በኢትዮጵያ የአንድ ወር ጨቅላ ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኘ

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 1257 ደርሷል። እስካሁን ድረስ በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከልም 12 ሰዎች መሞታቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። የወረርሽኙ ስርጭት በስፋት የሚታየው አዲስ አበባ ሲሆን በሌሎች ክልሎችም በአነስተኛ ቁጥር ይሁን እንጂ ተከስቷል። እስካሁን ድረስ በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 209 ሰዎች ማገገም ችለዋል። ማንኛውም ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መታደግ የሚችለው አካላዊ ርቀቱን ሲጠብቅ፣ እጁን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ ሲታጠብ እንዲሁም አፉንና አፍንጫውን ሲሸፍን መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ክሮሺያ ድንበሯን ለአስር አገራት ክፍት አደረገች

    ክሮሺያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ክሮሺያ ድንበሯን ለአስር አገራት መክፈቷን ገለፀች።

    ድንበሯን ከከፈተችላቸው አገራት መካከል የቱሪስት ፍሰት ያላቸው ኦስትሪያ፣ ጀርመን እና ቼክ ሪፐብሊክ ይገኙበታል።

    ነገር ግን ማንኛውም ጎብኚ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑን የሚያሳይ ሰነድ ይዞ መምጣት እንዳለበት ደንግጋለች።

    ክሮሺያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት 100 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ወረርሽኙን ለመከላከል በፍጥነት ምላሽ መስጠቷ ተገልጿል።

    የአገሪቱ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በታህሳስ ወር ከቻይና ዉሃን ለመጡ ቱሪስቶች አገሪቱ ውስት ከመግባታቸው በፊት መመሪያዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረጉ ተገልጿል።

    የኮሮነቫይረስ ወረርሽኝ የአገሪቱን ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ጎድቶታል።

    ከዛሬ ጀምሮ ከሀንጋሪ፣ ኦስትሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስሎቫኪያ፣ ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዋኒያ፣ ፖላንድና ጀርመን የሚመጡ መንገደኞች እንዲገቡ ተፈቅዷል።

  2. በጀርመን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ጭማሬ አሳየ

    በጀርመን ጭምብል ያጠለቀ ሰው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መዛመት በመግታት ጥሩ እመርታ አሳይታለች በምትባለው ጀርመን በትናንትናው ዕለት 741 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች።

    ይህም በሃገሪቱ በቫይረሱ የተያዙትን ሰዎች ቁጥር 180 ሺህ 458 አድርሶታል።

    በሃገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር ከሰሞኑ ዝቅ ብሎ የነበረ ቢሆንም በትናንትናው እለት የተመዘገበው እጥፍ ነው ተብሏል። በሟቾች ላይ ይህን ያህል ለውጥ አልታየም።

    ከዚህም በተጨማሪ 39 ሰዎችም በኮቪድ-19 መሞታቸውም ተገልጿል። ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ ሃገሪቷ ያጣችው ዜጎችም ቁጥር 8ሺህ 450 ደርሷል።

    እንደ ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥላቸው የነበሩ መመሪያዎችንም ጀርመን እያላለች ቢሆንም ወረርሽኙ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋትም እንዳለ ነው።

  3. ወረርሽኙ ለአፍሪካ እድገት ዋነኛ መሰናክል ነው-የአፍሪካ ሕብረት

    አፍሪካ

    የፎቶው ባለመብት, Getty

    የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ታዳጊ አገራት የእድገት ግባቸውን እንዳያሳኩ እንቅፋት መሆኑን ገለፁ።

    የታዳጊ አገራቱ ትምህርት፣ ጤና እና ድህነትን ለማጥፋት ያስቀመጧቸውን ግቦች በወረርሽኙ ምክንያት ለማሳካት እንደሚቸገሩ የሕብረቱ ሊቀመንበር ተናግረዋል።

    የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ራማፎሳ ለተባበሩት መንግሥታት በወረርሽኙ ምክንያት ደሃ አገራት የገቡበትን የኢኮኖሚ ቀውስ አስመልክተው ሲናገሩ ለሁለት አመት ያህል ብድር እንዲነሳ እንዲሁም የእዳ መክፈያ እፎይታ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

