በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሆነ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል።ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

  2. በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

  3. በሴቶች የሚመሩ አገራት ወረርሽኙን በተሳካ ሁኔታ እንዴት ተቆጣጠሩት?

  4. እንደምን አደራችሁ

    በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ አልፏል። በኢትዮጵያም ውስጥ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 114 ሲሆን በአጠቃላይ የተመረመረውም ሰው ቁጥር 8698 ነው። የኢትዮጵያ የምርመራ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ የምርመራ ቁጥር እንደሚጨምርና በቀንም ከአራት እስከ አምስት ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ለመርመር እቅድ መያዙ ተገልጿል።

    የምርመራ ቁጥር መጨመርም ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ መሰራጨት አለመሰራጨቱን ለማየት ያስችላል ተብሏል። በሽታው ተገኘባቸው በተባሉ አካባቢዎች በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ ባህርዳርና አዲስ ቅዳም የሙቀት ልኬትና ሁኔታዎችንም የመቃኘት ስራ እየተሰራ ነው። አገሪቷ በበሽታው ንክኪ ነበራቸው የተባሉ ሰዎች ላይ ክትትል ማድረግ፣ ከየትኛውም ውጭ አገራት የመጡ ሰዎችን አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስገባት ስራዎችን እየሰራች ነው። የቫይረሱንም መዛመት ለመግታት አገሪቷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ውሳኔ በማሳለፍ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው። ስብሰባዎችን ከማገድ ጀምሮ አካላዊ ርቀቶችን መጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችንም አየተገበረች ነው።

    ቢቢሲ አማርኛ በኮሮና ቫይረስ ላይ አገራት እየወሰዱ ስላሉት እርምጃዎች፣ እየተሞከሩ ስላሉ ክትባቶች፣ ተስፋን የሚፈነጥቁ የግለሰቦች ማገገም ታሪክ እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባችን ታገኛላችሁ።

  5. በጣልያን በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው ተባለ

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተመታችው ጣልያን ከሰሞኑ ተስፋ የሚፈነጥቅ ዜና ተሰምቷል። በተከታታይ ለሁለት ቀናት ያህልም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ አሳይቷል።

    በዛሬው እለት የተመዘገበውን ቁጥር በማየት በ528 ያህል መቀነሱን የጠቆመው የጣልያን የሲቪል ጥበቃ ኤጀንሲ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 107 ሺ 709 መድረሱን አመላክቷል።

    የቫይረሱ ወረርሽኝ ከተነሳበት እለት ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የነበረ ቢሆንም በትናነትናው እለት መቀነስ ማሳየቱ ተገልጿል።

    በሮም የቢቢሲ ዘጋቢ ማርክ ሎወን "ምንም እንኳን ቁጥሩ መቀነሱ ተስፋን ቢሰጥም፤ አሁንም ቢሆን ጣልያን ከፍተኛ ዜጎቿን በኮሮና እያጣች ነው" በማለት ያለውን ሁኔታ አስረድቷል።

    በሃያ አራት ሰአት ብቻ 534 ሰዎች በመሞታቸው በዛሬው እለት የሟቾችን ቁጥር ወደ 24 ሺ 648 አድርሶታል።

    ይህንንም ተከትሎ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሰፔ ኮንቴ "አገሪቷን ሙሉ በሙሉ ክፍት ማድረግ ኃላፊነት የጎደለው ነው" ብለዋል።

    ጣልያን ከሁለት ሳምንታት በኋላ ከተሞቿን የመክፈት እቅድ ይዛ ነበር።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷን ሙሉ በሙሉ የመክፍት ስራ ሳይንሳዊ የሆኑ ጥናቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባና ደረጃ በደረጃም እንደሚሆን አፅንኦት ሰጥተዋል።

  6. ለኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ በጎ ፈቃደኞች እየተፈለጉ ነው

    በለንደን የሚገኘው የኢምፔሪያል ኮሌጅ የተላላፊ በሽታዎች የትምህርት ክፍል በዚህ ሳምንት ለሚያደርገው የክትባት ሙከራ ለበጎ ፈቃደኞች ጥሪ አቅርቧል።

