በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ250 ሺህ በላይ ናሙናዎች ላይ ምርመራ ተደርጓል

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቻይናዋ ዉሃን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ የዓለማችን ሕዝቦች 10 ሚሊየን መሻገሩን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያሳያል። ይህ ወረርሽኝ በብዛት በአሜሪካና አውሮጳ ተስፋፍቶ ቢገኝም በአሁኑ ሰዓት ግን በአሜሪካ ከምን ግዜውም በላይ ስርጭቱ ጨምሯል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ስድስት ቀናት ብቻ አንድ ሚሊየን ገደማ ሲሆን፣ በአፍሪካና በምዕራብ እስያ ይህ ቁጥር መጨመር እያሳየ ነው ተብሏል። በኢትዮጵያም ቢሆን የኮቪድ-19 በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በአግባቡ መከተል ራስንም ሆነ ሌሎችን ለመከላከል ሁለኛ መላ መሆኑን ባለሙያዎችና መንግሥት ዘወትር ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሊባኖስ አየር መንገድ ዳግም በረራ ጀመረ

    ከቤሩት የተነሳው የመጀመሪያው አውሮፕላን በአዲስ አበባ አድርጎ ካይሮ፣ ለንደን የሚሄድ መሆኑ ተገልጿል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሊባኖስ ብቸኛው ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ከሶስት ወራት በኋላ ዳግም ተከፈተ።

    ለአሁኑ የቤሩት አየር መንገድ ካለው አቅም 10 በመቶ ብቻ የሚጠቀም ሲሆን መንገደኞች የኮቪድ-19 ምርመራ እንደሚያደርጉ ቫይረሱም ከተገኘባቸው በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው እንደሚቀመጡ ተገልጿል።

    ከቤሩት የተነሳው የመጀመሪያው አውሮፕላን በአዲስ አበባ አድርጎ ካይሮ፣ ለንደን የሚሄድ መሆኑ ተገልጿል።

    ሊባኖስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ለማድረግ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ብትጥልም የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ግን እንዲንኮታኮት አድርጎታል።

    በቅርብ ወራት ውስጥ የሊባኖስ የገንዘብ ያለውን አቅም 80 በመቶ ማጣቱ ተነግሯል።

    በርካታ ሊባኖሳውያንም የሚበላ ለመግዛት መቸገራቸው ተገልጿል።

    ሊባኖሳውያን ይህ የምጣኔ ሃብት ድቀት በአገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት እንዳያባብሰውና በርካታ የተማሩ ሰዎች አገራቸውን ጥለው እንዳይሰደዱ ሰግተዋል።

  2. የደበብ አፍሪካ የተቃዋሚ ፓርቲ ዳግም የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል ጠየቀ

    ደቡብ አፍሪካ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲ (የደቡብ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ተፋላሚዎች ፓርቲ) በአገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመጥቀስ ዳግም የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል ጠየቀ።

    እንደ ተቃዋሚው ጥያቄ ከሆነ የሚጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ጠንከር ያለ እንዲሆን ይፈልጋል።

    ተቃዋሚው ፓርቲ አክሎም ደቡብ አፍሪካ ጥላ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ያነሳችው የቫይረሱ ስርጭት መቀነስ ከመጀመሩ በፊት መሆኑን በመጥቀስ የቫይረሱ ስርጭትን ለመግታት ያለው ብቸኛ አማራች ዜጎች ቤታቸው ከተቀመጡ ነው ብሏል።

    "ምን ያህል አካላዊ ርቀት ብንጠብቅ፣ አፍና አፍንጫችን ብንሸፍንና እጃችንን ብንታጠብ የቫይረሱን መስፋፋትና ሞት አንቀንሰውም። ብቸኛው ቫይረሱን የመቆጣጠሪያ ስልት ቤት መቀመጥ ነው" ሲልም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

