በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሆነ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል።ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በስፔን የኮሮናቫይረስ ህሙማን ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ

    ስፔን ውስጥ በኮሮንቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ደረሰ።

    የስፔን የጤና ሚኒስቴር እንዳለው በምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 200,210 እንደሆነ ተናግሯል።

    በተጨማሪም በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን አሁን 20,852 ሰዎች በወረሽኙ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ስፔን በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ በወረርሽኙ በተያዙ ሰዎች ብዛት ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ መሆኗን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩንቨርስቲ መረጃ ያመለክታል።

  2. አያቶላ በወረርሽኙ ምክንያት ሙስሊሞች በረመዳን ወቅት የመጾም ግዴታ የለባቸውም አሉ

    የሳኡዲ አረቢያ ከፍተኛ የሐይማኖት አካል በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ሲባል በቅዱሱ ወር ረመዳን ለጸሎት መሰብሰብ እንደሌለባቸው አሳስበ።

    የሐይማኖት ምክር ቤቱ ሙስሊሞች "አንድ ላይ መሰብሰብን ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የቫይረሱን ስርጭት ያባብሰዋል" ስለማለቱ የሳኡዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

    የሱኒ ሙስሊሞች በብዛት የሚገኙባት ሳኡዲ፤ በመካ የሚገኘውን ታላቁን መስጅድ ጭምሮ የመስጅዶችን በር ዝግ አድርጋለች።

    በተመሳሳይ የኢራኑ የሐይማኖታዊ መሪ የአያቶላ ካህሜኒ ሙስሊሞች በረመዳን ወቅት የመጾም ግዴታ የለባቸውም ብለዋል።

  3. ኮሮናቫይረስን በአምስት ደቂቃ ውስጥ መለየት የሚያስችል ሙከራ እየተካሄደ ነው

    ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳውዝ ዌልስ በግማሽ ሰዓት ውስጥ ኮሮናቫይረስን መርምሮ የሚያሳውቅ መሳሪያ ሰራ።

    ምርመራው ምን ያህል ትክክለኛ ነው የሚለው የሚፈተሽ ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ቦርድ ግን ተስፋ ሰጪ ምርምሮች አሉ ብሏል።

    በኖርዊች የምርምር ማዕከል ያሉ ተመራማሪዎች ከሳውዝ ዌልስ የዩኒቨርስቲ ቡድን ጋር ተመሳሳይ የሆነ መንገድ በመጠቀም ፈጣን መመርመሪያ እየሰሩ መሆኑን አሳውቋል።

    ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኤዚተር በበኩሉ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ታመው ከነበሩ መለየት የሚያስችል ባለመንታ ፋይዳ መመርመሪያ እየሰራሁ ነው ብሏል።

    ዩኒቨርስቲው በሎንዶን ከሚገኘው ቅዱስ ቶማስ ሆስፒታል ጋር በመሆን ሙከራ እያደረገ ሲሆን ውጤታማ ከሆነ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ውጤቱን ያሳውቃል።

  4. በድሬዳዋ ሦስት ታዳጊዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

    በድሬዳዋ ከተማ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሦስት ታዳጊዎች ተገኙ።

    ከሦስቱ ታዳጊዎች መካከል ሁለቱ ከጅቡቲ የመጡና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

    ሁለቱ የ11 ዓመትና የ15 ታዳጊዎች ከጅቡቲ መጥተው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ያሳወቀ ሲሆን፤ ሌላኛው በሽታው የተገኘበት የ18 ዓመቱ ወጣት የጉዞ ታሪክ የሌለውና በንክኪ ምከንያት የተያዘ መጀመሪያ ላይ ተገልጾ ነበረ።

    ነገር ግን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ባወጣው ማስተካከያ ላይ የጉዞ ታሪክ የሌለው ተብሎ የተገጸው ወጣትን በተመለከተ በተደረገው ማጣራት ከጅቡቲ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያለ መሆኑ ተረጋግጧል።

    ኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት 396 ሰዎች ምርመራ ያደረገች ሲሆን አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 111 ደርሷል።

  5. ናይጄሪያ በ24 ሰዓት 86 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አገኘች

    ናይጄሪያ በ24 ሰዓት ውስጥ ባደረገችው ምርመራ 86 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች አግኝታለች።

    ይህ ቁጥር እስካሁን በሃገሪቱ ከታየው የቫይረሱ ጥፋት ከፍተኛው ነው ተብሏል።

    ባለሥልጣናት በአንድ ቀን ውስጥ የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መያዛቸው የተረጋገጠው ብለዋል።

