በዓለም ላይ ያሉ የኦሮቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል አከባበር

በዛሬው ዕለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሳኤ በዓል ይከበራል። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ አብይ በሆነው የትንሳኤ በዓል ብዙ ኢትዮጵያዊ በጉንም፣ ዶሮውን በቻለው አቅሙ ያርዳል። ዘመድ ለዘመድ መጠያየቅም ሆነ ከጎረቤት ጋር በአንድ ማዕድ መቋደስ፣ መጎራረረስ የበዓሉ አንድ ኣካል ነው። የኮሮናቫይረስ ስጋት ለዓለም ጠንቅ በሆነበት በዚህ ወቅት ከንክኪ ጋር የተገናኙ ልማዶችን ማስቀረት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በተቻለ መጠን ሰብሰብ ብሎ በዓሉን ከማክበር መታቀብም ይመከራል። በሽታውን አካላዊ ርቀታችንን በመጠበቅ፣ መሰባሰባችንን በመቀነስ፣ እጃችንን በሚገባ በመታጠብ እንከላከል። መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆን እየተመኘን የቀጥታ ዘገባችንን ከዚህ ገጽ ላይ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጀርመን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መቆጣጠሯን ገለጸች

    ጀርመን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የጀርመን ጤና ሚኒስትር የንስ ስፓን በአገራቸው በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ማሳየቱን ተከትሎ አገራቸው ወረርሽኙን መቆጣጠሯን ተናገሩ።

    ሚኒስትሩ እንዳሉት ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከበሽታው የሚያገግሙት በበሽታው ከሚያዙት ሰዎች ቁጥር በቋሚነት እየጨመረ መሄዱ የእንቅስቃሴ ገደቡ ውጤታማ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።

    "ዛሬ ወረርሽኙ መቆጣጠር የሚቻል መሆኑን ተገንዝበናል" ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ሚኒስትሩ የአገራቸው የጤና እንክብካቤ ሥርዓት እስካሁን በወረርሽኙ ምክንያት ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር እንዳላጋጠመው ተናግረዋል።

    በጀርመን የበሽታዎች መቆጠጠሪያ ተቋም ይፋ የተደረገ አሃዝ እንዳመለከተው በወረርሽኙ የተያዘ አንድ ሰው በሽታውን የማስተላለፍ አቅሙ ከአንድ በታች እንደሆነ ተገልጿል።.

    ጀርመን የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ባካሄደችው ከፍተኛ ምርመራ አድናቆትን ያገኘች ሲሆን፤ በዚህም 138 ሺህ የሚጠጉ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሲገኙ 3,868ቱ ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያመለክታል።

  2. "አምላክን እንጂ ኮረናቫይረስን አንፈራም"

    ቤተ ክርስቲያን ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በበርካታ አገራት አማኞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት በቤተ ዕምነቶች ተሰብስበው ጸሎትና ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችን እንዳይፈጽሙ ተከልክለዋል። ነግር ግን ይህ ሁሉም ቦታ እየተከበረ ያለ አይደለም።

    በተባበሩ መንግሥታት ድርጅት የእምነት ነጻነት ተሟጋች ዶክትር አህመድ ሻሂድ መንግሥታት አንዳንድ የእምነት መለገጫዎችን ለምዕመኑ ጤና ሲሉ ሊሽሯቸው ግድ ይላል፤ ይህም የዓለም አቀፍ ሕግ ድጋፍ አለው ይላሉ።

    ዶ/ር አሕመድ በተለይ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ የእምነት አባቶች ምዕመኖቻቸው ርቀታቸውን እንዲጠብቁ የማበረታታትና የማሳመን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

    ጨምረው እንደሚሉትም የዕምነት ተቋማት ምዕመናን የማኅበረሰቡን ጤና ከሚያቃውሱ ተግባራት እንዲጠበቁ የማሳመን የሕግ ባይሆንም የሞራል ግዴታ አለባቸው። ዝርዝሩን ለማንበብ፡ "አምላክን እንጂ ኮረናቫይረስን አንፈራም"

  3. ጉግል፡ “በየቀኑ 18 ሚሊዮን ሐሰተኛ ኢሜሎች ይላካሉ”