    ፓርቲው በመግለጫው ላይ የአገሪቱ የጤና ስርዓት እየጨመረ ያለውን የወረርሽኙን ስርጭት ሊሸከመው አይችልም ሲልም አስፍሯል።

    ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረጉ ሰዎች መካከል 151 ሺህ 209 ያህሉ ቫይረሱ ሲገኝባቸው 2 ሺህ 657 ሞተዋል።

    የጤና ሚኒስትር ዝዌለ ማክሂዜ ማክሰኞ እለት እየጨመረ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት በመጥቀስ “ነገሮች እየከበዱ ነው” ብለዋል።

    ደቡብ አፍሪካ ለረዥም ጊዜ የቆየ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ከቆየች በኋላ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ብትከፍትም አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ መገኘታቸው ስጋቱን አባብሶታል።

  3. "ሠርግና ሞት አንድ ነው" ብለው የተሰባሰቡ በኮሮናቫይረስ ተያዙ

    ቢሃር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሕንድ ሰሜናዊ ቢሃር ግዛት በአንድ ሠርግ ላይ የታደሙ 111 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገለፀ።

    አንድ የአገር ውስጥ መገናኛ እንደዘገበው ምንም እንኳ ቫይረሱ ይኑርበት አይኑርበት ባይረጋገጥም ሙሽራው በማግስቱ ሞቷል ብሏል።

    በሠርጉ ላይ 350 ሰዎች መታደማቸውን ሙሽራው በሠርጉ ላይ ለመገኘት 1ሺህ 95 ኪሎ ሜትር ነድቶ መምጣቱ ተገልጿል።

    የአካባቢው ባለስልጣናት በሠርጉ ላይ የተገኙ እና ንክኪ ያላቸውን የመለየት ሥራ እየሰሩ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

    ባለስልጣናቱ በተጨማሪም ለምን ከ50 ሰው በላይ በሰርጉ ላይ እንደተገኘ እንደሚያጣሩም አሳውቀዋል።

    በሕንድ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከተቀመጡ መመሪያዎች አንዱ ከ50 ሰው በላይ መሰብሰብ አይችልም የሚለው ይገኝበታል።

    በሕንድ በቢሃር ብቻ 9 ሺህ 500 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ 60 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

  4. ደቡብ ኮርያ ከአሜሪካው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ሬምዴስቪርን በእርዳታ አገኘች

    መድሃኒት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ደቡብ ኮሪያ የኮቪድ-19 ሕሙማንን ለማከም የሚውለውን ሬምዴስቪር መድሃኒትን ማከፋፈል ጀመረች።

    መድሃኒቱ ከአሜሪካው ጊሊድ ሳይንስስ በእርዳታ የተሰጣት ሲሆን በነሐሴ ወር ላይ ሌላ ለመግዛት እየተወያዩ መሆኑ የኮሪያ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል አስታውቋል።

    “ሬምዴስቪርን ለመውሰድ የሚችሉ ሕሙማን በሳምባ ምች ክፉኛ የተጎዱና የኦክስጅን ቴራፒ የሚያስፈልጋቸው ውስን ሕሙማን ናቸው “ ብለዋል በመግለጫቸው።

    ሬምዴስቪር ፀረ ቫይረስ መድሃኒት ሲሆን ኢቦላን ለማከም ነበር ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው።

    መድኃኒቱ ሕሙማን ለ15 ቀን የሚያሳዩትን ምልክት ወደ 11 እንደሚያሳጥረው በሆስፒታሎች ውስጥ በተደረገው ሙከራ ተረጋግጧል።

    በዚህ የአሜሪካ ኩባንያ ለደቡብ ኮሪያ የተሰጠው መድሃኒት መጠን ምን ያህል እንደሆነ አልተገለፀም።

    ሬምዴስቪር ቫይረሱ በሰዎች ሕዋስ ውስጥ ለመራባት የሚጠቀምበት ኢንዛይም በማጥቃት እንዳይባዛ ያደርጋል።

    መድሃኒቱ ጥቅም ላይ እንዲውል በአሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም ማረጋገጫ ያገኘ ሲሆን ሌሎች አገራትም ይጠቀሙታል።

