በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሆነ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል።ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ለኡጋንዳ የሕዝብ እንደራሴዎች ኮሮና መከላከል ዘመቻ የተመደበው ገንዘብ ታገደ

    የኡጋንዳ ፍርድ ቤት የሕዝብ እንደራሴዎች በተመረጡበት ስፍራ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት እንዲረዳቸው በሚል የተመደበላቸውን 2.6 ሚሊዮን ዶላር አገደ።

    እያንዳንዱ የሕዝብ ተወካይ 5,300 ዶላር ይቀበላል ተብሎ የነበረ ሲሆን ፤ከዚህ በተጨማሪም በተመረጡበት ስፍራ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ሲንቀሳቀሱ ለሚጠቀሙበት መኪና ነዳጅና ለሹፌር የሚከፈል አበል ይሰጣቸው ነበር ተብሏል።

    ይህ ውሳኔ እንደተሰማ ኡጋንዳውያን ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን 'በኦንላይን' ፊርማ አሰባስበዋል። አክለውም በርካቶቹ የሕዝብ እንደራሴዎች በቤት የመቀመጥ ገደቡ የተነሳ ወደተመረጡበት አካባቢ እንዳልሄዱ ገልፀዋል።

    ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባላት ማክሰኞ እለት ከፍርድ ቤት የተመደበውን ገንዘብ እግድ ማግኘት መቻላቸው ታውቋል።

    ይህንን በማስመልከት የአገሪቱ ጋዜጣ ዴይሊ ሞኒተር በትዊተር ገፁ ላይ አስነብቧል።

  2. ለሕክምና ከሄዱበት ሕንድ መመለስ ያልቻሉ ኢትዮጵያዊያን ችግር ላይ ነን አሉ

  3. "የኮሮናቫይረስ ከአገሪቱ በመጥፋቱ አምላክን እናመሰግናለን" የሞሪታንያ ጤና ሚኒስትር

    በሞሪታንያ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል የመጨረሻው ህመምተኛ ማገገም ተከትሎ በተከታታይ ሁለት ቀናት ምርመራ ብታደርግም በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው እንደሌለ አስታውቃለች።

    በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሞሪታንያ ሰባት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበረ ሲሆን፤ አንደኛው ህይወቱ ሲያልፍ ስድስቱ ደግሞ አገግመዋል።

    የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ምንም እንኳን ሁሉም ህመምተኞች ከበሽታቸው ቢያገግሙም ለአስራ አራት ቀናት ያህል በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ይደረጋሉ ተብሏል።

    ይህም ሁኔታ በሽታው የሚዛመትበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድና ፍፁም እርግጠኛ ለመሆን ነው ተብሏል።

    ቅዳሜ እለት የጤና ሚኒስትሩ "ቫይረሱ በአገሪቱ በመጥፋቱ አምላክን እናመሰግናለን" በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ሞሪታንያ በኮሮና የተያዘ ሰው መኖሩን ያረጋገጠችው ከአንድ ወር በፊት ነበር።

    ይህንንም ተከትሎ በሳምንቱ አገሪቱ የሰአት እላፊ አወጀች እንዲሁም አለም አቀፍ በረራዎችን በሙሉ አገደች።

  4. ኢኳዶር፡ በኮሮናቫይረስ መቅሰፍት የተመታችው አገር

    በኢኳዶር በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች አስክሬን በየመንገዱ እየተጣለ ነው።

    በኢኳዶሯ ትልቋ ከተማ ጉዓያኪል ነዋሪዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ዘመዶቻቸውን ሳይቀብሩ ለቀናት መቆየት ግድ ሆኖባቸዋል።

    የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ መንግሥት የሚሞቱ ሰዎችን አስክሬን ለመቅብር ከአቅሙ በላይ ሆኗል።

