ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከ62 ሺህ በላይ ሆነ
በኢትዮጵያ በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት 3271 የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን ተከትሎ፣ በአጠቃላይ በሃገሪቷ የተደረገውን ምርመራ 62 ሺህ 300 አድርሶታል። ሃገሪቷ የመመርመር አቅሟንም በመጨመር በቀን ውስጥ 10ሺህ ሰዎችንም የመመርመር እቅድ እንዳላትም የጤና ሚኒስትሯ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። በሃገሪቷም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 365 የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 238ቱ በህክምና ላይ ይገኛሉ፤120ዎቹም አገግመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሃገሪቷ በኮሮናቫይረስ አምስት ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች ሲሆን፤ ሁለቱም ወደመጡበት ሃገራት ተመልሰዋል። ስለወረርሽኙ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የቢቢሲ አማርኛን የቀጥታ ዘገባ ከእዚህ ገጽ ይከታተሉ።
የቀጥታ ሽፋን
አሜሪካ ክትባቱ ቀድሞ ለእኔ ይደረስ ማለቷን ተከትሎ በርካቶች ተቃውሞ እያሰሙ ነው
የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት እየተደረጉ ያሉት ምርምሮች ውጤታማ ወደ መሆን በተቃረቡበት በአሁኑ ወቅት ሐብታም አገራት ቀድመው በተናጠል ምርቱን በማግኘት ለዜጎቻቸው ለማቅረብ ሽሚያ መጀመራቸውን ተከትሎ የአገራት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች ደብዳቤ ፅፈዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ፕሬዝዳንት የሆኑትን ሲሪል ራማፎሳ፣ የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሴኔጋሉና የጋና ፕሬዝዳንቶች፣ የአፍሪካ ሕብረት ዋና ጸሐፊን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ 140 ታዋቂ ፖለቲከኞችና ባለሙያዎች ደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
አሜሪካ ክትባቱን ሊያመርት ይችላል የተባለውን የፈረንሳይ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ሳኖፊ የኮቪድ-19 ክትባትን መስራት ከጀመረ ለአሜሪካ ገበያ ቀድሞ መስጠት አለበት በማለት ግፊት እያደረገች ነው።
ለዚህ ጥያቄዋ ተቀባይነትም "የአሜሪካ መንግሥት ምርምሩ ላይ ቀድሞ ኢንቨስት በማድረጉ በብዛት ቀድሞ የማዘዝ መብት አለው" የሚል ነው።
ይህንንም ተከትሎ አንድ ከፍተኛ የፈረንሳይ ባለስልጣን ጥያቄው "ተቀባይነት የለውም" ሱሉ ተቃውመውታል። ተጨማሪ እዚህ ያንብቡ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለዓለም ሕዝብ በነጻ እንዲቀርብ ግፊት እየተደረገ ነው
የኔዘርላንድስ መንግሥት 'ነጠላ ሰዎች አጋር ፈልጉ' እያለ ነው
ትራምፕ ‘ክትባት ተገኘም አልተገኘም እንቅስቃሴ እንጀምራለን’ አሉ
አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሲገኝ ቅድሚያ ማግኘት አለብኝ ማለቷ እያወዛገበ ነው
