በኢትዮጵያ የአንድ ወር ጨቅላ ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኘ

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 1257 ደርሷል። እስካሁን ድረስ በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከልም 12 ሰዎች መሞታቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። የወረርሽኙ ስርጭት በስፋት የሚታየው አዲስ አበባ ሲሆን በሌሎች ክልሎችም በአነስተኛ ቁጥር ይሁን እንጂ ተከስቷል። እስካሁን ድረስ በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 209 ሰዎች ማገገም ችለዋል። ማንኛውም ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መታደግ የሚችለው አካላዊ ርቀቱን ሲጠብቅ፣ እጁን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ ሲታጠብ እንዲሁም አፉንና አፍንጫውን ሲሸፍን መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራዝምፕ ዝነኛ አድርጎናል- ዳንሰኞቹ ቀብር አስፈጻሚዎች

    dancing pallbearer

    ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቀስቀስ በኋላ ምስላቸው በበርካቶች እንደመቀለጃነት እየዋለ ዝነኛ የሆኑት የጋና ዳንሰኛ ቀብር አስፈጻሚዎች ዶናልድ ትራምፕ ተንቀሳቃሽ ምስላችንን በመጠቀማቸው እጅግ የበለጠ ዝነኛ አድርገውናል ብለዋል።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ከወራት በኋላ በሚደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተፎካካሪያቸው ሆነው የሚቀርቡትን ጆ ባይደንን ለመተቸት የቡድኑ አባላት ተንቀሳቃሽ ምስልን መጠቀማቸው ይታወሳል።

    የቡድኑ መሪ የሆነው ቤንጃሚን አይዶ ፕሬዝደንት ትራምፕ ይህን ምስል በመጠቀማቸው ደስተኞች ነን ብሏል።

    ትራምፕ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የለጠፉት ቪዲዮ፤ ቀብር አስፈጻሚ ደንሰኞቹ 'ፕሬዝደንት ባይደን' የሚል ጽሑፍ ያለበት የአስክሬን ሳጥን ይዘው እየደነሱ ወደ ቀብር ቦታ ሲሄዱ ያሳያል።

    ፕሬዝደንቱ ይህን መጠቀማቸው ለሥራችን "ድጋፍ የሚሰጥ ነው" ብሏል።

    ከሶስት ዓመታት በፊት ቢቢሲ የቀብር አስፈጻሚዎችን ታሪክ በቪዲዮ ካጋራ በኋላ ዝነኛ ሆነዋል። በአሁኑ ወቅትም ሰዎች የቡድኑን ተንቀሳቃሽ ምስል እንደ አዲስ እየተጠቀሙት ይገኛል።

  2. የኬንያው ፕሬዝዳንት ልጃቸው የእንቅስቃሴ ገደቡን እንደተላለፈ ገለጹ

    ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ወንድ ልጃቸው መንግሥት ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር ያስቀመጠውን የሰዓት እላፊ ሕግ መጣሱን ‘ኤንቲቪ’ በተባለው ጣቢያ ላይ ገልጸዋል።

    እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ከሁለቱ ወንድ ልጆቻቸው መካከል አንደኛው በባህር ዳርቻዋ ከተማ ሞምባሳ በምሽት ክበብ ውስጥ ሲዝናና ነበር።

    ሞምባሳ ደግሞ በኬንያ ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የሚገኝባት አንዷ ግዛት ነች።

    በኬንያ ማህበራዊ ክንዋኔዋዎችና ስብሰባዎች ተከልክለዋል። ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ከቤት መውጣት ክልክል ነው። ከምሽቱ 1 ሰዓት በኋላም መንቀሳቀስ በሕግ ያስቀጣል።

    ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ከዋና መዲናዋ ናይሮቢ ወደ ሌሎች ከተሞች እንቅስቃሴዎችን ከልክሏል።