    ባሳለፈው ሳምንት በኢኳዶር ጓያኩል ከተማ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች አሰክሬን በየመንገዱ ተጥሎ የሚያሳይ ምስል የበርካቶችን ትኩረት ስቦ ነበር።

  5. በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች ተገኙ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተጨማሪ ሰዎች ተገኙ። ይህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ወደ 114 ከፍ አድርጎታል።

    የጤና ጥበቃ ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደስ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ745 ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ መደረጉን በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

    በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሦስቱም ወንዶች መሆናቸውን እና ከሦስቱ አንዱ የቻይና ዜግነት ያለው ነው።

    ቻይናዊው የሰበታ ነዋሪ የሆነ እና የጉዞ ታሪክ እንዳልነበረው ጤና ሚንስትሯ የተናገሩ ሲሆን ቻናይዊው እንዴት ለቫይረሱ እንደተጋለጠ እንደሚጣራ በመግለጫው አሳውቀዋል።

    ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ከሳኡዲ አረቢያ የተመሰለ እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የቆየ መሆኑን እና አንዱ ኢትዮጵያዊ ደግሞ በሥራ ባህሪው ምክንያት ለቫይረሱ ተጋላጭ ነው ሲሉ የጤና ሚንስትሯ አስታውቀዋል።

  6. ኢንዶኔዥያ በረመዳን በቡድን የሚደረጉ ጉዞዎችን ከለከለች

    የኢንዶኔዥያ ፕሬዚደንት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ረመዳንን ተከትሎ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በቡድን የሚያደርጉትን ጉዞ አገዱ፡፡

    ውሳኔው የዘገየ ነው ሲሉ በአንዳንድ ባለሙያዎች ትችት ገጥሞታል፡፡

    ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ውሳኔው ከመተላለፉ ቀድሞ ከጃካርታ ወደ ትውልድ ቀያቸው ሄደዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

    አብዛኞቹ ወደ ትውልድ ቀያቸው የሄዱት የረመዳን ጾም ከሚጀመርበት ከዚህ ሳምንት ቀድሞ ነው፡፡

    በብዛት የእስልምና እምነት ተከታዮች ያሏት ኢንዶኔዥያ፤ በኢድ አል ፈጥር በዓል ወቅት ‘ሃላል ቢ ሃላል’ የሚባል የተለየ ዝግጅት ይደረጋል፡፡

    በዚህ ዝግጅት ላይ በርካታ ሰዎች ተሰባስበው ይቅርታ ይጠያየቃሉ፡፡ በመሆኑም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዳይሄዱ ማገድ ለአብዛኛው ሙስሊም ማህበረሰብ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡

    ዘንድሮ ግንቦት መጨረሻ አካባቢ ይውላል ተብሎ በሚጠበቀውና በኢድ በዓል ወቅት የእግር ኳስ መጫዎቻ ሜዳዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች እና የተለያዩ መንገዶች ተሰባስቦ ጸሎት ለማድረስ ወደ መስጅድነት ይቀየራሉ፡፡ በዚህ ሥነ-ስርዓት ላይም በርካቶች አዳዲስ የጸሎት ልብሶቻቸውን ያስተዋውቁበታል፡፡

    ይሁን እንጅ የጤና ባለሙያዎች ምርመራ በማይደረግባቸውና ደካማ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት ባለባቸው የገጠር አካባቢዎች ሥነ-ሥርዓቱ አደጋ ሊሆን እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው፡፡

  7. በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት በሌጎስ የሚገኝ ሆስፒታል ተዘጋ

    ከ20 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሏት ሌጎስ ይሰራ የነበረው ትልቁ የግል ሆስፒታል ለኮሮናቫይረስ በመጋለጡ ለመዘጋት መገደዱ ተነገረ።