ለፈረንሳዩ ግዙፉ የመድኃኒት ኩባንያ ሳኖፊ፤ የኮቪድ-19 ክትባትን መስራት ከቻለ ለአሜሪካ ገበያ ቀድሞ መስጠት "ተቀባይነት እንደሌለው" የፈረንሳይ ሚኒስትር አስጠነቀቁ።
በሳኖፊ ከፍተኛ የበላይ ኃላፊ ፓል ሁድሰን "የአሜሪካ መንግሥት ምርምሩ ላይ ቀድሞ ኢንቨስት በማድረጉ በብዛት ቀድሞ የማዘዝ መብት አለው" ብለው ነበር።
በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ ቤተ ሙከራዎች ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ምርምር እያደረጉ ቢሆንም ክትባቱን ለማምረት ግን ዓመታት ይወስዳል እየተባለ ነው።
ምክትል የገንዘብ ሚኒስትሩ አግነስ ፓኔር ሩናቼር "ለእኛ ለዚህኛው አገር እና ለዚህኛው አገር ቅድሚያ መስጠት የሚለው ከገንዘብ አንፃር ተቀባይነት የለውም" ብለዋል ለፈረንሳዩ ሬዲዮ።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ሕብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ የሚደረጉ ምርምሮችን ለመጨመር ያለመ ጉባኤ ተካሂዶ ስምንት ቢሊየን ዶላር ከአርባ አገራትና ከለጋሽ አገራት ማግኘት ተችሏል። ተጨማሪ ለማንበብ፡ ፈረንሳይ ክትባቱን ለአሜሪካ ቀድማ ለመሸጥ ፍላጎት የላትም
በመካከለኛው ምሥራቅ ኮሮናቫይረስን ያዛመተው አየር መንገድ
የሱዳን ሐኪሞች፡ 'በቂ ጓንት የለንም'
ሱዳናዊቷ ዶክተር ሳራህ አሊ በአፍሪካ በአንድ ዓመት 250 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮናቫይረስ ይያዛሉ ሲል የወጣ አንድ ዘገባ አላስደነቃትም።
ሳራህ "ኮሮናቫይረስ በጣም ፈታኝ ወረርሽኝ ነው። የሱዳን የጤና ሥርዓት እንዲሁም ቢሆን ጠንካራ አልነበረም" ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
ወጣቷ ዶክተር የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ስለታዩባት ራሷን አግልላ እያስታመመች ትገኛለች። ቢሆንም የሱዳን ሆስፒታሎች ያለባቸው ፈተና አያስተኛትም።
"ካርቱም ውስጥ ያለ አንድ ትልቅ ሆስፒታል ዶከተሮች አጥረውት ነበር። ምክንያቱም ሆስፒታሉ ሦስት ዶክተሮች ብቻ ነው ያሉት።»
እሷና ሌሎች ዶክተሮች በሱዳን ያሉ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ቁጥር መንግሥት ካስታወቀው እጅጉን የላቀ ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራሉ።
ዶ/ር ሳራህ በሆስፒታሎች ውስጥ የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት እንዳለም አትሸሽግም።
"በየቀኑ አንድ ቬንቲሌተር [አጋዥ መተንፈሻ መሣሪያ] የሚያስፈልገው ነገር ግን ያለገኘ ህመምተኛ አይጠፋም። ለመላ አገሪቱ የሚሆኑ 200 ቬንቲሌተሮች ብቻ ነው ያሉን።"
"ለምሳሌ የጓንት እጥረት ስላጋጠማቸው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት የተዘጉ ሆስፒታሎች አሉ። ዶክተሮች በቂ የእጅ ጓንት ስለሌላቸው በሽተኞችን መንከባከብ አልቻሉም። ግላዊ መከላከያ ቁሳቁሶች እንደሚመጡልን ቃል ተገብቶልናል።"
ሱዳን 1964 ዜጎቿ በቫይረሱ እንደተያዙ ይፋ አድርጋለች።
በዝንጀሮዎች ላይ የተሞከረው የኮቪድ-19 ክትባት ውጤት አሳየ
ኮሮናቫይረስን ይከላከላል የተባለለት ክትባት በስድስት ሬሰስ ማኩዌ በተሰኙ የዝንጀሮ ዝርያዎች ላይ ተሞክሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳይቷል።
