በኢትዮጵያ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከ62 ሺህ በላይ ሆነ

በኢትዮጵያ በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት 3271 የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን ተከትሎ፣ በአጠቃላይ በሃገሪቷ የተደረገውን ምርመራ 62 ሺህ 300 አድርሶታል። ሃገሪቷ የመመርመር አቅሟንም በመጨመር በቀን ውስጥ 10ሺህ ሰዎችንም የመመርመር እቅድ እንዳላትም የጤና ሚኒስትሯ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። በሃገሪቷም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 365 የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 238ቱ በህክምና ላይ ይገኛሉ፤120ዎቹም አገግመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሃገሪቷ በኮሮናቫይረስ አምስት ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች ሲሆን፤ ሁለቱም ወደመጡበት ሃገራት ተመልሰዋል። ስለወረርሽኙ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የቢቢሲ አማርኛን የቀጥታ ዘገባ ከእዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

  2. "ዜጎች የአልኮል መጠጥ ከታገደ ወዲህ አደብ ገዝተዋል" የናሚቢያ ፖሊስ

    የናሚቢያ ፖሊስ ኃላፊ "ለአልኮል መጠጥ እገዳው ምስጋና ይግባውና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ናሚቢያዊያን አደብ ገዝተዋል" ማለታቸውን 'ናሚቢያን ሰን' የተባለው ጋዜጣ ዘገበ።

    ኃላፊው ሴባስቲያን ዴይቱንጋ እንዳሉት የአገሪቷ ዜጎች መስከር አቁመዋል፣ ወንጀል ቀንሷል፣ በሳምንቱ የእረፍት ቀናት በሚፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ የሚጨናነቁት ሆስፒታሎችም አርፈዋል።

    አክለውም ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተጣሉ ገደቦች ሲጠናቀቁም የሚወሰድ የአልኮል መጠጥን ለመቀነስ ሲባል በመጠጦች ላይ ዋጋ ስለመጨመር የፓርላማ አባላት እንዲያስቡበት አሳስበዋል።

    "ይህ ማኅበረሰብ ከአልኮል ውጪ በጣም ጤናማ ማኅበረሰብ እየሆነ ነው፤ እንደዚህ ቢቀጥል ምኞቴ ነው" ብለዋል ኃላፊው።

    ናሚቢያ የጣለችውን ገደቦች እያላላች ቢሆንም መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛ ክለቦች እና የአልኮል መጠጥ መሸጫዎች አሁንም እንደተዘጉ ናቸው።

    ምግብ ቤቶች የተከፈቱ ሲሆን ደንበኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እንዲያደርጉ እና ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲቀመጡም ይገደዳሉ።

    በአገሪቷ እስካሁን 16 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 13ቱ አገግመዋል። በቫይረሱ ምክንያት የሞተ የለም።

  3. የኮንቴነር ውስጥ ሰቆቃ፡ የ64 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የኮንቴነር ውስጥ ሞት የተረፈው ደጀኔ

  4. ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ባልደረቦች በኮሮናቫይረስ ተያዙ

    ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ተጨዋቾች ወይም አሰልጣኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገለጸ።

    በሊጉ 20 ክለቦች ተጨዋቾች ወይም አሰልጣኞች የሆኑ 748 የሚሆኑ ሰዎች ሊጉ ከንክኪ ነጻ የሆነ ልምምድ ከመጀመሩ በፊት ምርመራ የተደርገላቸው ማክሰኞ ዕለት ነበር፡፡

    ለሦስት የተለያዩ ክለቦች የሚሰሩት ግለሰቦች ለሰባት ቀናት ራሳቸውን ማግለል አለባቸው ተብሏል።

    ሊጉ በሚቀጥለው ወር እንደሚጀመር ተስፋ ተደርጎ የነበረ ሲሆን መቼ እንደሆነ ግን ቁርጥ ቀን አልተቀመጠም።

  5. በኮሮናቫይረስ የተያዘው ነርስ ከ45 ቀናት በኋላ ከጽኑ ሕሙማን ክፍል ወጣ

    በዩናይትድ ኪንግደም በኮቪድ -19 በጠና ታሞ ሕክምና ሲከታተል የነበረው ነርስ ከ45 ቀናት በኋላ ከጽኑ ሕሙማን ክፍል መውጣቱ ተገለጸ።