    በአፍሪካ ቁጥር አንድ የሕዝብ ሃብታሟ ሃገር ናይጄሪያ እስካሁን ባደረገችው ምርመራ 627 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ አድርጋለች። 21 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መሞታቸው ተረጋግጧል።

    ዋና ከተማዋ አቡጃ፣ የንግድ መናገሻዋ ሌጊስ፣ ኦጉንና ካኖ የተባሉ ግዛቶች ውስጥ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።

  6. ደ.አፍሪካ፡ ፍቅረኛውን በመኪናው የኋላ ጉያ ደብቆ ሲዘዋወር የነበረው ተያዘ

    ደቡብ እፍሪካ ውስጥ አንድ ግለሰብ ፍቅረኛውን የመኪናው የኋላ እቃ መጫኛ ውስጥ ደብቆ ሲዘዋወር እጅ ከፍንጅ ተይዟል።

    ሰውዬው የተያዘው ጉዋቴንግ በተባለ ግዛት በገጠመው ፍተሻ ነው። ግለሰቡ የመንጃ ፈቃድ የሌለው ሲሆን ምፑማላንጋ ወደ ተባለችው ግዛት ለማቋረጥ ነበር ሀሳቡ።

    ግለሰቡ በኮሮና ምክንያት ከቤት አትውጡ የተባለውን ትዕዛዝ ተላልፎ ሲዘዋወር ነው የተገኘው ሲሉ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን በትዊተር ገፃቸው አስነብበዋል።

    የመኪናው ጉያ ውስጥ የተገኘችው ሴትም ለወንጀል በመተባበር ለእሥር ተዳርጋለች።

    ደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ ምክንያት ለ3 ሳምንታት አውጃ የነበረውን የእንቅስቃሴ እገታ እስከያዝነው ወር መጨረሻ ድረስ አራዝማዋለች።

    እስካሁን ድረስ በተደረገ ምርመራ 3 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  7. የኬንያ ፍርድ ቤቶች ይከፈቱ መባሉ አከራካሪ ሆኗል

    የኬንያ ዳኞች ፍርድ ቤቶች ይከፈቱ መባላቸውን ተከትሎ በቂ የሆነ የቪድዮ ማሠራጫ ቴክኖሎጂ ሳይኖር እንዴት ሆኖ በማለት ተቃውመውታል።

    ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዳቪድ ማሪጋ የፍርድ ሂደቶች ክፍት በሆነ ሥፍራ ከረቡዕ ጀምሮ ይከናወናሉ፤ የምንጠብቀው የጤና ሚኒስቴርን ይሁንታ ነው ብለዋል።

    ነገር ግን ዳኛችና የፍርድ ቤት ሠራተኞች አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ሳይሟላ መክፈት ለጤናችን አስጊ ነው እያሉ ነው።

    ቅሬታ አቅራቢዎቹ ፍርድ ቤቶች ፀረ-ቫይረስ እንዲረጩ፣ የተወሰኑ ሠራተኞች ብቻ ሥራ እንዲገቡና የግል መኪና የሌላቸው መኪና እንዲመደብላቸው ይሻሉ።

    አልፍም ዕድሜያቸው ከ58 በላይ የሆነ ከቤታቸው ሆነው ይሥሩ የሚል ማመልከቻ አቅርበዋል።

    አንዳንድ የኬንያ ፍርድ ቤቶች ቪድዮ ኮንፈረንሲንግ የተሰኘውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የፍርድ ሂደት እያከናወኑ ነው።

    • ዩኬ ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ጨርሳ ከቱርክ እየጠበቀች ነው

      የዩኬ ባህል ሚኒስትር ኦሊቨር ዶውደን 48 ሺህ ቶን የሚመዝን ቫይረስ መካለከያ ቁሳቁስ ከቱርክ ይገባል ብለው ተስፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

      ሰኞ ማምሻውን ከቱርክ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ቁሳቁሶቹ መካከል 400 ሺህ ጋዎኖች ይገኙበታል።

      ''ቁሳቁስ የጫነው አውሮፐላን ዛሬ ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አለን። ጋዎኖቹን ዛሬውን እንደምናገኝ እምነታችን ነው''

      «ከቱርክ ወገን አንዳንድ መሰናክሎች ገጥመውን ነበር። ደግኔ ደጋግሜ ቃል መግባት አልፈልግም ነገር ግን አውሮፕላኑ ዛሬ ከሰዓት እንደሚነሳ አውቃለሁ። ቁሳቁሶቹም ይደርሳሉ።»

      ሚኒስትሩ ከቱርክ ብቻ ሳይሆን ከቻይናም ግላዊ መከላከያ ቁሳቁሶች በቅርቡ እንደሚገቡ አሳውቀዋል።

      ዩናይትድ ኪንግደም ግላዊ መከላከያ ቁሳቁሶች እየጨረሰች እንደሆነና የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ሊቸገሩ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

    • የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያበቃው መቼ ነው?

