በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል። ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የቶተንሃም ተጨዋቾች የኮሮና ሕግን በመጣሳቸው ይቅርታ ጠየቁ

    የቶተንሃም እግር ኳስ ተጨዋቾች ሰርጅ ኦሪየር እና ሞሳ ሲሶኮ ኮሮናቫይረስን ተከትሎ የተጣለውን ገደብ በመጣሳቸው ይቅርታ ጠየቁ።

    ተጨዋቾቹ ይቅርታ ያሉት አብረው ልምምድ ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ከለቀቁ በኋላ ነበር።

    ኦሪየር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀውና በኋላ ያጠፋው ቪዲዮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አድርጎ ከሲሶኮ ጋር ጎን ለጎን ሲሮጡ ያሳያል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ለብቻ አሊያም አብረዋችሁ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ብቻ ይሁን ሲል ውሳኔ አሳልፏል።

    ተጨዋቾቹ ይቅርታቸውንም ለመግለፅ ለብሔራዊ የጤና አገልግሎት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    እንደ ጆንሆፕኪንስ መረጃ በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን 130 ሺህ 184 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 17 ሺህ 337 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  2. የበርሊን ማራቶን መቼ እንደሚካሄድ አልታወቀም

  3. በርካታ ኬንያውያን ከለይቶ ማቆያ ማምለጣቸው ተነገረ

    የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በርካታ ኬንያውያን ከአስገዳጁ ለይቶ ማቆያ ማምለጣቸውን ተናግረዋል።

    በመዲናዋ ናይሮቢ ከሚገኘው ለይቶ ማቆያ ያመለጡት እነዚህ እስርም እንደሚጠብቃቸው ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

    ግለሰቦቹ ሲያመልጡ የሚያሳየው ቪዲዮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው ፕሬዚዳንቱ በዛሬው እለት መግለጫ የሰጡት።

    በአንደኛው የለይቶ ማቆያ ማዕከል አጥሩን እየዘለሉ ሲወጡም ቪዲዮው ያሳያል።

    ፕሬዚዳንት ኡሁሩ እነዚህ ያመለጡ ሰዎች ግለሰብ ማንነት እንደሚታወቅና ተፈልገውም ወደ ለይቶ ማቆያ ማእከሉ እንደሚገቡ ቃል ገብተዋል።

    የኬንያው ሲትዝን ቴሌቪዥን እንደዘገበው ከሆነ ዝናብ እየዘነበ በነበረበት ወቅት የማዕከሉ ጠባቂዎች ፈረቃ ሲቀያየሩ ግለሰቦቹ እንዳመለጡ ነው።

    አገሪቷ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መጠጥ ቤቶች እንዲዘጉ ውሳኔን ያስተላለፈች ሲሆን ይህንንም ጥሰው የተገኙ 400 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።

    ከዚሀም በተጨማሪ አለም አቀፍ በረራዎች ከመታገዳቸው በፊት የገቡ መንገደኞችም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ከገቡ ሁለት ሳምንታት ቢያልፋቸውም አንዳንድ ማእከላት አካላዊ ርቀትን አልጠበቁም በሚል እንዳይወጡ ተደርገዋል።

    ማዕከላቱ በአግባቡ ያልተያዙ፣ ንፅህናቸው የተጓደለ እንደሆነም እየተነገረ ሲሆን በርካቶችም እዚሁ በቫይረሱ እንያዛለን የሚል ስጋት ላይ ናቸው።

  4. በጀርመን ለሁለተኛ ቀን በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጭማሪ አሳየ

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መቆጣጠር እንደቻለች የሚነገርላት አውሮፓዊቷ አገር ጀርመን፤ ለሁለተኛ ቀን በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

    ጀርመን ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 2 ሺህ 237 አዲስ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አግኝታለች።

    ባለሥልጣናቱ እንደገለፁት በጀርመን በአጠቃላይ 145 ሺህ 694 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ከእነዚህ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከበሽታው ድነዋል።

    ይሁን እንጅ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለተከታታይ ሁለት ቀናት በመጠኑም ቢሆን ጨምሯል።

    በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ አገሪቷ ጥላው የነበረውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ እርምጃ በመጠኑም ቢሆን አለዝባለች።

    በዚህም የተወሰኑ ሱቆች እንዲከፈቱና አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም ትምህርት እንዲጀምሩ ፈቅዳለች።

    በጀርመን እስካሁን 4 ሺህ 879 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል።

  5. በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሆነ

  6. ዓለማችን ከፍተኛ ረሃብ ተጋርጦባታል- የዓለም ምግብ ድርጅት

  7. ደቡብ አፍሪካ ለኮሮና የሚውል 26 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ እፎይታ መደበች

    የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምጣኔ ኃብቷ እየተመታ ያለችውን አገራቸውን ለመታደግ የ26 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ እፎይታ መመደባቸው ተሰምቷል።

    ገንዘቡም አንዳንድ ኩባንያዎች እንዳይወድቁ ለመጠበቅ እና ለሦስት ሚሊዮን ሰራተኞች ይውላል ተብሏል።

    ፕሬዚዳንቱ ውሳኔያቸውን አስመልክቶ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት የገንዘቡ መጠን የአገሪቱን 10 በመቶ አጠቃላይ ብሔራዊ ምርት (ጂዲፒን) የሚያህል ነው ብለዋል።

    ከምጣኔ ኃብት እፎይታው መካከልም ግብር ቅነሳ፣ ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍና ሥራ ለሌላቸው የሚሰጥ የገንዘብ ድጎማ ተካቶበታል።

    የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት አገሪቷ የጣለችው አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥሯን የድህነት አረንቋ ውስጥ እንደዘፈቀው ገልፀው፤ በርካቶችም በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ውሳኔው ፈታኝ መሆኑን አምነው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ማዳን እንደተቻለም አስረድተዋል።

    በአገሪቱ ውስጥ 3400 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 58 ሞቶችም ተከስተዋል። ይህንንም ሁኔታ በማየት ፕሬዚዳንት ሲሪል በወረርሽኙ የመጀመሪያዎቹ ወቅት እንደሆነች አስታውቀዋል።

  8. አሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት ልታቆም ነው

  9. የጉልት ነጋዴ በኮሮና መሞቱን ተከትሎ ህንድ ትልቁን ገበያዋን እንድትዘጋ እየተጠየቀ ነው

    በእስያ ውስጥ ካሉ የአትክትልትና ፍራፍሬዎች መሸጫ ትልቁ የሆነው ኣዛድፑር ማንዲ ገበያ ውስጥ የጉልት ቸርቻሪ በኮሮና መሞቱን ተከትሎ ሻጮች ገበያው እንዲዘጋ መንግሥትን ጠይዋል።

    የ57 አመቱ ነጋዴ የሞተው በትናንትናው እለት ሲሆን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው ሰኞ እለት መሆኑንም ሂንዱስቲያን ታይምስ ጋዜጣ አንድ ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

    ዘገባው አክሎም አትክልትና ፍራፍሬ ሲቸርችር ከነበረው ግለሰብ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎችንም የመለየትና የክትትል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስነብቧል።

    አንዳንድ ነጋዴዎች ገበያው ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ ጥያቄ ቢያቀርቡም ባለሥልጣናቱ ችላ እንዳሏቸው አስረድተዋል።

    "ባለሥልጣናቱ በገበያው ውስጥ የኮሮና ቫይረስ መዛመትን አስመልክቶ ችላ እያሉ ነው። ገበያው ቢያንስ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሊዘጋ ይገባል" በማለት አንደኛው ነጋዴ ተናግሯል።

    በህንዷ መዲና ደልሂ የሚገኘው ይህ ገበያ በቀን ውስጥ 200 ሺህ ሰዎችን ያስተናግዳል።

    ህንድ አስገዳጅ የሆነውን የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔ ገበያው ላይ ተግባራዊ ያላደረገች ሲሆን፤ በገበያው ውስጥ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ውስጥ ነው ሸማቾች እየተገበያዩ ያሉት በማለት ባለሥልጣናቱ ይከራከራሉ።

  10. የአሜሪካ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ ሁለተኛ ዙር የኮሮና ወረርሽኝ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠነቀቁ

    የአሜሪካ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ ሁለተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሁን ካለው ሊብስ እንደሚችል አስጠነቀቁ። ይህም ጉንፋን በሚከሰትበት የክረምት ወቅት ጋር አብሮ ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል።

    በበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ሮበርት ሬድፊልድ “በአገሪቷ በመጭው ክረምት ወቅት ቫይረሱ የሚያደርሰው ጉዳት አሁን እያለፍንበት ካለው የባሰ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።

    ባለሙያው አክለውም ሁለት የመተንፈሻ አካል ህመሞችን አንድ ላይ ማስተናገድ ለጤና አገልግሎት ሥርዓቱ የሚያሳድረው ተፅዕኖም ከሚታሰበው በላይ ነው ብለዋል።

    ባለሙያው እንዲህ ሲሉ ያስጠነቀቁት በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የንግድ ተቋማትን ለመክፈት መዘጋጀታቸውን ተከትሎ ነው።

    በመሆኑም መጭዎቹ ወራቶች ወደፊት ለሚመጣው የምንዘጋጅበት መሆን አለበት፤ አካላዊ ርቀትን መጠበቅም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ መክረዋል ሮበርት ሬድፊልድ።

  11. በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

  12. በሴቶች የሚመሩ አገራት ወረርሽኙን በተሳካ ሁኔታ እንዴት ተቆጣጠሩት?

  13. የአሜሪካዋ ግዛት፤ ሚዙሪ ቻይናን ከሰሰች

    የአሜሪካ ግዛት የሆነችው ሚዙሪ የቻይና መንግሥትንና ገዢውን የኮሚኒስት ፓርቲ የኮሮናቫይረስን በሚመለከት ሆን ብለው የዓለምን ህዝብ አታልለዋል በሚል ከሰሰች።

    “የቻይና መንግሥት የዓለምን ህዝብ የኮቪድ-19 ምን ያህል አደገኛና ተላላፊ እንደሆነ ዋሽቷል፣ መረጃ የሚያወጡትንም አፍኗል፤ ቫይረሱንም ለማስቆም እዚህ ግባ የሚባል ተግባር አላከናወነም” ሲሉ ተናግረዋል የሚዙሪ አቃቤ ህግ ኤሪክ ሽሚት።

    “ለዚህ ተግባራቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ብለዋል አክለውም።

    ክሱ በግዛቲቱ ለጠፋው የሰው ሕይወት፣ ለደረሰው ስቃይ እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ውድቀት ካሳ ይጠይቃል።

    ቻይና ይህንን ቀውስ በአግባቡ አልያዘችም የሚለውን ክስ አምርራ ትቃወማለች።

    ይህ የሚዙሪ ግዛት ክስ የተሰማው ቻይና ላይ ጣታቸውን የሚጠቁሙ በበዙበት ወቅት ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቅድሚያ ቻይናን ከወረርሽኙ ጋር አያይዘው አንቆለጳጵሰው የነበረ ቢሆንም እርሳቸው ለቫይረሱ የሚሰጡት ምላሽ ላይ ትችት ሲቀርብባቸው ግን ቻይናን መልሰው መውቀስ ጀምረዋል።

    የሚዙሪ ባለስልጣናት ይህንን ክስ “ታሪካዊ” ቢሉትም ሌሎች ግን ክሱ የህግና የአካሄድ እንቅፋት ይገጥመዋል በማለት አሜሪካ በእንዲህ አይነት ክስ ወቅት ለውጪ መንግሥታት የምትሰጠውን ያለመከሰስ ዋስትና በማንሳት ይከራከራሉ

  14. እንደምን አደራችሁ?

    በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ አልፏል። በኢትዮጵያም ውስጥ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 114 ሲሆን በአጠቃላይ የተመረመረውም ሰው ቁጥር 8698 ነው።

    የኢትዮጵያ የምርመራ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ የምርመራ ቁጥር እንደሚጨምርና በቀንም ከአራት እስከ አምስት ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ለመርመር እቅድ መያዙ ተገልጿል።

    የምርመራ ቁጥር መጨመርም ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ መሰራጨት አለመሰራጨቱን ለማየት ያስችላል ተብሏል።

    በሽታው ተገኘባቸው በተባሉ አካባቢዎች በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ ባህርዳርና አዲስ ቅዳም የሙቀት ልኬትና ሁኔታዎችንም የመቃኘት ስራ እየተሰራ ነው።

    አገሪቷ በበሽታው ንክኪ ነበራቸው የተባሉ ሰዎች ላይ ክትትል ማድረግ፣ ከየትኛውም ውጭ አገራት የመጡ ሰዎችን አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስገባት ስራዎችን እየሰራች ነው።

    የቫይረሱንም መዛመት ለመግታት አገሪቷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ውሳኔ በማሳለፍ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው። ስብሰባዎችን ከማገድ ጀምሮ አካላዊ ርቀቶችን መጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችንም አየተገበረች ነው።

    ቢቢሲ አማርኛ በኮሮና ቫይረስ ላይ አገራት እየወሰዱ ስላሉት እርምጃዎች፣ እየተሞከሩ ስላሉ ክትባቶች፣ ተስፋን የሚፈነጥቁ የግለሰቦች ማገገም ታሪክ እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባችን ታገኛላችሁ።