ኮሮናቫይረስ፡ በታንዛኒያ የተቃዋሚው መሪ 'ለዜጎች የሀሰት ተስፋ መስጠት' እንዲቆም አሳሰቡ
በታንዛኒያ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዚቶ ካብዌ በአገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተዛመተ ባለበት ሰዓት መንግሥት ለዜጎች የማይሆን ተስፋ መስጠቱን ማቆም አለበት ሲሉ አሳሰቡ፡፡
መሪው አክለውም ዜጎች የወረርሽኙ ትክክለኛ ምንነት ሊነገራቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በታንዛኒያ ትንናት ብቻ በቫይረሱ የተያዙትን 30 ሰዎች ጨምሮ እስካሁን 284 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ 10 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃሲም ማጃሊዋ ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ዜጎች መንግሥትንና የጤና ባለሙያዎች የሚሉትን ማመን እንዳለባቸው ትናንት አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትሩ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ጥብቅ እገዳዎችን ከማሳለፍ በፊት መንግሥት በቅድሚያ ሊያጤነው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በታንዛኒያ እስካሁን ሃይማኖታዊ ስብሰባዎችን ማድረግ አልተከለከለም፡፡
እንዲያውም ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ “ኮሮናቫይረስ በክርስትና ውስጥ አይኖርም በመሆኑም ቤተክርስቲያን እንሂድ፤ በርትተን እጸልይ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