    መድሃኒቱ ከበሽታው የማገገሚያ ቀናትን በአራት ቀናትን ቢያሳጥርም በርካታ ሰዎችን ከሞት ስለመታደጉ ግን የተገኘ ምንም አይነት መረጃ የለም።

    ጊሊድ ሳይንስስ አቅርቦቱን ለማሳደግ በደቡብ እስያ ከሚገኙ የመድሃኒት አምራቾች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

    ኩባንያው በሕንድና ፓኪስታን ከሚገኙ መድሃኒት አምራቾች ጋር ያደረገው ስምምነት ድርጅቱ መድሃኒቱን ለ127 አገራት እንዲያቀርብ ያስችለዋል ተብሏል።

  5. ቼክ ሪፐብሊክ ኮሮናቫይረስን 'ደህና ሁን' ስትል ደግሳ ተሰናበተች

  6. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች

    ከመላው ዓለም የምናገኛቸውን ኮሮናቫይረስን የሚመለከቱ አበይት ዜናዎች ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እናቀርብላችኋለን።

    ራስዎንና ወዳጆችዎን ከኮቪድ-19 ለመጠበቅ በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክርና ማሳሰብያ ተግባራዊ ማድረግ አትዘንጉ።

    መልካም ቀን!

    ቢቢሲ

    የፎቶው ባለመብት, ቢቢሲ

  7. በአሜሪካ በርካታ ሰዎች ከሳይንስ የተቃረነ አመለካከት አላቸው ተባለ

    አሜሪካ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    በመላው አሜሪካ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች አገራቸው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በመቀነስና በመቆጣጠር ላይ ያላትን ብቃት ስጋት እንደሚሰጉ ገለፁ።

    የአሜሪካ በሽታ መቆጣጣርና መከላከል ባለሙያዎች አገራቸው "መቆጣጠር ከምትችለው በላይ በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች" መኖራቸውን ገልፀዋል።

    የአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ "በአስደንጋጭ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አሜሪካውያን ከሳይንስ የተቃረነ" አመለካከት አላቸው ብለዋል።

    በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የቫይረሱ ስርጭት ሲስፋፋና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ማንሳታቸውን ገትተውታል።

    ማክሰኞ እለት በአንድ ቀን ብቻ 40 ሺህ ሰዎች መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህ በባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ ብቻ ለአራት ተከታታይ ቀናት የተከሰተ ነው።

    የቫይረሱ ስርጭት በአገሪቱ ደቡባዊና ምዕራባዊ አካባቢዎች ይበልጡኑ የተስፋፋ ሲሆን ቢያንስ 16 ግዛቶች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመግባት ይዘውት የነበረውን እቅድ ገትተውታል።

  8. ሪፐብሊካኖች ትራምፕን "እባክዎ ጭምብል አጥልቁ" ብለው እየተማፀኑ ነው

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሪፐብሊካኑ ላማር አሌክሳንደር ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ምክር አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል "ፕሬዚዳንት ትራምፕ እባክዎ ጭምብል ያጥልቁ። ትራምፕን የሚያደንቁ በርካታ ተከታዮች አሏቸው፤ እሳቸው ጭምብል ካጠለቁ የሳቸውን አርአያ የሚከተሉ ብዙ ስለሆኑም" ብለዋል።

    "በሚያሳዝን ሁኔታ ይሄ ቀላሉ ህይወትን የሚያድን ጭምብል የማጥለቅ ጉዳይ የፖለቲካው ክርክር አካል ሆኗል" በማለትም ተናግረዋል።

    አክለውም "የትራምፕ ደጋፊ የሆኑ ጭምብል አያጠልቁም፤ ደጋፊ ካልሆኑ ደግሞ የፊት ጭምብል የሚያጠልቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል።