    ቅዱስ ኒኮላስ ሆስፒታል ባወጣው መግለጫ ለቀጣይ ሁለት ሳምንታት የህክምና አገልግሎት አልሰጥም ብሏል።

    የሆስፒታሉ ክሊኒካል ዳይሬክተር በሁለቱ ሳምንታት ውስጥ መንግሥት በሰጠው ምክረ ሃሳብ መሠረት ዝግ ሆኖ በጸረ-ተዋሲያን ርጭት ይካሄድበታል ብለዋል።

    የሆስፒታሉ ታካሚዎች ከዶክተሮቻቸው ጋር በስልክ መገናኘት እንደሚችሉ ሆስፒታሉ አስታውቋል።

    የናይጄሪያ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ሆስፒታል በተጨማሪ በሌጎስ ግዛት የሚገኙ ሌሎች አምስት ሆስፒታሎችም በተመሳሳይ መልኩ በቫይረሱ በመጋለጣቸው ለመዘጋት ተገደዋል።

    ናይጄሪያ በጠቅላላው 655 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት ሲሆን 376 የሚሆኑት የሚገኙት በሌጎስ ግዛት ውስጥ ነው።

    በሳለፍነው ሳምንት በአንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሃኪም በኮቪድ-19 መሞታቸው ተዘግቦ ነበር።

  8. በኮቪድ-19 ህይወቱ ያለፈ ዶክተር ሥርዓተ ቀብር እንዳይፈጸም የተከላከሉ 20 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

    በኮቪድ-19 ህይወቱ ያለፈ ዶክተር ሥርዓተ ቀብር እንዳይፈጸም በኃይል የተከላከሉ 20 ሕንዳውያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

    ቀላል የማይባሉ የሕንድ የማህበረሰብ አባላት በኮቪድ-19 የሞተ ሰው ሥርዓተ ቀብር የተፈጸመበት አካባቢ ቫይረሱ ይሰራጫል የሚል እምነት አላቸው።

    በደቡብ ሕንድ በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈውን ዶ/ር ሳይመን ሄራኩሌስ ሥርዓት ቀብር ለመፈጸም እሁድ ጠዋት የተሰበሰቡ ወዳጅ ዘመዶች በበርካታ ሰዎች ድብደባ እና እንግልት ተፈጽሞባቸዋል ተብሏል።

    በዚህም ምክንያት ከ24 ሰዓታት በኋላ የሟቹ ወዳጅ የሆኑ አንድ ግለሰብ በድብቅ ብቻቸውን የዶክተሩን ሥርዓተ ቀብር መፈጸማቸው ተገልጿል።

    "የሚገባውን ሰብዓዊ ክብር እንኳን ማግኘት አልቻለም። ባለቤቱ እና ልጁ እንኳ መጥተው አልተሰናበቱትም" በማለት የሟቹ ዶክተር ወዳጅ የሆኑት ዶ/ር ፕራዲፕ ኒውስ ሚኒት ለተባለ ድረ-ገጽ ተናግረዋል።

  9. “የእንቅስቃሴን ገደብ ማንሳቱ ቀስ በቀስ መሆን አለበት” የዓለም ጤና ድርጅት

    በርካታ አገራት የእንቅስቃሴ ገደባቸውን በግማሽ አሊያም ሙሉ ለሙሉ ማንሳታቸውን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች ቀስ በቀስ መሆን እንደሚገባቸው አሳሰበ፡፡

    ድርጅቱ የአገራት ውሳኔ ወደ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ሊያመራ ይችላል ብሏል፡፡

    የምዕራብ ፓስፊክ ሪጅናል ዳይሬክተር ታከሺ ካሳይ “ቢያንስ ክትባት አሊያም ውጤታማ የሆነ ህክምና እስከሚገኝ ድረስ እየተከተልነው ያለውን ሂደት አዲሱ የተለመደ ተግባራችን መሆን ይገባዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

    አክለውም የተጣሉ ገደቦችን ለማለዘብ አሊያም ለማንሳት የሚያስብ ማንኛውም መንግሥት ቀጣይነት ባለው ቁጥጥር እና ደረጃ በደረጃ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

    ግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ ለአዲሱ የኑሮ ዘይቤም ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲሉ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

    እንደ ጃፓንና ሲንጋፖር ያሉ አገራት ወረርሽኙን ተቆጣጠርነው ካሉ በኋላ አዳዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን እያገኙ በመሆኑ በሁለተኛ ዙር የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ እንዳይጠቁ ስጋት ፈጥሯል፡፡

  10. የሲኤንኤኑ ሪቻርድ ኩዌስት በኮቪድ-19 መያዙን አስታወቀ

    የሲኤንኤኑ ቢዝነስ ዘጋቢ ሪቻርድ ኩዌስት በኮሮናቫይረስ መያዙን በትዊተር ገጹ ላይ አስታወቀ።

    ሪቻርድ በኮሮናቫይረስ መያዙን ባረጋገጠበት ጽሑፍ ከበሽታው ምልክቶች ሳል ብቻ እንዳለበት በመጥቀስ እድለኛነቱን ገልጿል።

  11. ኑሯቸውን በአሜሪካ ለማድረግ በብዛት የተጓዙት የየትኞቹ አገራት ዜጎች ናቸው?

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት በቋሚነት ለመኖር ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎችን ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚያግዱ ማሳታወቃቸውን መዘገባችን ይታወቃል።

    የፕሬዝደንቱ የጉዞ ክልከላ ዝርዝር እና ከመቼ ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ባይታወቅም፤ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ኑሯቸውን በአሜሪካ ለማድረግ በብዛት የተጓዙት የየትኞቹ አገራት ዜጎች እንደሆኑ ማወቅ ይቻላል።

    ከአሜሪካ ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ ድረ-ገጽ ላይ የተገኘው አሃዝ እንደሚጠቁመው በአውሮፓውያኑ 2019 ከአንድ ሚሊዮን በላይ የውጭ አገር ዜጎች በአሜሪካ የቋሚ ነዋሪነት ፍቃድ አግኝተዋል።

    ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የሜክሲኮ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ዶሚኒኪ ሪፓብሊክ፣ ፊሊፒንስ እና ኩባ አገራት ዜጎች ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ።

    በሌላ በኩል እአአ 2019 አሜሪካ ወደ 30ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ተቀብላለች።

    ከእነዚህም መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ከ5 አገራት የተወጣጡ ናቸው። እነዚህም ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ በርማ፣ ዩክሬን፣ ኤርትራ እና ሶሪያ ናቸው።

  12. ጃክ ማ ለዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ ሊያደርጉ ነው

    የአሊባባ ባለቤት ጃክ ማ ለዓለም ጤና ድርጅት 100 ሚሊየን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ)፣ አንድ ሚሊየን N95 ማስክ እና አንድ ሚሊየን የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ድጋፍ ሊያደርጉ መሆናቸውን አስታውቁ፡፡

    ድጋፉ በጣም በአንገብጋቢ ሁኔታ ለሚያስፈልጋቸው ይሰራጫል ብለዋል፡፡

    ጃክ ማ “ይህንን ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ለመፍታት አንድ ላይ በራስ በመተማመንና በፍጥነት መጓዝ አለብን” ብለዋል በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፡፡

    ቻይናዊው ቢሊየነር ከዚህ ቀደም የመመርመሪያ መሳሪያዎችንና የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ የሚከላከሉበት የህክምና ቁሳቁሶችን ለ54 የአፍሪካ አገራት መለገሳቸው ይታወሳል፡፡

  13. የሴራ ሊዮን ፕሬዚደንት ጠባቂ በኮሮና መያዙን ተከትሎ ፕሬዝደንቱ እራሳቸውን አገለሉ

    የሴራ ሊዮን ፕሬዚደንት ጁሊየስ ማዳ ጠባቂ በኮሮናቫይረስ መያዙ ተረጋገጠ፡፡

    ፕሬዚደንቱ ጠባቂያቸው በቫይረሱ መያዙን አረጋግጠው በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቁት ትናንት ምሽት ነበር፡፡