ክትባቱ በአሁኑ ወቅት በሰው ልጅ ላይ እየተሞከረ ይገኛል። ነገር ግን የሰው ልጅ ላይ ያለው ውጤታማነት ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጠም።
ስድስቱ ዝንጀሮዎች ሳርስ-ኮቭ-2 የተሰኘው ቫይረስ እንዲሰጣቸው ከተደረገ በኋላ ክትባቱን እንዲወጉ ተደርገዋል።
ዝንጀሮዎቹ ክትባቱ ከተሰጣቸው በኋላ ሳንባቸውና በመተንፈሻ አካላቸው ውስጥ ያለው ቫይረስ እየቀነሰ መጥቷል።
ከአሜሪካ መንግሥት ብሔራዊ የጤና ኢንስቲትዩት እና የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ናቸው ዝንጀሮዎቹ ላይ ሙከራ እያደረጉ ያሉት።
ክትባቱ እንስሳቱ የሳንባ ምች [ኒሞኒያ] በሽታ እንዳይዛቸው እንደተከላከለም ተዘግቧል። ሬሰስ ማኩዌ የተሰኙት የዝንጀሮ ዝርያዎች ከሰው ልጅ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው እንስሳት ናቸው። ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ፡ ዝንጀሮዎች ላይ የተሞከረው ክትባት ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል
የኢትዮጵያዊቷ የ'ማስክ' ሥራ ጅማሮ
ጣልያን የበረራ እገዳዋን ልታነሳ ነው
በጣልያን ከሰኔ ሦስት ጀምሮ በረራ እንዲጀመር የሚፈቅድ ስምምነት በአገሪቱ መንግሥት ተፈረመ። ሌሎች የእንቅስቃሴ ገደቦችም እየላሉ ነው።
ወደ አገሪቱ እንዲሁም ከአገሪቱ ውጪ የሚደረጉ በረራዎች ይጀመራሉ ተብሏል። ከግዛት ግዛት የሚደረግ በረራ ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብም ሰኔ 3 ይነሳል።
ጣልያን ከመላው ዓለም ክፉኛ በኮቪድ-19 ተጠቅታለች። ከፍተኛ የሟቾች ቁጥርም አስመዝግባች። ሆኖም ባለፉት ቀናት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።
በጣልያን የሞቱት ሰዎች ከ31,600 በላይ ናቸው። ይህም ከአሜሪካና ከዩኬ ቀጥሎ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ነው።
ከአውሮፓ አገራት ቀድማ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ የጣለችው ጣልያን ነበረች። በያዝነው ወር መባቻ ላይ እነዚህ ገደቦች እየላሉ መጥተዋል። ፋብሪካዎችና መናፈሻዎች ከሳምንታት በፊት መከፈታቸውም ይታወሳል።
አንዳንድ ግዛቶች እገዳው በቶሎ ይነሳልን ብለው ነበር። ጠቅላይ ሚንስትር ጁሴፔ ኮንቴ ግን አገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ በወረርሽኙ እንዳትጠቃ እንቅስቀሴ ላይ የተጣለውን ገደብ የምናነሳው ቀስ በቀስ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ጣልያን ከሦስት ቀናት በኋላ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ መደብሮችና ሬስቶራንቶች እንዲከፈቱ ፈቅደሳለች። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም በሯን ለአማኞች ትከፍታለች።
በኤርትራ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩ ሁሉም ህሙማን መዳናቸው ተነገረ
ኤርትራ የኮሮናቫይረስ ያለበት የመጀመሪያ ሰው እንደተገኘ ካወጀች በኋላ ጠቅላላ ቁጥሩ 39 ደርሶ ነበር።
አርብ ማምሻውን የኤርትራ ጤና ሚኒስቴር ሁለም ታማሚዎች ሙሉ በሙሉ ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸውን አሳውቋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዳሳወቀው የመጨረሻው ታማሚ በብሔራዊ የጤና ማዕከል በተደረገለት ምርመራ ከቫይረሱ ማገገሙ ታውቆ ከለይቶ ማቆያ ወጥቷል።
