በኢትዮጵያ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከ62 ሺህ በላይ ሆነ

በኢትዮጵያ በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት 3271 የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን ተከትሎ፣ በአጠቃላይ በሃገሪቷ የተደረገውን ምርመራ 62 ሺህ 300 አድርሶታል። ሃገሪቷ የመመርመር አቅሟንም በመጨመር በቀን ውስጥ 10ሺህ ሰዎችንም የመመርመር እቅድ እንዳላትም የጤና ሚኒስትሯ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። በሃገሪቷም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 365 የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 238ቱ በህክምና ላይ ይገኛሉ፤120ዎቹም አገግመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሃገሪቷ በኮሮናቫይረስ አምስት ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች ሲሆን፤ ሁለቱም ወደመጡበት ሃገራት ተመልሰዋል። ስለወረርሽኙ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የቢቢሲ አማርኛን የቀጥታ ዘገባ ከእዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ''አሜሪካ፤ ማስፈራራትሽን አቁሚ'' ቻይና

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እንደአዲስ ቻይና ላይ ትችት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ቻይና የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት መተባበር ብቻ ነው የሚያዋጣን ብላለች።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት "መንግሥታት ቫይረሱን በህብረት መዋጋት አለባቸው" ካለ በኋላ ነገር ግን ይህ ውጤታማ እንዲሆን አሜሪካ አብራን ልትሰራ ይገባል ብሏል። ''አሜሪካ፤ ማስፈራራትሽን አቁሚ'' ሲልም መሥሪያ ቤቱ መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ሐሙስ ዕለት ፕሬዝደንት ትራምፕ ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያቋርጡ ዝተው ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ የቤጂንግ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት እየወሰደ ያለው እርምጃ በቂ አይደለም ነው።

    አሜሪካ በቻይናዋ ዢንጂያንግ ሰብአዊ ጥሰት እየተፈጸመ በመሆኑ አገሪቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት መጠየቅ አለባት ካለች በኋላ ነው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየሻከረ የመጣው።

  2. የኢንዶኔዥያ አውሮፕላን ማረፊያ በሰዎች ታጭቆ የሚያሳየው ፎቶ ቁጣ ቀስቅሷል

    ኢንዶኔዥያ ውስጥ አንድ አውሮፕላን ማረፊያ በደንበኞች ተጨናንቆ የሚያሳይ ፎቶ ቁጣ ቀስቅሷል።

    ትላንት ሐሙስ የሃገር ውስጥ በረራዎች ሥራ መጀመራቸውን ተከትሎ 'ሶካርኖ ሃታ' የተባለ አንድ አውሮፕላን ማረፊያ በደንበኞች ተጨናንቋል።

    መብረር የሚችሉት ባለሥልጣናት፣ የመንግሥት ድርጅቶች ሠራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎችና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ተብሏል።

    ተሳፋሪዎችም ተመርምረው ከኮቪድ-19 ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ ወረቀት መያዝ አለባቸው።

    የኤርፖርት ሰዎች ተሳፋሪዎች ማሕበራዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እናስገድዳለን ቢሉም ፎቶው ላይ ብዙዎች ታጭቀው መታየታቸው ነው ቁጣ የቀሰቀሰው።

    ዋና ከተማዋ ጃካርታ የሚገኝ አንድ ማክዶናልድ የተሰኘ የትኩስ ምግብ አቅራቢ ሱቅ ተከፍቶ ሰዎች ጥቅጥቅ ብለው በመታየታቸው ብዙዎች ተበሳጭተው ነበር።

  3. 'ክቡር ፕሬዝደንት እባክዎ ትንባሆ እናጭስበት'

    አንድ የሲጋራ ጥም ያስጨነቃት ደቡብ አፍሪካዊት ለፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ አንድ ደብዳቤ ጽፋለች።

    ደብዳቤው ፕሬዝደንቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምባሆ ላይ የጣሉትን እግድ እንዲያነሱ የሚማፀን ነው።

    ስሟ ያልተጠቀሰው ይህች የ46 ዓመት ደቡብ አፍሪካዊት የዕድሜ ልክ አጫሽ መሆኗን ታይምስ ላይቭ የተሰኘው ጋዜጣ ከደብዳቤው ላይ አይቻለሁ ብሎ ዘግቧል።

    «ጭንቀት ሊገለኝ ነው። ለራሴ የምበላው ምግብ የለኝም በዚያ ላይ 700 ራንድ [1200 ገደማ ብር] እየከፈልኩ ነው ሲጋራ ከጥቁር ገበያ የምገዛው» ስትል ነው ደብዳቤዋ ላይ ሐሳቧን ያሰፈረችው።

