ህንድ ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች በነፃ ምግብ ልታከፋፍል ነው
የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት የጣለችውን የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ለሚደርስባቸው ማህበረሰብ አካላት ድጎማ እያደረገች ያለችው ህንድ፤ ለሁለት ወራትም ያህል በአገር ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች በነፃ ምግብ ልትሰጥ መሆኑን አስታውቃለች።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ኒርማላ ሲታራማን ከሰሞኑ እንደገለፁት 463 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጥራጥሬና እህል አቅርቦት ለ80 ሚሊዮን የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ይረዳል ብለዋል።
አገሪቷ እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ መገደቧን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ትውልድ ቦታቸው ለመመለስ በእግራቸው ረዥም ርቀትን እየተጓዙም ይገኛሉ።
አብዛኛዎቹ ኢ-መደበኛ የሆነው የኢኮኖሚው ዘርፍ የተሰማሩና የከተሞቹም ምጣኔ ኃብት የጀርባ አጥንት የሚባሉ ናቸው። በዚህ አስገዳጅ ቤት መቀመጥ ውስጥም ተርበን እንሞታለን በሚልም ነው ረዥም ርቀትን እየተጓዙ የሚገኙት።
በርካታዎችም ለቀናት ያህል ያለ በቂ ምግብና ውሃ ረዥም ርቀት መጓዛቸው በአገሪቱ ውስጥ ንዴትን ፈጥሯል።
አገሪቷ በአጠቃለይ በኮቪድ-19 እንቅስቃሴን መገደብ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም 266 ቢሊዮን ዶላር መድባለች።