    አክለውም የጠባቂያቸው የቤተሰብ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ፤ እስካሁን አንዳቸውም የኮሮናቫይረስ ምልክት አልታየባቸውም ብለዋል፡፡

    ፕሬዚደንት ጁሊየስም ከጠባቂያቸው ጋር ንክኪ ስለነበራቸው ራሳቸውን ለ14 ቀናት ያገላሉ ተብሏል፡፡

    በሴራ ሊዮን እስካሁን 43 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡

  14. በታንዛኒያ የምክርቤት አባሉ በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ስጋት ነግሷል

    በታንዛኒያ አንድ የምክር ቤት አባል በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ በምክር ቤቱ ስጋት ነግሷል፡፡

    ስማቸው ያልተጠቀሰው የምክር ቤት አባሉ የቫይረሱ ማዕከል ወደሆነችው ዳሬ ሰላም ተጉዘው እንደነበር ምክትል አፈ ጉባዔው ቱሊያ አክሶን ተናግረዋል፡፡

    ይህንን ተከትሎም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በፓርላማ አባላቱ ዘንድ ንትርክን ፈጥሯል፡፡

    የፓርላማ ስብሰባው ከሦስት ሳምንታት በፊት የተወሰኑ አባላት በምክር ቤቱ በተገኙበት እና ሌሎች በቪዲዮ ከየቤታቸው በመሆን ነበር የተጀመረው፡፡

    ይሁን እንጅ አሁንም እሰጥ አገባው ቀጥሏል፡፡

    አንዳንድ የምክር ቤት አባላት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ያሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ይህንን ተቃውመውታል፡፡

    አንዳንድ የምክርቤት አባላት፤ ምክር ቤቱ ጸረ ተህዋስ ኬሚካል እንዲረጭ መፈቀዱ እንዲሁም ሁሉንም የምክርቤት አባላቱን መመርመር ፤ ቫይረሱ የተገኘበትም በለይቶ ማቆያ እንዲገባ መደረጉ እንዲቆም ይፈልጋሉ፡፡

    በሌላ በኩል ደግሞ ለምክር ቤት አባላቱ እና ለሕዝብ ተብሎ የተቀመጠ ሁለት ሕግ የለም፤ በመሆኑም ሁሉም የፓርላማ አባላት ራሳቸውን ማግለል፣ መመርመር እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች መፈለግ አለባቸው ሲሉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ተናግረዋል፡፡

    አፈ ጉባዔ ጆብ ዱጋይ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አገሪቷ እየወሰደች ያለችውን እርምጃ መቀጠል የለበትም ሲሉ ከተቃወሙት መካከል አንዱ ናቸው፡፡

    አፈጉባዔው ከፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ ጋር በመወገን የእንቅስቃሴ ገደብን ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ እርምጃዎችን ሳያጸድቁ ቀርተዋል፡፡

    ሌላኛዋ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ኡፔንዶ ፔኔዛ በበኩላቸው፤ በዳሬ ሰላም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ፤ ከከተማዋ ውጭ የሚደረግ ጉዞ መከልከል አለበት፤ አስፈላጊና መሰረታዊ የሆኑ እቃዎችና ምርቶች እንዲሁም አገልግሎቶች ብቻ መፈቀድ አለባቸው ሲሉ ፔንሴማ የተባሉ የፓርላማ አባል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

    በታንዛኒያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 254 ሲሆን የ10 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የቫይረሱ ስርጭትም የአገሪቷን ግማሽ ያህል ክፍል አካሏል፡፡

  15. በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከዜሮ በታች ሆነ

    ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ቀንሷል። ማጠራቀሚያ ቦታዎችም ተጣበዋል። የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ደግሞ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከዜሮ በታች ሆኗል።

