በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል። ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኮሮናቫይረስ ክትባት ጀርመን ውስጥ በሰው ላይ ሊሞከር ነው

    የጀርመኑ ባዮኤንቴክ እንዲሁም የአሜሪካው ፋይዘር መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ያዘጋጁትን የኮሮናቫይረስ ክትባት በሰው ላይ ለመሞከር ፈቃድ ማግኘታቸው ተነገረ።

    የሙከራ ክትባቱ እድሜያቸው ከ18 እስከ 55 ለሆኑ 200 ጤናማ ሰዎች በመስጠት ይጀምራል።

    የጀርመን ጤና ሚኒስትር የንስ ስፓን ዛሬ እንደተናገሩት ይህ በአገራቸው የተጀመረው ለኮቪድ-19 የሚሆን ክትባት የማዘጋጀት ሥራ ውጤት እያሳየ መሆኑን አመላካች ነው።.

    "ነገር ግን ይህ ሙከራ ውጤት ለማሳየት ወራት ሊፈጅ እንደሚችል መታወቅ አለበት። ይህ ክትባት በሰውነት ላይ በመርፌ የሚሰጥ ነው፤ ስለዚህም ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው” ብለዋል።

    እስካሁን በዓለም ዙሪያ ክትባት ለመስራት ከሚደረጉት ጥረቶች መካካል የተወሰኑት ብቻ ናቸው በሰው ላይ ሙከራ እንዲደረግባቸው የተፈቀደው።

    ባለሙያዎች እንደሚሉት አስተማማኝና ዘላቂ ክትባት ለበሽታው ለማግኘት ቢያንስ አንድ ዓመት ያስፈልጋል።

    በብሪታኒያው ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎችም ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚሆን ክትባትን በሰው ላይ በዚህ ሳምንት ሙከራ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ሌሎች የክትባት ሙከራዎችም በአሜሪካና በቻይና ውስጥ እየተካሄዱ ይገኛሉ።

  2. ኮሮናቫይረስ፡ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 763 ሰዎች በቫይረሱ ሞቱ

    ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ763 ጨመረ።

    በጠቅላላው በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18 ሺህ 100 ደርሷል። ይህ ቁጥር ሆስፒታል ውስጥ እያሉ ሕይወታቸው ያለፈ እንጂ ሆስፒታል ሳይደርሱ የሞቱ ሰዎችን አያካትትም ተብሏል።

    ከ763ቱ ሟቾች መካከል እንግሊዝ ውስጥ ብቻ 665 የሟቾች ቁጥር እንደተመዘገበ የመንግሥት ሪፖርት ያሳያል።

    ስኮትላንድ 77፣ ዌልስ 15 ሰዎች መሞታቸው ሲዘገብ የሰሜናዊ አየርላንድ ቁጥር እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

  3. የዶ/ር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት የአፍና አፍንጫ ጭምብል ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

    የኮሮናቫይረስ የሌለባቸው ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ- ማስክ ማድረግ አለባቸው የለባቸውም የሚለው ርዕስ አከራካሪነቱ ቀጥሏል።

    በርካታ የዓለማችን ሃገራት የአፍና አፍኝጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን የዜጎቻቸው ግዴታ እያደረጉ ነው።

    ለምሳሌ ጀርመን ውስጥ የአፍና አፍንጫ ጭምብል ሳያደርጉ መንቀሳቀስ ክልክል ነው። ኬንያ ጭምብል ያላደረጉ ሰዎችን በገንዘብ እቀጣለሁ ብላለች።

    ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት በአፍና አፍንጫ ጭምብል ዙሪያ ምን ይላል?

