በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ነገር ግን በኮቪድ-19 ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው። ይህም ቫይረሱ ቀስ በቀስ እግሩን በማህበረሰቡ ውስት እያስገባ መሆኑን ያሳያል። ለዚህ ግን ትልቁ መፍትሄ የሕክምና ባለሙያዎችና መንግሥት የሚሰጧቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ነው። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቤተ ክርስትያን መሄድ ያቆሙት የ89 ዓመት አዛውንት

  2. በሩሲያ በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ10ሺዎች ጨመረ

    በሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት 86 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሩሲያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለአራተኛ ቀን ከአስር ሺህ በላይ በሆኑ ሰዎች ጨመረ።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ከተመረመሩ ሰዎች መካከል 10 ሺህ 559 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የአገሪቱን ቁጥር 165,929 ማድረሱን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የተቋቋመው ቡድን ገልጿል።

    በሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት 86 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው የተመዘገበ ሲሆን ይህም የሟቾችን ቁጥር 1 ሺህ 537 አድርሶታል።

  3. ጋና በርካታ ሰዎችን እንዴት ልትመረምር ቻለች?

    ጋና

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ጋና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ እጥረት በመመልከት በአንድ መመርመሪያ በርካታ ናሙናዎችን መመርመር መጀመሯ ተገልጿል።

    ይህ የምርመራ ዘዴ “ፖል ቴስቲንግ” የሚባል ሲሆን በአንድ መመርመሪያ አስር ናሙናዎችን መመርመር ያስችላል።

    ከሚመረመሩት ናሙናዎች አንዱ ቫይረሱ ከተገኘበት እያንዳንዱ ናሙና ለየብቻው እንዲመረመር ተደርጎ የትኛው ናሙና ቫይረሱ እንዳለበት የሚለይ ይሆናል።

    ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ይህ የምርመራ ስልት በኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ትግል ውስጥ ጊዜ ቆጣቢ ሲሆን ጋናን እስካሁን ድረስ ከ100ሺህ በላይ ናሙናዎችን መመርመር አስችሏታል።

    ነገር ግን ይህ የምርመራ ዘዴ ውጤታማ የሚሆነው በጋና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ሆኖ ከቀጠለ ብቻ ሲሆን በአንዳንድ ምርመራዎችም ላይ ትክክለኛውን ውጤት ላያሳይ ይችላል ተብሏል።

    “ የዚህ የምርመራ ዘዴ ክፍተት የሚመጣው በርካታ ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው ነው፤ ያኔ እንደገና ምርመራውን ማድረግ ስለሚያስፈልግ ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል” ያሉት በኒዮርክ ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ ተመራማሪ የሆኑት ናና ኮፊ ኩዋኪ ናቸው።

    ጀርመንና ሕንድ ተመሳሳይ የሆነ የምርመራ ስልት የተከተሉ ሲሆን ይህም የመመርመር አቅማቸውን በማሳደግ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት ለመለየት ረድቷቸዋል።

    ጋና በዓለማችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው አልባ አውሮፕላኖች የኮቪድ-19 ናሙናዎችን ወደ ቤተ ሙከራ ለምርመራ ለማድረስ ተጠቅማለች።

  4. የጀርመን ቡንደስሊጋ ሊጀመር ነው

    ባር ሙኒክ ወደ ልምምድ ሜዳ ከተመለሱት መካከል አንዱ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በጀርመን በዚህ ወር የእግር ኳስ ግጥሚያው እንደሚጀምር የሚያሳይ የስምምነት ሰነድ መዘጋጀቱ ተገለፀ።

    ቡንደስሊጋው ከመጋቢትወር አጋማሽ ጀምሮ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቾች ግን ወደ ልምምድ ሜዳ ተመልሰዋል።

    ፖለቲከኞች ዛሬ በስልክ በሚያደርጉት ስብሰባ ጨዋታው መቼ መጀመር እንዳለበት ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    በስምምነቱ ላይ የተቀመጠው ቀን ቡንደስሊጋው ከአስር ቀን አልያም ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ እንዲጀምር ነው።

    በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዲቪዚዮን 36 ቡድኖች ውድድራቸውን እንዲጀምሩ ማድረግ ቡድኖቹ የሚደርስባቸውን "የምጣኔ ሃብቱን ጉዳት ለመቀነስይረዳል፤ተቀባይነት አለው" ተብሏል።

    ሮይተርስና የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ባገኙት ሰነድ መሰረት ግጥሚያዎቹ ከመጀመራቸው በፊት ለሁለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ፤ ምናልባትም በስልጠና ካምፖች ውስጥ እንዲሆኑ ይጠይቃል።

    ጀርመን እስከ መጪው ጥቅምት ወር ድረስ ትልልቅ ስብሰባዎችን ማገዷ የሚታወስ ሲሆን በዚህም የተነሳ ጨዋታዎቹ ከተመልካች ውጪ የሚካሄዱ ይሆናል።

  5. ህንድ በሌሎች አገራት እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ያሉ ዜጎቿን ልታስወጣ ነው

    ኤር ኢንዲያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ህንድ በወረርሽኙ ሳቢያ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በሌሎች አገራት የሚገኙ ዜጎቿን ለማውጣት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የሆነውን ተልዕኮ ለማሳካት ሰፊ ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡

    እነዚህን ዜጎቿን ወደ አገራቸው ለማስገባትም ከፈረንጆቹ ግንቦት 7 እስከ 13 ባሉት ስድስት ቀናት ውስጥ 64 በረራዎችን ለማድረግ አቅዳለች፡፡

    በመሆኑም በመጀመሪያው ሳምንት ወደ 12 አገራት በረራ የሚደረግ ሲሆን 15 ሺህ ህንዳውያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የአገሪቷ ሲቪል አቪየሽን ሚኒስተር ሃርዲፕ ፑሪ ማክሰኞ እለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

    አገራቱም አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሲንጋፖር፣ ኳታር እና ማሌዥያ መሆናቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡

    ነገር ግን መመለስ የሚፈልጉ ህንዳውያን የበረራ ትኬታቸውን ዋጋ ራሳቸው እንዲሸፍኑ ይጠበቃል፡፡

    ከዚህም በተጨማሪ መሳፈር የሚችሉት ምንም ዓይነት የቫይረሱ ምልክት ካልታየባቸው እንደሆነ ተነግሯል፡፡

    ዜጎቹ ሲመለሱ ምርመራም የሚደረግላቸው ሲሆን ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩም ይደረጋል ተብሏል፡፡

    ከበረራ በተጨማሪ የአገሪቷ የባህር ኃይል ጦር መርከቦችም በዚህ ሰፊ ተልዕኮ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሦስት መርከቦች እንቅስቀሴያቸው ተገድቦ የሚገኙ ዜጎችን ለማውጣት በደቡብ እስያ ወደምትገኘው ማልዲቭስ ደሴት እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተጉዘዋል፡፡

    የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ እስካሁንም 20 ሺህ ህንዳዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ይህ ተልዕኮ ውጤታማ ከሆነም በአገሪቷ ታሪክ ከጎርጎሮሳዊያኑ 1990 ወዲህ ዜጎችን ለማውጣት ከተደረጉ የዓለማችን ትልቅ እንቅስቃሴዎች አንዱ ይሆናል ተብሏል፡፡

    ህንድ በገልፍ ጦርነት ወቅት 170 ሺህ የሚሆኑ ዜጎቿን ከኩዌት ማስወጣቷ ይታወሳል፡፡

  6. በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የመናገር ነፃነት አደጋ ላይ ነው- ሂዩማን ራይትስ ዎች

  7. ኮሮናቫይረስ፡ በ14 ቀናት ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ በርካቶች ይራባሉ - ጥናት

    ሲቪል ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, ኡጋንዳ በምሽት የጣለችውን ሰዓት እላፊ ለማስከበር የሲቪል ወታደሮችን ስትጠቀም ነበር

    መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን እንዴት መከላከል እንዳለባቸው የወደፊት ፖሊሲዎቻቸውን ለመንደፍ የሚረዳ አንድ ጥናት ተካሂዷል፡፡

    በአፍሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል እና በዓለም ጤና ድርጅት በኩል የተሰራው ጥናቱ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል የሚያስከትላቸውን ችግሮች አሳይቷል፡፡

    በ20 የአፍሪካ አገራት የተሰራው ይህ ጥናት እንዳመለከተው፤ በጥናቱ ከተጠየቁ ሰዎች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ለ4 ቀናት በቤት ውስጥ መቀመጥ ቢኖርባቸው የውሃና የምግብ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ከመላሾቹ ግማሽ የሚሆኑትም ገንዘብ እንደሚያጡ ተናግረዋል፡፡

    በእርግጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በፍጥነት ምላሽ የሰጡ በርካታ የአፍሪካ አገራት አሁን ላይ ጥላዋቸው የነበሩ ገደቦችን እያላሉ ነው፡፡

    ይሁን እንጅ የሚወሰዱ እርምጃዎች የአገራቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ ከሆነ የአፍሪካ አገራት ለሰላም መደፍረስ እንደሚዳረጉ ሪፖርቱ አሳስቧል፡፡

    ለዚህም "የመንግሥትን እርዳታ የሚጠይቁ አንዳንድ ሰላማዊ ሰልፎች መበራከታቸው መንግሥታት ወረርሽኙን ለመከላከል በወሰዷቸው እርምጃዎች ሳቢያ የተፈጠሩ ችግሮችን የሚያሳዩ ናቸው" ሲሉ የጥናቱ ጸሃፊዎች ምሳሌ አጣቅሰዋል፡፡

    ምንም እንኳን በሽታውን ለመከላከል የተጣሉ ገደቦች አጠቃላይ ተቀባይነት የነበራቸው ቢሆንም መንግሥታት ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ከዜጎቻቸው ጋር መመካከር እና ገደቦቹ የተጣሉባቸውን ምክንያቶች በትክክል መናገር እንደሚገባቸው ጥናቱ መክሯል፡፡

  8. በናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ተቃውሞ አካሄዱ

    ማስክ ያደረገ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በናይጄሪያ በዋና ዋና ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ ቢጣልም የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ ነው

    በናይጄሪያ ሰሜን ምስራቅ ግዛት ጎምቤ የሚገኙ በርካታ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች የሚደረግልን እንክብካቤ በቂ አይደለም ሲሉ ከሕክምና መስጫው በመውጣት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

    ህሙማኑ የመድሃኒት እጥረትና የምግብ አቅርቦት ችግር ቅሬታ ያሰሙበት ዐብይ ጉዳይ ነው፡፡

    ማክሰኞ ምሽት በነበረው በዚህ ተቃውሞ ከማህበረሰቡ አባላት ጋር በመሆን ከዋና መዲናዋ አምስት ኪሎሜትር በምትርቀው ክዋዶን መንደር የሚገኘውን አውራ ጎዳና ዘግተዋል፡፡

    የጤና ከሚሽን ኮሚሽነር አህመድ ጋና ሊቢሲ እንደገለጹት ታማሚዎቹ ምልክት ስላላሳዩ መድሃኒት አያስፈልጋቸውም ብለዋል፡፡

    ባለሥልጣናቱ ከታማሚዎቹ የቀረበውን የምግብ አቅርቦት ችግር ቅሬታ በተመለከተም ውድቅ አድርገውታል፡፡

    ይሁን እንጅ በኋላ ላይ ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎቹን በማግባባት ወደ ህክምና ማዕከሉ ያስገቡ ሲሆን ቫይረሱ በመንደሩ ተቃውሞውን ለማየት ወጥተው ወደ ነበሩ ነዋሪዎች ተሰራጭቶ ይሆን በሚል ስጋት ገብቷቸዋል፡፡

    በመሆኑም ለተቃውሞ ከወጡ ታማሚዎች ጋር ንክክኪ ያላቸው ነዋሪዎች ለ14 ቀናት ራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ ባለሥልጣናቱ አሳስበዋል፡፡

