የነዳጅ ዘይት ዋጋ ቀንሷል። ማጠራቀሚያ ቦታዎችም ተጣበዋል። የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከ20 ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው አሽቆልቁሏል።
የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዋጋ አንድ የበርሜል ነዳጅ በ19.3 በመቶ ቀንሶ በ14.74 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።
ለነዳጅ ፍላጎቱ መቀነስ ምክንያቱ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መገታቱ ነው።
በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ነዳጅ የሚከማቹባቸው ስፍራዎች የነዳጅ አቅርቦቱን የሚያስቀምጡበት ጠፍቷቸው ተቸግረዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የነዳጅ አምራች አገራት ስብስብ የሆነው ኦፔክ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የምርት አቅርቦቱን በ10 በመቶ ለመቀነስ ተስማምቷል። ሩሲያም የምታቀርበውን የነዳጅ ዘይት ምርት ለመቀነስ ከውሳኔ ደርሳለች።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ግን አምራቾቹ የምርት አቅርቦቱን ለመቀነስ የተስማሙበት መጠን ልዩነት የሚያመጣ አይደለም ይላሉ።
አሁንም ቢሆን ዓለማችን በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልጋት በላይ ድፍድፍ ነዳጅ አከማችታለች።
የቢቢሲ የምጣኔ ሃብት ተንተኝ የሆነው አንድሩው ዎከር እንደሚለው ከሆነ፤ አሁን ላይ ጉዳዩ ያለውን የነዳጅ ዘይት እንጠቀመዋለን የሚለውን ብቻ ሳይሆን ተጥለው የሚገኙት የእንቅስቃሴ ገደቦች እስከሚነሱ ድረስ የሚመረተውን ነዳጅ የምናከማችበት ስፍራ አለ ወይ? የሚለው መመለስ አለበት ይላል።