    ድርጅቱ በቅርቡ ካደረገው ስብሰባ በኃላ የአፍና አፍንጫ ጭምብል በተለይ ደግሞ ለሕክምና ባለሙያዎች ተብለው የሚሠሩ ጭምብሎች በባለሙያዎች ብቻ ነው መደረግ ያላባቸው የሚል አቋም ይዟል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ሆስፒታል ኃላፊዎች መንግሥት ዜጎች የአፍን አፍንጫ ጭምብል እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ከሆነ ሐኪሞች ጭምብል ያጣሉ ሲል አሳስቧል።

  4. ከሩስያ ጋር ድንበር የምትጋራው የቻይና ከተማ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

    ከሩስያ ጋር የምትዋሰነው የቻይና ከተማ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ገደብ ጥላለች።

    ሃርቢን የተሰኘችው ከተማ ነዋሪዎች ለአስፈላጊ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከቤት ንቅንቅ እንዳይሉ ስትል ገደብ ጥላለች።

    ገደቡ ዉሃን የተሰኝችው ከተማ መስከረም ወር ጥላ ከነበረው ገደብ ጋር ተመሳሳይነት አለው ተብሏል።

    መገናኛ ብዙኃን የሃርቢን ከተማ አስተዳደር ማንኛውም ሰው ወደ ከተማዋ እንዳይገባ እንዲሁም እንዳይወጣ ማዘዙን እየዘገቡ ነው።

    ነዋሪዎች የአፍ አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ እንደማይችሉና የሙቀት መጠናቸውን የመለካት ግዴታ እንዳለባቸውም ተነግሯቸዋል።

    ሃርቢን ውስጥ አሁን 52 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል።

    ትላንት 4016 ሰዎች ተመርምረው ሁለት ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው መረጋገጡን የቻይና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያ ዘግቧል።

    ግለሰቦቹ ቫይረሱ የያዛቸው ኒው ዮርክ ከተሰኘችው የአሜሪካ ግዛት ከተመለሰ ተማሪ መሆኑንም ዘገባው አትቷል።

  5. ሞሮኮ፡ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ሺዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

    የሞሮኮ ፖሊስ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 3 ሺህ ሰዎችን አሠረ።

    ግለሰቦቹ የታሠሩት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የወጡ ሕጎችን በመተላለፋቸው ነው።

    የሞሮኮ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያ ቢያንስ ግማሽ ያክሉ ተለቀዋል፤ የተቀሩት ግን ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ሲል ዘግቧል።

    ሞሮኮ ባለፈው ወር አጋማሽ ቫይረሱን ለመግታት ከቤት አለመውጣትና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ነው ብላ ካወጀች ወዲህ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ሕጉን ተላልፈው ታሥረዋል።

    ሃገሪቱ እስካሁን 3337 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ይፋ አድርጋለች። ይህም በአፍሪካ ሶስተኛው ከፍተኛ ቁጥር ያላት ሃገር ያደርጋታል።

  6. የደቡብ አፍሪካዋ ሚኒስትር የኮሮና ሕግ መተላለፋቸውን አመኑ

    የደቡብ አፍሪካ ኮሚኒዩኬሽን ሚኒስትር ስቴላ ንዳቤኒ ከቤት አትውጡ የተባለውን ሕግ መተላለፋቸውን አምነው፤ ቅጣቱን ለመክፈል ተስማሙ።

    ሚኒስትሯ ሕጉ በሚያዝው አንድ ሺህ ራንድ [1700 ብር ገደማ] ቅጣታቸውን እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል።

    ብሔራዊው ሕግ አስፈፃሚ መሥሪያ ቤት ኃላፊ፤ የሚኒስትሯ የፍርድ ሂደት ማንም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አልፎም ማንም ሕግ ሊጥስ እንደማይገባ አሳስበዋል።

    ሚኒስትሯ፤ የቀድሞ የሥራ ባልደረባቸው ቤት ምሳቸውን ሲበሉ በመታየታቸው ነው የተከሰሱት። በወቅቱ መንግሥት ከቤታችሁ አትውጡ የሚል አዋጅ ካፀደቀ ቀናት አልተቆጠሩም ነበር።

    የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሚኒስትሯን ቢሯቸው ድረስ አስጠርተው ከገሰጿት በኋላ የሁለት ወር አስገዳጅ እረፍት እንድትወጣ አስደርገዋል።

    ሚኒስትሯ የፈፀሙት ተግባር ያልተገባ መሆኑን አምነው በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