      በቻይና ዉሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም ተሰራጭቷል። ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

      በዚህ ሁኔታ ውስጥ የመላው ዓለም ጥያቄ 'ይህ ወረርሽኝ መቼ ያበቃ ይሆን?' የሚለው ነው። ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እየተሰሩ ነው፤ ግን እስከመቼ በተስፋ ብቻ?

    • በምሥራቅ ሸዋ ዞን በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ሰባት ወጣቶች ሞተው ተገኙ

    • ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ደም ለመድኃኒትነት ሊሞከር ነው

      ዩናይትድ ኪንግደም ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎችን ደም ቫይረሱ ያለባቸውን ለማከም ጥቅም ላይ ልታውል ነው።

      ብሔራዊው የጤና አገልግሎት [ኤንኤችኤስ] ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ደም እንዲለግሱ ጥሪ እያቀረበ ነው።

      ኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ያዳበሩት በሽታውን የመከላከል አቅም ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ላይ እንዲሞከር ታስቦ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሙከራ ተጀምሯል።

      አሜሪካም ይህንን መላ በመጠቀም መፍትሄ ይገኝ እንደሆን ለማቀው በ1500 ሆስፒታሎች ውስጥ ጥናት ማካሄድ ጀምራለች።

      ፕላዝማ የተሰኘው የሰው ልጅ ደም ውስጥ የሚገኝ ቅንጣትን በመውሰድ ሕክምና ወይም መድኃኒት ለማዳበር ጥረት እየተካሄደ ያለው።

    • የአሜሪካው አምባሳደር ኬንያውያንን አስቆጡ

      በኬንያ የአሜሪካ አምባሳደር ካየል ማክካርተር ኬንያኖችን አስቆጡ። አምባሳደሩ ኬንያውያን የአፍና የፊት መሸፈኛ አያደርጉም፤ አካላዊ ርቀታቸውንም አይጠብቁም በማለታቸው ነው ኬንያውያን የተቆጡት።

      አምባሳደሩ "በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያደረጉት አካላዊ ርቀታቸውንም የሚጠብቁት። ማንኛችንም ይህንን የዉሃን ፍሉ ምን ያህል እንደተስፋፋ ማወቅ አንችልም። ስለዚህ መሰረታዊ የሆኑትን የሚታወቁ መከላከያዎችን መጠቀም አለብን" ነበር ያሉት።

      ኬንያውን በትዊተር ላይ አምባሳደሩ አገራቸው ለድሃ ኬንያውያን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ምን ያህል እንደረዳች ጠይቀዋል።

      አምባሳደር ማክካርተር በምላሹ "አሜሪካ ባትኖር በኬንያ ምርመራ ማድረግ አትችሉም ነበር" ብለዋል።

      ሌሎች ደግሞ የዕለት ጉርሳቸው ከእጅ ወዳፍ የሆነ እና በደሳሳ ጎጆ የሚኖሩ ሰዎች እንዴት አካላዊ ርቀታቸውን መጠበቅ ይችላሉ ሲሉ ጠይቀዋል።

      "ማህበራዊና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በድሆች መንደር እንደምን መጠበቅ ይቻላል?" ሲሉ ጠይቀዋል።

    • ቻይና ኮሮናቫይረስን እንደምን በቴክኖሎጂ ታግዛ ተቆጣጠረች?