    ሞምባሳን ጨምሮ ሌሎች ሦስት የባህር ዳርቻ ከተሞች ላይም ተመሳሳይ እገዳ ተጥሏል። የቀዳማዊ እመቤቷ ቤተሰቦችና የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እናት ደግሞ የሚኖሩት በሞምባሳ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ በቃለ መጠይቃቸው ወቅት ማንም ሰው ይህ ወረርሽኝ እንዳይዘው የሚያደርግ ተፈጥሯዊ መከላከያ የለውም ብለዋል።

    ነገር ግን ልጃቸውን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገባ አለማድረጋቸው ትችት አስንዝሮባዋል። እሳቸው ግን የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣሉ እንደገሰጹት ገልጸዋል።

  3. እናት ልጅ በሶስት ቀናት ልዩነት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞቱ

    ሳይመን ዛሙዲኦ

    የፎቶው ባለመብት, US Army Reserve

    ሳይመን ዛሙዲኦ የ34 ዓመት የአሜሪካ ተጠባባቂ ጦር አባል ነው። ኮቪድ-19 የነበረበት ሲሆን ከአንድ ሳምንት በፊት ግንቦት 14 ህይወት አልፏል።

    ከሶስት ቀናት በኋላ ደግሞ የ70 ዓመት ወላጅ እናቱ በተመሳሳይ መልኩ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህይወታቸው አልፏል።

    ሳይመን ባለትዳር እና የ11 ወር ጨቅላ ሴት ልጅ አባት ነበር ተብሏል።

    "እድሜውን በሙሉ ልጁን በፍቅርና እና በእንክብካቤ ያሳድግ ነበር" ስትል እህቱ አሊሺያ ተናግራለች።

    አሊሺያ ለኤቢሲ ስትናገር፤ "ከመሞቱ በፊት በነበረው ቀን አናግሬው ነበር። በጣም እያመመው እንደሆነ ያስታውቃል። ለመጨረሻ የማናግረው ቀን ያ እንደነበረ ግን አልገመትኩም ነበር" ብላለች።

    ሳይመን ህመም ይሰማው የጀመረው እናቱን ወደ ሆስፒታል ከወሰደ ከ9 ቀናት በኋላ መሆኑን ቤተሰቡ ይናገራል።

    ከዚህ ቀደም ምንም ተጓዳኝ በሽታ እንዳልነበረበት እና በቀጣይ ወር ለግዳጅ እጠራለሁ ብሎ በዝግጅት ላይ እንደነበረ ተነግሯል።

    እናት እና ልጅ የህክምና ክትትል ተደርጎላቸው ህይወታቸው ያለፈው በተመሳሳይ ሆስፒታል ውስጥ ነው።

  4. በአሜሪካ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በእድሜ ሲከፋፈል፡

    US death

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከያ ማዕከል-ሲዲሲ በአገሪቱ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በእድሜ ከፋፍሎ አስቀምጧል።

    ይህም በአሜሪካ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከታህሳስ 22 እስከ ግንቦት 12 ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃልል ነው።

    በዚህ ጊዜ ውስጥ 70 ሺህ ሞቶች በአሜሪካ ተመዝግበዋል። ከማዕከሉ የተገኘው አሃዝ እንደሚያሳየው አብዛኛዎቹ ሟቾች እድሜያቸው ከ85 ዓመት በላይ የሆኑ ናቸው።

    ኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ እና ማሳቹሴት ግዛቶች ደግሞ በርካታ ሰዎች የሞቱባቸው ቀዳሚ የአሜሪካ ግዛቶች ናቸው።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ መሰረት፤ በብራዚል 15 በመቶ የኮቪድ-19 ሟቾች እድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ናቸው።

    በሜክሲኮ ደግሞ 25 በመቶ የሚሆኑት ከ25 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ናቸው።

  5. በኢትዮጵያ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ሆነ

    ዲዛይነር ማኅሌት አፈወርቅ (ማፊ)

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ዲዛይነር ማኅሌት አፈወርቅ (ማፊ)

    በኢትዮጵያ ማንም ሰው ከቤት ውጪ በሚሆንበት ጊዜ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ግዴታ ሆነ።