  7. ሕንድ፡ 'ዶክተር የተተናኮሰ 7 ዓመት ይታሰራል'

    የሕንድ መንግሥት ዶክተሮችና ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎችን በፅኑ ሊቀጣ መሆኑን አስታውቋል።

    ቅጣቱ እስከ 7 ዓመት እሥር ሊደርስ እንደሚችል ነው መንግሥት ያወጣው አዲስ ሕግ የሚያሳየው።

    ሕንድ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ተያዦች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለማሰስ መንደር ለመንደር የሚዘዋወሩ የጤና ባለሙያዎች ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ይዘገባል።

    ቫይረሱ ከጤና ባለሙያዎች ይደርስብናል ያሉ ሕንዳውያን ሐኪሞችን ማሳደድ መጀመራቸውም ተነግሯል።

    ይህን ተከትሎ ዕለተ ረቡዕ የወጣው አዲስ ሕግ አጥፊዎች የ6500 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ጨምሮ እሥር ሊፈረድባቸው እንደሚችል ያትታል።

  8. 'በኮሮና ምክንያት በርካቶች የካንሰር ምርመራ እያደረጉ አይደለም'

    ካንሰር ሪሰርች ዩኬ የተሰኘ አንድ ድርጅት በኮሮቫይረስ ምክንያት በርካታ ሰዎች የካንሰር ምርመራ ማድረግ አልቻሉም ብሏል።

    የእርዳታ ድርጅቱ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ በሳምንት 200 ሺህ ሰዎች የካንሰር ምርመራ ያደርጉ ነበር፤ አሁን ቁጥሩ እጅግ ቀንሷል ሲል ጥናቱን ይፋ አድርጓል።

    በስኮትላንድ፣ ዌልስና ሰሜናዊ አየርላንድ የካንሰር ምርመራ በይፋ ተቋርጧል። እንግሊዝ ውስጥ ደግሞ የመመርመሪያ ጣብያው በአግባቡ ሥራውን እየሠራ አይደለም ሲል ድርጅቱ አስታውቋል

    አልፎም የድርጅቱ ጥናት እንደሚያሳየው በኮቪድ-19 ሥርጭት ፍራቻ ምክንያት የካንሰር ሕክምናዎች በአግባቡ እየተካሄዱ አይደለም።

    የድርጅቱ ሠራተኛ የሆኑት ፕሮፌሰር ቻርልስ ስዋንቶን ሆስፒታሎች ውስጥ 'ከኮቪድ-ነፃ' የሆነ ከባቢ ካልተፈጠረ ሁኔታው አስጊ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  9. የኔዘርላንድስ የጤና ባለሙያዎች የገንዘብ ጉርሻ ሊያገኙ ነው

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከፊት ሆነው ከሚዋጉት የጤና ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ናቸው።

    አውሮፓዊቷ ኔዘርላንድስ፤ የቫይረሱን ስርጭት በመግታት ረገድ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት የጤና ባለሙያዎች የገንዘብ ጉርሽ እንደሚያገኙ አስታውቃለች።

    የፋናይንስ ሚንስትሩ ዎፕኬ ሆከሰትራ የጤና ባለሙያዎች እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ ከጭብጨባ የዘለለ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

    የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚሰሩ ባለሙያዎች የገንዘብ ጉርሻ ይሰጣቸው የሚለው ሃሳብ ከአንድ ወር በፊት በኔዘርላንድስ ፓርላማ መነጋገሪያ ነበር።

    ለባለሙያዎቹ ገንዘቡ እንዲሰጥ ይወሰን እንጂ መጠኑ አልታወቀም።

  10. ደቡብ አፍሪካ ቤት የመቀመጥ ውሳኔን ለማስከበር 70 ሺ ተጨማሪ ወታደሮችን አሰማራለሁ አለች

    ደቡብ አፍሪካ አስገዳጅ ቤት የመቀመጥ ውሳኔን ለማስከበር 70 ሺ ተጨማሪ ወታደሮችን ልታሰማራ መሆኑን የሃገሪቱ ሚዲያ ኤስኤቢሲ ዘግቧል።

    የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጆን ስቴንሁዜይን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለፓርላማ የፃፉትን ደብዳቤ በትዊተር ገፃቸው ያጋሩ ሲሆን፤ በደብዳቤውም መሰረት 73 180 ወታደሮች ይሰማራሉ ተብሏል።

    በአገሪቷ ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጠቀሰው ደብዳቤው የኮሮናቫይረስ ስርጭትንም ለመግታት ጥብቅ የሆነ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሷል።

    ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያ ቤት የመቀመጥና ከማንኛውም እንቅስቃሴ መገደብን የሚያስፈፅሙ ሶስት ሺ ያህል ወታደሮችን ማሰማራት መፍቀዳቸው የሚታወስ ነው።

    በእግር መራመድ፣ መሮጥ ሆነ ማንኛውም እንቅስቃሴ፣ መጠጥ ሽያጭ ሙሉ በሙሉ በተከለከለባት ደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ኃይሎች እነዚህን እርምጃዎች ማስከበር ሲሳናቸው ታይቷል።

    መከላከያ ሚኒስትሯ ኖሲቪዌ ማፒሳ ናኪላም በበኩላቸው "የቫይረሱ መዛመት በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ከዚህም በበለጠ የወታደር ኃይል ማሰማራታችን አይቀርም" ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የአገሪቱን ሚዲያ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

    በደቡብ አፍሪካ 3ሺ 465 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ 58 ሰዎችም ህይወታቸው አልፏል።

  11. በስፔን በኮሮና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨመረ

    ስፔን ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች መካከል 435 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጋለች።

    ይህ ቁጥር ትናንት ከነበረው በመጠኑ ከፍ ያለ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን እስካሁን በአገሪቱ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 21,717 ደርሷል።

    ስፔን እስከ መጪው ግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጇን አራዝመዋለች።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ከዚህ ቀን በኋላ በአገሪቱ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ቀስ በቀስ እንደሚከፍቱት አስታውቀዋል።

    " ወረርሽኙ እንዴት እንደሚሄድ እያየን የምንወስን ይሆናል" ነው ያሉት።

    በስፔን እስካሁን ድረስ 205,000 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በዓለም ላይ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት ሁለተኛዋ ያደርጋታል።

  12. በቦትስዋና ከፍተኛ የጤና ኃላፊዎች ተባረሩ

    የቦትስዋናው ፕሬዚዳንት ሞክግዌትሲ ማሲሲ የጤና ምክትል ሚኒስትሩን እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ቋሚ ፀሐፊ ከሥራ ማባረራቸው ተሰምቷል።

    የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት በሆነበት ወቅት ከሥራ ለምን እንደተባረሩ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

    ሆኖም ሁለቱም የሥራ ኃላፊዎች በትናንትናው ዕለት መባረራቸውን ከመንግሥት የወጣው መግለጫ አትቷል።

    አገሪቷ የኮሮና ቫይረስን ለመግታት አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔንም ለሃያ ስምንት ቀናት ያህል አሳልፋለች።

    በቦትስዋና ውስጥ እስካሁን ባለው መረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 20 ሲሆን የአንድ ሰው ህይወት አልፏል።

    በምክር ቤት ውስጥ ትሰራ የነበረች አንዲት ነርስ በኮሮና መያዟንም ተከትሎ ሁሉም የምክርቤቱ አባለት ለአስራ አራት ቀናት ያህል በለይቶ ማቆያ እንዲገቡም ተወስኗል።

  13. በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች መካከል እስካሁን ድረስ 21 ሰዎች አገግመዋል

    በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጡት 116 ሰዎች መካከል አምስት ተጨማሪ ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው ቁጥራቸው 21 መድረሱ ተገለጸ።

    ከወረርሽኙ ያገገሙት አምስቱ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማዕከል ውስጥ የቆዩ ሲሆን አራቱ ከአዲስ አበባ አንዱ ደግሞ ከድሬዳዋ መሆናቸው ተጠቅሷል።