    ፌሊክስ ኮር የተባለው ይህ ነርስ ህክምና እየተከታተለ ያለው ለ15 ዓመታት ባገለገለበትና በኢሴክስ በሳውዝኢንድ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ነው።

    አሁን የጤንነቱ ሁኔታ ለውጥ በማሳየቱ ከጽኑ ሕሙማን ክፍል የወጣ ሲሆን ሕይወቱን ለማትረፍ ሲተጉ ለነበሩት በሙሉ ምስጋና አቅርቧል።

    ሆስፒታሉ እንደገለጸው ፌሊክስ ከጽኑ ሕሙማን ክፍል ወደ ሌላ ክፍል ሲሸጋገር የሥራ ባልደረቦቹ በኮሪደር ላይ ተደርድረው ደስታቸውን ሲገልጹና ሲያለቅሱ ነበር።

    ፌሊክስ "በጣም ደስ ብሎኛል፤ በሽታውን እንድጋፈጠው የረዳችሁኝ ምስጋና ይድረሳችሁ" ሲል የሥራ ባልደረቦቹና ጓደኞቼ ለሰጡት ከፍተኛ ፍቅርና ድጋፍም ምስጋና አቅርቧል።

    አክሎም "አሁንም ረዥም መንገድ ይቀራል ግን የሆነው በጣም ትልቅ ነገር ነው" ብሏል።

  6. ጉባዔው በዓለም ጤና ድርጅት የወረርሽኝ ምላሽ ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ተስማማ

    የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ድርጅቱ ለዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ተስማማ፡፡

    በድርጅቱ ዓመታዊ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ አውስትራሊያ፣ ቻይና እና ጃፓንን ጨምሮ ከ100 በላይ አገራትን ወክሎ የአውሮፓ ህብረት ያቀረበው ሃሳብ ላይ አሜሪካን ጨምሮ ማናቸውም 194ቱ የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት ተቃውሞ አላቀረቡም፡፡

    የባሃማስ አምባሳደርና የጉባዔው ፕሬዚደንት ሆነው የሚያገለግሉት ኬቫ ቤን፤ "የቀረበውን የመፍትሔ ሃሳብ ለመቀበል ጉባዔው ተዘጋጅቷል?" ሲሉ የጠየቁ ሲሆን "እንደማየው ከቤቱ ምንም ጥያቄ አልቀረበም፤ በመሆኑም በሃሳቡ ላይ የቀረበ ተቃውሞ እንደሌለ እወስዳለሁ፤ ስለዚህ የመፍትሔ ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቷል" ብለዋል፡፡

    ቀደም ብሎ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም "ምን እንደምንማር የሚያመላክትና ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለብን የሚጠቁም ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ይካሄዳል" ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

  7. "መቼም ቢሆን ኮሮቫይረስ ላይጠፋ ይችላል" ባለሙያዎች

    በኮሮናቫይረስ ላይ የሚሰጡ መላ ምቶች በርካታ ናቸው። ከሰሞኑ ደግሞ የእንግሊዝ የጤና ተመራማሪዎች ኮሮናቫይረስ በጭራሽ ላይጠፋ እንደሚችል ተናግረዋል።

    በግላስጎው ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሮበርትሰን በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ ላለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚቴ እንደተናገሩት ኮቪድ- 19 በመተላለፍ ሁኔታው የላቀ ስፍራ የሚሰጠው ነው ብለዋል።

    "በከፍተኛ ሁኔታ ሁሉንም ሊያጠቃ የሚችልና የመተላለፍ ሁኔታውም ታይቶ የማያውቅ ቫይረስ ነው። ሁላችንም ተጋላጭ ነን። ሆኖም የቫይረሱ ሁኔታ ከዚህ በበለጠ ሊከፋ እንደሚችል መናገሩ አሳሳች ነው። ባለንበት ወቅት ከዚህ ሊከፋ አይችልም" ብለዋል።

    ኮሮናቫይረስን ከኢቦላ ጋር በማነፃፀር ያዩት ተመራማሪው፤ በኢቦላ የተያዙት ሰዎች በርካቶቹ ቢሞቱም ነገር ግን በሽታውን ከመዛመት ለመግታትም ሆነ ህሙማኑም እንዳያስተላልፉት በማድረግ መቆጣጠር እንደተቻለም አስረድተዋል።

