በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ነገር ግን በኮቪድ-19 ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው። ይህም ቫይረሱ ቀስ በቀስ እግሩን በማህበረሰቡ ውስት እያስገባ መሆኑን ያሳያል። ለዚህ ግን ትልቁ መፍትሄ የሕክምና ባለሙያዎችና መንግሥት የሚሰጧቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ነው። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. አባትና ልጅ በቀናት ልዩነት በኮሮናቫይረስ ሞቱ

    የዊንከፕ ቤተሰቦች

    የፎቶው ባለመብት, Whincup family

    ባለቤታቸውን እንዲሁም ልጃቸውን በቀናት ልዩነት በኮሮናቫይረስ የተነጠቁት ሴት ድንጋጤው እንዳልለቃቸውና ህይወትን ትርጉም እንዳጡበት ተናግረዋል።።

    የ52 አመቷ ልጃቸው ጆዋን ሬኒንሰን በሰሜናዊ እንግሊዝ፣ በዮርክሺር በሚገኝ ሆስፒታል መጋቢት 27፣ 2012 ዓ.ም ስትሞት፤ ከሰባት ቀናት በኋላ የ79 አመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ባለቤታቸው ዴቪድ ዊንከፕ በሁል ሮያል ሆስፒታል ህይወታቸው አልፏል።

    ማርጋሬት ዊንከፕ በልጃቸው እንዲሁም በባለቤታቸው ሞት ልባቸው ተሰብሯል።

    "ሰውነቴን መቆጣጠር አልችልም፤ የት እንደምሄድ ሁሉ አላውቅም። በቃ ደንዝዣለሁ" ብለዋል።

    ከልጆቻቸው እንዲሁም ከተለያዩ ጓደኞቻቸውም እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን "ሰዎች በዚህ ወቅት ደግነታቸውን አበባ በማምጣት መልዕክት በመላክ አሳይተውኛል" ብለዋል።

  2. በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

  3. የኢራኑ አየር መንገድ በመካከለኛው ምስራቅ ኮቪድ-19 እንዲስፋፋ አድርጎ ይሆን?

    የማሃን አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጠቃች እና አገራት የዓለም አቀፍ በረራዎችን ካገዱ በኋላ የኢራን አየር መንገድ የሆነው ማሃን ኤር ወደ ቻይና እና መካከለኛው መስራቅ አገራት ይበር እንደነበር የቢቢሲ አረብኛ ምርመራ ዘገባ ይፋ አደረገ።

    ማሃን ኤር ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት አለው የሚባል ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ የበረራ እገዳ በተጣለበት ወቅት ወደ ኢራቅ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ፣ ሶሪያ ይበር እንደነበር ተገልጿል።

    በዚህ ወቅት አየር መንገዱ ወደ ኢራን የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡ ታውቋል።

    በአየር መንገዱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ የኮቪድ-19 ምልክት ያሳዩ የበረራ ሠራተኞች ያሉ ሲሆን ለኃላፊዎቻቸው ያለቸውን ስጋት ቢገልፁም ዝም እንዲሉ ተደርጓል ተብሏል።

  4. ትራምፕ በአሜሪካ በኮሮና ምክንያት 3ሺህ ሰው ይሞታል የሚለው መረጃ ስህተት ነው አሉ

    አስከሬኖች የሚቀመጡበት ቦታ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሪዞና ወደሚገኘው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማምረቻ አብረዋቸው ለሄዱ ጋዜጠኞች ከፌደራል መንግሥቱ ወጣ ተብሎ የተነገረውና በአሜሪካ በሰኔ ወር በቀን ሶስት ሺህ ሰዎች በኮሮና ምክንያት እንደሚሞቱ ይገመታል የሚለው መረጃ ስህተት ነው አሉ።

    የፌደራሉ አደጋ ጊዜ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ማስታወሻን በመጥቀስ " ሪፖርቱ መቀነስን የሚያሳይ አይደለም፤ እኛ ደግሞ እየቀነስን ነው" ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም የእንቅስቃሴ ገደቡን ያነሱ የተለያዩ ግዛት አስተዳዳሪዎችን ከሚደርስባቸው ወቀሳ ተከላክለው " የግዛቲቱ ነዋሪዎች አካላዊ ርቀታቸውን እየጠበቁ የቫይረሱን ስርጭት የሚቀንሱ ተግባራትን እያከናወኑ ነው" ብለዋል።