    ኢትዮጵያ እስካሁን በየዕለቱ ታደርግ የነበረውን የኮሮናቫይረስ ምርመራ መጠን ከፍ አድርጋ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ሰዎች ላይ ምርመራ በማድረግ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውም ተረጋግጧል።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሌሎቹ ቀናት በተለየ የቫይረሱ ምርመራ የሚደረግላቸው ሰዎች ከፍ ብሎ 1023 የደረሰ ሲሆን በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም ሁለት መሆኑ ተገልጿል።

    ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከተገለጸበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ሲመረመር ይህ የመጀመሪያው ነው።

    በቫይረሱ ከተያዙት ሁለት ሰዎች መካከል አንደኛው በአፋር ክልል ገዋኔ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ የውጪ ጉዞ ታሪክ የላቸውም ተብሏል።

    በቫይረሱ እንዴት ሊያዙ እንደቻሉ እየተጣራ መሆኑን መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል።

    ሌላኛው በሽታው የተገኘባቸው ግለሰብ ግን ከአሜሪካ የመጡና በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደነበሩ ተገልጿል።

  14. የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የኮሮና ምርመራ ውጤታቸውን እየተጠባበቁ ነው

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን የኮሮናቫይረስ የምርመራ ውጤታቸውን እየተጠባበቁ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርመራ የተደረገላቸው ቫይረሱ ከተገኘበት አንድ በጎ አድራጎት ቡድን መሪ ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ከታወቀ በኋላ ነው።

    የጤና ባለሥልጣናት ትናንት ናሙና የወሰዱ ሲሆን የምርመራ ውጤቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ እንደሚታወቅ የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለጋሹ ግለሰብ ጋር የተገናኙት ባለፈው ሳምንት ሲሆን፤ በወቅቱ አገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት ገንዘብ ለመለገስ ቼክ ሰጥተዋቸው ነበር።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ካህን ባለፉት ቀናት የሚንስትሮች ስብሰባን ጨምሮ በርካታ ስብሰባዎች እንዳካሄዱም ተነግሯል።

    በፓኪስታን እስካሁን ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ መዳናቸው ይታወሳል።

    እንዲሁም የካናዳ ፕሬዚደንት ጀስቲን ትሩዶ ባለቤታቸው በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ራሳቸውን አግልለው ነበር።

  15. በሲንጋፖር ከ10,000 ሰዎች በላይ በኮቪድ-19 ተያዙ

    በሲንጋፖር በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10ሺህ በለጠ።

    ይህ የሆነው በዛሬው ዕለት በቫይረሱ መያዛቸውን የተረጋገጡ 1016 ሰዎችን ጨምሮ ነው ተብሏል።

    በደቡብ ምስራቅ እስያ ካሉ አገራት በሙሉ ሲንጋፖር በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎች ይገኙባታል።

    በሲንጋፖር በቫይረሱ የተያዙ አብዛኞቹ ሰዎች የውጪ አገር ሰራተኞች ሲሆኑ በአንድ ላይ በጋራ መኖሪያ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ተብሏል።

    ከዚህ በፊት ቫይረሱን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል መልካም ምሳሌ በመባል የተጠቀሰችው ሲንጋፖር፣ አሁን ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣልና በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማሸግ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየሞከረች ነው።

    በሲንጋፖር ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎች ይህ ለምን ቀድሞውንም አልተደረገም ሲሉ ይተቻሉ።

    የሲንጋፖር መንግሥት በርካታ ሰዎችን እየመረመረ ሲሆን ጤነኛ የሆኑ ሰራተኞችን እያስወጣ ነው።

    ነገር ግን አሁንም በጋራ መኖሪያዎች ውስጥ የሚኖሩ የውጪ አገር ሰራተኞች በቫይረሱ እንያዛለን የሚል ፍራቻ እንዳላቸው እየገለፁ ይገኛሉ።

  16. አር ኬሊ "ክሴን በውጪ ልከታተል" ሲል ያቀረበው ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ

    ድምጻዊ አር ኬሊ ከእስር ተለቅቆ ክሱን በውጪ እንዲከታተል ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገበት።