    «እኔ ግልፅ፣ ሕግ አክባሪ ዜጋ ነኝ። አሁን አሁን ግን ሲጋራ ለማግኘት ብዬ በየጉራንጉሩ ስንከራተት የወንጀለኝነት ስሜት እየተሰማኝ ነው።»

    ደቡብ አፍሪካ ኮቪድ-19ን ተከትሎ ከበድ ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ የዓለም አገራት አንዷ ናት። ብዙዎች እግዱ የጥቁር ገበያ እንዲደራ አድርጓል ሲሉ የመንግሥትን ውሳኔ ይተቻሉ።

    የሲጋራ ማጨስ ደጋፊዎችም ማዕቀቡ እንዲነሳ አጥብቀው እየተከራከሩ ይገኛሉ።

  4. በዚምባብዌ የኮቪድ-19 የተገኘባትን ሴት ማንነት ይፋ ያደረገው ግለሰብ ተከሰሰ

    የሰዎችን የኮሮናቫይረስ ምርመራ ውጤት በዋትስአፕ ላይ ይፋ ያደረገው የዚምባብዌ ዜጋ ችሎት ፊት ቀረበ።

    ጂሚ ማህላንጋ፣ የመንግሥት ሠራተኛ ሲሆን ፍርድ ቤት የቀረበው ቅዳሜ ዕለት ቢሆንም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዜናውን ያወጡት ትናንት ነው።

    ግለሰቡ የተከሰሰው " የግለሰቦችን የጤንነት፣ የህክምና ሁኔታ ይፋ በማውጣት" በሚል ሲሆን በዋስ መለቀቁም ተሰምቷል።

    አቃቤ ሕግ፣ አንድ ኮቪድ-19 የተገኘባትን ግለሰብ እና እርሷን ያገኛትን ፖሊስ ማንነት በዋትስ አፕ መልዕክቱ ላይ ይፋ አድርጓል በሚል መከሰሱን አስታውቋል።

    በዋትስ አፕ ቡድኑ ላይ ያሉ ሰዎች ለምስክርነት ተጠርተዋል።

    ዚምባብዌ እስካሁን ድረስ 37 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል አራት ሰዎች ሞተዋል።

  5. አሜሪካ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አሳማዎችን ልትገድል ትችላለች

    በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ አስር ሚሊዮን አሳማዎች ሊገደሉ እንደሚችል የአሜሪካ ፖርክ ኢንዱስትሪን የሚወክለው ድርጅት አስጠነቀቀ።

    ድርጅቱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ገበሬዎች አሳማዎቻቸውን ወደ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች መላክ አልቻሉም ብሏል።

    ስለዚህም ገበሬዎቹ ያላቸው አማራጭ የምግብና የቦታ እጥረት ስለሚገጥማቸው እንስሳቱን መግደል ነው ሲል አስታውቋል።

    በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተነሳ የስጋ ፋብሪካዎች ተዘግተዋል አልያም የሠው ሃይላቸውን ቀንሰዋል።

    በሚያዚያ ወር ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስጋ የሚያሽጉ ኩባንያዎች እንዳይዘጉ አዝዘዋል።

    ነገር ግን የአሳማ ስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች አቅም በአርባ በመቶ መቀነሱ ተነግሯል።

    በስጋ ማቀነባበሪያዎች ብቻ ወደ 14 ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 54 ሠራተኞች መሞታቸው ተነግሯል።

  6. ከአውሮፓ አገራት ማን ቀድሞ ኮቪድ-19ን መቆጣጠር ይቻለዋል? ስሎቫንያ ወይስ ሞንቴኔግሮ?

    ስሎቫንያ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን የምታውጅ አውሮፓዊት አገር ትሆናለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ጃኔዝ ጃንሳ እንዳሉት አገራቸው "ከአውሮፓ ሁሉ ምርጡ የበሽታው ስርጭት መቀነስ ደረጃ ላይ የታየባት ነች" ብለዋል።

    ነገር ግን የስሎቫንያ ጎረቤቶች በዚህ አይስማሙም። ሞንቴኔግሮ ለሳምንታት አንድም አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘችም። በተጨማሪም ስምንት ሕሙማን ብቻ ነው ያላት። ስሎቫንያ ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 35 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አግኝታለች።

    የወረርሽኙን በይፋ መቆም ማወጅ የአውሮፓ ሕብረት አገራት ዜጎች ለይቶ ማቆያ ሳይገቡ በነፃነት ድንበሮችን ማቋረጥ ያስችላቸዋል።

    ነገረ ግን ከአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ውጪ ያሉ ዜጎች አሁንም ሁለት ሳምንት አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ መቀመጥ ይጠብቃቸዋል።