    ሐሰተኛ ኢሜል

    የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች (Scammers) በየቀኑ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ 18 ሚሊዮን ሐሰተኛ ኢሜሎችን ለጂሜል ተጠቃሚዎች እየላኩ መሆኑን ጉግል ገለጸ።

    መዝባሪዎቹ፤ ሰዎች ግላዊ መረጃቸውን እንዲሰጡ አታላይ መልዕክት እየላኩ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል። ከነዚህ ኢሜሎች መካከል ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከተለያዩ አገራት የመንግሥት አካላት የተላኩ እንዲመስሉ በአጭበርባሪዎች የተጻፉት ይጠቀሳሉ።

    ጉግል በአንድ ቀን 100 ሚሊዮን ሐሰተኛ ኢሜሎችን አግዷል። ባለፈው ሳምንት ከተላኩ ሐሰተኛ መረጃ የያዙ ኢሜሎች አንድ አምስተኛው ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ናቸው።

    የቴክኖሎጂ ተቋሞች እንደሚሉት ከሆነ ቫይረሱ ሰዎችን ለማጭበርበር ከዋሉ ርዕሰ ጉዳዮች ግንባር ቀደሙ ሆኗል።

    በመላው ዓለም ጂሜል የሚጠቀሙ ሰዎች 1.5 ቢሊዮን ይሆናሉ።

  4. በሲንጋፖር በሠራተኞች የጋራ መኖሪያ ወረርሽኙ በስፋት እተሰራጨ ነው

    የኮሮናቫይረስ ምርመራ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሲንጋፖር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመቆጣጠር ረገድ ስትመሰገን ነበር። አሁን ግን የተለያዩ አገራት ዜጎች በሚኖሩበት የጋራ መቆያ ውስጥ በሽታው ተሰራጭቷል።

    ወደ 300 ሺህ የሚደርሱ ዝቅተኛ ተከፋዮች በሲንጋፖር ይኖራሉ። ከነዚህ አብዛኞቹ ከደቡብ እስያ የሄዱ ሲሆን፤ በጥገናና በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

    ሠራተኞቹ በአብዛኛው የሚኖሩት በትልልቅ የጋራ መኖሪያዎች ውስጥ ነው። በአንድ ክፍል እስከ 17 የሚደርሱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

    በእነዚህ የጋራ መኖሪያዎች የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ መጥቷል። ወደ መኖሪያዎቹ ማንም እየገባ፣ እየወጣም አይደለም። ስለዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተፋፈገ ክፍል መውጣት አልቻሉም።

  5. ኮቪድ-19፡ ፋሲካና የአውሮፓ አገራት አዳዲስ ውሳኔዎች

    የቡልጋሪያ ቤተ ክርስቲያን

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ቡልጋሪያ፡ ፋሲካን በማስታከክ የሚጨምረውን የዜጎች እንቅስቃሴ ለመገደብ፤ ከትላንት እኩለ ለሊት ጀምሮ በመዲናዋ ሶፊያ እንቅስቃሴ እንዲቆም ተወስኗል።

    ግሪክ፡ ዜጎች ለፋሲካ ወደ ቤተ ክርስቲያን እና ወዳጅ ዘመድ ጥየቃ እንዳይሄዱ ለመከላከል ወደ አስር ሺህ የሚደርሱ ፖሊሶች ተሰማርተዋል። እስካሁን በአገሪቱ በበሽታው የሞቱት 105 ሰዎች ሲሆኑ፤ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ባደረገችው ጥረት ግሪክ እየተመሰገነች ነው።

    ዴንማርክ፡ ከሰኞ ጀምሮ የጥርስና የዓይን ሀኪሞች፣ የመንጃ ፍቃድ ትምህርት ቤቶችና የውበት ሳሎኖች እንዲከፈቱ ይፈቀዳል ተብሏል። ከሌሎች የአውሮፓ አገራት አንጻር የእንቅስቃሴ እገዳውን ፈጥና ያላላችው ዴንማርክ ናት።

    ስዊድን፡ አሁንም ድረስ ካፌ እና ሬስቶራንቶች አልተዘጉም። እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት የዜጎችን እንቅስቃሴ እንደማይገታም መንግሥት አስታውቋል።