    በናይጄሪያ እስካሁን 2ሺህ 950 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 100ዎቹ የተመዘገቡት በጎምቤ ግዛት ነው፡፡

  9. ኮቪድ-19 የአፍሪካ የዱር እንስሳት ላይ የደቀነው አደጋ

    አንበሳ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አንድ የአፍሪካን የዱር እንስሳት የሚከላከል በጎ አድራጎት ድርጅት ኮሮናቫይረስ ለዱር እንስሳት ጥበቃ አደጋ ደቅኗል አለ።

    ምንም እንኳ በአፍሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስፋት ባይከሰትም የአህጉሪቷ የቱሪዝም ኢንደስትሪ ግን ክፉኛ መጎዳቱ ተገልጿል።

    አፍሪካ በየዓመቱ ከቱሪዝም ኢንደስትሪው 30 ሚሊየን ዶላር እንደምታገኝ ይገመታል።

    ቻርሊ ሜይሂው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ከተሰረዙ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ብቻ ሁለት ሚሊየን ዶላር ማጣቱን ተናግረዋል።

    ሜይሂው እንዳሉት ድርጅታቸው በአህጉሪቱ ቀጥሮ ያሰማራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹን ለማሰናበት የተገደደ ሲሆን ሥራ የፈቱ ሰዎችም ዳግም ወደ ሕገ ወጥ አደን ይመለሳሉ የሚል ስጋት እንዳለው ገልጿል።

    "ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ ስንሰራ ካየነው ስጋት የከፋውን ነው አሁን እየተመለከትን ያለነው" ካሉ በኋላ ኮቪድ-19 አሁን በአፍሪካ ዱር እንስሳት ላይ የሚያስከትለው ጥፋት " በፍጥነት የምንቀለብሰው" እንደማይሆን እገምታለሁ ብለዋል።

  10. ላኦስ ለተከታታይ ሶስት ሳምንታት አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘሁም አለች

    ላኦስ ለተከታታይ 23 ቀናት አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው አለማግኘቷን የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ፋኦቶን ሚኦግፓክ ተናገሩ።

    በላኦስ እስካሁን ድረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 2,223 ሰዎች መካከል 19 ብቻ በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ አንድም ሞት አልተመዘገበም።

    ምንም እንኳ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም እውነታውን በትክክል ላያሳይ ይችላል እየተባለ ነው።

    ላኦስ ሰባት ሚሊየን ህዝብ ያላት ሲሆን የኮቪድ-19 ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር በጣም ትንሽ መሆናቸው ተገልጿል።

    አገሪቱ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ አስፈላጊውን ማህበራዊ ርቀት እንዲጠበቅ በማዘዝ ምግብ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ሆቴሎች ስራ እንዲጀምሩ አድርጋለች።

    ነገር ግን መጠጥ ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ የቁማር ቤቶችና የምሽት ገበያዎች እንደተዘጉ ይቆያሉ ተብሏል።

  11. አሜሪካ ለኮሮና መከላከል ያቋቋመችውን ግብረ ኃይል ልትበትን ነው

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዋይት ሃውስ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይልን ሊበትኑ መሆኑን በመግለጽ ቀጣዩ ትኩረታቸው "ጥንቃቄ እና ዳግም ወደ እንቅስቃሴ መመለስ" መሆኑን ተናገሩ።

    በአሪዞና የሚገኝ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያመርተውን ፋብሪካ ከጎበኙ በኋላ "አገራችንን ዳግም ወደ ሥራ እያስገባን ነው" ብለዋል።

    አሜሪካ በአሁኑ ሰዓት ከ20ሺህ በላይ ሰዎች በየእለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን ከአንድ ሺህ በላይ ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ይሞታሉ።

    በአሜሪካ እስካሁን ድረስ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

  12. መኪና ለመግዛት የወላጆቹን መኪና አስነስቶ የሄደው የ5 ዓመት ህጻን ተያዘ

  13. በቻይና ሁቤ ግዛት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመለሱ

    ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በተከፋፈለ ቦታ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የወረርሽኙ ማዕከል በነበረችው የቻይናዋ ሁቤ ግዛት የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