    አር ኬሊ በኒውዮርክና ቺካጎ በተመሰረተበት የወሲብ ትንኮሳ ክስ የፍርድ ቀጠሮውን በእስር ቤት በመሆን እየተጠባበቀ ይገኛል።

    አር ኬሊ የታሰረው በቺካጎ ሲሆን ያለበት ማረሚያ ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችና እስረኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል።

    አር ኬሊ ለጤንነቱ በመስጋት እንዲለቀቅ የጠየቀ ቢሆንም ከእስር ቢፈታ ሊጠፋ አልያም ምስክሮችን ሊያስፈራራ ይችላል በማለት ማመልከቻው ውድቅ ተደርጎበታል።

    ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በእስር ላይ የሚገኙ በርካታ ታዋቂ ሰዎች፣ ቢል ኮዝቢን ጨምሮ በማመልከቻቸው ላይ ኮሮናቫይረስ ለጤናቸው ስጋት መሆኑን በመግለጽ ጉዳያችንን በውጪ ሆነን እንከታተል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

    የዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ ጠበቃ ማይክል ኮኸን እና ራፐሩ ቴካሺ በቤታቸው በመሆን የእስር ጊዜያቸውን እንዲያጠናቅቁ ከተወሰነላቸው ሰዎች መካከል ይገኙበታል።

    • በናይጄሪያ 30 የእግር ኳስ ተጫዋቾች የእንቅስቃሴ ገደቡን በመተላለፍ በቁጥጥር ስር ዋሉ

      የናይጄሪያ ፖሊስ በካኑ ግዛት 30 እግር ኳስ ተጫዋቾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገለፀ።

      እነዚህ የእግር ኳስ ፍቅር ያሳበዳቸው ወጣቶች በአገሪቱ የተጣለውን የመንቀሳቀስ ገደብ ቸል ብለው ጨዋታዎችን አዘጋጅተዋል፤ ተጫውተዋልም ተብሏል።

      የናይጄሪያ ዜና ኤጀንሲ (ናን) እንደዘገበው እግር ኳስ ተጫዋቾቹ በግዛቲቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የተጫወቱ ሲሆን ደጋፊዎቻቸውም ተሰብስበው ሲመለከቷቸው ነበር።

      ተጫዋቾቹ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ይህንኑ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርተዋል።

      የካኖ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ የሆኑት አብዱላሂ ሃሩና እንዳሉት ተጫዋቾቹ የተያዙት ግጥሚያ ካደረጉ በኋላ ነው።

      እንደ ዜና ኤጀንሲው ዘገባ ከሆነ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመተላለፍ ይከሰሳሉ።

      በካኖ ግዛት ለሰባት ቀናት ያህል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል። በአሁኑ ሰዓት በናይጄሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ 73 ሰዎች ተገኝተዋል።

    • አሜሪካ ለቀጣዮቹ 60 ቀናት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት ልታቆም ነው

      ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአሜሪካ ለቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚያመለክቱ የውጭ ዜጎች መቀበል ማቆማቸውን ተናገሩ።

      ፕሬዝዳንቱ አሻሚ የሆነ ትዊታቸውን ከጻፉና እርምጃቸውን ካሳወቁ በኋላ ውሳኔው የአሜሪካውያንን ሥራ ይታደጋል ብለዋል።

      አብዛኛዎቹ የቪዛ ጥያቄዎች በወረርሽኙ ምክንያት ቀድመው የተቋረጡ በመሆኑ አሁን ይህ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን የታወቀ ነገር የለም።

      የፕሬዝዳንቱ ተቺዎች ግን ዶናልድ ትራምፕ የቫይረሱን ወረርሽኝ ምላሽ የሰጡበት መንገድ ስላስተቻቸው ትኩረት ለመስረቅ ያደረጉት ነው ብለዋል። ተጨማሪ ለማንበብ ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ ለቀጣዮቹ 60 ቀናት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት ልታቆም ነው

    • ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመመከት አሜሪካ እና ቻይና ሲነጻጸሩ

    • ፌስቡክ ከእንግሊዛውያን የጤና መረጃ ሊሰበስብ ነው