    ስሎቫንያ ቀድማ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን ማወጇ ኮቪድ-19ን በመከላከል እና በማሸነፍ ቀዳሚዋ አውሮፓዊት አገር ያደርጋታል። ነገር ግን ስሎቫንያ ይህንን ትበል እንጂ ለብዙዎች አልተዋጠላቸውም።

    በተጨማሪም ይህ የአገሪቱ ርምጃ ከአውሮፓ ህብረት ለንግዶች፣ ግለሰቦች የሚሰጣትን የአደጋ ጊዜ ድጋፍ ወዲያውኑ የሚያቋርጥ ሲሆን ይህም በዚህ ወር መጨረሻ የሚታይ ይሆናል።

  7. የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጉባኤ የህፃናትን ወሲባዊ ጥቃት በሚያሳይ ቪዲዮ ተጠለፈ

  8. በቤንሻንጉል ጉባ ለይቶ ማቆያ ሁለት ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

    በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት በጋራ ባወጡት መግለጫ 15 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል። በዚህም እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 287 ደርሷል።

    ቫይረሱ የተገኘባቸው እነዚህ ሰዎች እድሜያቸው ከ17 እስከ 38 ሲሆን ሁሉም ወንዶች መሆናቸውን ተመልክተናል።

    እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ለ3ሺህ 707 ሰዎች ምርመራ ተደርጓል።

    ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ስምንት ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ ሁለት ሰዎች ደግሞ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ለይቶ ማቆያ አንድ ሰው ከአፋር፣ ሌላ አንድ ሰው ከአማራ ክልል መተማ ለይቶ ማቆያ እንደሁም ሶስቱ ከጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

    ከእነዚህም መካከል ሰባቱ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ ሰባቱ በቫይረሱ ጋር ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው መሆናቸው ሲገለጽ ምንም አይነት የጉዞም ሆነ የንክኪ ታሪክ የሌለው ደግሞ አንድ ግለሰብ መሆኑ ተቀምጧል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለ 49000 ያህል ናሙናዎች ምርመራ ተደርጓል።

  9. የተባበሩት መንግሥታት 10 ሺህ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ መለሰ

    የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወደ 10ሺህ የሚጠጉ ሰነድ አልባ ስደተኞችን፣ በአብዛኛው ከመካከለኛው ምስራቅ፣ መመለሱን ገለፀ።

    ከስደተኞቹ መካከል መጋቢት ወር ላይ ሞዛምቢክ ውስጥ ከሞት የተረፉት 11 ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።

    11 ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ በእቃ መጫኛ ከሌሎች ጋር ተጭነው እየሄዱ የነበረ ሲሆን 64ቱ ሲሞቱ እነርሱ ግን መትረፋቸው ይታወሳል።

    ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ለአስራ አራት ቀን በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን ረቡዕ እለት ከለይቶ ማቆያ ወጥተው ቤተሰቦቻቸውን መቀላቀላቸው ተሰምቷል።

    እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከሆነ ወረርሽኙ ስደተኛ ተጓዦችን ለመታደግ የሚያደርገው ጥረትን እያደናቀፈው መሆኑን ገልጿል።

    " ስደተኞቹን የመመለሱ ሂደት የተከናወነው ጤንነታቸው በሂደቱ ውስጥ አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ነው። ስለዚህ ከዚህ በፊት ተግባራዊ የማናደርገውን የጥንቃቄ እርምጃ ማድረግ ነበረብን" ያሉት የድርጅቱ ኃላፊ ማውሪን አቺንግ ናቸው።

    አክለውም " የኛ አቋም ግልፅ ነው፤ በዚህ በወረርሽኝ ወቅት አገራትን የሚያቋርጡ እንቅስቃሴዎች አይመከሩም" ብለዋል።

    • ጓንት ከኮሮናቫይረስ ሊከላከለን ይችላልን?

    • ደቡብ ሱዳን የመጀሪያዋን ሞት መዘገበች

      ደቡብ ሱዳን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የመጀመሪያዋን ሞት እንደመዘገበች የመንግሥት መረጃ ጠቁሟል።

      በአገሪቷ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 230 ደርሷል።

      በመዲናዋ ጁባ አቅራቢያ በሚገኝ የተፈናቃዮች ጣቢያ ማዕከልም ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ስጋትን አጭሯል።

      የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት 30 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በተጨናነቀ ሁኔታ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ መኖራቸው የቫይረሱን የመዛመት ሁኔታ መቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል ብሏል።

      ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት መጠለያ ጣቢያው ከፍተኛ ጥንቃቄን እንዲሁም የቦታውን ንፅህና ሁኔታ ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም ፤ ሶስት ሰዎች የወባ መከላከያ መረቦችን መጋራታቸው ጥንቃቄ ሊወሰድበት የሚገባ ጉዳይ ነው ተብሏል።

      ከደቡብ ሱዳን ግጭት ጋር ተያይዞ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሱዳናውያን ንብረታቸውን ጥለው ቀያቸውን ለቀው ተሰደዋል።

    • በሊቢያ በተደጋጋሚ ሆስፒታሎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የበርካቶችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል

      ዓለም አቀፉ ሬስኪዩ ኮሚቴ (አይአርሲ) ሊቢያ በተደጋጋሚ በሆስፒታሎች ላይ በሚደርስ ጥቃት የተነሳ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት ያላት አቅም አደጋ ላይ መውደቁን ተናገረ።

      የትሪፖሊ ማዕከላዊ ሆስፒታል ላይ ትናንት ጥቃት የደረሰ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በመኖሪያ አካባቢ በደረሰ ጥቃት14 ሰላማዊ ዜጎች ተጎድተዋል።

      ሆስፒታሉ በከተማዋ ከሚገኙ ትልልቅ ሆስፒታሎች አንዱ ሲሆን አገሪቱ የኮሮናን ስርጭት ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው ተብሏል።

      " እስከዛሬ ድረስ ማንም የተጎዳ ባይኖርም በሊቢያ ሆስፒታሎች ላይ የሚደርስ ጥቃት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ትሪፖሊ ማዕከላዊ ሆስፒታል 5000 ሠራተኞችና 950 አልጋዎች ሲኖሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አደጋ ላይ ናቸው" ብሏል የአይ አርሲ ሊቢያ ኃላፊ ቶም ጋሮፋሎ።

      በሊቢያ በጎርጎሳውያኑ 2011 የተደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ ሙዓመር ጋዳፊን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ ጀምሮ በግጭት እየታመሰች ትገኛለች።

    • ብራዚል በቫይረሱ የተያዙ ከፍተኛ የሚባለውን ቁጥር መዘገበች

      በብራዚል በትናንትናው ዕለት በሃያ አራት ሰአታት ውስጥ 13 ሺህ 944 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መመዝገቧን ተከትሎ፤ ቫይረሱ ከተነሳበት እለት ጀምሮ የቀኑ ሬከርድ ሆኗል።

      በላቲን አሜሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባላት ብራዚል እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 202 ሺህ 918 የደረሰ ሲሆን፤ 13 ሺህ 933 ብራዚላውያን ህይወታቸውን ማጣታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

      የጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ቢያስጠነቅቁም፤ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮ በተፃራራ መንገድ የተለያዩ የንግድ ተቋማት የእንቅስቃሴ ገደቡን እንዲነሻ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

    • ምርመራ የተጀመረባቸው የአሜሪካ ምክር ቤት ደህንነት ኃላፊ ከስራ ለቀቁ

    • ሲንጋፖር የ900 ሃጂ ተጓዦችን እቅድ ወደ ሚቀጥለው ዓመት አስተላለፈች

      900 ሲንጋፖራውያን ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሃጂ ጉዞ ለማድረግ የያዙትን እቅድ ወደሚቀጥለው ዓመት ማስተላለፉን የሲንጋፖር እስላማዊ ምክር ቤት ማስታወቁን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘገቡ።

      ሳዑዲ አረብያ በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የሚደረገውን የሃጂ ጉዞ በሚመለከት እስካሁን ድረስ ያለችው ነገር የለም።

      ምክር ቤቱ ወደ ሳዑዲ ለመሄድ ተመዝግበው ከነበሩ መካከል 80 በመቶዎቹ እድሜያቸው ከ50 በላይ መሆኑን ሲገልፅ የጤና ባለሙያዎች ደግሞ ከኮቪድ-19 ጋር ተያያዘ ለጤና ስጋት ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።

      በየዓመቱ ከመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ወደ መካ የሚጓዙ ሲሆን አቅማቸው የሚፈቅድ ሙስሊሞች ይህንን ጉዞ በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንዴ እንዲያደርጉት ይጠበቃል።

    • በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት 47 ሚሊየን ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ላያገኙ ይችላሉ-የተባበሩት መንግሥታት

    • የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ ዓመት 250 ሚሊዮን አፍሪካውያን በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ ሲል አስጠነቀቀ

      በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ተመራማሪዎች 250 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን በአንድ አመት ውስጥ ብቻ በኮሮናቫይረስ ሊያዙ ይችላሉ ሲሉ አስጠነቀቁ።

