የእስልምና እምነት ተከታዮች ላልተለመደው የረመዳን ጾም ወር እየተዘጋጁ ነው
የረመዳን ወር ሊጀምር የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው። በዓለም ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች ይህንን ወር አገራት ከጣሉት የእንቅስቃሴ ገደብና ማህበራዊና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አንጻር እንዴት አድርገው ማሳለፍ እንዳለባቸው እያሰቡ ነው።
በረመዳን ወር ቀን ሲጾም ተውሎ ማታ ከቤተሰብና ከሌሎች ሙስሊም ወገኖች ጋር ሰብሰብ ብሎ ማፍጠር የተለመደ ነው። በርካቶች ምሽቱን አልያም ለሊት በጋራ የሚደረግ የፀሎት ስነስርዓትን ለመካፈል በመስጂዶች ይገኛሉ።
ይህ ዓመት ግን እንደ ከዚህ በፊት እንደነበሩት ረመዳኖች ያለ አይደለም።
በርካታ የሙስሊም አባቶችና ባለስልጣናት በረመዳን፣ ህዝበ ሙስሊሙ ከቤቱ ሆኖ እንዲፀልይ እና የአካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለሳምንታት መካ ጭር ብሎ ታይቷል።
በመካ ታላቁ መስጂድ ሙዘይን የሆኑት አሊ ሙላ መካን ያለ አማኘቹ ግርግር ሲመለከቱ " ልባችን ያለቅሳል" ሲሉ ተናግረዋል። " ቅዱሱ መስጂድ ቀን ማታ በሰዎች ተጨናንቆ ነበር የምናውቀው፤ አሁን ግን እንዲህ በመሆኑ ውስጤ ተሰብሯል"