    "በብዙ አጋጣሚዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ምንም ምልክት እንዲሁም መካከለኛ ምልክት ማሳየታቸው የቫይረሱን የመዛመት ሁኔታ መቆጣጠርን አዳጋች ያደርገዋል" ብለዋል ባለሙያው።

    አክለውም "በእኔ አስተያየት ቫይረሱን መቼም ቢሆን እንደማናጠፋው ግልፅ ሊሆን ይገባል። ለረዥም ዓመታትም ከሕዝቡ ጋር አብሮ የሚኖር ቫይረስ ይሆናል። በጊዜም ብዛት የተለመደ ቫይረስ ይሆናል" በማለት ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    ሆኖም በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም ሊኖራቸው እንደማይችልም እየተነገረ ነው።

    በለንደን ዩኒቨርስቲ የተላላፊ በሽታዎች ፕሮፌሰር ጆን ኤድመንድስ በበኩላቸው በሳርስ ተጠቅተው ያገገሙ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ በሽታን የመከላከል አቅማቸው እየተዳከመ እንደሚመጣ ታይቷል ብለዋል።

    "ይህ ሁኔታ ለእኛ መጥፎ ዜና ነው። በቫይረሱ ምክንያት የሰውነት የመከላከል አቅም እየተዳከመ መምጣት ችግሩን የበለጠ ያወሳስበዋል" ብለዋል።

  8. "የዓለም ጤና ድርጅት ቻይና በአፍሪካዊያን ላይ የፈጸመችውን ዘረኛ ድርጊት ችላ ብሏል" ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይናዋ ደቡባዊ ከተማ ጉዋንዡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቀስቀሱን ተከትሎ በአፍሪካዊያን ላይ ሲፈጸም ለነበረው ዘረኛ ድርጊትና መድልዎ የዓለም ጤና ድርጅት ጠንካራ ምላሽ አልሰጠም ሲሉ ትችት ሰነዘሩ፡፡

    ትራምፕ ለድርጅቱ ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በጻፉት ደብዳቤ ላይ አፍሪካዊያን በግድ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ፣ ከመኖሪያቸው እንዲባረሩ፣ እንዲሁም አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግን ጨምሮ ዘረኛ እና አድሎአዊ ድርጊት ደረሰብን ቢሉም፤ ድርጅቱ በቻይና ዘረኛ ድርጊት ላይ አስተያየት አልሰጠም ሲሉ ከሰዋል፡፡

    ባለፈው የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ በጉዋንዡ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ላይ ሰፊ ምርመራ የተደረገ መሆኑን በደብዳቤያቸው ላይ የጠቀሱት ፕሬዚደንቱ፤ ይህም አፍሪካዊያን በዘራቸው ምክንያት ኢላማ እንደሆኑ ቅሬታቸውን በመናገራቸው መጋለጡን አስረድተዋል፡፡

    አፍሪካዊያን ቤታቸውንና የነበሩበትን ሆቴል እንዲለቁ በመገደዳቸው በጎዳናዎች ላይ ተኝተው የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወጥተዋል፡፡

    በተንቀሳቃሽ ምስሉ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሰዎችም ተገደው ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

    በወቅቱ የጉዋንዡ ባለሥልጣናት የቀረበውን ቅሬታ ውድቅ አድርገውታል፡፡

    ፕሬዚደንት ትራምፕ ግን የዓለም ጤና ድርጅት ዘረኛና አድሎአዊ የሆነውን ድርጊት ሊያወግዝ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡

    ትራምፕ ለዶክተር ቴድሮስ የጻፉትን ደብዳቤ በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል፡፡

  9. የናይጄሪያ አንድ ግዛት የጁመዓ ሶላትን ፈቀደች

    የናይጄሪያ ካኖ ግዛት አስተዳዳር የተወሰኑ የሐይማኖት መሪዎች ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ የጁመዓ ሶላትንና የኢድ አልፈጥር አምልኮን መፍቀዱን አስታወቀ።

    ይሁን እንጂ ባህላዊ የሆነው የኢድ አልፈጥር በዓል አከባበር አይፈቀድም ብለዋል አስተዳዳሪው።

    ኢማሞችም (የሐይማኖት አባቶች) ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረጋቸውን፣ አካላዊ ርቀት መጠበቃቸውን እና እጃቸውን በሚገባ መታጠባቸውን ለማረጋገጥ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

    አስተዳዳሪው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ሰፊ ምክክር ካደረጉ በኋላ እንደሆነ የአስተዳዳሪው የሚዲያ ልዩ አማካሪ ሳሊሁ ያካሳይ ገልጸዋል።

    አማካሪው "የግዛቷ አስተዳዳሪ የእጅ ማጽጃ ኬሚካሎች ስርጭትን፣ የንጽህና መሳሪያዎችን እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስኮችን) የሚቆጣጠር ኮሚቴ አዋቅረዋል" ሲሉ በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።

    የናይጀሪያዋ ካኖ ግዛት አሁንም በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ያለች ሲሆን በናይጀሪያ ካሉ ሌሎች ግዛቶች በበለጠ በቫይረሱ ክፉኛ ተጠቅታለች።

  10. በትራምፕ ደብዳቤ የተጠቀሰው መረጃ ስህተት እንዳለበት አንድ ባለሙያ ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ቴድሮስ ባለ አራት ገጽ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል።

    ፕሬዝደንቱ በደብዳቤያቸው የዓለም ጤና ድርጅት 'የቻይና አሻንጉሊት ነው' ከማለታቸውም በተጨማሪ ድርጅቱ አሰራሩን እንዲያስተካከል የ30 ቀናት የጊዜ ገደብ ሰጥተዋል። አሜሪካ ለድርጅቱ ታድረግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ በቋሚነት ሙሉ ለሙሉ ሊያቋርጡ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።

    ታዲያ ትራምፕ ለዶ/ር ቴድሮስ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንደማስረጃ ካቀረቡት መከራከሪያ ነጥባቸው መካከል አንዱ ዘ ላንሴት የሚሰኘው የህክምና መጽሄትን ጨምሮ እአአ ዴሴምበር 2019 ላይ በዉሃን የቫይረሱን ስርጭት አስመልክቶ ዘገባዎች ቢወጡም የዓለም ጤና ድርጅት ግን በተደጋጋሚ በቸልተኝነት ዘገባዎቹን አልፏቸዋል የሚለው ይገኝበታል።

    የዘ ላንሴት የህክምና መጽሄት አርታዒው ሪቻርድ ሆርተን ግን መጽሄቱ እስከ ጄኒዋሪ 24 2020 ድረስ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ሪፖርት አለማውጣቱን በመግለጽ የትራምፕ መከራከሪያ ነጥባቸውን ለማጠናከር የጤና መጽሄቱን መጥቀሳቸው ስህተት መሆኑን ጠቁሟል።

    አርታዒው በትዊተር ገጹ ላይ፡ "ክቡር ፕሬዝደንት ትራምፕ- የዓለም ጤና ድርጅትን በኮነኑበት ጽሁፍ ላይ ዘ ላንሴትን ጠቅሰዋል። እባክዎን ይህን ላስተካክል። ዘ ላንሴት በዴሴምበር 2019 መጀመሪያ ቫይረሱ በዉሃን እየተሰራጨ ስለመሆኑ ያወጣው ሪፖርት የለም። የመጀመሪያው ሪፖርት ያወጣነው ከቻይናውያን ሳይንቲስቶች የተገኘውን ጄነዋሪ 24፤ 2020" ነው ብሏል።

  11. ባለፉት 24 ሰዓታት ተጨማሪ 14 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተነገረ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ተጨማሪ 14 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተነገረ።

    የጤና ሚንስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው ባለፉት 24 ሰዓታት ለ3271 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ 11 ወንዶች እና 3 ሴቶች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ከእነዚህም መካከል አንዱ የውጪ አገር ጉዞ ታሪክም ሆነ ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌለው ነው ተብሏል።

    በጠቅላላው በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 365 የደረሰ ሲሆን፤ 4 ሰዎች ደግሞ ባለፉት 24 ሰዓታት አገግመዋል ተብሏል። ይህም ያገገሙ ሰዎች ጠቅላላ ቁጥርን ወደ 120 ከፍ አድርጎታል።

  12. በወረርሽኝ ወቅት በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ የሚወስዷቸው "ልብ ሰባሪ አማራጮች"

    ፌርዌልስ የተሰኘ ድርጅት እአአ ከ2005 ጀምሮ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ህይወትን ለመቀየር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

    በጎ አድራጊው ድርጅት እንደሚለው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሰዎች በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ መወሰኑ፤ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ያለምንም ገቢ በቤት እንዲቆዩ አልያም ራሳቸውን ለአደጋ በማጋለጥ በሥራ መቀጠል የሚል ሁለት ልብ የሚሰብሩ አማራጭ እንዲኖራቸው አድርጓል ይላል።

    ሚስትረስ ፐርል መቀመጫዋን ደቡብ ዌልስ ሲሆን በዚህ በወሲብ ንግድ ላይ ከተሰማራች ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗታል። ብቸኛ የገቢ ምንጯም ይኼው ሥራ ነው።

    እሷ እንደምትለው 'አገልግሎት የምትሰጠው በኢንተርኔት አማካኝነት ኦን ላየን ብቻ ነው።' ይሁን እንጂ ደንበኞቿ በአካል ለማግኘት ተጸእኖ ያሳድሩባታል።

    "አሁንም በአካል ሰዎችን እያገኘሁ እንደሆነ ይጠይቁኛል። 'አይሆንም' ስላቸው 'እባክሽን ትንሽ ደቂቃ ብቻ ነው የሚወስደው' ይሉኛል። ግን በእነዛ ትንሽ ደቂቃዎች በቫይረሱ ሊያሲዙኝ ይችላሉ" ትላለች።

    የእንቅስቃሴ ገደቦች ከመጣላቸው በፊት እንደየቀናቱ ቢለያይም ሁለት ወንድ ደንበኞች ጋር ልትገናኝ እንደምትችል ትናገራለች፤ ይሁን እንጂ የኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት እርሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎች በዚህ ሥራ የተሰማሩ ሴቶችም ወንዶችን በአካል ከማግኘት እንዲቆጠቡ ታሳስባለች።

    "እባካችሁ አቁሙ። ራሳችሁን ጠብቁ። ደንበኞቻችሁ ቫይረሱ እንደሌለባቸው ልታውቁ አትችሉም። አታውቋቸውም። እባካችሁ ጥንቃቄ አድርጉ" ትላለች።

  13. ዛምቢያ የቻይና ምግብ ቤትን "ማግለል አድርሷል" በሚል ዘጋች

    የዛምቢያ ባለሥልጣናት አንድ የአገሬው ተወላጅ ወደ ቻይና ምግብ ቤት እንዳይገባ መከልከሉን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ሉሳካ የሚገኝ አንድ የቻይና ሬስቶራንትን ዘጉ።

    ምግብ ቤቱ ዛምቢያዊው እንዳይገባ መከልከሉ ተገልጿል። ግለሰቡ ጉዳዩን ዘረኛ ሲል ገልጾታል።

    የሉሳካ ከንቲባ ሚለስ ሳምፓ በምግብ ቤቱ የሚሸጡ ምግቦች በሕግ የተከለከሉ ቢሆንም በቻይንኛ ብቻ የተጻፉ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።

    ከንቲባው "በሉሳካ ከረዥም ጊዜ በፊት፣ ዛምቢያ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ፣ አፓርታይድ አክትሟል" ማለታቸውን ሉሳካ ታይምስ ድረ ገጽ ዘግቧል።

  14. የ64 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የኮንቴነር ውስጥ ሞት የተረፈው ደጀኔ

  15. ታንዛንያ የውጪ አገር ጎብኝዎች ላይ ጥላ የነበረው የ14 ቀን ለይቶ ማቆያ መግባት አነሳች

    ታንዛንያን ከባህር ማዶ የሚመጡ እንግዶች ላይ ጥላ የነበረው የ14 ቀን ለይቶ ማቆያ ማንሳቷን የጤና ሚኒስትሯ ገለፁ።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚል የውጪ አገራት ዜጎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የተወሰነው ባለፈው ወር ነበር።

    ነገር ግን ሰኞ ዕለት በባለስልጣናት የተጣለው አዲሱ መመሪያ እንደሚገልፀው ከውጪ አገራት የሚመጡ ዜጎች በአውሮፕላን ጣብያ ላይ ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ መግባት ይችላሉ።

    ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ "ሁሉም መንገደኞች የተዘጋጀውን ቅጽ በታማኝነት እንዲሞሉ ይጠየቃሉ" ብለዋል።

    ነገር ግን ከውጪ የሚመጡም ሆኑ በአገር ውስጥ ያሉ ታንዛናውያን የእጅ ንጽህናቸውን መጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አንዲሁም ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    ይሀ ውሳኔ የተሰማው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ሆስፒታል የሚገቡ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ከመጣ አገሪቱ ለጎብኚዎች ዳግም ለመክፈት እንደሚያስቡ ከገለፁ በኋላ ነበር።

    የአሁኑ የመንግሥት እርምጃ አገሪቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በቁጥጥሯ ስር አውላዋለች የሚል አንድምታ አለው ያሉም አልጠፉም።

    ነገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲው አባል ዋዛሌንዶ፣ በቫይረሱ የተያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    • ዶናልድ ትራምፕ ለዶ/ር ቴድሮስ የ30 ቀን ጊዜ ገደብ ሰጡ

    • ፍቅረኛዬን ያለችው ኬንያዊት ነርስ ለይቶ ማቆያ ገባች

      ኬንያዊቷ ነርስ ፍቅረኛዋን ለማግኘት፣ 'አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለመስጠት' በሚል ሽፋን ከምትኖርበት ናይሮቢ ወደ ናኩሩ ከተማ በመሄዷ ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እንድትገባ ተደረገች።

      የኬንያ መንግሥት ከዋና ከተማዋ የሚገቡም ሆኑ የሚወጡ የትኛውንም እንቅስቃሴ፣ ከከባድ መኪኖች ውጪ፣ አግዷል።

      የጤና ባለሙያዎች አስፈላጊ አገልግሎት አቅራቢዎች በሚል ተለይተው ከከተማዋ መውጣት እና በሰዓት እላፊ ወቅት እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዶላቸዋል።

      ነርሷ ፍቅረኛዋ ቤት ከደረሰች በኋላ የፍቅረኛዋ ጎረቤቶች መምጣቷን ለፖሊስ ማሳወቃቸው ተነግሯል። ፖሊስ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ያዋላት ሲሆን የነርሷ የሰውነት ሙቀቷ ከፍ በማለቱ ለ14 ቀን በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንድትቆይ ወስኗል።

      ነርሷ ግን መንገድ ተዘግቶባት እንጂ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለመስጠት እየሄደች እንደነበር ለፖሊስ ተናግራለች።

      ዘገባውን የሰራው ሲቲዝን ቲቪ ቪዲዮውን አጋርቶታል።

    • ዩናይትድ ኪንግደም የፓስተር ክሪስን የቴሌቪዥን ጣቢያን ዘጋች

      ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በታዋቂው ናይጄሪያዊ ፓስተር ባለቤትነት የሚተዳደረው አንድ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ባስተላለፈው ፕሮግራም ምክንያት ተቀጣ።

      የአገሪቱ ኦፍኮም የተባለው የመገናኛ ብዙኀን የበላይ ተቆጣጣሪ የፓስተር ክሪስ ኦያኪሎሜ ንብረት በሆነው ‘ላፍዎርልድ’ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ “በዜናና የቀጥታ መንፈሳዊ ፕሮግራም ስርጭት ላይ የኮሮናቫይረስን ምክንያትና ህክምናን በተመለከተ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ይዘቶችን” አስተላልፏል በሚል ነው ቅጣት የተጣለበት።

      የፓስተር ክሪስ ኦያኪሎሜ በቴሌቪዥናቸው ላይ የኮሮናቫይረስን ከ5ጂ (የአምስተኛው ትውልድ) የሞባይል ኔትወርክ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነው በማለት ይህም “አዲስ የዓለም ሥርዓት” ለመፍጠር የሚካሄድ ሴራ አካል ነው በማለት ከሰዋል።

      ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ኮሮናቫይረስንና 5ጂን የሚያያይዘው አመለካከት “ዋጋ ቢስ” ከመሆኑ በላይ በሥነ ህይወት እሳቤም ሊሆን የማይችል ሐሰተኛ ነገር ነው በሚል በተለያዩ ሳይንቲስቶች በስፋት ውድቅ ተደርጓል።

      የዩናይትድ ኪንግደም የመገናኛ ብዙኀን የበላይ ተቆጣጣሪ ኦፍኮም እንዳለው የቴሌቪዥን ጣቢያው “በዜናው ላይ ያለማስረጃ የ5ጂ ቴክኖሎጂ ወረርሽኙን አስከትሏል ከማለቱ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ ጉዳዩን ለመሸፋፈን እየተሞከረ መሆኑን አቅርቧል” ሲል ዎርልድላቭ ቲቪን ከሷል።