ይህ ማለት ግን ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት ስላልሆነ ጥንቃቄ አሁንም እንዳይለይ ሲል ማስታወቂያ ሚኒስቴሩ ሕዝቡን መክሯል።
ቫይረሱ በመላ አገሪቱ በቁጥጥር ሥር መዋሉ እንዲረጋገጥ ዜጎች መንግሥት ያወጣውን ሕግ እንዲያከብሩ ሚኒስቴሩ ጨምሮ አሳስቧል።
ኤርትራ በኮቪድ-19 አማካይነት አንድም ሰው እንዳልሞተባት አሳውቃለች።
ብራዚል በሁለት ወራት ልዩነት ሁለተኛ የጤና ሚኒስትሯን አጣች
የብራዚሉ ፕሬዝደንት ጃይር ቦልዞናሮ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሁለተኛ የጤና ሚኒስትራቸውን አጥተዋል።
አዲሱ ሚኒስትር ኔልሰን ቴይክ ከተሾሙ በኋላ የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ያስገቡት ከሳቸው በፊት የነበሩት ሉዊዝ ሄንሪኬ ማንዴታን ተክተው አንድ ወር እንኳ ሳይሆናቸው ነው።
ቦልዞናሮ ባለፈው ሰኞ ጂምና የውበት ሳሎኖች አስፈላጊ ናቸው ሲሉ እንዲከፈቱ መወሰናቸው ይታወሳል። ኔልሰን ግን ይህ ውሳኔ የኔን ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሳያማክር የተደረገ ነው ሲሉ ትችታቸውን አሰምተዋል።
የብራዚል መገናኛ ብዙሃን የጤና ሚኒስትሩ ከፕሬዝደንቱ ጋር የተጋጩት ቦልዞናሮ ክሎሮኪን ኮሮናቫይረስን ያክማል ማለታቸውን ተከትሎ ነው ሲሉ ዘግበዋል። ክሎሮኪን ኮቪድ-19ን ስለማከሙ የተረጋገጠ ነገር የለም።
ብራዚል በላቲን አሜሪካ በኮሮናቫይረስ እጅጉን ከተጠቁ ሃገራት ቁንጮዋ ናት። የሃገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ሲረጋገጥ 14 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
ዝንጀሮዎች ላይ የተሞከረው የኮሮናቫይረስ ክትባት ተስፋ ሰጪ ሆኖ ተገኝቷል
ኮሮናቫይረስና የስኳር በሽታን ምን አገናኛቸው?
እንግሊዝ ውስጥ በኮሮናቫይረስ አማካይነት ሆስፒታል ገብተው ከሞቱ ሕመምተኞች መካከል አንድ አራተኛው የስኳር በሽታ ነበረባቸው። የስኳር በሽታ፣ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ እንዲል የሚያደርግ በሽታ ነው።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 90 በመቶ ያክል የስኳር በሽተኞች 'ታይፕ 2' የተሰኘው አይነት የስኳር በሽታ አለባቸው።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለታይፕ 2 የስኳር በሽታ ሊያጋልጥ ይችላል። አልፎም በኮቪድ-19 የመጠቃትን ዕድል ሊያሰፋው ይችላል።
ለምን? ምክንያቱም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሰዎች የሳንባና ልብ ሥርዓታቸው የተዛባ ሊሆን ይችላል።
አልፎም ውፍረት በሰውነት ውስጥ ለሚከሰት እብጠት በማጋለጥ የመከላከል አቅምን ሊጎዳ ይችላል።
እንግሊዝ ውስጥ በኮቪድ-19 በፅኑ ከታመሙ ሰዎች መካከል በደማቸው ውስጥ ከፍ ያለ የስኳር መጠን ያላቸው እንዲሁም ከጥቁር፣ እስያዊ ወይም ከሌላ አናሳ ጎሳ የተወለዱ ሰዎች ይበዛሉ።
ምንም እንኳ ባለሙያዎች ከ40 ዓመት በታች ያሉ ሰዎች የሚያጋጥማቸው አደጋ ያነሰ ነው ቢሉም ታይፕ 2 የስኳር በሽታ ያላቸው ሰዎች በተለይ ደግሞ ሥራቸው ውጭ የሚያውላቸው ሰዎች ድጋፍ እንዲሰጣቸው እየተጠየቀ ነው።
በሌባኖስ ኢትዮጵያውያን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው እየተነገረ ነው
ዲጄ በጥይት በመምታት የተከሰሱት የኬንያ እንደራሴ የኢንተርኔት ትምህርት መስጠት ጀምረዋል
አንድ ሰሞን የኬንያውን ፕሬዝደንት የውሻ ልጅ ብለው የጠሩትና በአንድ መሸታ ቤት ሙዚቃ አጫዋች [ዲጄ] በጥይት በመምታት የተከሰሱት አነጋጋሪው የኬንያ የሕዝብ እንደራሴ አሁን ደግሞ በአዲስ ሙያ ብቅ ብለዋል።
ባቡ ኦዊኖ በኢንተርኔት አማካይነት ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሒሳብ እና ኬሚስትሪ ትምህርት እየሰጡ ነው።
ኬንያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተማሪዎች ወደ ት/ቤት እንዳይመጡ ብላ ከልክላለች። አልፎም ከናይሮቢና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች መውጣትም ወደ ከተሞቹ መግባት አይቻልም።
ከምሽት 1፡00 እስከ ንጋት 11፡00 ሰአት የሚዘልቅ ሰዓት እላፊም ተጥሏል።
የትምህርት ሚኒስቴር ብቃት የሌለው ሰው ማስተማር አይችልም ቢልም እንደራሴ ባቡ ግን እያስተማሩ ነው።
ወጣቱ እንደራሴ በአክቹዋሪያል (አፕላይድ) ሳይንስ የመጀመሪያ ድግሪ አላቸው። የአስተማሪነት ሥልጠና ይወሰዱ አይውሰዱ ግን የታወቀ ነገር የለም።
እንደራሴው ከማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች አድናቆት እየጎረፈላቸው ነው።
ቢሆንም ዲጄ በጥይት መተዋል ተብለው ተከሰው በዋስ ነው የተለቀቁት። እንደራሴው ዲጄውን በጥይት ሲመቱት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ቢለቀቅም ወንጀሉን አልፈፀምኩም፤ ነገር ግን የግለሰቡን የሕክምና ወጪ እሸፍናለሁ ብለዋል።
ስዊድን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ አለመዝጋቴ ስህተት አይደለም አለች
ስዊድን በርካቶችን ቢያስገርምም እንቅስቃሴ መገደብን አልፈልግም ብላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፋን ሎፍቨንም ቢሆኑ ሁሉንም ሰው በእኩል የሚስማማ እርምጃ ባለመኖሩ እንቅስቃሴን በሕግ መከልከሉ ብዙም አስፈላጊ አይደለም በማለት ውሳኔያቸው ተገቢ እንደበረ ገልጸዋል።
አክለውም መገናኛ ብዙሀን የስዊድንን ፖሊሲ በተሳሳተ መልኩ ሲዘግቡ ነበር በማለት "ህይወት ልክ ቀድሞ እንደነበረው እየቀጠለ አይደለም፤ በርካቶች ከቤታቸው መውጣትም አቁመዋል" ብለዋል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ።
ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ በፈቃድ የሚደረግ እንጂ ግዴታ አይደለም ነገር ግን ስዊድናውያን ርቀታቸውን ለመጠበቅ መርጠዋል።
ነገር ግን ዜጎች መንግስት ያስቀመጣቸውን የጤና መመሪያዎች መከተል ግዴታቸው ነው፤ ይህ አማራጭ የሌለው ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በተጨማሪም መንግስት እድሜኣቸው የገፉ ዜጎችን ከቫይረሱ ለመከላከል የሰራው ስራ በቂ አይደለም፤ በአጠቃላይ በአገሪቱ ከሞቱት 3529 ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ እድሜያቸው ከ70 በላይ ነው ብለዋል።
10 ሚሊየን ዜጎች ያሏት ስዊድን እስካሁን ድንበሮቿን ያልዘጋች ሲሆን ሰዎች ወደ ውጪ አገራት ጉዞ እንዳያደርጉ ግን መክራለች።
ናይጄሪያ የተላኩት ቻይናዊያን ዶክተሮች የት ገቡ?