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቻይና ይሆናል የተከሰተው። ነገር ግን አገሪቱ ከአሜሪካ፣ ጣሊያን እና ስፔን ያነሰ ታማሚ እና ሟች የተመዘገበባት ሆናለች።

      ቻይና በሽታውን በሦስት ወር ውስጥ ለመቆጣጠር እንደቻለች ይነገራል። በዚህ ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂ የቻይናን ጥረት ምን ያህል አግዟል? ይመልከቱት።

    • የወባ መድኃኒት ለኮቪድ-19 ሊሞከር ነው

      ኖቫርቲስ የተባለ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በገባው ውል መሠረት ሃይድሮክሲክሎሮኪን የተሰኘውን የወባ መድኃኒት በ440 የኮቪድ-19 ተኝቶ ታካሚዎች ላይ ሊሞክር ነው።

      መድኃኒቱ ለዘመናት ወባን ለማከም ጥቅም ይውል የነበረ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኮሮናቫይረስን ለማከም ያግዛል ማለታቸው አይዘነጋም። ምንም እንኳ ሃይድሮክሲክሎሮኪን ኮሮናቫይረስን ለማከም ያስችል እንደሆን ሳይንሳዊ ድጋፍ ባያገኝም መድኃኒቱን ገበያ ላይ ማግኘት ከባድ እየሆነ መጥቷል።

      መቀመጫውን ስዊዝ ያደረገው ይህ ኩብንያ «የወባ መድኃኒት የሆነው ሃይድሮክሲክሎሮኪን ኮቪድ-19ን ለማከም ይረዳ ይሁን አይሁን ማወቁ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተረድተናል» ይላል።

      በዓለም ዙሪያ ያሉ ቤተ-ሙከራዎች አዲሱን ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ መድኃኒት ለመፍጠር ሽር ጉድ ላይ ናቸው።

    • ኮሮናቫይረስ በአፍጋኒስታን ቤተመንግሥት

    • ሕንድ፡ ሙስሊሞችን አናክምም ያለው ሆስፒታል ቁጣ ቀሰቀሰ

      ሚሩት በተሰኘች አንድ የሕንድ ከተማ የሚገኝ የግል ሆስፒታል ሙስሊሞች ከኮቪድ-19 ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ወረቀት እስካላመጡ ድረስ የሕክምና አገልግሎት አልሰጥም ሲል ማስታወቂያ ማስነገሩ ቁጣ ቀስቅሷል።

      ይህ ጉዳይ ያስቆጣቸው ሕንዳውያን በማሕበራዊ ድሮች ስሜታቸውን ሲያጋሩ ሰንብተዋል። ይህንን ተከትሎ ሆስፒታሉ ይቅርታ ለመጠየቅ ተገዷል።

      ቫለንቲስ የተሰኘው ይህ የካንሰር ሆስፒታል አንድ የእስልምና አስተምህሮት ቡድንን በከተማዋ ላለ የኮቪድ-19 ሥርጭት ተጠያቂ አድርጓል።

      ባለፈው መጋቢት የተከናወነ አንድ ኃይማኖታዊ ዝግጅት ቢያንስ 15 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች የተካፈሉ ሲሆን፣ በዚህ መርሃ ግብር ላይ አብዛኞቹ የታደሙ በቫይረሱ ተይዘዋል እየተባለ ይነገራል።

      በሜሩት ከተማ ካሉ ቫይረሱ የያዛቸው ሰዎች ሁለቱ ሲቀሩ ሌሎቹ ከኃይማኖታዊ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላቸው ሲሉ የሆስፒታሉ ዶክተር ማስታወቂያው ላይ ተናግረዋል።

      ይህ በርካታ ሕንዳውያን ቫይረሱን ከሙስሊሞች ጋር እንዲያይዙት ሆኗል እየተባለ ነው።

      በርካታ 'ሙስሊም ጠል' የሆኑ የማሕበራዊ ሚድያ መልዕክቶች አይቻለሁ ያለው የሕንድ መንግሥት ከፋፋይ መልዕክቶች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

    • የቶኪዮ ኦለምፒክ የዛሬ ዓመትም ላይካሄድ ይችላል

      አንድ ጃፓናዊ የቫይረስ ልሂቅ ከአንድ ዓመት በኋላ ሊካሄድ ዕቅድ የተያዘለት የቶኪዮ ኦለምፒክስ ላይሳካ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ።

      ዘንድሮ ሊካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቆ የነበረው የቶኪዮ ኦለምፒክስ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለአንድ ዓመት መራዘሙ አይዘነጋም።

      "ኦለምፒክ ማዘጋጀት ሁለት ቅድመ-ሁኔታዎች ይጠይቃል። አንደኛው ኮቪድ-19ን ከጃፓን ማስወገድ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ቫይረሱን ከሌሎችም ቦታዎች ማስወገድ ነው። ምክንያቱም አትሌቶችና ታዳሚዎች ከመላው ዓለም ይመጣሉና" ይላሉ የኮቤ ዪኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ኬንታሮ ኢዋታ።