    ወሳኝ ፈተና የሚጠብቃቸው የ12ኛ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የመጀመሪያዎቹ ይሆናሉ፡፡ ጋኦካኦ የተሰኘው ይህ ፈተና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የትኛው ዩኒቨርሲቲ እንደሚገቡ የሚወሰንበት ነው፡፡

    ሁሉም የሁቤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ ነበረባቸው፡፡

    በትምህርት ቤት ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜም አካላዊ ርቀታቸውን ለመጠበቅ ሲባል በመማሪያ ክፍል ውስጥ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በማያገናኝ መልኩ በተለየ ቦታ እንደሚቀመጡም የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡

    በሌሎች የቻይና ክፍሎች አብዛኞቹ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የተመለሱት በፈረንጆቹ መጋቢት ወር ነበር፡፡

  14. 'ሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ' አግባብነት የለውም-ጃዋር መሀመድ

  15. አቅመ ደካሞችን እያማለለ የሚገኘው የማፊያዎች ገንዘብ

  16. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች?

    ማስክ ያደረጉ ሴቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቢቢሲ አማርኛ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ የተለያዩ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዘገባዎችን ወደ እናንተ ማድረሱን ቀጥሏል፡፡

    በወረርሽኙ ጭንቅ ውስጥ ባሉት የዓለም አገራት ምን አዲስ ነገር ተሰማ?

    ቢቢሲ አማርኛ ከእናንተ ጋር አለ፡፡ የትናንት ማክሰኞ ዘገባችንን ለመከታተል ወደታች ይውረዱ።

    አስተያየትና ጥቆማችሁንም በፌስቡክ ገጻችን በኩል ማድረሳችሁን አትዘንጉ፡፡

    መልካም ቆይታ ይሁንላችሁ!

  17. ሥጋው የታለ?

    ዌንዲ የፈጣን ምግቦች መደብር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ የንግድ ተቋማት በእርድ ማካሄጃ ስፍራዎች ከተከሰተ የኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሥጋ እጥረት ገጥሟቸዋል።

    ዌንዲ የፈጣን ምግቦች መደብር "ሥጋው የታለ?" በሚል መሪ ቃሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ በመላው አገሪቱ ከሚገኙ ሱቆቹ፣ 20 በመቶ መደብሮቹ የምግብ ዝርዝር ላይ በርገርን አንስቷል።

    "በምግብ ዝርዝራችን ውስጥ ከሚገኙት የተወሰኑት በወቅታዊ ሁኔታዎች ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የአቅርቦት እጥረት ገጥሟቸዋል።" ብሏል ዌንዲ የፈጣን ምግቦች መደብር በመግለጫው።

    "ይህ ለጊዜው መሆኑን እያሳወቅን በደንበኞቻችንና በምግብ ቤቶቻችን ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ጠንክረን እየሰራን ነው" ብሏል።

    ሌላው የአሳማ፣ የዶሮ፣ የበሬ ስጋ የሚያቀርበው ኮስትኮም በበኩሉ እጥረት እንደገጠመው አስታውቋል።

    እንደ አሜሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ከሆነ በ19 ግዛቶች በሚገኙ በ115 የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ውስጥ ከ 5ሺህ በላይ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

  18. በአፍሪካ ዳግመኛ የእንቅስቃሴ ገደብ ቢጣል ምን ይከሰታል?