    በተጨማሪም የእንቅስቃሴ ገደቡ ቢቀጥል የሰው ሕይወት ይቀጥፋል በማለትም፤ ራሳቸውን የሚያጠፉ እና አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ ሰዎችን ጠቅሰዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከወር በላይ ከዋይት ኃውስ ሳይወጡ ቆይተው የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በአሪዞና አድርገዋል።

    አብረዋቸው በኤር ፎርስ ዋን የተጓዙትን ሰዎችን በተመለከተ ሲናገሩ " በጣም ጥሩ መመርመሪያ አለን፤ ወይንም ከእኔ ጋር እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም ነበር" ብለዋል።

  5. “ያልተፈተነ መድኃኒት አትውሰዱ” የአለም ጤና ድርጅት

  6. ኬንያ የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር የሚያደርጉ አገራትን ተቀላቀለች

    ኬንያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በመላው ዓለም የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት አገራት በየፊናቸው እንዲሁም በጋራ የተለያዩ ምርምሮችን ያደርጋሉ።

    ኬንያ ለዓለም ጤና ድርጅት በክትባት ምርምሩ ላይ ለመሳተፍ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ የኮቨድ-19 ክትባትና ሕክምና ላይ የሚደረገውን የምርምር ሥራ ተቀላቅላለች።

    የምስራቅ አፍሪካ ተመራማሪዎች የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን ለምርምር ሥራቸው ከመምረጣቸው በፊት የኬንያ ሳይንስ ምክር ቤት እንዲሁም ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽንን ፈቃድ እየጠበቁ ነው ተብሏል።

    የሚያደርጉት ምርምር ከተፈቀደ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሕሙማን ላይ አራት ዓይነት መድሃኒቶችን ለመሞከር ይመለምላሉ ተብሏል።

    አራቱ መድሃኒቶች ከዚህ ቀደም ቫይረሱን ለመዋጋት ፍንጭ ያሳዩ መሆናቸው ተገልጿል።

    የዓለም ጤና ድርጅት አራቱን መድሃኒቶች በቤተ ሙከራ፣ በእንስሳት እንዲሁም በክሊኒክ ውስጥ ፍተሻ ከተደረገባቸው በኋላ ባገኘው ውጤት መሰረት መምረጡ ተገልጿል።

    ተመራማሪዎቹ ሙከራ እስከሚደረግባቸው የሚጠብቋቸው መድሃኒቶች ኢቦላን ለማከም የሚውለው ሬምደስቪር፣ የወባ መድሃኒት እና ከኤችአይቪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚውለው ሊፖናቪር ናቸው።

    በአሁኑ ሰዓት ለኮቪድ-19 ፈዋሽ መድሃኒት የሌለ ሲሆን፤ ነገር ግን በዓለም ላይ ያሉ ተመራማሪዎች በጋራ የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች ክትባቱን በፍጥነት ለማግኘት ይረዳል ብለው ያምናሉ።

    ከ 35 በላይ የአፍሪካ አገራት በምርምር ሥራው ላይ ለመሳተፍ ቢጠይቁም ስድስት አገራት ብቻ ይኹንታን ማግኘታቸው ተገልጿል።

    ከኬንያ በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ዛምቢያ፣ ናይጄሪያ እና ቱኒዚያ ይገኙበታል።

  7. በሕንድ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

    ሕንድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሕንድ ባለፉት 24 ሰዓታት 3,900 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር መጨመራቸውን ያሳያል ተብሏል።

    በሕንድ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ ተይዘው የተገኙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 46,433 የደረሰ ሲሆን፤ በአገሪቱ የሚመረመሩ ሰዎች በጨመረ ቁጥር በቫይረሱ ተይዘው የሚገኙ ሰዎችም መጨመራቸው ተነግሯል።

    ሰኞ ዕለት ብቻ ከ 80 ሺህ በላይ ምርመራዎች የተደረገ ሲሆን ሕንድ ከ20 ቀን በኋላ በመላ አገሪቱ ላይ ጥላ የቆየችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ታላላች ተብሏል።

  8. ኮቪድ-19 አውሮፓ ምድር መጀመሪያ የረገጠው መቼ ይሆን?