    ባለፈው ወር የቡድን 20 አባል አገራት ለበርካታ ድሃ አገራት እስከዚህ አመት መጨረሻ ድረስ የሚቆይ እዳቸውን ከመክፈል እንዲዘገዩ የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት አድርገዋል

    በዚሁ ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ የንግድ ብድር አቅራቢ አገራት የእዳ እፎይታ እንዲሰጡ ጠይቀው ነበር።

  4. በህንድ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቻይና በለጠ

    የህንድ የጤና ባለሙያዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በህንድ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቻይና መብለጡን የሃገሪቱ የጤና ሚኒስትር አሳውቀዋል።

    በህንድ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 4 ሺህ 706 ሲሆን በቻይና ደግሞ 4 ሺህ 638 ነው።

    በሃገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 160 ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም ቁጥር በቻይና ካለው ብልጫ ያሳየው ባለፉት ሳምንታት ነው።

    ሃገሪቱ ለአራተኛ ጊዜ ያራዘመችው ውሽባም(የእንቅስቃሴ ገደብ) ከሰሞኑ የሚያልቅ ሲሆን ለወደፊቱም ታራዝመዋለች የሚለው ግልፅ አይደለም።

    ሆኖም በሃገሪቱ የቫይረሱ ጣራ ገና እንዳልደረሰና የሚቀጥለው ወርም ላይ ይደርሳል የሚል አስተያየትም እየተሰጠ ነው።

  5. በኒውዚላንድ በኮሮናቫይረስ የተያዘ አንድ ሰው ብቻ መኖሩ ተገለፀ

    የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃኪንዳ አርደርን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ኒውዚላንድ ሳምንቱን በሙሉ አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘችም። ከመጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ የቆየችው ኒውዚላንድ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበችው የሞተ ሰውም የለም። በሆስፒታሏም አንድ ታማሚ ብቻ እንዳላት ሪፖርት አድርጋለች።

    ኒውዚላንዳውያን እስካሁን ድረስ 1500 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን የመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 22 ሰዎች ሞተዋል። ባለፈው ወር በማህበረሰብ ውስጥ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት " ድል ማድረጋቸውን " አስታውቀው ነበር።

    ኒውዚላንድ ከዛሬ ጀምሮ 100 ሰዎች በአንድ ላይ መሰብሰብ ይችላሉ ስትል የፈቀደች ሲሆን ከአውስትራሊያ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር ትከፍታለች ተብሎ ይጠበቃል።

  6. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ወዳጆች!

    የኮሮናወረርሽኝ በአገራችን ከተከሰተ ወዲህ፣ በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ጀምሮ፣ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው። ትናንት ሩቅ የመሰለን የታማሚ ቁጥር ላይ በአንድ ቀን መድረስ እየጀመርን ነው። በትናንትናው እለት ብቻ 100 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እለታዊ ሁኔታ መግለጫ ይፋ አድርጓል።

    በተደጋጋሚ እንደሚባለው አዲስ አበባ የወረርሽኙ ማዕከል ስትሆን በተለይ ደግሞ አዲስ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታማሚዎች ተገኝቶባቸዋል። ዛሬም ቢሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም አፍንና አፍንጫን መሸፈን ወሳኝ ናቸው። ስለኮሮናቫይረስ ከመላው ዓለም የምንሰበስባቸውን መረጃዎች ለማንበብ የቀጥታ ዘገባ ገፃችንን ይከታተሉ!

    የሙቀት ልየታ ሲደረግ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  7. የማዳጋስካሩ ከአሪቲ የተቀመመ "የኮሮና መድሃኒት" ምን ደረሰ?