    የፌደራል አቃቤ ሕጓ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በራሳቸው የትዊተር ሰሌዳ እንዳሰፈሩት "ከዛሬ ጀምሮ ማስክ ከቤት ውጪ በሁሉም ቦታዎች ማድረግ ግዴታ የሚጥል መመሪያ አጽድቀናል" ብለዋል።

    አቃቤ ሕጓ እንዳሉት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ የሚያጋጥም መዘናጋት፣ ቸልተኝነት፣ የተላለፉትን ደንብ እና መመሪያዎችን አለማክበር ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ብራዚልን በምሳሌነት ጠቅሰው ጠንከር ወዳሉ ርምጃዎች መግባት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

    ጨምረውም "ለእራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለወገን እና ለሀገር ብለን ከሌሎች ስህተት በመማር ጥንቃቄያችንን ከበፊቱ በላይ እናጠናክር" ሲሉ መክረዋል።

    ሕዝቡም በመንግሥትና በባለሞያዎች የተላለፉትን የጥንቃቄ መመሪያዎችን ችላ ሳይል ተግባራዊ እንዲያደርግና ለሕግ አስከባሪዎችም እንዲታዘዝ ጠይቀዋል።

    የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳሰፈረው ከሆነ ከአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ በተጨማሪም የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

    መደበኛ የወንበር አቅማቸዉ ከ45 ሰው በላይ የሆነ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ከመደበኛ ዋጋዉ 75% እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፤ መደበኛ የወንበር ቁጥራቸው እስከ 45 ሰው የሆኑ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ደግሞ የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ደግሞ 100% መሆኑ ተወስኗል።

    ይህም የተወሰነው የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ማድረግ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ለመገደብ አሰተዋጽኦ እንደሚያደረግ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተደረገው ጥናት ስለሚያሳይ መሆኑ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

    የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ በሚልም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሰራተኞች የስራ መግቢያ ሰዓት 1፡30 እንዲሆን የተቀመጠ ሲሆን መዉጫ ስአቱም 9፡30 እንዲሆን ተደርጎ ተሸጋሽጓል።

  6. በአሜሪካ የሟቾች ቁጥር 100,000 አለፈ

    በመቃብር ስፍራ ያላች ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በኮሮና የሞቱባት ዜጎች ቁጥር በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታንና በኮሪያ ጦርነቶች በድምሩ ከሞቱትም በላይ ሆኗል፡፡

    በጥር 21 የመጀመርያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው በአሜሪካ ተገኘ፡፡

    ዶናልድ ትራምፕ ለነገሩ ፊትም አልሰጡትም ነበር፡፡ ‹‹መለስተኛ ጉንፋን ነው›› ሲሉት ነበር፡፡ ቀጥለው ደግሞ ‹‹ሥራ ፈት ዲሞክራቶች እኔን ለማሳጣት የፈጠሩት አሉባልታ ነው›› እያሉ አጣጣሉት፡፡

    ትንሽ ቆይተው ‹‹ተራ ነገር ነው፤ ሰሞኑን ብን ብሎ ይጠፋል›› አሉ፡፡ በኋላ ላይ ነገር ዓለሙ ሲምታታባቸው ከልብስ ማጽጃ ኬሚካል እስከ ወባ መድኃኒት ውሰዱበት ማለት ጀመሩ፡፡

    እውነት ለመናገር ትራምፕም ሆነ ሌሎች ፖለቲከኞች ወረርሽኙ በዚህ አጭር ጊዜ እንዲህ አሜሪካን የሚያህል አገር በእምብርክክ ያስኬዳል ያለ አልነበረም፡፡

  7. እንደምን አደራችሁ?

    ኢትዮጵያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ተከታታዮች

    ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ዜናዎችን የምናቀርብበት ዕለታዊ የቀጥታ ዘገባችን አሁን ተጀምሯል።

    አብራችሁን ቆዩ።