    የፀጥታ ኃይሎች በኡጋንዳ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    መንግሥታት ወደፊት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ለማገዝ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት አገራት የገቡበትን አጣብቂኝ አሳይቷል።

    በ20 አፍሪካ አገራት የተደረገው ይህ የዳሰሳ ጥናት ላይ የተሳተፉ ሁት ሶስተኛ ሰዎች ለ14 ቀናት ከቤት ያለመውጣት የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለ የሚላስ የሚቀመስ ሊያጡ እንደሚችሉ መናገራቸው ሰፍሯል።

    ከጥናቱ ተሳታፊዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ገንዘብ እንደሚጨርሱ ተናግረዋል።

    የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠርና የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ ያሰሩት ይህ ጥናት በአፍሪካ ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል ያለውን ፈተና ኣሳይቷል።

    በርካታ የአፍሪካ አገራት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ አሁን እያላሉና እያነሱ ነው።

    ጥናቱ የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ካልተቃኙ አገራት " አለመረጋጋትና ብጥብጥ ይገጥማቸዋል" ሲል አስቀምጧል።

    በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች እንደገለፁት በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የታየው መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የሚጠይቁ ሰልፎች በአሁኑ ወቅት የተወሰደው ርምጃ ክፍተቶችን ያሳየ ነው ብሏል።

    ነገር ግን አሁን የተወሰደው የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃ በበርካታ ሰዎች ድጋፍ አግኝቷል።

    በመጨረሻም የጥናቱ አድራጊዎች የአፍሪካ መንግሥታት ከዜጎቻቸው ጋር በሚገባ መነጋገርና የሚወሰዱ እርምጃዎች ምክንያተቸው ምን እንደሆነ በተገቢው ሁኔታ ማሳወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

  19. በአውሮፓ በኮሮናቫይረስ የሟቾች ቁጥር ዩናይትድ ኪንግደም ቀዳሚ ሆነች

    በኮሮና የሞቱ ሰዎች አስከሬን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር በማስመዝገብ ከአውሮፓ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛ የነበረችው ጣልያን ነበረች።

    በዛሬው ዕለት ግን 693 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በዩኬ የሟቾችን ቁጥር 29 ሺህ 427 አድርሶታል። ይህም በጣልያን ከሞቱት 29ሺህ 315 በልጦ በአውሮፓ ቀዳሚ አድርጓታል።

    በአለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሆነ በሟች አሜሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።

  20. ሶማሊያ ከኬንያ እርዳታ ጭኖ ሲመጣ የተከሰከሰውን የአውሮፕላን አደጋ እየመረመረች ነው

    የእርዳታ እቃዎች በአውሮፕላን ላይ ሲጫን

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    ሶማሊያ ከኬንያ የኮሮናቫይረስ ሕክምና ቁሳቁስ ጭኖ ወደ ባይዶዋ እያመራ የነበረውን የኬንያ የግል አውሮፕላን አደጋ ለማጣራት ምርመራ መጀመሯን አስታውቃለች።

    በአደጋው አብራሪዎቹን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ሞተዋል።

    ፖሊስ እንዳለው ንብረትነቱ የአፍሪካን ኤክስፕረስ የሆነው አውሮፕላን ከመከስከሱ በፊት አየር ላይ እያለ በእሳት ተያይዞ ነበር።

    ባለስልጣናት አደጋው እንዴት እንደተከሰተ የሚለውን ጉዳይ አለመታወቁን ቢገልፁም ነገር ግን ተመትቶ ወድቆ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለ።

    የኬንያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ የሶማሊያ መርማሪ ቡድንን የኬንያ ባለሙያዎች እንዲቀላቀሉ ግብዣ ቀርቦላቸዋል።

    አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሁለት ኬንያውያንና አራት ሶማሊያውያን መሆናቸው ተገልጿል።

    በበርዳሌ እስላማዊው ታጣቂ ቡድን፣ አልሸባብ፣ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከተማዋና የአውሮፕላን ማረፊያው በሶማሊያ መንግሥትና የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ አካል በሆነው በኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ጥበቃ ይደረግለታል።

    የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበርዳሌ ከደረሰው አደጋ ጋር የኢትዮጵያ ጦር ግንኙነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።

    በርዳሌ ከሞቃዲሹ በሰሜን ምስራቅ 300 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት።

    የቀድሞ የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር፣ አብዲራሺድ አብዱላሂ መሀመድ፣ ለሮይተርስ የዜና ወኪል አውሮፕላኑ ተመትቶ ስለመውደቁ የአይን እማኞች እንደነገሯቸው መናገራቸው ተዘግቧል።