    ማዳጋስካር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ባለፈው ወር የማዳጋስካሩ ፕሬዝዳንት ከእጽዋት ያዘጋጁትን የኮሮናቫይረስ መከላከያና ፈዋሽ መድሃኒት አስተዋውቀው ነበር።

    ይህ የፕሬዝዳንቱ እርምጃም ከዓለም ጤና ድርጅት ሳይንሳዊ ድጋፍ የለውም በሚል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

    አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ግን አውሮፕላን ማዳጋስካር ድረስ ልከው መድሃኒቱን አስጭነዋል።

    የማዳጋስካር ብሔራዊ ሕክምና አካዳሚ በዚህ ከአሪቲ በተዘጋጀ ፈሳሽ ፈዋሽነት ላይ ያለውን ጥርጣሬ ለሰው ልጅ ጤና አደጋ ሲል ገልጾት ነበር።

    ይህ ሁሉ ሆኖ ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ እለት ይህንን ከአሪቲ የተዘጋጀ የባህል መድሃኒት በክትባት መልክ መስጠት እንደሚጀምሩ ገልፀው የክሊኒክ ፍተሻውም በአሜሪካ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

    ነገር ግን አሁን የማዳጋስካር ፍትህ ጥናት ውስጥ የሕክምና ዶክተር የሆኑት ሳሆንድራሪማላላ ፕሬዝዳንቱን ተክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

    እርሳቸው እንደሚሉት የፕሬዝዳንቱን ሃሳብን ጋዜጠኞች አልተረዱትም።

    ይህንን ከአሪቲ ቅጠል የተሰራ መድሃኒት በክትባት መልክ ለመስጠት ፍላጎት የለም የሳይንስ ኮሚቴውም አላፀደቀውም ብለዋል።

  8. በዩናይትድ ኪንግደም ከሰኞ ጀምሮ እስከ ስድስት ሰዎች ድረስ በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራ መገናኘት ተፈቀደ

    ቦሪስ ጆንሰን

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከሰኞ ጀምሮ የተወሰኑ የንግድ ተቋማት እንደሚከፈቱ አስታወቁ። የወረርሽኙ ስርጭት እየታየ ደግሞ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል።

    ከሰኞ ዕለት ጀምሮ በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች ስድስት ሰዎች በጋራ መገናኘት እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

    እነዚህ የሚገናኙት ሰዎች ከተለያየ ቤት የሚመጡ ከሆነ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰዋል።

    " በዚህ ውሳኔ መሰረት ጓደኛሞች እና ቤተሰብ መገናኘት ይችላሉ ማለት ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ " ሲጠበቅ የነበረውና የደስታ ጊዜ " ሲሉም ገልፀውታል።

    " ንቁ መሆንና በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ" ተገቢ መሆኑንም አስምረውበታል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳ በጓደኛ ወይም በቤተሰብ ቤት ውስጥ ቢሆንም እንኳ በርካታ የቤት ውስጥ ስብሰባዎች አለመፈቀዳቸውን አስታውቀዋል።

  9. ቀነኒሳ በበይነ መረብ በሚካሄድ የማራቶን ውድድር ላይ ሊሳተፍ ነው

    ቀነኒሳ በስተቀኝ፣ ኢሉድ ኪፕቾጌ በስተግራ

    የአትሌቲክሱ ስመ ገናናዎች ቀነኒሳ በቀለ፣ ኢሉድ ኪፕቾጌ፣ ጆሽዋ ቼፕቴጌ፣ ጂዮፌሪ ካማዎሮር በሚቀጥለው ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ምናባዊ ማራቶን (የበይነ መረብ ማራቶን) እንደሚሳተፉ ታወቀ።

    የማራቶን ውድድሩ በጎርጎሳውያኑ ሰኔ ሰድስት እና ሰባት የሚካሄድ ሲሆን የአትሌቲክስ ወዳጆችና አድናቂዎች ሊሳተፉ ይችላሉ ተብሏል።

    የሃሳቡ አመንጪዎች ኤንኤን የሩጫ ቡድን፣ ውድድሩ የበይነ መረብ ሩጫ ሲሆን በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች አራት በመሆን ቡድን መስርተው የማራቶንን ርቀት የሚሸፍኑበት ነው ሲል አስታውቋል።