      በቢኤምጂ ግሎባል ሄልዝ ላይ የታተመው ጥናታቸው እንደሚለው ከሆነ ከ150 000 እስከ 190 000 አፍሪካውያን በኮቪድ-19 ምክንያት ይሞታሉ።

      እንዲሁም ቲቢ፣ ወባንና ኤች አይቪን ለማከም የተጨናነቁት የአፍሪካ የሕክምና ተቋማት 5.5 ሚሊዮን ሰዎችን ሕክምና መስጠት ሊያስፈልጋቸው ይችላል ብለዋል።

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአፍሪካ የመስፋፋት ሂደቱ አዝጋሚ ቢሆንም በደቡብ ሱዳን በተፈናቃዮች መጠለያ ጣብያ ውስጥ መከሰቱ ተሰምቷል።

    • በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአለም ምጣኔ ኃብት 8.8 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ ሊያጋጥመው እንደሚችል ተገለፀ

      በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የአለም ምጣኔ ኃብት ከ5.8- 8.8 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ተገለፀ።

      ሃገራት ወረርሽኙን መዛመት ለመግታት እያሳለፏቸው ባሉ ውሳኔዎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ቀጥ ማለትን ተከትሎ የበርካታ ሃገራት ኢኮኖሚ እየተሽመደመደ ነው።

      የእስያ የልማት ባንክ ከሰሞኑ 6.4- 9.7 በመቶ የሚሆነው የአለም ኢኮኖሚ ሊዳሽቅ እንደሚችል ግምቱን ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ከባለፈው ወር ካስቀመጠው ትንበያ በእጥፍ ጨምሮ ተገኝቷል።

      ባንኩ መሰረት ያደረገው ሃገራት የጣሏቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ለስድስት ወራት የሚቀጥሉ ከሆነ በሚል እሳቤ ነው።

      ሆነም ቀረም የንግድ እንቅስቃሴዎች መገደብ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት የሚቀጥል ይሆናል።

    • ቻይና አራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን አስታወቀች

      ቻይና በአገሪቷ ሰሜን ምስራቅ ግዛት ጂሊን ግዛት አራት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገለፀች። የግዛቲቱ ከተማ የሆነችው ሹላንም የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባታል።

      በግዛቲቱ ስም የምትጠራው ጂሊን ከተማ ደግሞ ስድስት ነዋሪዎች መያዛቸው ከተገለፀ ወዲህ በከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባታል።

      በተያያዘ ዜና የዉሃን ባለስልጣናት እስካሁን ድረስ ከሶስት ሚሊየን በላይ ሰዎችን የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

      ይህ በከተማዋ ያለውን የኮቪድ-19 ስርጭት ምን እንደሚመስል ያለመ ምርመራ 11 ሚሊየን የከተማዋን ነዋሪዎች ለመመርመር አቅዶ የተጀመረ ነው።

      ይህ የከተማዋን ነዋሪዎች በአጠቃላይ በአስር ቀን ውስጥ የመመርመር እቅድ የተሰማው በከተማዋ አንድ የመኖሪያ ስፍራ የተወሰኑ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ከተገኙ በኋላ ነው።

      ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ የቻሉት በመጋቢት ወር ታምመው ከነበሩ አንዲት የ89 ዓመት አዛውንትጋር ከነበራቸው ግንኙነት በኋላ ነው ተብሏል።

      ዉሃን በቫይረሱ ተይዘው የሕመም ምልክት የማያሳዩ ነገር ግን ወደ ሌላ የሚያስተላልፉ ሰዎችን ለመመርመር የኑክሊክ አሲድ ምርመራ እንደምትጠቀም ገልፃለች።

    • የአለም ንግድ ድርጅት ኃላፊ ከስራ ለቀቁ

      ሃገራት የጣሏቸውን የእንቅስቃሴ ገደቦችን በማላላት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለመመለስ እየጣሩ ባሉበት ወቅት የአለም ንግድ ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ሮበርቶ አዜቬዶ ከስራ ለቀዋል።

      ለአለም የምጣኔ ኃብት ማንሰራራት ቁልፍ በሚባለው ወቅት ኃላፊው ከስራቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

      የስራ ዘመናቸው በሚቀጥለው አመት ቢያልቅም ቀድመው ለመልቀቅ የወሰኑትም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ድርጅቱ እየደረሰበት ባለው ጫና እንዲሁም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ትችት ተከትሎ ነው።

      ሮበርቶ አዜቬዶ የለቀቁበት ምክንያት የግል ውሳኔና ድርጅቱንም በማይጎዳ መልኩ ነው ማለታቸው ተሰምቷል።