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ባለፈው ወር ከቻይና የመጡ 15 የሕክምና ባለሙያዎች እምጥ ይግቡ ስምጥ አናውቅም እያሉ ነው።
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከቻይና ወደ ናይጄሪያ የመጡት እኚህ የጤና ሙያተኞች ናይጄሪያ ሲደርሱ በባለሥልጣናት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።
ነገር ግን ሐሙስ ዕለት የናይጄሪያ ጤና ሚኒስትር ኦሳጊ ኢሃኒሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ቻይናውያኑ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች አይደሉም። እንዲያውም ግማሾቹ የአንድ ግንባታ ተቋም ሠራተኞች ናቸው።
«ሰለነዚህ ዶክተሮች ብዙዎቻችሁ ማወቅ እንደምትፈልጉ አውቃለሁ። የት እንዳሉ ባትጠይቁኝ ግን ደስ ይለኛል» ሲሉ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ የመረጃ ሚኒስትሩ ደግሞ ቻይናውያኑ ዶክተሮች በሃገሪቱ ባሉ የተለያዩ የለይቶ ማቆያ ሥፍራዎች እየሰሩ ነው ሲሉ መናገራቸው ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።
ባለፈው ወር የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዣዎ ሊጂያን ዶክተሮች ወደ ምዕራባዊ አፍሪካዊቷ ሃገር የተላኩት በናይጄሪያ መንግሥት ጥያቄ መሠረት ነው ብለው ነበር።
የቻይናውያኑ ወደ ናይጄሪያ መምጣት የሃገሪቱ ጤና ባለሙያዎች ማሕበርን ቢያስቆጣም መንግሥት ግን ሊረዱን ነው የመጡት ብሎ ነበር።
በኮሮናቫይረስ የሞተ የቤተሰብ አባል ሬሳ ካልተሰጠን ብለው ግርግር የፈጠሩት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ
ፓኪስታን ውስጥ በኮሮናቫይረስ የሞተ የቤተሰብ አባል ሬሳ ይዘን ካልሄድን በማለት የሆስፒታል ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ 10 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ጂናህ በተባለው የሕክምና ማዕከል ላይ ሰዎቹ ጥቃት ሲያደርሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች ተሰራጭቷል።
የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶክተር ሰሚ ጃማሊ እንደገለጹት በማዕከሉ ውስጥ 37 የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ህክምናቸውን እየተከታተሉ ነበር።
በሌላ ሆስፒታል ውስጥ ህክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩት የ60 ዓመት አዛውንት የጤና ሁኔታ መባባሱን ተከትሎ ነው ባለፈው ረቡዕ ወደዚህ ሆስፒታል የተዘዋወሩት።
በዛኑ ቀን ምሽትም ሕይወታቸው አልፏል። ነገር ግን ጥቂት የማይባሉ የቤተሰብ አባላት የሟችን ሬሳ ይዘን ካልሄድን በማለት ከሆስፒታሉ ሰራተኞች ጋር እሰጥ አገባ ገብተዋል።
ይህ አልበቃ ብሏቸውም በሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ መቀመጫዎች፣ መስኮቶች፣ ኮምፒውተሮችና ፕሪንተሮችን ከሰባበሩ በኋላ የሟችን ሬሳ እስከ ምድር ቤት ድረስ ወስደዋል።
በኢትዮጵያ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከ62 ሺህ በላይ ሆነ