    እያንዳንዱ ግለሰብ ባለበት ቀዬ 10.5 ኪሜ መሮጥ ይኖርበታል። አጋሮቹም ይህንን ያደርጉና ሙሉ ማራቶን ይሞላል። ይህ የሆነው ሯጮች ከንክኪ ውጭ በያሉበት ሥፍራ ማራቶን እንዲሳተፉ ለማስቻል ነው። ሁሉም ነገር በበይነ-መረብ አማካይነት ይመዘገባል።

    ኪፕቾጌ "እኔና የቡድን አባላቶቼ ሩጫውን ለመቀላቀል በጉጉት እየጠበቅን ነው" ያለ ሲሆን ወቅቱ ሁሉም ሯጮች እቅዳቸውን መለስ ብለው የሚከልሱበት መሆኑን ተናግሯል።

    በተጨማሪም፣ መጻኢው ጊዜ መልካም እንደሚሆን እምነት አለኝ ካለ በኋላ "ይህም ወደ በጎው ነገር የሚወስደውን አንዱ ርምጃ ነው" በማለት፣ ማራቶን እውቅ ስፖርተኞች እንዲሁም ስፖርት ወዳድ ማህበረሰብ አባላት በጋራ የሚሮጡበት መስክ መሆኑን አስታውሷል።

    ለዚህም ነው ማራቶንን ውብና ልዩ የሚያደርገው በማለት ለሌሎች ተወዳዳሪዎች ጥሪውን አቅርቧል።

  10. በአዲስ አበባ ኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች 552 ደረሰ

    አዲስ አበባ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአዲስ አበባ እስከዛሬ ድረስ በተደረጉ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች 552 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    ከእነዚህም ውስጥ 138 በአዲስ ከተማ፣ 133 ደግሞ በልደታ ክፍለከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ መግለጫ ያሳያል።

    በሶስተኛነት ደረጃ ቦሌ ክፍለ ከተማ 62 ሰው የተገኘ ሲሆን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደግሞ 10 ሰዎች ብቻ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በአዲስ አበባ በኮቪድ-19 መያዛቸው ከተረጋገጠ 552 ሰዎች መካከል 237 የውጪ ጉዞ ታሪክ እንዲሁም ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆናቸው ተገልጿል።

    የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ በመግለጫቸው ላይ፣ "ቫይረሱ አገራችን መግባቱ ከተገለጸበት ዕለት በኋላ ባሉት የመጀመርያ ሳምንታት እየተወሰዱ የነበሩት ጥንቃቄዎች በመቀዛቀዝ ላይ መሆናቸውን እያየን ነው። በተቃራኒው ግን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትና ሥጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል" ብለዋል።

    በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች 831 ደርሰዋል።

  11. ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ህንዳውያን ወዛደሮች ወጪያቸውን መንግሥት መቻል አለበት ሲል ፍርድ ቤት ወሰነ

    ህንድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የህንድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ስደተኞች የመጓጓዣ ወጪያቸውን መቻል ያለባቸው የአካባቢወው ባለስልጣናት እንጂ ወዛደሮቹ አይደሉም ሲል ወሰነ።

    ፍርድ ቤቱ አክሎም በጉዞ ወቅት ምግብና ውሃ በነፃ ሊቀርብላቸው ይገባል ብሏል።

    ሕንድ የእንቅስቃሴ ገደብ በጣለችበት ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወዛደሮች መሄጃ አጥተው ተቸግረው የነበረ ሲሆን የተወሰኑት በእግራቸው ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ተስተውለዋል።

    ከጎርጎሳውያኑ ግንቦት 1 ጀምሮ መንግሥት ወዛደሮቹ የሚመለሱበት ልዩ ባቡር አዘጋጅቷል።

    ነገር ግን ስደተኞቹ ወዛደሮች የሚጠየቀውን ለማሟላትና የጉዞ ክፍያውን ለመሸፈን መቸገራቸው ተግልጿል።

    በቅርብ ጊዜያት ወዲህ የህንድ መገናኛ ብዙኃን ስደተኞቹ ወዛደሮች በሙቀት፣ በተቸናነቀ ባቡር ምክንያት እየሞቱ መሆኑን ዘግበው ነበር።