    ቤልጄም፡ ባለፉት 24 ሰዓታት 313 ሰዎች ሞተዋል። ይህም የሟቾችን ቁጥር 5,163 አድርሶታል። ከሞቱት ሰዎች ግማሹ በአረጋውያን ማቆያ የነበሩ ናቸው።

    ሩስያ፡ 4,070 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እና 41 ሞት ተመዝግቧል። ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድን ለመዘከር የተዘጋጀ ትዕይትን አግደዋል።

  6. አምስት የሆቴል ሠራተኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ኬንያ አስታወቀች

    በኬንያ ከተማዋን የማፅዳት ሰራ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዛሬው እለት በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጡ አስራ ሁለት ኬንያውያን መካከል አምስቱ የሆቴል ሠራተኞች መሆናቸውን የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ሙታይ ካግዌ አስታውቀዋል።

    ሚኒስትሩ ዛሬ ጠዋት ብቻ በተደረው 450 ምርመራዎች አስራ ሁለት ሰዎች መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ እስከ ምሽት ባለው ምርመራ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል አመላክተዋል።

    ኬንያ ዓለም አቀፍ በረራዎችን እንዲሁም አየር ማረፊያዋን ከመዝጋቷ በፊት ከውጭ ለሚገቡ መንገደኞች በመዲናዋ ናይሮቢ የሚገኙ ሆቴሎች በለይቶ ማቆያነት እያገለገሉ ነበር።

    በለይቶ ማቆያ ከነበሩት መንገደኞች መካከል በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ቢኖሩም በአሁኑ ሰዓት በበሽታው የተያዙት ሰዎች በለይቶ ማቆያ ሆቴሎች ይሰሩ የነበሩ መሆናቸው አልተገለፀም ።

    አገሪቷ የመመርመር አቅሟን በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመር እቅድ እንዳለት የተናገሩት ሚኒስትሩ በተለይም በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ መመርመር የቫይረሱን መዛመት ይቀንሰዋል ብለዋል።

    ኬንያ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔ ባታስተላልፍም የሰዓት እላፊን ጨምሮ፣ መጠጥ ቤቶችና የምሽት ክበቦች እንዲዘጉ እንዲሁም ከናይሮቢ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ላይ ገደብ ጥላለች።

    እስካሁን ባለው መረጃ በኬንያ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 246 ደርሷል።

  7. አፍሪካ ቀጣይዋ የኮቪድ-19 ወረርሽኘ ማዕከል ልትሆን ትችላለች-የዓለም ጤና ድርጀት

  8. ሰበር, አራት ተጨማሪ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

    የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ከበደ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው አራት ተጨማሪ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ሚኒስቴሩ ባለፉት 24 ሰዓታት 842 ምርመራዎች ማድረጉን ገልጾ ከእነዚህም መካከል አራት ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ብሏል።

    በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት መካከል ሶስቱ ሰዎች ከዱባይ የመጡና በለይቶ ማቆያ የነበሩ ሲሆኑ አንዱ ግን ገና እየተጣራ ነው ተብሏል።

    በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 96 ደርሷል።

  9. የትራንስፖርት ሚኒስቴር የተለያዩ መመሪያዎችን አወጣ

    ተሽከርካሪ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፤ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለዉን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም በሚኒስትሮች ኮሚቴ የወጣ የትራንስፖርት ዘርፍ አፈፃጸም መመሪያ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።

    በዚሀም መሠረተ፤ አዉቶቢሶች፣ ታክሲዎች፣ የግል ተሸከርካሪዎች፣ የመንግስት ተሸከርካሪዎች እንዲሁም የአዲስ አበባም ሆነ የኢትዮ-ጅቡቲ የመንገደኞች የባቡር ትራንስፖርት በህግ ከተፈቀደላቸዉ የሰው ብዛት 50% ብቻ እንዲጭኑ ተወስኗል።

    ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች መጫን የሚችለት ከአሽከርካሪው በተጨማሪ አንድ ሠው ብቻ ሲሆን ባለሁለት እግር የሞተር ወይም ሞተር አልባ ሳይክሎች ከአሽከርካሪው ሌላ ምንም ሰው መጫን እንደማይፈቀድላቸዉ ተገልጿል።