    ይህ ማለት የነዳጅ ዘይት አምራቾችን፤ የምርት ማከማቻ ስፍራ በመጣበቡ ገዢዎቻቸው ምርቶች እንዲያነሱላቸው እየከፈሏቸው ነው ማለት ነው።

    ነዳጅ ዘይት አምራቾች ማጠራቀሚያ ስፍራዎች ወረሃ ግንቦት ላይ ሙሉ ለሙሉ ይሞላሉ ብለው ገምተዋል።

    ለዚህ ሁሉ ችግር ደግሞ የነዳጅ ፍላጎት መቀነስ ነው። ለነዳጅ ፍላጎቱ መቀነስ ምክንያቱ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መገታቱ ነው።

    አምራቾች ተጨማሪ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን ተከራይተው ምርቶችን እያከማቹ ነው።

    የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማነጻጸሪያ የሆነው የ “ዌስት ቴክሳስ ኢንተርሚዲየት” አንድ የበርሜል ዋጋ ከዜሮ በታች $37.63 ሆኗል።

    የነዳጅ ዘይት ዘረፍ ኮሮናቫይረስ ሁለት ፈተናዎችን ጋርጦበታል። የገበያ ፍላጎት መቀነስ እና አምራቾች ምርታቸውን አልቀንስም የማለት።

    በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የነዳጅ አምራች አገራት ስብስብ የሆነው ኦፔክ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የምርት አቅርቦቱን በ10 በመቶ ለመቀነስ ተስማምቶ ነበር። ሩሲያም የምታቀርበውን የነዳጅ ዘይት ምርት ለመቀነስ ከውሳኔ ደርሳለች።

    የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ግን አምራቾቹ የምርት አቅርቦቱን ለመቀነስ የተስማሙበት መጠን ልዩነት የሚያመጣ አይደለም ይላሉ።

    የነዳጅ ምርት መትረፍረፍ ካለ አምራቾች ማምረታቸውን ለምን አያቆሙም?

    የቢቢሲ ቢዝነስ ሪፖርተር ነገሮች እኛ እንደምናስባቸው ቀላል አይደሉም ይላል።

    የነዳጅ ዘይቱን ስቦ ማውጣት እና ምርት ማቆም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው ይላል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የቆመውን ሥራ እንደ አዲስ ማስጀመር እጅጉን ከባድ ነው። ሌላ ጉዳይ አምራቾች የገቢ ምንጫቸው የነዳጅ ዘይት ማምረት ብቻ ነው። ምርት አቆሙ ማለት የገበያ ድርሻቸው ወደቀ ማለት ጭምር ነው።

    አሁንም ቢሆን ዓለማችን በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልጋት በላይ ድፍድፍ ነዳጅ አከማችታለች። የቢቢሲ የምጣኔ ሃብት ተንታኝ የሆነው አንድሩው ዎከር እንደሚለው ከሆነ፤ አሁን ላይ ጉዳዩ ያለውን የነዳጅ ዘይት እንጠቀመዋለን የሚለውን ብቻ ሳይሆን ተጥለው የሚገኙት የእንቅስቃሴ ገደቦች እስከሚነሱ ድረስ የሚመረተውን ነዳጅ የምናከማችበት ስፍራ አለ ወይ? የሚለው መመለስ አለበት ይላል።

  16. በእነዚህ ሁለት ምስሎች መካከል ያለውን ልዩነት ያስተውሉ

    ይህ በተለያየ ወቅት የተነሳ በዴልሂ ከተማ የሚገኝ ቦታ ነው። በሁለቱ ምስሎች ላይ ምን ልዩነት አስተዋሉ?