    ሊቀመንበሩ ይህንን ያሉት በምክር ቤቱ ስብሰባ የመግቢያ ንግግራቸው ነው።

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶችና የንግድ ተቋማት መከፈታቸውን ተናግረው ተሳታፊዎች በሙሉ ንግግር ሊያደርጉ ብቻ ካልሆነ ጭምብላቸውን እንዳጠለቁ እንዲቆዩም አሳስበዋል።

  9. የአፍሪካ ዋንጫ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተራዘመ

    የአፍሪካ ዋንጫ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሚቀጥለው አመት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ 2014 እንደተራዘመ ተገልጿል።

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጨዋታዎቹ እንደተራዘሙም የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

    ጨዋታዎቹ ሊካሄዱ ታቅዶ የነበረው በታህሳስና ጥር ወራት 2013 ዓ.ም ነበር።

    በተያያዘ ዜና በዚህ አመት ሚያዝያ ወር ላይ መካሄድ የነበረበት የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮን ሺፕ (ቻን) በሚቀጥለው አመት ጥር ወር እንደሚካሄድ ተገልጿል።

    ሁለቱም ውድድሮች በካሜሮን ሊካሄዱ እቅድ ተይዞላቸዋል።

  10. ለአልጄሪያ፣ሞሮኮና ሩዋንዳ አውሮፓ መግባት ሲፈቀድ አሜሪካ፣ ቻይናና ብራዚል ተከለከሉ

    አውሮፓ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    የአውሮፓ ሕብረት 14 አገራትን ወደ ሕብረቱ አባል አገራት መግባት እንደሚችሉ ሲፈቅድ አሜሪካ፣ ብራዚልና ቻይና በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው ሳይሰፍር ቀረ።

    ስማቸው በዝርዝር ውስጥ ከሰፈረው መካከል አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያ፣ ሩዋንዳ እና ደቡብ ኮሪያ ይገኙበታል።

    ዲፕሎማቶች እንዳሉት ሕብረቱ የቻይናን ስም የሚያካትተው ቻይና በምላሹ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ዜጎች ወደ ግዛቷ እንዲገቡ የምትፈቅድ ከሆነ ብቻ ነው።

    የአውሮፓ አባል አገራት ድንበሮቻውን እየከፈቱ ይገኛሉ።

    የአውሮፓ ኮሚሽን እንዳለው የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች የብሬግዚት ድርድር እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚታዩት እንደ አውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ዜጎች ነው።

    ስለዚህ በዘህ ወቅት የዩኬ ዜጎች ልክ እንደ አውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ዜጎች ታይተው የሕብረቱ የጉዞ እገዳ አይመለከታቸውም ብሏል።

  11. በሃይድሮክሲክሎሮኪን የሚደረገው ሙከራ እንደገና ሊጀመር ነው

    የሃይድሮክሲክሎሮኪን እንክብሎች

    ለኮሮናቫይረስ መድኃኒትነት መዋል አለበት ተብሎ ሲያወዛግብ የነበረው ለወባ ህመም ፈውስ የሆነው ሃይድሮክሲክሎሮኪን ላይ ዩናይትድ ኪንግደም ሙከራ ልታደርግ መሆኑን አስታውቃለች።

    ሃይድሮክሲክሎሮኪን እንዲሁም ተመሳሳዩ ክሎሮኪን የኮሮናቫይረስ ፈውስ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥም በጤና ባለሙያዎች ላይ እንደሚሞከርም ተገልጿል።

    ከዚህ በፊት በመድኃኒቱ ላይ ሊደረግ የነበረው ሙከራ ከጎንዮሽ ጉዳቱ ጋር ተያይዞ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም እንደገና እንዲጀመር ተወስኗል።