      ጃፓን ቫይረሱን እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ትቆጣጠረዋለች። ሁሉም ይቆጣጠሩታል ማለት ግን ከባድ ነው ባይ ናቸው ምሁሩ።

      ጃፓን ምንም ቢመጣ ኦለምፒኩን ከማስተናገድ አያግደኝም እያለች ሳለ ነው ኮቪድ-19 ዕቅዷን ያደናቀፈው። ሃገራት አትሌቶችን አንልክም ማለታቸውን ተከትሎ ስፖርታዊ ጨዋታዎቹ ለሚቀጥለው ዓመት ቀን ተቆርጦላቸዋል።

    • የአዲስ አበባው ሚሌኒየም አዳራሽ 1000 አልጋዎችን እንዲእዝ ተደርጎ እየተዘጋጀ ነው

      በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሚሌኒየም አዳራሽ ተገኝተው የኮቪድ-19 ሕሙማንን ለማከም እየተዘጋጀ ያለውን ስፍራ ጎብኝተዋል

      የሚሌኒየም አዳራሽ 1000 አልጋዎችን የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየተዘጋጀ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

      ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይና የጤና ሚኒስትሯ እንዲህ አይነት ዝግጅቶች በሌሎች ቦታዎችም እንዲቀጥሉ መመሪያ መስጠታቸውም በወቅቱ ተገልጿል።

      በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች 108 ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ሶስት ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል።

    • ፓኪስታን የረመዳን ፀሎት በመስጂዶች እንዲካሄድ ፈቀደች

      ፓኪስታን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚል ከረመዳን ወር አስቀድማ በመስጂዶች ለፀሎት መሰባሰብ ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ ከሀይማኖት አባቶች በመጣ ጫና ምክንያት አነሳች።

      በረመዳን ወር ማታ ማታ ሙስሊሞች ለፀሎት በመስጂድ ይሰባሰባሉ።

      የፓኪስታን መንግሥት ከሃይማኖት አባቶች ጋር ባደረገው ስምምነት እድሜያቸው ከ50 በላይ የሆነ እና ሕጻናት እንዲሁም ጉንፋን ያዛቸው መስጂድ መግባት አይፈቀድላቸውም።

      ሁሉም ምንጣፎች ተነስተው ወለሉ በፀረ ተዋህሲያን እንዲፀዳም ስምምነት ላይ ተደሰርሷል ተብሏል። ሙስሊሞች በመስጂድ ሲገኙ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ እና መተቃቀፍና መሳሳም እንዲያስወግዱም ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

      መንግሥት ከዚህች አንዷ እንኳ ዝንፍ ብትል መስጂዶቹን እስከመዝጋት የሚያደርስ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቋል።

      በተጨማሪም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጨመረ ይህንን ውሳኔያቸውን ለማጤን እንደሚገደዱም ገልፀዋል።

      የፓኪስታን ባለስልጣናት ለአርብ ፀሎት በመስጂድ መሰባሰብን ለማስቀረት የሰዓት እላፊና በመስጂድ የመሰባሰብ እገዳ ጥለው የቆዩ ቢሆንም ይህ ግን ተግባራዊ የሆነው በከፊል ነበር።

    • ጋና ለበርካቶች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረገች በኋላ የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ አነሳች

      የጋናው ፕሬዝደንት አኩፎ-አዶ በሃገሪቱ በተወሰኑ ቦታዎች እንቅስቃሴ እንዲጀመር ሲፈቅዱ ዜጎች የአፍና አፍንጫ ጭንብል ማጥለቃቸው እንዳይዘነጉ በማሳሰብ ነው።

      ቢሆንም ጋና የድንበር በሮቿን ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደማትከፍት አሳውቀዋል። ዋና ከተማዋ አክራ፣ ሁለተኛዋ ግዙፍ ከተማ የምትባለው ኩማሲና የንግድ ከተማዋ ቴማ ውስጥ እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል። ዘጠኝ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

      በቀጥታ ቴሌቪዥን ሥርጭት መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝደንቱ በሽታውን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

      ምንም እንኳ ጋና እንቅስቃሴ ብትፈቅድም ትምሀርት ቤቶች አሁንም ዝግ ናቸው። አልፎም ከተገቢው በላይ ሰው መሰባሰብ አይችልም።

      ከስድስት ሺህ በላይ ምርመራዎችን ያካሄደችው ጋና 1.5 በመቶ ፖዘቲቭ ውጤት አግኝታለች። አብዛኛዎቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከውጭ የመጡ፤ አልያም ከውጭ ከመጡ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው።