 268 ሺህ 292 ሺህ ናሙናዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

    • የቴክሳስ የሕግ አስከባሪዎች ጭምብል የማያደርጉትን ማስገደድ እንቸገራለን አሉ

      በቴክሳስ ሕግ አስከባሪዎች ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲደረግ የሚያዘውን መመሪያ እንደማያስፈጽሙ ተናገሩ።

      የቴክሳስ አገረ ገዢ በሚያስተዳደሩት ግዛት በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች መጨመሩን ተከትሎ በየትኛውም የግዛቲቱ ክፍል የአፍና አፍንጫ እንዲደረግ ቢያዙም አንዳንድ አስተዳዳሪዎች ግን አሻፈረኝ ብለዋል።

      የዴንቶን ካውንቲ ፖሊስ “ይህ ህግ ሳይሆን ትዕዛዝ ነው” በማለት ለማስፈፀም አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል።

      የሞንቶጎሜሪ ካውንቲ ፖሊስ በበኩላቸው መመሪያውን ለማስፈፀም የሚያስቸግረው ሰዎች መብታችን ተጣሰ ብለው ሊከሱ ይችላሉ በሚል ነው።

      አገረ ገዢው በትዕዛዛቸው ሰዎች በሚሰበሰቡበት ስፍራ ጭምብል የማያደርጉ የግዛታቸውን ነዋሪዎች ያስጠነቀቁ ሲሆን በተደጋጋሚ ሳያደርጉ የተገኙ 250 ዶላር እንደሚቀጡ ገልፀዋል።

      መመሪያው አክሎም ማንኛውም ዜጋ የአፍና አፍንጫ ጭምብል ባለማድረጉ ምክንያት በቁጥጥር ስር አይውልም አይታሰርም ይላል።

      የአገረ ገዢውን ትዕዛዝ የሚተቹ አካላት ይህ ለማስፈፀም አስቸጋሪ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

    • የኬንያ ትምህርት ቤቶች እስከ መጪው አመት ጥር ወር ድረስ ተዘግተው እንዲቆዩ ተወሰነ

      በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጭማሬ እያሳየባት ባለው ኬንያ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ መጪው አመት ጥር ወር ድረስ ተዘግተው እንዲቆዩ ተወስኗል።

      የኬንያ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳሳወቀው ሁሉም ተማሪዎች አሁን ባሉበት የክፍል ደረጃቸው በመጪው አመት እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።

      ሚኒስትሩ ጆርጅ ማጎሃ እንዳሉት ለአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የአመቱ ማጠቃለያ ፈተናም አይሰጥም ብለዋል።

      ፈተናው ይሰጥ የነበረው ጥቅምትና ህዳር ወራት ላይ ነበር።

      ነገር ግን ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ከጥብቅ መመሪያ ጋር በመስከረም ይከፈታሉ ብለዋል።

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ኬንያ ትምህርት ቤቶችን የዘጋችው በመጋቢት ወር ነበር።

      አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በኢንተርኔት ትምህርት እየሰጡ ነበር።

      በትናንትናው ዕለት አገሪቷ ዘግታው የነበረውን የሶስት ግዛቶች እንቅስቃሴ መክፈቷን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስታውቀዋል።

      ፕሬዚዳንቱ ለትምህርት ሚኒስቴርም ያለውን እቅድ እንዲያቀርብ ሃያ አራት ሰአት በትናንትናው ዕለት ሰጥተው ነበር።

    • ብሩንዲ ሰፊ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ልታካሄድ ነው

      ብሩንዲ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመዋጋት አዲስ የኮቪድ-19 ምርመራ ዘመቻ ለመጀመር ይፋ አድርጋለች።

      ይህ የምርመራ ዘመቻ ይፋ የተደረገው በአዲሱ አስተዳደር ነው።

      የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፒሬ ንኩሩንዚዛ ስለኮሮናቫይረስ እምብዛም ትኩረት አልሰጡም ተብለው ይተቹ ነበር። በልብ ድካም ከመሞታቸው 15 ቀን ቀደም ብሎ " ፈጣሪ ኮሮናቫይረሰን ከብሩንዲ ሰማይ ላይ አጥርቶታል" ሲሉ ተደምጠው ነበር።

      ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ሟቹን ፕሬዝዳንት የተኩት ኤቫርስቴ ንዳዪሺሚዬ ኮሮናቫይረስ "የብሩንዲ ቀንደኛ ጠላት" ሲሉ በመናገር "በጠላት" ላይ ውጊያ ማወጃቸውን ተናግረዋል።