    ሃይድሮክሲክሎሮኪን በኮሮናቫይረስ በጠና ለታመሙ መድኃኒት እንደሆነ የሚያሳዩ ጥናቶች ቢኖሩም በተፃራሪው ፈዋሽነቱ አልተረጋገጠም የሚሉም ጥናቶች አሉ።

    በአሁኑ ሰዓት ተመራማሪዎች መድኃኒቱ ጭራሽ በቫይረሱ መጠቃትን ይከላከል ይሆን የሚለው ላይ የሚመራመሩ ይሆናል።

    የአሁኑ ሙከራ አርባ ሺ በሚጠጉ ከአውሮፓ፣ አፍሪካ፣ እስያና ደቡብ አሜሪካ የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ላይ የሚሞከር መሆኑም ተገልጿል።

  12. በጃፓን የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ተጀመረ

    ክትባት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በጃፓን የሚገኘው አንገስ የተሰኘው የሕክምና ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ክትባትን በሰው ላይ መጀመሩን አስታውቋል።

    ሙከራው በዲኤንኤ ቴክኖሎጂ ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን፣ የሕሙማንን በሽታ የመከላከል አቅም በማሳደግ በሰፊው ለማምረት መታሰቡ ተገልጿል።

    ሙከራው እስከሚቀጥለው ዓመት በኦሳካ ከተማ ዩነቨርስቲ ሆስፒታል ውስጥ የሚካሄድ ይሆናል።

    በአሁኑ ሰዓት በሕንድ በሰው ላይ አማራጭ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ሙከራ እየተደረገ ነው።

    እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በመላው ዓለም የኮሮናቫይረስን ክትባት ለማግኘት 150 ምርምሮች እየተደረጉ ነው።

  13. ሴኔጋል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና የሰአት እላፊውን አነሳች

    ሴኔጋል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የኮሮረናቫይረስን ስርጭት ለመግታት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የሰአት እላፊ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚነሳ አስታውቀዋል።

    በአገሪቱ ቴሌቪዥን ወጥተው ባስተላለፉት መልዕክት ከጥብቅ መመሪያዎች ጋር ከሁለት ሳምንት በኋላ ዓለም ዓቀፍ በረራዎች ይከፈታሉ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከነበረበት 6.8 በመቶ ወደ 1.1 በመቶ ዝቅ ብሏል።

    ኢኮኖሚውን ወደነበረበት የእድገት መንገድ ለመመለስ ዜጎች በቶሎ ወደስራቸው እንዲመለሱም ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል። ነገር ግን መዝናኛ ቦታዎች ለጊዜው ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።

    የገበያ ስፍራዎች በሳምንት አንድ ጊዜ ለጽዳት የሚዘጉ ሲሆን እንደ ትራንስፖርትና ሱቆች ባሉ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ደግሞ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ ግዴታ ነው።

    የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በቅርቡ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ነበራቸው ተብሎ ለሁለት ሳምንታት ራሳቸውን ለይተው ነው የሚገኙት።

    በሴኔጋል እስካሁን 6698 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 108 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  14. በቻይና እንደ ኮሮናቫይረስ የመዛመት እድል ያለው አዲስ ቫይረስ ተገኘ

  15. ሕንድ አዲስ የኮሮና ክትባትን በሰው ላይ ልትሞክር ነው

  16. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአፍጋኒስታን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ

    አፍጋኒስታን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለዓመታት በጦርነት ውስጥ በቆየችው አፍጋኒስታን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በጤና ሥርዓቷ ላይ ከባድ ምስቅልቅልን መፍጠሩ ተገልጿል።

    ወረርሽኙ በአገሪቱ እየተስፋፋበት ባለበት በአሁኔ ጊዜ የአገሪቱ የጤና ተቋማት ህሙማንን ለማስተናገድ ከባድ ፈተና እንደገጠማቸው እየታየ ነው።

    በመንግሥት በሚተዳደሩ ሆስፒታሎች ውስጥ በጽኑ ለታመሙ ሰዎች የሚያስፈልገው የኦክስጂን አቅርቦትም ከአሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