    ፈረንሳይ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በፓሪስ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በፈረንጆቹ 2019 ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) መታመሙ ተጠርጥሮ ሕክምና ካገኘ ግለሰብ የተወሰደ ናሙና ሲመረመር ኮቪድ-19 እንዳለበት መረጋገጡ ተገለፀ።

    ይህም ማለት ቫይረሱ ወደ አውሮፓ ገብቷል ከተባለበት በአንድ ወር ጊዜ ቀድሞ መከሰቱን ያሳያል ተብሏል።

    ዶ/ር ዬቪስ ኮሃን እንዳሉት ከታካሚው በወቅቱ ተወስዶ የነበረ ናሙና በቅርቡ ምርመራ የተደረገለት ሲሆን ኮቪድ-19 ተይዞ እንደነበር ተረጋግጧል።

    ታካሚው በበኩሉ በወቅቱ የኮሮናቫይረስ ስለመያዙ ምንም ዓይነት እውቀቱ እንዳልነበረው ገልጾ የጉዞ ታሪክም እንደሌለው አክሏል።

    የመጀመሪያው በቫይረሱ የተያዘ ሰውን ማግኘት ስርጭቱ እንዴት ሊስፋፋ እንደቻለ መረጃ በመስጠት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል።

    የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ቀደም ብለው በተያያዥ ሕመም ወደ ሆስፒታል ጎራ ብለው የነበሩ ታማሚዎችን ታሪክ መመልከት በየአገራቱ ወረርሽኙ በምን መልኩ እንደተሰራጨ ለመገንዘብ ስለሚረዳ መንግሥታት የቀደሙ ታካሚዎችን ታሪክ መለስ ብለው እንዲመለከቱ መክሯል።

    የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር ለቢቢሲ መንግሥት ስለታካሚው መረጃ እንደደረሰው ገልፀው ተጨማሪ ምርመራዎች እናደርጋለን ብለዋል።

    ከሁለት ሳምንት በካሊፎርንያ በተደረገ ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ ሞት የተመዘገበው ቀድሞ ሲታሰብ ከነበረው አንድ ወር ቀድሞ መሆኑ ተነግሯል።

  9. የጀርመን ዳንሰኞች ቤት መቀመጥን ተቃወሙ

    በዳንስ እየተቃወሙ ያሉ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ መዛመቱን ለመግታት በወሰደቻቸው እርምጃዎች ምስጋና የተቸራት ጀርመን፤ በርካታ መመሪያዎቿን በማሻሻል የተለያዩ የንግድ ቦታዎችንም እየከፈተች ነው።

    ነገር ግን የተለያዩ የዳንስ ቡድኖች በሙኒኳ ባቫሪያ ግዛት በመሰባሰብ መንግሥት ቫይረሱን ለመዛመት እየወሰደ ያለውን እርምጃዎች ተቃውመዋል።

    ብዙዎች የቡድኑ መሰባሰብ ያስደነገጣቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል ፖለቲከኛዋ ካትሪና ሹልዝ ተቃውሟቸው የሚያሳየው ቪዲዮ ላይ "አምላኬ ሆይ!" የሚል አስተያየት ሰጥታለች።

    ምንም እንኳን ስብሰባዎች አሁንም ባይፈቀዱም ውጭ ከሆነ ግን አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው 50 ሰዎች ለአንድ ሰአት ያህል መሰብሰብ እንደሚችሉ ፖሊስ አስታውቋል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    የባቫሪያ ግዛት ከንቲባ ማርኩስ ሶዴር በበኩላቸው ግዛቷ መመሪያዎችን ለማላላት እቅድ እንዳላት በዛሬው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልፀዋል። ከነገ ጀምሮም ቤተሰብ መጎብኘት የሚፈቀድ ሲሆን የህፃናት መጫወቻዎችም ክፍት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

    ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ደግሞ የመዋቢያ ሳሎኖችን ጨምሮ የንግድ ቦታዎች በሙሉ እንደሚከፈቱ ገልፀው ፤ሆኖም የፊት ጭምብልም ሆነ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አሁንም ቢሆን አስገዳጅ ናቸው ብለዋል።

  10. በናይጄሪያ የእንቅስቃሴ ገደብ ቢነሳም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አምሳ በመቶ ጨመረ

    ሌጎስ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የሌጎስ ከተማ አስተዳዳሪ የከተማዋን የጤና በጀት በ20 በመቶ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ለቢቢሲ ገለፁ።

    ባባጂዴ ሳንዎ ኦሉ፣ እንዳሉት ከእርሳቸው በፊት የነበሩ አስተዳዳሪዎች ለከተማዋ የጤና አገልግሎት ተቋማት በቂ በጀት መመደብ ላይ ደካማ ነበሩ።

    በናይጄሪያ ከሚገኙ ከተሞች ሁሉ ሌጎስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕከል ስትሆን፣ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ 1,183 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 30 ደግሞ ሞተዋል።

    በናይጄሪያ ለተከታታይ አምስት ሳምንታት ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ሰኞ እለት ያበቃ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በሌጎስ፣ አቡጃ እንዲሁም ኦጉን ከተሞች ሕይወት ዳግም አንሰራርቷል።

    ይኹን እንጂ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 50 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።

    በሌጎስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተከትሎ በርካታ አለመረጋጋቶች መኖራቸውን አስተዳዳሪውን አምነዋል።

    አስተዳዳሪው ሳንዎ ኦሉ አክለውም በከተማዋ የኮቪድ-19 መመርመሪያዎችን ለማብዛት ቃል ገብተዋል።

  11. የኒጀር ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ሞቱ

    የኒጀር ሰንደቅአላማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኒጀር የሰራተኛ ሚኒስትር ሞሃመድ ቤን ኦማር በኮሮናቫይረስ መሞታቸውን የአገሪቱ ሚዲያ ገልጿል።

    ፓርቲያቸው ማህበራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ፒኤስዲ) ባወጣው መግለጫ የአምሳ አምስት ዓመቱ ሚኒስትር እሁድ እለት መዲናዋ ኒያሙ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ መሞታቸውን አስታውቋል። የሞታቸውን ምክንያት ግን ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

    ሚኒስትሩ ለሶስት አመታት በሰራተኛ ሚኒስትርነት ማገልገላቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

    በኒጀር 755 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 37 ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

  12. ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ የክትባት ሙከራ በጤና ባለሙያዎች ላይ ልትጀምር ነው

    የክትባት ሙከራ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ የክትባት ሙከራ በጤና ባለሙያዎች ላይ ልትጀምር መሆኑን አስታውቃለች። ከዚህ ቀደም ለሳንባ ህሙማን የሚሰጠውን 'ቢሲጂ' ተብሎ የሚታወቀውን ክትባት ነው ለኮሮናቫይረስ ክትባትነት የምትሞክረው።

    በጥናቱ ላይ 500 የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ግማሹ በመርፌ መልክ 'ቢሲጂ' የሚሰጣቸው ሲሆን ግማሾቹ ደግሞ መድኃኒቱ እንደተሰጣቸው ተደርገው እንዲያስቡ ተመሳሳይ መድኃኒት ይሰጣቸዋል።

    ጥናቶች እንደሚያሳዩት በልጅነታቸው የቢሲጂ ክትባት የተሰጣቸው አስምን ጨምሮ ለመተንፈሻ ችግሮች እንደማይጋለጡ የሙከራ ክትባቱን በገንዘብ እየረዳ ያለው ድርጅት ተመራማሪ ፕሮፌሰር አንድሪያስ ዲያኮን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

    "ደቡብ አፍሪካ የተወለዱ ህፃናትን በሙሉ ቢሲጂ ክትባት ትሰጣለች። ምናልባት አዋቂዎችንም እንደገና ክትባቱን መክተብ የወረርሽኙን መዛመት ይቀንሰዋል ብለን እናምናለን" ብሏል ክትባቱን የሚያስተባብረው ግብረ ኃይል በመግለጫው

