በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል። ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኤርትራ ላልተወሰነ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደቡን አራዘመች

    የኤርትራ መንግሥት የኮሮና መከላከል ግብረኃይል በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላልተወሰነ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደቡን አራዘመ።

    የኤርትራ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የ21 ቀን የእንቅስቃሴ ገደብ ያስቀመጠው ባለፈው ወር ነበር።

    ግብረ ኃይሉ በሰጠው መግለጫ የእንቅስቃሴ ገደቡን ማራዘም ያስፈለገው የሕዝቦችንና የአገሪቱን ደህንነት ለመከላከል መሆኑን ከገለፀ በኋላ ከሶስት ሳምንት በፊት ተቀምጦ የነበረው መመሪያ ተግባራዊ ሆኖ እንደሚቆይ አስታውቋል።

    የኤርትራ መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቡ የኮቪድ-19 ስርጭት መስፋፋት ያለበት ሁኔታ በሚገባ እስኪፈተሽና የሚገኘው ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ እስኪገለፅ ድረስ ይቆያል ተብሏል።

    በዚህ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ጊዜ ባለፉት ሰላሳ ቀናት ወደ ኤርትራ ከተለያዩ አገራት የመጡ 1660 ዜጎች፣ ከእነርሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው ለ21 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ይሆናል ተብሏል።

    መንግሥት አክሎም ማንኛውም በኮቪድ-19 መያዙ የተጠረጠረ ሰው አስፈላጊው ምርመራ እንደሚደረግለት ገልጾ ቫይረሱ የተገኘበት አስፈላጊውን ህክምና እንደሚያገኝ አስታውቋል።

    ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ “በዜጎች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና ይኖረዋል” ያለው መግለጫው በንግድ ላይ ለተሰማሩም ሆነ ለሌሎች ምንም አይነት ድጎማም ሆነ ድጋፍ እንደሚሰጥ አልተጠቀሰም።

    ኤርትራ በኮሮናቫይረስ የተያዙ 39 ሰዎች ማግኘቷን የገለፀች ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስድስት ሰዎች ማገገማቸው ተገልጿል።

  2. የኮሮና ህግን የተላለፉ ፖሊሶችን ሊቀርፅ ያስፈረራው ሞዛምቢካዊ ተገደለ

    በሞዛምቢክ አካላዊ ርቀትን ባለመጠበቅ እግር ኳስ ሲጫወቱ ያያቸውን ፖሊሶች እቀርፃለሁ ብሎ ያስፈራራው ግለሰብ ተገድሏል።

    ፖሊሶቹም ግለሰቡን ደብድቦ በመግደል ክስ ሊቀርብባቸው መሆኑም ተነግሯል።

    ቤይራ በምትባለው ከተማ ነዋሪ የነበረው የ44 አመቱ አብዱል ራዛቅ ፖሊሶቹን እግር ኳስ ሲጫወቱ ሲያያቸው አካላዊ ርቀታችሁን አልጠበቃችሁም በማለት ሞግቷቸዋል።

    የአካባቢው ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤስቲቪ እንደዘገበው ከሆነ እነዚህ ፖሊሶች በአካባቢው ኳስ ሲጫወቱ ያያዋቸውን ታዳጊዎች ተሰባስባችኋል በሚል በትነዋቸው ነበር ተብሏል። ከዚያም ራሳቸው እግር ኳስ ወደ መጫወት ገቡ።

    የሞዛምቢክ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኦርላንዶ ሙዱማኔ እንደተናገሩት በግድያው እጃው አለበት የተባሉት ፖሊሶች በቁጥጥር ስር እንደዋሉና በድርጊታቸውም ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም በወንጀል ድርጊታቸውም ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ገልፀው ህይወቱን ያጣው ግለሰብ ቤተሰቦችም በህጉ መሰረት ፖሊስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

    በሞዛምቢክ እስካሁን ድረስ 41 ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  3. አራት የአርሰናል ተጫዋቾች የኮሮና መመሪያን ተላልፈው ተገኙ