    ኮሌጁ በትዊተር ገፁ ላይ ፈቃደኛ የሆኑና መስፈርቱን የሚያሟሉ ሰዎች መጥተው እንዲመዘገቡ መልዕክት አስተላልፏል።

    የተገለፁት መስፈርቶችም ከ18-55 እድሜ፣ በሙሉ ጤንነት ያሉ ሰዎች ሲሆኑ ይህንንም ማሟላት ከቻሉ 625 ፓውንድ ወይም ወደ 26 ሺህ የሚጠጋ ብርም ይከፈላቸዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማግኘት እየሰሩ ላሉ ሁለት ፕሮጀክቶች የሚውል 40 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም ወደ 1.7 ቢሊዮን ብር መድቧል።

    የአንደኛው ፕሮጀክት መሪዎች በዚህ ሳምንት የክትባት ሙከራው በሰዎች ላይ እንደሚጀምር አሳውቀዋል።

  7. ሐሙስ ዕለት የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ በሰዎች ላይ ይጀመራል

    የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚኒስትሩ ማት ሃንኮክ ዛሬ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ላይ ለኮሮናቫይረስ የተዘጋጀው ክትባት በዚህ ሳምንት ሐሙስ እለት በሰው ላይ ሙከራ ይካሄድበታል ሲሉ አሳወቁ።

    ሚኒስትሩ ጨምረውም መንግሥታቸው ለበሽታው ክትባት ለመስራት በሚያስችሉ ጥረቶች ላይ የሚችለውን ሁሉ ነገር እንደሚያደርግ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።

    አክለውም ዩናይትድ ኪንግደም ለወረርሽኙ ክትባት ለማግኘት በሚደረጉ ምርምሮች ላይ “ከየትኛውም አገር ክትባት በላይ ከፍተኛ ገንዘብ” መድባ እየሰራች መሆኑን አመልክተዋል።

    በዚህ መስክም ሚኒስትሩ ኦክስፎርድን ዩኒቨርስቲንና የለንደኑን ኢምፔሪኣል ኮሌጅን ጠቅሰው “ሁለቱም ፈጣን ውጤትን እያሳዩ ያሉ ተስፋ ሰጪ” ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ማት ሃንኮክ አክለውም መንግሥታቸው የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ቡድን ለሚያካሂደው የክትባት ሙከራ 20 ሚሊዮን ፓውንድ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሙከራውም በመጪው ሐሙስ በሰዎች ላይ እንደሚጀመር ገልጸዋል።

  8. ስድስት ናይጄሪያውያን ጋና ውስጥ በልደት በዓል ላይ በመገኘታቸው ተቀጡ

    ቅዳሜ ዕለት ስድስት ናይጄሪያውያን መሰብሰብ በተከለከለባት የጋና ዋና ከተማ አክራ የልደት ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘታቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ።

    ናይጄሪያውያኑ በልደት በዓሉ ላይ በመገኘታቸው ፍርድ ቤቱ ስድስቱም ጥፋተኛ ናቸው ሲል 2000 ዶላር ቀጥቷቸዋል።

    ናይጄሪያውያኑ ይህንን የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት መክፈል የማይችሉ ከሆነ አምስት ዓመት እንዲታሰሩ ተወስኗል።

    በአክራ በልደት በኣሉ ላይ ቢያንስ 50 ሰዎች መገኘታቸው ተገልጿል።

    ፖሊስ መያዝ የቻልኩት ስድስቱን ብቻ ነው ያለ ሲሆን ቀሪዎቹ ማምለጣቸው ተነግሯል።

    በአክራ የመሰብሰብ ክልከላውን ጥሰው የተገኙ ሌሎችም ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

    ጋና የእንቅስቃሴ ገደቡን ብታነሳም አሁንም ግን መሰብሰብ እንደተከለከለና ትምህርት እንደተዘጋ ነው።

    የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት የአገሪቱ ድንበሮች ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።

    በጋና በኮቪድ-19 የተያዙ 1,042 ሰዎች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ መሞታቸው ተገልጿል።

  9. ኡጋንዳ ድንበሯን ብትዘጋም አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ ነው

    ኡጋንዳ ሁለት በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ማግኘቷን አሳውቃለች።

    ከነዚህም መካከል አንዱ የብሩንዲ ዜግነት ያለው ስደተኛ መሆኑ ተገልጾ፣ በታንዛኒያ በኩል ወደ አገሪቱ የገባ ነው ተብሏል።

    ኡጋንዳ የገባው ከ10 ቀናት በፊት ሲሆን ምርመራው ሲደረግለት በለይቶ ማቆያ ውስጥ ነበር።

    ኡጋንዳ ድንበሯን የዘጋችው ከወር በፊት ቢሆንም ፖሊስ ሁሉንም መግቢያ በሮች መቆጣጠር ያዳግተዋል እየተባለ ነው።

    በርካታ ወደ ኡጋንዳ የሚገቡ ሰዎች በመንደሮች ውስጥ መደበኛ ያልሆነ የጉዞ መስመር እንደሚጠቀሙ ተገልጿል።

    ኡጋንዳ ባለፈው ሳምንት ድንበር አቋራጭ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርጋለች።

    ከምስራቅ አፍሪካ አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ያልጣሉ አገራት ብሩንዲ፣ታንዛንያ እና ደቡብ ሱዳን ብቻ ናቸው።

    ኡጋንዳ እስካሁን ድረስ 13,700 ሰዎችን የመረመረች ሲሆን 58 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

  10. ኦስትሪያ በግንቦት ወር ምግብ ቤቶችና ቡና ቤቶችን ለአገልግሎት ልትከፍት ነው

    የእንቅስቃሴ ገደብን በማላላት ጭምብል መጠቀምና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ግዴታ በተደረገባት ኦስትሪያ ባለፈው ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ሱቆች ሥራ እንዲጀምሩ ተደርገው ነበር።

    አሁን ደግሞ የአገሪቱ መራሔ መንግሥት ሴባስቲያን ኩርዝ እንዳሉት በኮሮናቫይረስ የሚያዙት ሰዎች ቀጥር እየቀነሰ የሚቀጥል ከሆነ በግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች እንደሚከፈቱ ገልጸዋል።

    አከላዊ ርቀትን መጠበቅን በተመለከተም በእነዚህ ስፍራዎች ምን ያህል ሊሰበሰቡ እንደሚችሉ ሰዎችና ሊኖራቸው የሚገባውን ርቀት የተመለከተ ማብራሪያ በሚቀጥለው ሳማንት ይሰጣል ተብሏል። በተጨማሪም የሚያስተናግዱ ሰራተኞች የአፍን የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል።

    የእምንት ተቋማት አገልግሎትም ይጀመራል የተባለ ሲሆን፤ ከግንቦት ወር ጀምሮ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ደረጃ በደረጃ ቀስ በቀስ መልሰው ይከፈታሉ።

    የአገሪቱ መሪ እንዳሉት ኦስትሪያ ከበሽታው ጋር ተያይዞ ወደ መደበኛ ህይወት በመመለስ በኩል እያወሰደችው ያለው እርምጃ ከሌሎች አገራት የፈጠነ ነው። ነገር ግን ወረርሽኙ መልሶ የሚያገረሽ ከሆነ መንግሥታቸው የተከፈቱት በሮች መልሰው እንዲዘጉ ያደርጋል ብለዋል።

  11. ቤት የመቀመጥ ገደቡን የተቃወሙ ሰዎች በኒጀር ታሰሩ

    በኒጀር የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጣለውን ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ ተቃውመው አደባባይ ከወጡ ሰዎች መካከል አስሩ ታሰሩ።

    ኒጀራውያን የእንቅስቃሴ ገደቡን ተቃውመው ለበርካታ ቀናት ሰልፍ የወጡ ሲሆን ከፀጥታ ኃይሎች ጋርም ተጋጭተዋል።

    ከመሸ በኋላ መንቀሳቀስ የሚከለክለውንና በቤተ እምነቶች መሰብሰብ ያገደውን መመሪያ የተቃወሙ ወጣቶች መንገድ ዘግተው ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ነበር።

    ፖሊስ በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሜ ከ100 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።

    የአገሪቱ ባለስልጣናት እንዳሉት ሞተር ብስክሌቶች እየዞሩ ነዳጅ የያዘ ቆርቆሮዎችን ሲያድሉ የነበረ ሲሆን በርካታ ቤቶችና ንብረቶችም በእሳት ወድመዋል።

    እሁድ እለት ፖሊስ በዋና ከተማዋ በመስጂድ ውስጥ ፀሎት ለማድረግ እየተዘጋጁ የነበሩ የዋና ከተማዋ ነዋሪዎችን በአስለቃሽ ጋዝ በትኗቸዋል።

  12. በአሜሪካ ነርሶች ከዋይት ሐውስ ፊት ለፊት ሰልፍ አካሄዱ

    በአሜሪካ የብሔራዊ ነርሶች ኅብረት ማህበር አባላት ከፕሬዝዳንቱ ጽህፍት (ዋይት ሐውስ) ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ አካሄዱ።

    የሰልፋቸው ምክንያት የግዛቶች አስተዳዳሪዎችና የፌደራል መንግሥቱ ባለስልጣናት ወረርሽኙን ለመከላከል እየሰሩ ላሉ የህክምና ባለሙያዎች በቂ የሆነ የመከላከያ ቁሳቁስ እንዲቀርቡ ለመጠየቅ ነው።

    ወረርሽኙን ለመከላከል እየሰሩ ያሉ ነርሶች፣ ዶክተሮች፣ የጤና እንክብካቤ ሠራተኞች በአጠቃላይ የሕክምና ባለሙያዎች የሚያደርጉትን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም ሌሎች የመከላከያ ቁሳቁሶች "አሁኑኑ እንዲሟላልን እንጠይቃለን" ብለዋል።

    "ካልተከላከላችሁን ታካሚውን መከላከል አንችልም" የሚለ መፈክርም አሰምተዋል።

    ሰልፈኞቹ በኮቪድ-19 ተይዘው ሕይወታቸውን ያጡ ነርሶችና ዶክተሮችን ምስል ይዘው ታይተዋል።

    ማኅበሩ 150 ሺህ ነርሶችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን በአሜሪካ የተመዘገቡ ነርሶችን በአባልነት የያዘ ትልቁ ማኅበር ነው ተብሏል።

  13. በአለማችን በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ከሆነ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,494,915 ደርሷል።

    ከዚህ ቁጥር ውስጥ ደግሞ 171,152 ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቧል።

    የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን የሚያስከትለው ይህ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በፈረንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ነበር። በየደቂቃው በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች አሁናዊ መረጃ

  14. ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተዘጋጁ ድረገጾች የትኞቹ ናቸው?

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቴክኖሎጂ በመታገዝ የከፍተኛ ትምህርትን ለማስቀጠል ያዘጋጃቸውን ድረ ገጾች ይፋ አደረገ።

    ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት የሁሉም ትምህርት አይነቶች ሞጁሎች፣ አጋዥ ንባቦች እና ሌሎችም በየትምህርት አይነቱ ተሰንደው የሚገኙባቸው ድረ ገጾች የማሟላት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጿል።

    በዚህም የተነሳ http://ndl.ethernet.edu.et/ በተሰኘው ድረገጽ የተዘጋጁ የኮርስ ማቴሪያሎችና አጋዥ የትምህርት መጽሃፍት ተደራሽ የሚሆኑበት የዲጂታል ላይብረሪ ዝግጁ መደረጉን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

    አክሎም ይህ ድረገጽ (http://ndl.ethernet.edu.et/) አስፈላጊ በሆኑ የትምህርት ይዘቶች እየበለፀገ ይገኛል ብሏል።

    እንዲሁም ሚኒስቴሩ በርካታ ይዘቶችን የያዘ የTechIn ላይብረሪዝግጁ (http://library.techin.et/) መሆኑን አስታውቋል።

    ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኦንላይን ትምህርት መስጠት የሚያስችላቸው የLearning Management System/MOOCS (https://courses.ethernet.edu.et/) ዝግጁ መደረጉንም በመግለጫው ላይ አመልክቷል።እንዲሁም ተማሪዎች ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው በመሆኑ በስልክም ይሁን በላፕቶፕ እንዲሁም በታብሌት ወደ ተዘጋጁት ድረገጾች ገብተው በሚያነቡበት ጊዜ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን ገልጿል።

    የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸዉ ጋር የሚገናኙበት የኦንላይን የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማድረግ፣ ማንኛዉንም ሰነዶችን ማጋራት ሌሎችንም የቨርቹዋል ግንኙነቶች ማድረግ የሚያስችል የO.365 Teams ቴክኖሎጂ ዝግጁ መደረጉንም አሳውቋል።

  15. በኮሮና ምክንያት ለረሃብ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል ተባለ

    የተባበሩት መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለከፋ ረሃብ የሚጋለጡ ሰዎችን ቁጥር በእጥፍ ሊጨምረው ይችላል ሲል አስጠነቀቀ።

    በተለይም በደቡብ ሱዳንና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላሉ ሕዝቦች ያለውን ስጋት ገልጿል።

    የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዳለው ቫይረሱ ድሮም ሕይውታቸው ከእጅ ወዳፍ ለነበሩ ሰዎች የከፋ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲል ገልጿል።

    ድርጅቱ ባጠናቀረው ሪፖርት ባለፈው አመት በዓለማችን በረሃብ የተጠቁ 135 ሚሊየን የዓለማችን ሕዝቦች መኖራቸውን አስታውሶ፣ ዘንድሮ ይህ ቁጥር ወደ 250 ሚሊየን ከፍ ሊል ይችላል ብሏል።

    እነዚህ በረሃብ ሊጠቁ ይችላሉ የተባሉ ሕዝቦች የሚገኙት በግጭት በሚታመሱ፣ በምጣኔ ሃብት ድቀትና በአየር ንብረት ለውጥ በተጠቁ 10 አገራት እንደሆነም ተጠቅሷል።

    እነዚህ አገራትም የመን፣ ሶሪያ፣ደቡብ ሱዳን፣ ኮንጎ፣ ቬንዝዌላ፣ ሃይቲ እና አፍጋኒስታን ናቸው።

  16. የነዳጅ ዋጋ መውደቅ ምርቱን በነጻ እንድናገኝ ያስችለናል?

  17. በስፔን ዝነኛው የኮርማ ትግል ፌስቲቫል ተሰረዘ

    በስፔን በመጪው ሐምሌ ወር ይካሄድ የነበረው ዝነኛው ሳን ፈርሚን " ኮርማ ሰዶ የማሳደድ ፌስቲቫል" በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ፍራቻ ተሰርዟል።

    በስፔን የበጋ ወራት "ኮርማን ሰዶ የማሳደድ" ጨዋታ እጅግ የሚወደድ ነው።

    በስፔን ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ፓፕሎና በምትገኘው ለሳምንት ያህል የሚካሄደው ይህ ፈርሚን ፌስቲቫል በየዓመቱ በርካታ ሰዎች ከኮርማ ጋር በሚያደርጉት ትግል ተወግተው አንዳች ጉዳት ይደርስባቸዋል።

    " እንደሚታወቀው እጅግ በጣም አዝነናል" ብለዋል የፓፕሎና ጊዜያዊ ከንቲባው አና ኤሊዛልዴ። ይህ የኮርማ ትግል ፌስቲቫል በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች አሉት።

    በአውሮፓ ቱሪስቶችን በመሳብ ሁለተኛው መሆኑ የሚነገርለት ይህ ፌስቲቫል መሰረዙ የተነገረው የጀርመን የቢራ ጠጪዎች ፌስቲቫል መሰረዙ ከተነገረ በኋላ ነው።

    ይህ የቢራ ጠጪዎች ፌስቲቫል ስድስት ሚሊየን ቢራ ጠጪዎች ወደ ሙኒክ ቢራ የተጠማ ጉሮሯቸውን ይዘው የሚተሙበት ሲሆን አሁን ግን ኮሮና እስኪያልፍ የቢራው ድግስ ተሰርዟል።

  18. ቦሪስ ጆንሰን ንግስቲቱን ሊያነጋግሩ ነው

    በኮቪድ-19 መያዛቸው ከታወቀ በኋላ ሆስፒታል ገብተው ያገገሙት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ንግሥቲቱን በዚህ ሳምንት በአንዱ ቀን እንደሚያነጋግሩ ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።

    ቦሪስ ጆንሰን ንግሥቲቱን የሚያነጋግሩት በስልክ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ይህም ከታመሙ ወዲህ በሶስት ሳምንት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

    በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ይደውላሉ ተብሏል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንዳለው ቦሪስ ጆንሰን ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚደውሉት በአሁኑ ሰአት የቡድን 7 አባል አገራትን የምትመራው አሜሪካ በመሆኗና ከኮሮና ጋር በተያያዘ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን ለመስማት ሲሆን በተጨማሪም ታምመው በነበሩበት ወቅት " ለላኩት የአጋርነትና የመልካም ምኞት መግለጫ" ለማመስገን መሆኑ ተገልጿል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም "ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያገገሙ ሲሆን ወደ መደበኛ ስራቸው አልተመለሱም" ብለዋል።

    ጠቅላዩ ከጽህፈት ቤታቸው " በኮሮናቫይረስ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ይከታተላሉ፤ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ከሌሎች አባላት ጋር ተነጋግረዋል" ብለዋል።

  19. የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ተከትሎ አለም አቀፍ የምግብ ቀውስ እንዳይከሰት አገራት ሊሰሩ እንደሚገባ ተዋናዩ ኢድሪስ ኤልባ ጥሪ አቅርቧል።

    የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር የሆነው ተዋናይ አርባ ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣ ወጪ አለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ እንዳቋቋመ በትናንትናው እለት ይፋ አድርጓል።

    ይህም ገንዘብ በአለም ላይ ላሉ አርሶ አደሮች በወረርሽኙ ወቅት ድጋፍ ለማድረግ ይውላል ተብሏል።

    "ምግብ ለሰው ልጅ መሰረታዊና አስፈላጊ ነው። በዚህ ወረርሽኝ ወቅት አርሶ አደሮች ማረስ ካልቻሉ የምንበላው ምግብ እንደሚያልቅና የሰው ልጅ ህልውናም ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ መረዳት አለብን" ብሏል።

    ኢድሪስና ሞዴል ባለቤቱ ሳብሪና ዶውሪ ኤልባ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ ከባለፈው ወር ጀምሮ ለንደን በሚገኘው ቤታቸው በለይቶ ማቆያ ይገኛሉ።

    መካከለኛ ምልክት ታይቶባቸው የነበረ ሲሆን በህይወት መትረፋቸውን አመስግነው ይህንን ፈንድም ለማቋቋም ያነሳሳቸው ይኸው መሆኑን አስረድተዋል።

    በዚህ ወቅት የሰው ልጅ ሊረዳዳ ይገባል ያሉት ባልና ሚስቱ 200 ሚሊዮን ዶላር የማሰባሰብ እቅድም እንዳላቸው ገልፀዋል። ገንዘቡም በአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካና መካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ አርሶ አደሮችን ለመደጎም ይውላልም ተብሏል።

    እነዚህ አርሶ አደሮች ክፉኛ በቫይረሱ ሊጎዱ እንደሚችሉ የተጠቆመ ሲሆን የጤናቸውም ሁኔታ ድጋፍ ያሻዋል።

    የቫይረሱን መዛመት ከመከላከል ጎን ለጎን ኮሮና ሊያስከትለው የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊታሰብበት እንደሚገባም ጠቆም አድርገዋል።

    "ሁላችንም ቢሆን የዚች አለም አካል ነን፤ የምንኖረው በዚችው በአንድ አለም ነው። የወደፊቱንም በማሰብ መረዳዳት አለብን፤ ይህም የብዙ ሰዎችን ህይወት ይታደጋል" በማለት ተዋናዩ ለቢቢሲ አስረድቷል።

  20. የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኛ የኮቪድ-19 ናሙና ሲሰበስቡ ተገደሉ