    አንድ ዶክተር ሲናገር ህሙማን ኦክስጂን ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ ለማግኘት “ከባድ ትግል” ማድረግ አለባቸው ሲል ያለውን ችግር ገልጾታል።

    የእራሱ የግል ሆስፒታል ያለው ሌላ ዶክተር አብረውት የሚሰሩ ሠራተኞች ቤተሰቦች ሳይቀሩ ህክምና ለማግኘት በጣም እንደተቸገሩ ተናግሯል።

    "አንድ ዶክተር ደውሎ 'አንዱ ዘመዴ የመተንፈስ ችግር ስላጋጠመው ወደ አንተ ጋር እየላኩት ነው፤ እባክህ አልጋ አስይዘው” አለኝ፤ ነገር ግን ይቅርታ ጠይቄው ቦታ እንደሌለን ነገርኩት። ለስራ ባልደረባዬ ምንም ማድረግ ካልቻልኩ ለሌላው ዜጋ ምን እንደሚሆን ማሰብ አያስቸግርም” ብሏል።

    እስካሁን አፍጋኒስታን ውስጥ 31 ሺህ የሚደርሱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንዳሉ የተመዘገበ ሲሆን፤ በአገሪቱ ምርመራ ከተደረገላቸው ግማሽ የሚሆኑት ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።

    ይህም በዓለም አገራት ከተመረመሩና ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ላይ በሽታውን ካስመዘገቡ አገራት መካከል አፍጋኒስታን እንድትገባ አድርጓታል።

  17. ብቻቸውን ለሚኖሩ ሰዎች ጤና የቤት እንስሳት ያላቸው ጠቀሜታ

    ውሻ

    የፎቶው ባለመብት, Clare Pooley

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ መነገር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። ታዲያ ብቻቸውን የሚኖሩ ሰዎች በሁኔታው እንደሚቸገሩ መገመት አይከብድም።

    ነገር ግን የቤት እንስሳት ያሏቸው አንዳንድ ሰዎች ግን በቤት ውስጥ ብቻቸውን መሆናቸው ሊፈጠርባቸው የሚችለውን ሥነ ልቦናዊ ጫና እንደቀነሳለቸው ይናገራሉ።

    በዚህም ምክንያት አንዳንድ በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ ሰዎች የቤት እንስሳዎቻቸውን ብቻቸውን ለሚኖሩ ሰዎች ማዋስ ጀምረዋል።

    ለጎረቤቶች፣ ለጓደኛ፣ ቤተሰብና ለሥራ ባልደረቦች የቤት እንስሳዎቻቸውን የሚያውሱ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል።

    ክሌር ፖሊይ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንደኛዋ ስትሆን ውሻዋን ብቻውን ለሚኖረው አባቷ ማዋሷን ለቢቢሲ ገልጻለች።

    ‘’ውሻዬ ከአባቴ ጋር በመሆኑ እረፍት ይሰማኛል። ብቻውን እንዳልሆነ ስለማውቅ ጭንቀቴ ቀንሶልኛል’’ ብላለች።

  18. ለመታከም ከ18 በላይ ሆስፒታሎች የተንከራተተው ሕንዳዊ ሕይወቱ አለፈች

    የ52 ዓመቱ ሕንዳዊ በደቡባዊ ባንጋሎር ከተማ ህክምና ለማግኘት 18 ሆስፒታሎች በመሄድና 32 ሆስፒታሎች ደግሞ በስልክ ቀጠሮ ለማስያዝ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ሕይወቱ ማለፏ ተሰምቷል።

    ሰውዬው የትንፋሽ እጥረትና ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት እንደነበረው የገለጸው ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር።

    ህክምና ለማግኘትና ሆስፒታል ለመግባት ለ36 ሰዓታት ጥረት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በስተመጨረሻ አንድ ሆስፒታል ሊቀበለው ፈቃደኛ ሆኖ ነበር።

    ነገር ግን ሐኪሞች መጥተው ለህክምና ሊያስገቡት ሲሉ ሕይወቱ አልፋለች። በሆስፒታሉ በራፍ ላይ ሕይወቱ ማለፏ ደግሞ በርካቶችን አሳዝኗል።

    ምንም እንኳን ግለሰቡ በኮሮናቫይረስ ስለመያዙ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም ናሙና ግን መወሰዱ ተገልጿል።

    "አጎታችን ኮቪድ-19 ይኑርበት አይኑርበት የምናውቀው ነገር የለም፤ ሕይወቱ ያለፈችው በቫይረሱ ምክንያት ወይም ቫይረሱ በፈጠረው ፍርሀት ምክንያት እንደሆነ ማወቅ እንፈልገለን’’ ብሏል የወንድሙ ልጅ።

  19. የአሪዞና ግዛት በድጋሚ ኢኮኖሚውን ላለመክፈት ወሰነች

    አሪዞና

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    በአሜሪካዋ አሪዞና ግዛት የእንቅስቃሴ ገደቡን በማንሳት ኢኮኖሚውን ወደ እንቅስቃሴ ለመለለስ ታስቦ የነበረውን እቅድ ተግባራዊ እንደማይደረግ ተገለጸ።

    የግዛቲቱ አስተዳዳሪ መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የውሀ ፓርኮች እንዲዘጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

    በተጨማሪም ከ50 በላይ የሆኑ ሰዎች በአንድ ቦታ ላይ እንዳይሰባሰቡም ተብሏል።

    "ወደቀደመው ሕይወታችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አንመለስም’’ ብለዋል አስተዳዳሪው ዳግ ዱሲ።

    የፍሎሪዳና የቴክሳስ ግዛቶችም ቢሆኑ እገዳዎችን የማላለት ሂደቱ ስጋት ይፈጥራል በማለት ጠበቅ ያሉ ደገቦችን ማስቀመጣቸው የሚታወስ ነው።

    የቫይረሱን በድጋሚ ማንሰራራት ተከትሎ ቢያንስ 16 የአሜሪካ ግዛቶችን መልሶ የመክፈት ሂደቱን ለጊዜው አቁመዋል አልያም ከነጭራሹ እንቅስቃሴ ከልክለዋል።

    በአሪዞና ባሳለፍነው እሁድ ብቻ 3858 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ነው አስተዳዳሪው ይህንን ውሳኔ ያስተላለፉት።

  20. ቻይና ውስጥ ሌላ ጉንፋን መሰል ቫይረስ ተገኘ

    አሳማ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    ልክ እንደ ኮረሮናቫይረስ በመላው ዓለም የመሰራጨት አቅም ያለው አዲስ ጉንፋን መሰል በሽታ ማግኘታቸውን ቻይናውያን ሳይንቲስቶች አስታወቁ።

    ቫይረሱ በቅርቡ የተገኘ ሲሆን እስካሁን በአሳማዎች ተሸካሚነት ነው ያለው። ነገር ግን ወደ ሰዎች መተላለፍ ይችላል ተብሏል።

    ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ቫይረሱ በቀላሉ እራሱን የመቀያየርና ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት የመተላለፍ አቅሙ ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ ስጋትን የሚፈጥር ነው።

    ቫይረሱ በአሁኑ ወቅት ገና በማያሰጋ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሊሆን እንደሚችል ብዙ ምልክቶች ስለታዩበት በቅርበት ክትትል ያስፈልገዋል ተብሏል።

    በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ በአሳማ ማቀነባበሪያ ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን እንዳረጋገጡ አስታውቀዋል።

    እስካሁን ያሉ ማንኛውም አይነት የጉንፋን መድኃኒቶችም ሰዎቹን ከህመማቸው ሊያድናቸው አልቻለም ተብሏል።