      ይህ በቡጁምቡራ የተጀመረው ዘመቻ ላይ ባልተለመደ ሁኔታም በርካቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ታይተዋል።

      በአንድ ቀን 640 ሰዎች የተመረመሩ ሲሆን ይህም በብሩንዲ ቫይረሱ መግባቱ ከታወቀበት መጋቢት ወር ጀምሮ ከፍተኛ ነው ተብሏል።

      አዲሱ ፕሬዝዳንት የስልጣን መንበሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ 1900 ሰዎች ሲመረመሩ ነገር ግን በቀድሞው ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን 1200 ብቻ መመርመራቸው ተገልጿል።

      የጤና ሚኒስትሩ ትክክለኛ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ የምርመራ ዘመቻው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

      በብሩንዲ 191 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ባለፈው ሶስት ወር ለ3 ሺህ 200 ሰዎች ብቻ ነው ምርመራ የተደረገው።

    • "የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለማያደርጉ ክብር የለኝም"-ቶም ሃንክስ

      በመጋቢት ወር አውስትራሊያ ለሥራ በተጓዘበት የኮቪድ-19 ተይዞ ያገገመው ቶም ሃንክስ "ህዝብ በተሰበሰበበት የአፍና አፍንጫ ለማያደርጉ ሰዎች " ክብር የለኝም" ሲል ተናግሯል።

      ተዋናይ ቶም ሃንክስና ባለቤቱ ሪታ ዊልሰን መጋቢት ወር ላይ ኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠው ለፊልም ቀረጻ አውስትራሊያ ሂደው በነበረበት ወቅት ነው።

      በርካታ መንግሥታት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ቢመክሩም አሁንም ግን በበርካታ ስፍራዎች ግዴታ አይደለም።

      ሃንክስ እንዳለው " አይገባኝም፤ በጭራሽ አይገባኝም፤ ልናደርገው የምንችለው ትንሹን ነው"

      የኦስካር አሸናፊው ተዋናይ ይህንን ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ያለው፣ አዲሱን ፊልሙን በሚያስተዋውቅበት ወቅት ነው።

      “ማንም ሰው ማድረግ የሚችለውን ትንሹ ነገር ላይ ክርክር ማካሄድ ከፈለገ፣ በመንጃ ፈቃዱ ላይ እምነት አይኖረኝም” ብሏል።

      አክሎም “መኪና ስናሽከረክር፣ የፍጥነት ወሰንን ማክበር አለብን፣ ቅድሚያ መስጠት ለሚገባን ቅድሚያ እንሰጣለን፣ እግረኞችን ላለመግጨት እንጠነቀቃለን፤ እነዚህን ሶስት ነገሮች ካላደረግን መኪና መንዳት የለብንም” ብሏል።

      “ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለማያደርግ፣ እጆቹን ለማይታጠብና እና አካላዊ ርቀትን ለማይጠብቅ፣ ክብር የለኝም፤ መከራከሪያውም ጉንጭ አልፋ ነው” ሲል ተናግሯል።

      የኦስካር ተሸላሚው ቶም ሃንክስ በአሜሪካ አንዳንድ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ላለመድረግ ሲያመነቱ በመመልከቱ ነው ይህንን ሊል የቻለው።

      ይህ ደግሞ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም የተንፀባረቀ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በፎክስ ኒውስ የዜና ወኪል ላይ ቀርበው “ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

    • ጭምብል አለማድረግ "የማኅበረሰብ ጠንቅ" መሆን ነው ተባለ

    • 'ኸርድ ኢሚዩኒቲ' ውጤታማ ላይሆን ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ

    • የኮሮናቫይረስ "መድኃኒቶች" በጥቁር ገበያ እየተቸበቸቡ ነው

    • በምርመራ ኮቪድ-19 ከተገኘባቸው ሰዎች አብዛኞቹ ምልክት አያሳዩም ተባለ

      ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ምርመራ ተደርጎባቸው በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ ሰዎች 78 በመቶው ወይም ሦስት አራተኛው የሚሆኑት ምርመራ በተደረገላቸው ጊዜ ምንም አይነት የበሽታውን ምልክት እንዳላሳዩ ዛሬ ይፋ የተደረገ መረጃ አስታወቀ።

      የአገሪቱ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ መሰረት እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙ ቤቶች አለፍ አለፍ ተብሎ በተደረገ ምርመራ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