  12. ፕሪሚየር ሊጉ ከ15 ቀን በኋላ ሊጀምር ነው

    የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 10 2012 ዓ.ም እንደሚጀምር ተገለፀ። የመጀመሪያው ጨዋታ በአስቶን ቪላ እና በሼፊልድ ዩናይትድ ፣ ማንቸስተር ሲቲ ከአርሴናል ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል ተብሏል።

    ከሰኔ 12 ጀምሮ ሙሉ ጨዋታዎቹ የሚካሄዱ ይሆናል።

    የሊጉ ክለቦች አሁንም ውይይት ላይ ናቸው። ነገር ግን በመርህ ደረጃ ተግባብተዋል ሲል የቢቢሲ ስፖርት ዘጋቢው ኒክ ካቬል ነግሮናል።

  13. ቱሪዝም ወደ ቀደመው አቋሙ መቼ ይመለሳል?

    ቱሪዝም

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በዚህ ዓመት የዓለም አቀፉ ቱሪዝም 70 በመቶ ይቀንሳል ሲል የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን ይህም ከጎርጎሳውያኑ1950 ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

    የድርጅቱ ኃላፊ ዙራብ ፖሎሊካሽቪል ከጀርመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ወቅት እንዳሉት 110 ሚሊየን ሥራዎች አደጋ ላይ ናቸው።

    ይሀ ግምት የተሰራው ሁሉም አገራት በነሐሴ ወር የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደብ ያነሳሉ በሚል መሆኑ ተገልጿል።

    ትልቁ የዓለም ቱሪዝም ምንጭ የሆነው የአውሮፓ አገራት የእንቅስቃሴ ገደባቸውን እያነሱ ነው።

    ነገር ግን እንደ ደቡብ አሜሪካ ያሉ የእረፍት ቀናት መዳረሻዎች የቫይረሱ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ሲሆን እንደ ብራዚል ባሉ አገራት ዓለም አቀፍ በረራዎች መቼ እንደሚጀመሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም

    "በዚህ የፈረንጆቹ በጋ በርካታ ጎብኚዎች በቤታቸው መቀመጥ ይመርጣሉ" ብለዋል ፖሎሊካሽቪሊ

    " የአየር መንገዶች የአውሮፕላኖቻቸውን ሙሉ አቅም መጠቀም የሚችሉት የሐምሌ ወር መጨረሻ እና የነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ነው" ብለዋል።

    • የአሜሪካ አንድ አራተኛው የሠራተኛ ኃይል ሥራውን አጥቷል ተባለ

      አሜሪካ

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      የአሜሪካ ሠራተኞች መሥሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት ብቻ 2.1 ሚሊየን አሜሪካውያን የሥራ አጥ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ማመልከታቸውን አስታወቀ።

      ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ከ40 ሚሊየን አሜሪካውያን በላይ ስራቸውን ያጡ ሲሆን ይህም የአሜሪካ ሠራተኛ ኃይል አንድ አራተኛ ይሆናል ተብሏል።

      ባለፈው ወር ብቻ የሥራ አጥ መጠኑ 15 በመቶ የነበረ ሲሆን ይህም ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት "ዘ ግሬት ዲፕሬሽን" ወዲህ ትልቁ ነው ተብሏል።

      ይህ ቁጥር የተሰማው 50 የአሜሪካ ግዛቶች ጥለውት የነበረውን የአንቅስቃሴ ገደብ እያላሉ ባለበት ወቅት ሲሆን የንግድ እንቅስቃሴዎችም ቀስ በቀስ እየተከፈቱ መሆኑ ታውቋል።

      በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 100ሺህ ማለፉ ተገልጿል።

    • ሞዛምቢክ 43 በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ወደ አገራቸው አባረረች

      ሞዛምቢክ

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      የሞዛምቢክ ፖሊስ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተጣለውን እገዳ ተላልፈዋል ያላቸውን 43 በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ወደ አገራቸው አሰናበተ።

      በወሲብ ንግድ የተሰማሩት ሴቶች ከዛምቢያና ዚምቧብዌ የመጡ ናቸው የተባለ ሲሆን ፖሊስ ባደረገው ድንገተኛ አሰሳ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል።

      በሞዛምቢክ ቢየራ ከተማ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰው የተገኙ 109 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

      ከእነዚህም መካከል በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች፣ ነጋዴዎችና በመንገድ ዳር ሲጠጡ የተገኙ ግለሰቦች መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።

      77 የሚሆኑት በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ መሆናቸው ሲገለፅ፣ 43 ከጎረቤት አገራት መጥተው የሚሰሩ በመሆናቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የከተማው ፖሊስ አዛዥ ፈርናንዶ ሬቤሮ ጨምረው አስታውቀዋል።

      አክለውም መጠጥ ከሚሸጡት መካከል ሕጻናት ይገኙበታል ብለዋል።

      ሞዛምቢክ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረገችላቸው ሰዎች መካከል 227 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    • የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ "ለሰራተኞቼ የምከፍለው ደመወዝ የለኝም" አለ

      የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ

      የፎቶው ባለመብት, Reuters

      የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ለሰራተኞቹ የሚከፍለው ደመወዝ እንደሌለው አስታውቋል።

      አየር መንገዱ የግንቦት ወር ደመወዝንም ማክፈል እንደማይችል አክሎ ገልጿል።

      ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞቹም ከግንቦት ወር ጀምሮ ያለ ደመወዝ ፈቃድ ላይ ናቸው።በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹም የስራ አጥ ኢንሹራንስ ገንዘብ ብቻ መቀበል እንደሚችሉም በአቪየሽን ድርጅቱ ውስጥ የሰራተኞች ማህበር አስተባባሪ ዴሬክ ማንስን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ ዘግቧል።

      አየር መንገዱ አምስት ሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞቹን ያለምንም ጥቅማጥቅም ለማባረር አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ የሃገሪቱ የሰራተኞች ፍርድ ቤት እግድ ጥሎበታል። ሆኖም አየር መንገዱ ይግባኝ እንደጠየቀ ኢንዲፔንደንት ኦንላይን የተባለው ድረገፅ ዘግቧል።

    • ሰበር, በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ብቻ 100 ሰዎች ኮቪድ-19 ተገኘባቸው

      BBC

      ባለፉት 24 ሰዓታት ኢትዮጵያ ውስጥ 100 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚንስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውዋል።

      ባለፉት 24 ሰዓታት ለ4950 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉም ተነግሯል።

      3ቱ የውጪ አገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 35 በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው መሆኑ እና 62 የሚሆኑት ደግሞ የታወቀ ውጪ አገር ጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የላቸውም ተብሏል።

      በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ከ3-94 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው እና 94 ሰዎች ከአዲስ አበባ ናቸው ተብሏል።

      በተጓዳኝ ህመም ምክንያት ህክምና ላይ የነበሩ የ70 ዓመት ሴት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው የምርመራ ውጤታቸው ሳይመጣ ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል። የምርመራ ውጤቱ አዛውንቷ ቫይረሱ እንደነበረባቸው አረጋግጧል ተብሏል። ይህም በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ወደ 7 ከፍ አድርጎታል።

      በሌላ በኩል 10 ሰዎች በትናንትናው ዕለት ማገገማቸው ተገልጿል።

    • የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በቪዲዮ ኮፈረንስ ቡድናቸው ሲጫወት ሊደግፉ ነው

      ስታዲየም

      የፎቶው ባለመብት, Aarhus

      የእግር ኳስ አፍቃሪዎች የሚወዱትን የእግር ኳስ ክለብ ከቤታቸው ሆነው በቪዲዮ ስክሪን በስታዲየም ተገኝተው እንዲደግፉ ማድረግ ምናልባት የሆነ ሳይሳሰዊ ልብወለድ ሊመስል ይችላል።