    አራት የአርሰናል ተጫዋቾች መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አስቦ የዋጣውን መመሪያ መጣሳቸው ተነገረ።

    አራቱ ተጫዋቾች ማህብራዊ ርቀት መጠበቅ የሚለውን መመሪያ ጥሰዋል ተብሏል።

    ዴቪድ ሉዊዝ እና ግራኒት ዣካ በለንደን በሚገኝ መናፈሻ ቦታ ቀጠሮ ይዘው ተገናኘተዋል። ኒኮላስ ፔፔ ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር ኳስ ሲጫወት ነበር። አሌክሳንደር ላካዜት ደግሞ መኪናውን ከሚያጸዳ ሰው ጎን ቆሞ ታይቷል።

    አርሰናል በጉዳዩ ላይ ከተጫዋቾቹ ጋር መነጋገሩ ተነግሯል።

    ከአርሰናል ተጫዋቾች በተጨማሪ የቶተነሃሙ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪኒሆ፣ የማንችስተር ሲቲው ካይል ዎከር፣ የአስቶን ቪላው ጃክ ግሪሊሽ እና ዋይ ሮኒ መንግሥት የጣለውን ገደብ የተላለፉ እግር ኳሰኞች ናቸው።

  4. ሰበር, በቫይረሱ ከሞቱት ግማሽ ያህሉ በእንክብካቤ ተቋማት የነበሩ ናቸው - የዓለም ጤና ድርጅት

    በአውሮፓ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው ካለፈው ግማሽ ያህሉ በእንክብካቤ ተቋማት ነዋሪ የነበሩ መሆናቸውን በአውሮፓ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡

    ዶ/ር ሃንስ ክሉጌ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ለረዥም ጊዜ በእንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ የቆዩ ሰዎችን በተመለከተ እጅግ አሳስቢ ነገር ተፈጥሯል ብለዋል።

    ዳይሬክተሩ አክለውም በአውሮፓ ከሚገኙ አገራት በተሰራ ግምት በቫይረሱ የሞቱት ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለረዥም ጊዜ በእንክብካቤ ማዕከላት ይኖሩ የነበሩ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

    ይህም ከሚታሰበው በላይ አሳዛኝ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  5. የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን በመቆጣጠር የተሳካላቸው ሴት መሪዎች

  6. የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ራሳቸውን አገለሉ

    የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን በመኖሪያቸው የሚሰሩ ግለሰብ ቫይረሱ ከያዘው ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ እንደነበራቸው በመረጋገጡ ራሳቸውን አገለሉ፡፡

    መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሯ ምርመራ እንደተደረገላቸው ገልጾ፤ እስካሁን የቫይረሱ ምልክት አልታየባቸውም ብሏል፡፡

    የ34 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር የዓለማችን ወጣት መሪ በመሆን ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የዓለምን ትኩረት አግኝተዋል፡፡

  7. በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

    በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል በሽታው ያለበት ሰው አለመገኘቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ለወረርሽኙ መርምራ የተደረገላቸውን ሰዎች አሃዝና የተገኘውን ውጤት በየ24 ሰዓቱ በሚያወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው 965 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ ሆነው ተገኝተዋል።

    በዚህ ሳምንት በተደረጉት ምርመራዎች ሰኞ እና ማክሰኞ በተመሳሳይ ሦስት ሰዎች ላይ በሽታው ሲገኝ ትናንት ደግሞ ቁጥሩ ቀንሶ ሁለት ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገልጾ ነበር።

    ከሰኞ ጀምሮ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቶ ዛሬ ሐሙስ ላይ የኮቪድ-19 ቫይረስ ማንም ላይ ሳይገኝ ሁሉም ሰዎች ነጻ ሆነዋል።

    ነገር ግን ጤና ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ይህ ውጤት 'ናሙናቸው የተወሰደ ሰዎች ቫይረሱ አልተገኘባቸው ማለት እንጂ የቫይረሱ ስርጭት ቀንሷል ማለት አይደለም' በማለት ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ከማድረግ እንዳይዘናጋ አሳስቧል።

    ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር ምርመራው የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር ትንሽ እንደሆነ ቢነገርም በየዕለቱ የኮሮናቫይረስ ምርመራና ክትትልን በተመለከተ የሚወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ምርመራ የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

    በአገሪቱ እስካሁን በጠቅላላው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 116 ሲሆን 21 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል።

    ሦስት ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ተይዘው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

  8. የቼልሲው ተጫዋች ሩደጊር ለሲዬራ ሊዮን ነጋዴዎች ጭምብል ሊገዛ ነው

    የቼልሲው ተጫዋች አንቶኒዮ ሩዲገር ገንዘብ በማሰባሰብ ለወላጆቹ ሃገር ሲዬራ ሊዮን ለሚገኙ ነጋዴዎች የአፍና አፍንጫ ጭምብል ሊገዛ መሆኑን አስታወቀ።

    ተጫዋቹ ጭምብሎቹ በከፊልም ቢሆን የበሽታውን ሥርጭት ሊገቱ እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል።

    ሩዲገር፤ የጀመረውን የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ በትዊተር ገፁ ይፋ ባደረገበት ወቅት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን 60 ሺህ ጭምብሎችን ለመግዛት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

    ጀርመን ውስጥ ከሲዬራ ሊዮናዊ ቤተሰቦች የተወለደው ሩዲገር ከሌሎች ተጨዋቾች ጋር በመሆን በሌሎችም የገቢ ማሰባሰቢያዎች ላይ እየተሣተፈ ይገኛል።

    በርሊን ውስጥ የተወለደው ሩዲገር፤ ለተወለደበት ሆስፒታል የሶስት ወራት የምግብና መጠጥ የሚሆን ገንዘብም ለግሷል።

    • በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?

      ጅቡቲ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት መካከል በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ በርካታ ሰዎች ይገኙባታል።

      ታዲያ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ መዳረሻቸው መካከለኛው ምስራቅ አገራት አድርገው ከአገር ቤት የሚነሱ ኢትዮጵያውያን ጅቡቲ መሸጋገሪያቸው ናት።

      የኮሮናቫይረስን ስርጭትን ተከትሎ የሰዎች እንቅስቀሴ በመገደቡ እና ድንበሮች በመዘጋታቸው ያለ ሕጋዊ ሰነድ የሚንቀሳቀሱት ኢትዮጵያውያን በጅቡቲ በረሃዎች ላይ መውጫ አጥተው እንደሚገኙ ተነግሯል።

      ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ኦቦክ በሚባል ቦታ ያሉበትን ሁኔታ የተመለከተው የጅቡቲ ነዋሪው አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ እንዲህ ሲል ተናግሯል።

      "ባለፈው ወር ወደ ኦቦክ ሄጄ ነበር። የአገሪቱ ፖሊስ ህገ-ወጥ ስደተኞችን እያደኑ ወደ አገር ቤት ሲመልሱ ነበር። ብዙዎቹ ከዚህ ለማምለጥ ተደብቀው ይገኛሉ። ፖሊስ ከአካባቢው ዘወር ሲል ተደብቀው የሚገኙት ስደተኞች ከያሉበት ወጥተው የሚበላ እና የሚጠጣ ይለምናሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

      የዓለም የስደተኞች ድርጅት መረጃ፤ ኦቦኮ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ይገኙ የነበሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያን ገሚሱ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን እና የተቀሩት ወደ የመን መሻገራቸውን ይጠቁማል።

    • ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለረሃብ ከተጋለጡ 5 አገራት መካከል ናት ተባለ

    • ቡንደስ ሊጋ በሚቀጥለው ወር ሊጀመር ይችላል

      የጀርመን ቡንደስ ሊጋ በሚቀጥለው ወር በመጀመር በአውሮፓ ከሚገኙ የእግር ኳስ ሊጎች ቀዳሚው ሊሆን እንደሚችል ተዘገቧል።

      የጀርመን እግር ኳስ ሊግ ምሳ ሰዓት ላይ ተሰብስቦ ሊጉ መቼ ይጀመር በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