      ጽህፈት ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ በበሽታው ሰበብ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን መረጃ ያወጣ ሲሆን በዚህም ለሁለተኛ ተከታታይ ሳምንት የሟቾች ቁጥር መቀነሱን አመልክቷል።

      በዚህም መሰረት በኮሮናቫይረስ ሰበብ በዩናይትድ ኪንግደም መቀነስ ቢያሳይም ባለፈው ሳምንት የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ግን አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ በጣለችበት ወቅት ከነበረው አሃዝ የሚበልጥ ነው ተብሏል።

    • የዚምባብዌ ፖሊስ ያመፁ ነርሶችን እያሰረ ነው

      የዚምባብዌ ትልቁ የነርሶች ማሕበር፤ ፖሊስ በክፍያ ምክንያት ተቃውሞ ያሰሙ አባላቴን እያሰረ ነው ሲል ቅሬታ አሰምቷል።

      የዚምባብዌ ነርሶች ሃገሪቱ በገጠማት የኑሮ ውድነት ምክንያት ደመወዛችን በዶላር ይሁን ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

      የዚምባብዌ ኑሮ ውድነት 800 በመቶ ደርሷል።

      ቢያንስ 13 የማሕበራችን አመራሮችና አባላት ታሰረዋል ይላሉ የዚምባብዌ ነርሶች ማሕበር ፕሬዝደንት ኤኖክ ዶንጎ።

      ፕሬዝደንቱ አክለው አባሎቻቸው እሥር ቤት እንዳሉ ይታወቅ እንጂ ወንጀላቸው ምን አንደሆነ አልተነገራቸውም ይላሉ።

      ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪል ነርሶቹ በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ሲል ዘግቧል።

      15 ሺህ አባላት ያሉት ማሕበር ባለፈው ሳምንት ከደመወዝ ማነስ ጋር በተያያዘ አድማ እንመታለን ብሎ ነበር።

      ዚምባብዌ እስካሁን ድረስ 716 ዜጎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ አረጋግጣለች። 8 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

      • በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ

        በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ሆነ።

        የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ዝዌሊ ማኺዜ፤ አራት ግዛቶች የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ መጠን ሊጨምርባቸው እንደሚችል የተሰጋ መሆኑን ገልጸው፤ በእነዚህ አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ገደቦች ሊጣሉ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል።

        ግዛቶቹ ጉዋቴንግ፣ ምዕራባዊ ኬፕ፣ ምሥራቃዊ ኬፕ እና ክዋዙሉ ናታል ናቸው ተብለወል።

        በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የህሙማን ቁጥር የጨመረው በየቀኑ በሚደረገው ምርመራ በሺህዎች የሚቆጡ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው እየተረጋገጠ በመሆኑ ነው።

        በአገሪቱ ላይ አጠቃላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ባይጣል ኖሮ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በበሽታው የየተያዙ ሰዎች ሊገኙ ይችሉ እንደነበር የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

        ደቡብ አፍሪካ ለወራት ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ደረጃ በደረጃ በማላላት ሂደት ላይ ስትሆን፤ በዚህ ሳምንትም ትምህርት ቤቶች መልሰው እንዲከፈቱ አድርጋለች።

        በተያያዘም አገሪቱ በብሪታኒያው የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ አማካይነት የተዘጋጀውን የኮሮናቫይረስ ክትባት በሰዎች ላይ በሚደረገው ሙከራ ተሳታፊ ናት።

      • 'ጭምብል ማድረግ እራስንና ሌሎችን ከበሽታ ይጠብቃል' ባለሙያዎች

        የሮያል ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሰር ቬንኪ ራማክሪሽናን (ፕሮፌሰር) ጭንብል ማድረግ የሚያደርገውን ሰውና በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ከበሽታው እንደሚከላከል ማስረጃዎች አሉ ብለዋል።

        ፕሮፌሰር ራማክሪሽናን የሮያል ሶሳይቲ በጭምብል ላይ ባቀረባቸው ሁለት ሪፖርቶች ዙሪያ እንደተናገሩት "የተላለፉት መልዕክቶች ግልጽና ወጥ ስላልነበሩ" ሕብረተሰቡ ውስጥ "ጥርጣሬ" ተፈጥሯል።

        ከቤት ውጪ የአፍን የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አለመጠቀም ጠጥቶ እንደማሽከርከርና የመቀመጫ ቀበቶን እንዳለመጠቀም ሁሉ "ለኅብረተሰብ ጠንቅ" ድርጊት ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

        "ጭምብል አለማድረግ በእድሜ የገፉ ወላጆችንና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሁሉንም ሰው ለበሽታው ያጋልጣል" ብለዋል።

      • ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች መጨመር ስጋት ፈጥሯል

      • የቦሊቪያዋ ጤና ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

        የቦሊቪያዋ ጤና ሚኒስትር ኤይዲ ሮካ በኮቪድ-19 መያዛቸው ተነገረ።

        ሚኒስትሯ፤ በአራት ቀን ውስጥ ብቻ በኮሮናቫይረስ የተያዙ የቦሊቪያ ሦስተኛዋ የካቢኔ አባል ናቸው።

        በወረርሽኙ የተያዙት ሚኒስትር ከመሥሪያ ቤታቸው የወጣ መግለጫ እንደሚገልፀው ኤይዲ ሮካ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

        "ሚኒስትሯ የወረርሽኙን ሕግጋት አጥብቀው እየተከተሉ ነው። ራሳቸውን ለይተው፣ መድኃኒት እየተሰጣቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው" ይላል መግለጫው።

        "ኮሮናቫይረስን ለማጥፋት የምናደርገው ጥረት ይቀጥላል። የጤና ሚኒስትሯም አገግመው ይህንን ትግል እንዲቀላቀሉን እመኛለሁ" ያሉት ደግሞ የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝደንቱ ጀኒን አኔዝ ናቸው።

        11 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ያላት ቦሊቪያ እስካሁን ድረስ 38 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ አረጋግጣለች።

      • የብራዚሉ ፕሬዝደንት ቦልሶናሮ የኮቪድ-19 ውጤታቸውን እየጠበቁ ነው

        የብራዚሉ ፕሬዝንድት ጃይር ቦልሶናሮ ሌላ የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገዋል። ምርመራውን ያደረጉት ከፍተኛ ትኩሳት ስለታየባቸው ነው ተብሏል።

        ቦልሶናሮ፤ ሳንባቸውን ተምርምረው 'እጅግ ሰላም' መሆናቸውን አሳውቀዋል።

        የኮቪድ-19 ውጤታቸውን ዛሬ [ማክሰኞ] ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝደንቱም የነበሩባቸውን ቀጠሮዎች ሰርዘዋል።

        ፕሬዝደንቱ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲደርግላቸው ይሄ ለአራተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት የተደረጉ የሦስት ምርመራዎች ውጤት ፕሬዝደንቱ ኮሮናቫይረስ እንደሌለባቸው የሚያሳዩ ናቸው።

        ቦልሶናሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ሲያጣጥሉ እንደነበር አይዘነጋም። 'የማይጎዳ ጉንፋን' ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

        ብራዚል፤ በዓለማችን ከአሜሪካ በመቀጠል በርካታ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት አገር ናት። በበሽታው ምክንያት በሞቱ ሰዎች ቁጥርም አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

        ትላንት [ሰኞ] የብራዚል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአሜሪካ ኤምባሲ ተገኝተው ከፕሬዝደንቱ እና ከሌሎች የኤምባሲው ባለሥልጣናት ጋር ፎቶ ተነስተዋል።

        በፎቶው ላይ ባለሥልጣናቱ ምንም ዓይነት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አለማድረጋቸው የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል።

      • በሕንዷ ዋና ከተማ ብቻ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ ደረሰ

        በሕንዷ መዲና ደልሂ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነው።

        ሰኞ ዕለት ከ1000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ በጠቅላላው በከተማዋ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህን ተሻግሯል ሲል የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

        ቢሆንም ግን ከተያዙት ሰዎች መካከል ሦስት አራተኛው ከበሽታው ማገገም መቻላቸው ከከተማዋ የተሰማው በጎ ዜና ነው።

        የሟቾች ቁጥር ከ3 ሺህ በላይ እንደሆነ ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።

        ባለፈው ወር መጀመሪያ አካባቢ ደልሂ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙባት እንደነበር ተዘግቧል። አሁን ግን ሁኔታዎች ቀዝቀዝ ማለታቸው ተነግሯል።

        የከተማዋ ባለሥልጣናት በሽታውን ለመቆጣጠር አንድ መላ አድርገው የወሰዱት በርካታ ሰዎችን መመርመር ነው።

        ሕንድ፤ በኮሮናቫይረስ ብዙ ዜጎች የተያዙባት 3ኛዋ የዓለማችን አገር ሆናለች። ባለፈውት ጥቂት ቀናት በየቀኑ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘውባታል።

        በሕንድ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 690 ሺህ ነው።