      በተጨማሪም በጣቢያው በተላለፈ አንድ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ለበሽታው ክትባት ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎችን ፍላጎትን ተችቷል ተብሏል።

      የመገናኛ ብዙኀን የበላይ ተቆጣጣሪው ኦፍኮም በቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ የወሰደው ርምጃ አወዛጋቢ ሃሳቦችን ለመቃወም ሳይሆን፤ የቀረቡት ጉዳዮች በተጨባጭ ማስረጃ መደገፍ ያለባቸውና የጤና ባለስልጣናትን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል መሆን ስለሌለበት ነው ብሏል።

    • ኡጋንዳ ለዜጎቿ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ልታድል ነው

      የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የእንቅስቃሴ ገደቡን ከማንሳታቸው በፊት መንግሥታቸው እድሜያቸው ከስድስት ዓመት በላይ ለሆነ በሙሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ-ማስክ በነፃ እንደሚያከፋፍል ገለፁ።

      በኡጋንዳ የአፍና አፍንጫ ማድረግ ግዴታ መሆኑ የተደነገገው በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

      ፕሬዝዳንቱ ሰኞ ዕለት በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ስርጭቱ በሚቀጥሉት 14 ቀናት ውስጥ ይካሄዳል። እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ማስክ ከመንግሥት እንደሚሰጠው ጨምረው ገልፀዋል።

      ከዚያ በኋላ ሱቆች ይከፈታሉ፣ የሕዝብ መጓጓዣዎችም መጫን ከሚችሉት በግማሽ ቀንሰው እንዲሰሩ እንደሚደረግ፣ በምግብ መሸጫ ስፍራዎች የሚሰሩም በየዕለቱ መጨረሻ ወደቤታቸው እንዲሄዱ ይፈቀዳል ብለዋል።

      ይኹን እንጂ አሁንም በድንበር ከተሞች አካበቢ የመጓጓዣ አገልግሎት ለ21 ቀናት ያህል እንደታገደ ነው።

      ሁሉም ትምህርት ቤቶች ዳግም የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲጀምሩ የተፈቀደ ቢሆንም ለብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የሚቀመጡት ብቻ እንዲቀበሉና እንዲያሰተናግዱ ተነግሯቸዋል።

      ኡጋንዳ አሁንም ድንበሯን የዘጋች ሲሆን ከምሽት እስከ ንጋት የተጣለው የሰዓት እላፊም ለቀጣዩቹ 21 ቀናት ይቀጥላል ተብሏል።

      አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣለች 48 ቀን ሆኗታል።

      ኡጋንዳ እስካሁን ድረስ 248 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥአብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ድንበር አቋርጠው የሚመጡ መኪኖች አሽከርካሪዎች ናቸው ተብሏል።

    • የኒው ዚላንድ መንግሥት የቱሪዝምን ለማነቃቃት ለሰራተኞች የሥራ ፍቃድ ሊሰጥ ነው

      የኒው ዚላንድ መንግሥት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት ለሠራተኞች ተጨማሪ የሥራ ፍቃድ ለመስጠት እያጤነ መሆኑ ተነገረ።

      ጠቅላይ ሚንስትር ጃኪንዳ አርደረን እንዳሉት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት አንዱ እና ሁነኛ አማራጭ ለሠራተኞች የሥራ እረፍት መስጠት ነው ብለዋል።

      ቱሪዝም የኒው ዚላንድ የገቢ ምንጮች መካከል አንዱ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ግን ወደ ኒው ዚላንድ የሚያቀና ጎብኚ የለም። ይህንንም ተከትሎ የቱሪዝም ሴክተሩ እጅጉን እንደተጎዳ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

      ጠቅላይ ሚንስትሯ ዜጎች የራሳቸውን አገር እንዲጎበኙ እና የተጎዳውን የቱሪዝም መስክ እንዲያገግም ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

      ለአገሬ ዜጎች የማስተላልፈው መልዕክት ኑ እና የራሳችሁን አገር ጎብኙ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሯ።

      ኒው ዚላንድ የኮሮናቫይረስን በመግታት ረገድ ትልቅ ስኬት አስመዝግባላች የምትባል አገር ናት። የአገሪቱ መንግሥት 'ቫይረሱ ከአገራችን ተወግዷል' ሲል ማወጁ ይታወሳል።