      ሊጉ ግንቦት 8 ወይም 15 ይጀመር በሚለው ላይ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

      የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፉት ግን መራሂተ-መንግሥት አንግላ ሜርክል እና የጀርመን ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ናቸው።

      ትላልቅ የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሲቋረጡ የቤላሩስ ሊግ ግን እስካሁን እንደቀጠለ ይገኛል።

      በሌላ በኩል የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ቡድኖች ለሚቀጥለው ዘመን የአውሮፓ ውድድሮች እንዴት ያልፋሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

    • ኮሮናቫይረስ፡ የ'ቤትዎ ድረስ እናመጣለን' ቢዝነስ እየደራ ነው

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የብዙዎቻችንን የዕለተ'ለት ኑሮ እየቀያየረው ነው።

      ኮሮናቫይረስ፤ በአህጉረ አፍሪካ ከጥቂት ሃገራት በቀር ብዙም ያልተለመደውን የ'ዴሊቨሪ' ገበያ እያደራው ይገኛል።

      በናይጄሪያዋ የንግድ መዳረሻ 'ዴሊቨሪ' ከመቼውም ጊዜ በላይ እያበበ ነው። ብዙዎች እንቅስቃሴ በመከልከሉ ምክንያት ከቤታቸው ሆነው መሥራት መጀመራቸውን ተከትሎ የሚፈልጉትን ምግብና መጠጥ እንዲሁም አስቤዛ ወዳሉበት ማስላክ ጀምረዋል።

      'ደሊቨሪ' ብርቋ ያልሆነው ናይሮቢም ከመቼውም ጊዜ በላቀ የዚህ ቢዝነስ አዋጭነት እየታየባት መጥቷል።

      አዲስ አበባም ቢሆን በተለይ ደግሞ ከትንሳዔ በዓል ጋር በተያያዘ አስቤዛ ገዝተን ቤትዎ ድረስ እናመጣለን፤ ኬክ በነፃ እናደርሳለን የሚሉ ማስታወቂያዎች ማየት የተለመደ ሆኗል።

      ወረርሽኙ አኗኗራችንን እስከ ወዲያኛው ይቀይረው ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

    • ኢትዮጵያን የቢጫ ወባ ወረርሽኝ እንደሚያሰጋት የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ

    • "በጥንቃቄና በትጋት ቀጣዩን ዙር ወረርሽኝ መቆጣጠር አለብን" አንጌላ መርክል

      በጀርመን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ2 ሺህ 352 ጨምሮ 148 ሺህ 46 መድረሱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

      ከቫይረሱ ጋር በተያያዘም የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ215 ጨምሮ 5 ሺህ 94 ደርሷል።

      ይህንን ተከትሎ የአገሪቷ ቻንስለር አንጌላ መርክል የአገሪቷ ህዝቦች በጥንቃቄና በትጋት ቀጣዩን ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆጣጠሩ አሳስበዋል።

      ቻንስለሯ ለፓርላማው "የወረርሽኙ ማብቂያ ሳይሆን አሁንም መጀመሪያው ነው፤ ለረጅም ጊዜ ከወረርሽኙ ጋር ልንቆይ እንችላለን "ሲሉ ተናግረዋል።

      "የተጣሉት ገደቦች ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆኑ አውቃለሁ፤ ይህ የዲሞክራሲ ተግዳሮት ነው ፤ እርምጃዎቹ ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ይገድባሉ፤ ነገር ግን እንደ ፕረስ ነጻነት ያሉ ዲሞክራሲያዊ ግልጽነት ደግሞ ሁኔታውን ችለን እንዲንቆይ አስችሎናል" ብለዋል።

      ቻንስለሯ በዚህ ፈታኝ ወቅት ርስ በርሳቸው የሚያሳዩት መረዳዳትና መደጋገፍ አስገራሚ ነው ሲሉ የአገሬውን ሕዝብ አድንቀዋል።

      ቻንስለር አንጌላ መርክል በሚያከናውኗቸው ተግባራትም በምክር ቤት አባላቱ በተደጋጋሚ ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

    • በናይጄሪያ 200 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል

      ናይጄሪያ በቫይረሱ የተያዙ አዲስ 91 ሰዎችን አግኝታለች፡፡ ይህም በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 873 አድርሶታል፡፡

      የናይጀሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል በአንድ ቀን ከተመዘገቡት 91 ሰዎች መካከል 71ዱ የተገኙት በንግድ ከተማዋ ሌጎስ ነው ብሏል፡፡

      በከተማዋ ከ500 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የወረርሽኙ ማዕከል ሆናለች፡፡

      በዋና መዲናዋ አቡጃ ደግሞ 119 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ካኖ በተባለው ግዛት 73 ሰዎች ባቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ይህም በሰሜን ናይጀሪያ ከፍተኛው ቁጥር ነው፡፡

      የካኖ ግዛት አስተዳዳሪዎች የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሃይማኖት ትምህርት ቤቶችን እንዲዘጉ አድርገዋል፡፡

      አቡጃና ሌጎስም የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለዋል፡፡ በናይጄሪያ እስካሁን ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ከቫይረሱ አገግመው ከሆስፒታል የወጡ ሲሆን 28 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

    • የግብፃዊው ዶክተር ሰቀቀን በለንደን

      ለዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ጤና አገልግሎት [ኤንኤችኤስ] የሚሠራው ግብፃዊው ዶክተር ኑሮው በኮሮና ዘመን የሰቀቀን እየሆነበት እንደመጣ ይናገራል።

      ለንደን ለሚገኘው የቢቢሲ ራድዯ ጣብያ ድምፁን የሰጠው ዶክተር አላዲን የኮሮናቫይረስ በሽተኞችን በማከም ላይ ሳለ በሽታው ይዞት ቢሞት ቤተሰቦቹ ከእንግሊዝ ሊባረሩ እንደሚችሉ በማሰብ ፍራቻ ውስጥ እንደሆነ ያስረዳል።

      የአጣዳፊ ሕመሞች ሐኪሙ ዶክተር አላዲን ለኤንኤችኤስ ከሁለት ዓመት በላይ አገልግሏል። ቤተሰቡ እሱ ታሞ ቢሞት እንኳ ደኅንነታቸው ተጠብቆ ከሃገረ እንግሊዝ ሳይባረሩ እንዲኖሩ ነው ፍላጎቱ።

      የዶክተር ጭንቀት የሌሎች ከውጭ ሃገራት መጥተው ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎችም ጭንቀት ነው።

      ለዩናይትድ ኪንግደም ያለውን ፍቅር ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠትና የቤተሰቦቹን ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ በመጣል ከማሳየት ውጭ ምንም ማድረግ እንደማይችል ይናገራል።

      ከዶክተሩ ቃለ-ምልልስ በኋላ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የውጭ ሃገራት ዜግነት ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።

    • ኬንያ ከለይቶ ማቆያ ያመለጡ ግለሰቦችን አሠረች

      የኬንያ ፖሊስ ከለይቶ ማቆያ ያመለጡ ሁለት ግለሰቦችን ማሠሩን አስታወቀ።

      ታሣሪዎቹ ናይሮቢ ከሚገኝ አንድ ለይቆ ማቆያ ከሰሞኑ በአጥር ተንጠላጥለው ያመለጡ ናቸው ተብሏል። ከሁለቱ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎችም በርካታ ሰዎች ከለይቶ ማቆያ ማምለጣቸው ተዘግቧል።

      ሁለቱ ግለሰቦች ሮይሳምቡ በምትባል የሰሜን ናይሮቢ ቀበሌ ውስጥ ከሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት ቁጭ ብለው አልኮል ሲለጉ ነው የተያዙት ተብሏል።

      ሁለቱ ግለሰቦች የካቴና ሲሳይ ከሆኑ በኋላ ምንም ዓይነት ምርመራ እየተካሄደ ስላልሆነ ነው ለማምለጥ የወስንነው ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

      የኬንያ መንግሥት ሌሎችንም አምላጮች አሳዶ ለማሠር ቃል ገብቷል።

    • ኮሮናቫይረስንና የፀሐይ ብርሃንን ምን አገናኛቸው?

    • ኮሮናቫይረስን ድል እየነሳች ያለችው ደቡብ እስያዊት አገር ቪዬትናም

      ደቡብ እስያዊቷ አገር ቪዬትናም የኮሮናቫይረስን ወረርሽኘ ለመቆጣጠር እየወሰደች ያለችው ተግባር እጅጉን ውጤታማ አድርጓታል።

      በዚህም የአገሪቱ ባለስልጣናት ተጥሎ የሚገኘውን ጥብቅ ያለመንቀሳቀስ ትዕዛዝ እናላላለን ብለዋል።

      ባለፉት 7 ቀናት በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው በቪዬትናም ሪፖርት አልተደረገም። እስካሁን በጠቅላላው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 268 ብቻ ነው። በቫይረሱ የሞተ ሰው ደግሞ የለም።

      ቪዬትናም ይህን ማድረግ እንዴት ተቻላት?

      በቪዬትናም የመጀመሪያው በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ሪፖርት ሲደረግ የአገሪቱ ባለስልጣናት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ይጠቅማል ያሉትን ጠንካራ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አላሉም።

      ወዲያውም በረራዎች ተቋርጠዋል። ከቻይና ጋር የሚያዋሰኑ ድንበሮች ተዘግተዋል። እንዲሁም በቪዬትናም ጦርነት ጊዜ ተግባር ላይ ውሎ የነበረውን ቴክኒክ በመጠቀም ህዝቡ የኮቪድ-19 ግንዛቤ እንዲኖረው ስራዎች ተከናውነዋል።

      የቪዬትናም የጤና ስርዓት እንደ ጀርመን እና ደቡብ ኮሪያ በርካቶችን መመርመር ባያስችልም፤ ባለስልጣናት ግን ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ ማድረግ አልተሳናቸውም።

      ከላይ እስከ ታች ያለው የመንግሥት እርከን በቅንጅት መሥራቱ አገሪቱ ቫይረሱ ላይ ላስመሰገበችው ድል ትልቅ አስተዋጸዕኦ ማበርከቱም በስፋት ተንገሯል።

    • የኢንዶኔዥያዋ ግዛት አቼህ፤ በረመዳን በጋራ የሚደረግ ጸሎትን ፈቀደች

      በኢንዶኔዥያ ሰሜናዊ ግዛት አቼህ በረመዳን ወቅት የሚደረግ ጸሎትን ፈቀደች፡፡

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት መንግሥት በዚህ ዓመት ሰዎች ተሰባስበው በጋራ የሚያደርጉትን ጸሎት እገዳን በመጣስ ትናንት ምሽት የተወሰኑ መስጅዶች የታራዊሀ (ምሽት ላይ የሚደረግ የጸሎት ሥነ ስርዓት) አከናውነዋል፡፡

      የኢንዶኔዥያ የሃይማኖት ሚኒስትር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በረመዳን ወቅት ሊደረግ የሚገባው ጸሎትን በተመለከተ መመሪያ አውጥተዋል፡፡ በመመሪያው ላይ ሚኒስትሩም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከቤት ሆኖ እንዲጸልይ እና በመስጅዶች አካባቢ የሚያደርጓቸውን እንቅስቀሴዎች እንዲቀንሱ አሳስበዋል፡፡

      ይሁን እንጅ በኢንዶኔዥያ በሸሪዓ ሕግ የምትተዳደረው ብቸኛዋ ግዛት አቼህ፤ የሚገኘው ታላቁ መስጅድ በረመዳን ወቅት የሚደረገውን የታራዊህ ጸሎት ፈቅዷል፡፡

      የእምነቱ ተከታዮች የአፍና የእፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እስካደረጉ እና የራሳቸውን መስገጃ ምንጣፍ ይዘው እስከመጡ ድረስ በጋራ ሆነው መስገድ መጸለይ ይችላሉ ብሏል፡፡