የቤተክርስቲያኑ አገልጋዩ የቃልኪዳን ስነ ስርዓት በማስፈፀሙ በቁጥጥር ስር ዋለ
በደቡባዊ ናይጄሪያ በምትገኘው ካላባር ከተማ በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ የሚያገለግል ግለሰብ የወጣውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተላልፎ በቤተእምነቱ ውስጥ ለተጋቢዎች የቃልኪዳን ስነ ስርዓት በማስፈፀሙ በቁጥጥር ስር ዋለ።
በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ባለስልጣናት ወደ ቤተ እምነቱ ሲገቡ እንግዶች ለቅቀው ሲወጡ ይታያል።
የቤተ እምነቱ አገልጋይ በከተማዋ የኮቪድ-19 ግብረ ኃይል በቁጥጥር ስር የዋለው ቅዳሜ እለት ሲሆን ከቤተክርስትያኑ ውጪ በርከት ያለ መኪና በማየታቸው ተጠራጥረው መግባታቸው ተነግሯል።
"እየተዘዋወርን የእንቅስቃሴ ገደቡ በአግባቡ ተፈፃሚ መሆን አለመሆኑን እየቃኘን ነበር። በርካታ መኪኖች ቆመው ስናይ ለምን እንደመጡ ተገርመን ነበር የገባነው" ሲሉ ለቢቢሲ ፒጅን የቅኝቱ መሪ ተናግረዋል።
በቤተ እምነቱ ውስጥ ሲገቡ 300 ያክል ሰዎች አካለዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ተሰባስበው እንደነበር ጨምረው አስረድተዋል።
በግዛቲቱ ከአምስት ሰው በላይ መሰብሰብ የተከለከለ ሲሆን የአፍና አፍንጫም መሸፈኛ እንዲደረግ መመሪያ ተቀምጧል።