    ኮቪድ-19 የመተንፈሻ አካላትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠቃ በሽታ ቢሆንም አለም አቀፉ የጤና ድርጅት ቢሲጂ ከኮሮናቫይረስ ጥቃት ለመከላከሉ ምንም አይነት መረጃ የለም ብሏል።

    ነገር ግን ግብረ ኃይሉ ቢሲጂን ማዕከል ባደረገ የክትባት ሙከራው እንደሚቀጥልና ሲያልቅም ውጤቱን በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት እንዲገመገም እንደሚያደርጉት አስታውቋል።

    ደቡብ አፍሪካ ከሶስት ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችንም የሚያሳትፍ በቢሲጂ ላይ የክትባት ሙከራንም የማድረግ እቅድ እንዳላትም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

    ምንም እንኳን ቢሲጂ ኮሮናቫይረስን ለመፈወሱ ማስረጃ የለም ቢባልም በአለም አቀፉ ደረጃ ቢሲጂን በተመለከተ የሚደረጉ ምርመራዎች እንዲሁም ስለ ክትባቱ ለማወቅ መረጃዎች መፈለግ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጉግል አስታውቋል።

    ቢሲጂ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ለሳንባ ህሙማንም ሆነ ለህፃናት የሚሰጠው ክትባት ላይ የአቅርቦት ችግር ሊያመጣ ይችላልም የሚልም ከፍተኛ ስጋት እንዳለ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት አስታውቋል።

  13. አሜሪካ ያልታደመችበት የክትባት ጉባዔ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የትራምፕ አስተዳደር ሰኞ ዕለት በተካሄደው ለክትባት "ቃል የመግባት" ጉባዔ ላይ አልተገኘም። ይህም አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት ዓለም አቀፋዊ መሪነቱን ለመውሰድ አለመፈለጓን ያሳያል እየተባለ ነው።

    በርግጥ በጉባዔው ላይ ያልተገኘችው አሜሪካ ብቻ አይደለችም። ሩሲያም ተወካይዋን አልላከችም። በአውሮፓ ሕብረት የቻይና አምባሳደርም ቢሆኑ ስብሰባውን ቢካፈሉም ክትባቱና ሕክምናው ላይ ለሚደረገው ምርምር ለሚያስፈልገው ገንዘብ ምንም ዓይነት ቃል አልገቡም።

    የአሜሪካ ባለስልጣናት ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥትና የግል ፈንድ የኮቪድ-19 ክትባትን ለመስራት እንደሚውል ገልፀዋል።

    ነገር ግን ሁለቱ የአሜሪካና የቻይና ግዙፍ መድሃኒት አምራች ኩባንያዎችን ለብቻቸው ተጉዘው ክትባቱን ለማምረት የሚያደርጉት ጥረት ለቀሪው ዓለም ጥሩ ምልክት አይደለም።

    ይህ የአውሮፓውያን አመለካከት በሌሎች አገራትም ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ማንኛውም ክትባት እንደ ዓለም አቀፍ ንብረት መታየት አለበት ወይስ የአንድ አገርና ኩባንያ ብቻ ነው የሚለው መወያያ ሆኗል።

    በአሁኑ ወቅት ክትባቱን ለማምረት ሩጫ ላይ ያሉ ኩባንያዎች ከተስፋ ይልቅ ስጋት የሚያጭሩ እየሆኑ ነው።

    ፍርሃቱ አሜሪካ ወይንም ቻይና ክትባቱን ለቀሪው ዓለም ይከለክላሉ የሚል አይደለም።

    ከዚያ ይልቅ በመላው ዓለም በቫይረሱ ለተያዙም ሆነ አንዳይያዙ የሚያስፈልገው መድሃኒትን ለማምረት የተባበረ የምርምር ናጥናት ሥራ፣ ማምረትና ማከፋፈል ስለሚያስፈልገው ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አሜሪካ ትቅደም" መፈክር ብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሲሆን ይህ አሜሪካን ብቻ ከፊት የማስቀደም አዝማሚያ በምርጫ ቅስቃሳቸው ወቅትም ጎላ ብሎ ተደምጧል።