    ከላይ ያለው ምስል የተነሳው የሕንዷ ዴልሂ እንቅስቃሴ ከመገደቧ በፊት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ ትዕዛዝ ከተሰጣቸው በኋላ ነው።

    ዛሬ ላይ በዴልሂ የትራንስፖርት አገልግሎት የለም፤ በረራ ተቋርጧል፤ ሰዎች ወደ ሥራ ቦታ አይሄዱም፤ ተማሪዎችም ከትምህርት ቤት ቀርተዋል።

    በዚህም በከተማዋ ያለው የአየር ጥራት ታይቶ የማይታወቅ ነው እየተባለ ነው።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭት ምናልባትም ከተሞች የሚተነፍሱት የአየር ንጽህናን ለማሻሻል ጠንካራ የፖሊሲ ለውጥ እንዲወስዱ ያስችላቸው ይሆን? ሲሉ የሚጠይቁ በርካቶች ሆነዋል።

  17. በጣሊያን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ተስፋን ፈንጥቋል

    በጣሊያን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከጀመረ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡

    ትናንት በቤታቸው እና በሆስፒታል ሆነው ክትትል የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር 108 ሺህ 237 የነበረ ሲሆን ከቀደመው ቀን በ20 ቀንሷል፡፡

    ባለሥልጣናቱ ምንም እንኳን ቁጥሩ በጣም ትንሽ ቢሆንም የመልካም ለውጥ ምልክት ነው ብለዋል፡፡

    በጣሊያን የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ለ15 ቀናት ያህል የሚቀጥል ሲሆን የተወሰኑ የንግድ ተቋማት ግን ተከፍተዋል፡፡

    እነዚህ የንግድ ተቋማት የመጽሐፍት መደብሮች፣ የህጻናት ልብስ መሸጫ ሱቆች እና የጽህፈት መሳሪያዎች መደብርን የሚያካትት ሲሆን፤ ሰዎች አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቅ አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ አክለዋል፡፡

    ጣሊያን ከአሜሪካና ስፔን ቀጥላ በከፍተኛ ሁኔታ በኮሮናቫይረስ የተጠቃች አገር ናት፡፡

  18. ትራምፕ ወደ አሜሪካ በቋሚነት ለመኖር የሚደረግን ጉዞ ሊያግዱ ነው

    ትራምፕ በቫይረሱ ምክንያት ወደ አሜሪካ በቋሚነት ለመኖር የሚደረጉ ጉዞዎችን ሊያግዱ ነው።

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት በቋሚነት ለመኖር ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎችን ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚያግዱ አስታወቁ።

    ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ በሆነው ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ አስታውቀዋል።

    ፕሬዝደንቱ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ አይስጡ እንጂ በክልከላው ላይ የተማሪ ቪዛ ያላቸው እና ለሥራ ወደ አሜሪካ የሚያቀኑ እገዳው አይመለከታቸውም ተብሏል።

    ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ውሳኔያቸው የአሜሪካውያንን የሥራ እድልንም እንደሚያስጠብቅ ጠቅሰዋል።

    የትራምፕ ተቺዎች ግን ፕሬዝደንቱ ኮሮናቫይረስን ምክንያት በማድረግ የሌላ አገር ጥገኘነት ጠያቂዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያዙት እርምጃ ነው እያሉ ነው።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከአውሮፓ፣ ቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ለሚደረጉ ጉዞዎች ድንበራቸውን ዝግ አድርገዋል።

    ከአንድ ወር በፊትም የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች የቪዛ ቀጠሮዎቻቸውን ዝግ ማድረጋቸው ይታወሳል።

    አሜሪካ እስካሁን 782,159በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ያላት ሲሆን 41,816 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምንክያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

  19. የቀጥታ ዘገባችን አሁን ይጀምራል

    ውድ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ?

    ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ወደ እናንተ ማድረስ እንጀምራለን።

    መልካም ቀን።

  20. ዶ/ር ቴድሮስ ፖለቲካዊ አለመግባባት ህይወት ለማዳን የሚደረገን ጥረት እንዳያደናቅፍ አስጠነቀቁ