      ‘ኤጂኤፍ’ የተባለው የሆላንድ ክለብ ግን ይህን ሃሳብ ወደ እውነታ ለመቀየር ተዘጋጅቷል።

      በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሁሉም ለማለት በሚያስችል ደረጃ አብዛኛዎቹ ስፖርታዊ ውድድሮች ቆመዋል። ደጋፊዎችና አፍቃሪዎችም ውድድሮቹን ስቴዲየም አልያም ሌላ ቦታ ስብሰብ ብለው መመልከት አይችሉም።

      በዚሁ ምክንያት ወደ ስቴድየም መጥተው ቡድናቸው ማበረታታት ላልቻሉት ደጋፊዎቹ ይኀው ክለብ መላ ብሏል። እስከ 10 ሺ የሚደርሱ ደጋፊዎቹን ፊት ስታዲየም ውስጥ በሚገኝ አንድ ስክሪን ላይ በማድረግ ጨዋታውን እንዲያደምቁት ዝግጅቱን አጠናቋል።

      ዛሬ ‘ራንደርስ’ ከሚባል ቡድን ጋር ላለባቸው ጨዋታም ይኀው ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

      ‘’ዋናው ሃሳባችን የበፊቱን ያክል ባይሆንም የደጋፊዎችን ድምቀት መፍጠር ነው። በባዶ ስታዲየም ጨዋታን ከማካሄድ በእጅጉ ይሻላል’’ ብለዋል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ሶረን ካርልሰን።

    • በማላዊ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከለይቶ ማቆያ ማምለጣቸው ተነገረ

      በማላዊ ከ400 በላይ ሰዎች ከለይቶ ማቆያ ማምለጣቸው ተነገረ። በማላዊ ሁለተኛው ትልቋ ከተማ ብላንታየር የሚገኘው ይህ የለይቶ ማቆያ የሚሰጠው አገልግሎት ከደረጃ በታች ነው በሚል በለይቶ ማቆያው ያሉ ሰዎች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ነበር ተብሏል።

      የማላዊ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ከለይቶ ማቆያው ያመለጡት ከደቡብ አፍሪካ ወደ አገራቸው የተመለሱ የማላዊ ዜጎች ሲሆኑ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊደረግላቸው በዝግጅት ላይ ነበር ተብሏል።

      ከለይቶ ማቆያ ያመለጡት ሰዎች ከስታዲየምነት ወደ ለይቶ ማቆያነት የተቀየረው ቦታ፤ ሽንት ቤት፣ ውሃ እና የምግብ እጥረት አለበት ብለዋል።

      የአገሪቱ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

      ባዶውን የቀረው ስታዲየም የሚያሳዩ ምሰሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተጋርተዋል።

      የ X ይዘትን ይለፉት
      ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

      ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

      ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

      የ X ይዘት መጨረሻ

      በተመሳሳይ ትናንት በዚሁ ከተማ ከሚገኝ ለይቶ ማቆያ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ 8 ሰዎች ማምለጣቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

      ማላዊ እስካሁን 101 በቫይረሱ የተያዙ እና 4 በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎችን መዝግባለች።

    • የጋና የሕዝብ እንደራሴዎች በቫይረሱ ስጋት ፓርላማው ይዘጋ እያሉ ነው

      Ghana Parliament

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      ቁጥራቸው ከፍ ያለ የጋና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁለት የፓርላማው አባላት በኮቪድ-19 መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ፓርላማው በጊዜያዊነት እንዲዘጋ እየጠቁ ነው።

      ምዕራባዊት አፍሪካ አገር ጋና፤ እስካሁን ከ7ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን እና 34 ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት አድርጋለች።

      ምርመራ ከተደረገላቸው የፓርላማ አባላት እና የምክር ቤቱ ሰራተኞች መካከል ሁለት የሕዝብ እንደራሴዎችን ጨምሮ 15 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

      በርካታ የፓርላማ አባላት በቫይረሱ ሊጠቁ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረ ሲሆን በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የፓርላማው ስብሰባ በኢንተርኔት አማካኝነት ይደረግ የሚል ሃሳብ እየሰነዘሩ ነው።