    ስለዚህ አሜሪካ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ክትባትና ሕክምና ምርምር ሥራዎች ላይ ከሌሎች ጋር ትተባበራለች የሚለው ጥያቄ ውስጥ ነው።

  14. በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ250ሺህ በላይ ሆነ

    በኮሮናቫይረስ የሞተ ሰው ቀብር ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty images

    ከጥቂት ወራት በፊት በቻይናዋ ውሃን ከተማ ተነስቶ አለምን ያዳረሰው ኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ250 ሺህ በላይ መድረሱን ከጆንስ ሆፕኪንስ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

    በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ3.5 በላይ መሆኑ የተመዘገበ ሲሆን ከ1̀.2 ሚሊዮን ሰዎች በላይም ከቫይረሱ አገግመዋል።

    በቫይረሱ ክፉኛ በተጠቃችው አሜሪካ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ ከ65 ሺህ ሰዎች በላይም ህይወታቸውን አጥተዋል። አሜሪካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥርም ሆነ በሟቾች ከአለም ቀዳሚዋ አገር አድርጓታል።

  15. የዘንድሮ ሁሉም የሊግ ውድድር መሰረዙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ

    እእፌ

    የፎቶው ባለመብት, ኢእፌ

    የዘንድሮ ሁሉም የሊግ ውድድር መሰረዙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

    ኮሚቴው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቼ መቆጣጠር እንደሚቻል ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ እና አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኗን ከግምት በማስገባት ቀጣይ ውድድሮች መቼ እንደሚጀምሩ ስለማይታወቅ ወድድሮቹን ለመሰረዝ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።

    በዚህም መሰረት የ2012 ሁሉም የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ የተሰረዙ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።በዚህም በየትኛውም ሊግ አሸናፊ ወይም ወራጅ የሌለ በመሆኑ ቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክል ክለብ አይኖርም ብሏል።በ2012 ሰኔ 30 ኮንትራታቸው የሚጠናቀቅ ተጫዋቾች ኮንትራት ጊዜያቸው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ክለቦች ኮንትራታቸውን እንዲያከብሩ መወሰኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

  16. በኬንያ ሶስት መድሃኒቶች በሙከራ ላይ ናቸው ተባለ

    የጤና ባለሙያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኬንያ ተመራማሪዎች ለኮሮናቫይረስ መድሃኒት ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ ሶስት መድሃኒቶች የክሊኒክ ሙከራ እስከሚደረግባቸው እየጠበቁ እንደሆነ ተገለጸ።

    ተመራማሪዎቹ ሙከራ እስከሚደረግባቸው የሚጠብቋቸው መድሃኒቶች ኢቦላን ለማከም የሚውለው ሬምደስቪር፣ የወባ መድሃኒት እና ከኤችአይቪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚውለው ሊፖናቪር ናቸው።

    ዋና ተመራማሪዋ ሎይስ አቺንግ ኦምባጎ እንደገለጹት ሙከራዎቹ የሚደረጉት ዓለማ አቀፍ ስርዓቶችን ተከትሎ ነው። የምርምር ስራውን ማን በገንዘብ እየደገፈው እንደሆን ግን የተባለ ነገር የለም።

    በተመራማሪዋ መረጃ መሰረት የአገሪቱን የመድሃኒቶች ቦርድ እንዲሁም የብሄራዊ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ካውንስል ይሁንታ እስከሚያገኙ እየጠበቁ ነው።

    በኬንያ 490 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 24 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  17. ሰበር, በኢትዮጵያ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 4 ሆነ

    Getty

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ1047 ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተካሂዶ 5 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ተብሏል።

    ከእነዚህም መካከል 3ቱ ሴቶች ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ወንዶች ናቸው።

    በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋጋጡት መካከል የ75 ዓመት ሴት አዛውንት በተጓዳኝ ህመም በሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ሲታከሙ የነበሩ እና ባጋጠማቸው የመተንፈስ ችግር ምክንያት በኮቪድ-19 ተጠርጥረው ለምርመራ ናሙና ቢወሰድም ውጤታቸው ከመታወቁ በፊት ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።

    እኚህ አዛውንት የጉዞ ታሪክ እንደሌላቸው እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ኖሯቸው እንደሆነ በመጣራት ላይ እንደሆነ በዕለታዊ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

    የጤና ሚንስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ መሠረት በቫይረሱ ከተያዙት መካከል ከጂቡቲ ተመልሰው በአፋር ክልል በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ሁለት የ25 ዓመት ወንዶች ይገኙበታል።

    የተቀሩት ደግሞ የ8 እና የ19 ዓመት ሴቶች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መሆናቸው እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው መሆኑ ተነግሯል።

  18. ኮሮናቫይረስ ሕይወቴን አትርፎልኛል

    አንጄላ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮናቫይረስ ተይዛ ሆስፒታል የገባችው ሴት በቫይረሱ መያዟ ሕይወቷን እንዳተረፈላት ገልጻለች።

    በኮሮናቫይረስ መያዟ ከተረጋገጠ በኋላ በሆስፒታል የሚገኙ ዶክተሮች የተለያዩ ምርመራዎችን ሲያደርጉላት ከዚህ በፊት የማታውቀው የልብ በሽታ እንዳለባት ማወቅ ችለዋል።

    አንጄላ ሽሌገል የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን በማሳየቷ ለ 11 ቀናት በሆስፒታል አሳልፋለች። የልብ በሽታ እንዳለባትም የታወቀው በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እያለች ነው።

    "ልቤ መስራት ባለበት ልክ እየሰራ እንዳልነበር ተነግሮኛል፤ በጊዜ ብዛት ይገድለኝም ነበር’’ ብላለች የ 36 ዓመቷ አንጄላ።

    "በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሆስፒታል መግባቴ በጊዜ ብዛት በልብ ህመም ከመሞት ቢያድነኝም ቫይረሱ በራሱ ሊገድለኝ ተቃርቦ ነበር" ብላለች።

  19. የዓለም ጤና ድርጅት ባልተረጋገጡ መድሃኒቶች ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

    ባህላዊ መድሀኒት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዓለም ጤና ድርጅት ሰዎች የኮሮናቫይረስን ይካለከላሉ በሚል በአገር በቀል እውቀት የሚሰሩና ያልተረጋገጡ ባህላዊ መድሃኒቶችን መጠቀም እንደሌለባቸው አሳስቧል።

    ድርጅቱ ይህን ማስጠንቀቂያ ያወጣው ሶስት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከኮሮናቫይረስ ያድናል የተባለለትን ባህላዊ መድሃኒት ከማደጋስካር እናስመጣለን ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

    መድሀኒቱ በሳይንሳዊ መልኩ የማዳን አቅሙ ያልተረጋገጠ ሲሆን የአገሪቱ ሜዲካል አካዳሚም ጭምር ስጋቱን ገልጿል።

    የዓለም ጤና ድርጅት በመግለጫው በባህላዊ የመድሃኒት ቅመማ ለኮሮናቫይረስ መድሃኒት ለማግኘት እየተደረገ ያለው ጥረት እንደሚያደንቅ የገለጸ ሲሆን ማንኛውም ውጤት ግን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መረጋገጥ እንዳለበት አስጠንቅቋል።

  20. በዓለማችን በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ 250ሺ ተሻገረ።

    ማስክ ያደረገች ሀውልት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በሰጠው አሁናዊ መረጃ መሰረት በመላው ዓለም ኮሮናቫይረስ ለሕይወታቸው ማለፍ ምክንያት የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከእሩብ ሚሊዮን አልፏል።

    እስካሁን ከፍተኛ ዜጋ የሞተባት አሜሪካ ስትሆን 69 ሺ ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።

    ጣልያን ለ30 ሺ የቀረበ ሰው እንደሞተ ያስታወቀች ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ወደ 29 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

    ምንም እንኳን በእነዚህ አገራት የሟቾች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም የዓለም ጤና ድርጅት የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማላላት ተገቢ አይደለም እያለ ነው።