የኢራን አየር መንገድ በመካከለኛው ምስራቅ ኮቪድ-19 እንዲሰራጭ አድርጓል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማሃን የተሰኘው የኢራን አየር መንገድ በመካከለኛው ምስራቅ ለኮቪድ-19 መሰራጭት ምክንያት እንደነበረ ተረጋገጠ።
ከኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ጋር ግንኙነት ያለው ማሃን አየር መንገድ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ከኢራን ወደ ሌባኖስ እና ኢራቅ አጓጉዟል።
በሌባኖስ እና ኢራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጡት ሰዎች በዚህ አየር መንገድ ከኢራን የመጡ ናቸው።
በማሃን አየር መንገድ ውስጥ የሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች እንዳሉት፤ የአየር መንገዱ የበረራ አስተናጋጆች ስለቫይረሱ ስርጭት ስጋታቸውን እንዳይናገሩ ተደርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የበረራ ሠራተኞች በቂ የመከላከያ ቁሶችም አያገኙም ነበር።
የበረራ መከታተያ መረጃ እንደሚያሳየው ምንም እንኳን አገሪቱ የበረራ እገዳ ብትጥልም አየር መንገዱ በተደጋጋሚ ወደ ቻይና ጉዞዎችን አድርጎ ነበር።
ማሃን ኤር በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።