    በተጨማሪም የጭነት ተሽከርካሪዎች መጫን የሚፈቀድላቸው ከአሽከርካሪው በተጨማሪ አንድ ሠው ብቻ ነው።

    ማንኛውም አገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት ደግሞ አገልግልት መስጠት የሚችለዉ ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ባለዉ ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው።

    የግል ወይም የቤት ተሸከርካሪዎችን መጠቀም የሚቻለዉ የሠሌዳቸዉ የመጨረሻ ቁጥር ሙሉ ወይም ዜሮ የሆኑት ዛሬ አርብ ሚያዚያ 09/08/12 ሲሆን በቀጣዩ ቀን የሠሌዳቸዉ የመጨረሻ ቁጥር ደግሞ ጎዶሎ የሆኑት ነገ ቅዳሜ የሚንቀሳቀሱ ይሆናል ተብሏል።

    የፌደራል ሠራተኞች የሥራ መግቢያ ሰዓት ከጠዋቱ 1፡30 ሲሆን ከስራ መውጫ ሰዓት ደግሞ ከቀኑ 9፡30 ይሆናል።

  10. የበዓል ገበያዎች በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች

  11. የበዓል ገበያዎች በምስል

    አፍና አፍንጫዋን በሻርፕ የሸፈነች ሴት
    የምስሉ መግለጫ, በአዲስ አበባ ለስቅለት በዓል የተለያዩ ነገሮችን ለመሸማመት የወጡ ገበያተኞች ቸፍና አፍንጫቸውን በሻርፓቸው ሸፍነው ታይተዋል

    ቢቢሲ ቅኝት ባደረገባቸው አዲስ አበባ፣ ባህርዳርና ሰሜን ሸዋ የሚገኙ የገበያ ስፍራዎች ገበያተኞች ራሳቸውንና ሌሎችን ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ የተለያዩ ርምጃዎችን ሲወስዱ ተመልክቷል።

    እጇ ላይ ጓንት በማጥለቅ ዶሮ ለመግዛት የምትነጋገረ ገበያተኛ
    የምስሉ መግለጫ, በገበያ ስፍራ የሚኖር ንክኪን ለመቀነስ እጃቸው ላይ ጓንት ያጠለቁ ገበያተኞች ነበሩ

    በተለያዩ የገበያ ስፍራዎች አንዳንዶች የግላቸውን ትንቃቄ አድርገው ቢስተዋልም በርካቶች ግን መዘናጋታቸውን ቢቢሲ ታዝቧል።

    በአዲስ አበባ ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኝ ገበያ
    የምስሉ መግለጫ, በአዲስ አበባ በጃንሜዳ አካባቢ የሚገኝ የገበያ ስፍራ

    ይህ የበዓል ገበያ በባህርዳርም በተመሳሳይ መልኩ ሞቅ ያለ ቢሆንም በጥንቃቄ ረገድ ግን መዘናጋት የተስተዋለበት ነው።

    በባህር ዳር ከተማ የበዓል ገበያ

    የፎቶው ባለመብት, bb

    የምስሉ መግለጫ, በባህርዳር ከተማ የሚታየው የበዓል ገበያ መጠጋጋት የታየበት ነበር
  12. በዓለም ላይ ያሉ የኦሮቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል አከባበር

  13. በደቡብ አፍሪካ የሟቾች ቁጥር 48 ደረሰ

    የህክምና ባለሙያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተጨማሪ 14 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የሟቾች ቁጥር 48 መድረሱ ተገልጿል።

    የጤና ሚኒስትሩ ዝዌሊ ምኪዜ እንደገለጹት ሊምፖፖ እና ምስራቃዊ ኬፕታውን ግዛቶች በቫይረሱ የመጀመሪያውን ሞት አስመዝግበዋል።

    የክዋላዙሉ ናታል ግዛት ደግሞ 20 በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን በማስመዝገብ ከፍተኛ ዜጋ የሞተባት ግዛት ሆናለች።

    ደቡብ አፍሪካ እስካሁን 2606 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጣለች።

    በአሁኑ ሰአት አገሪቱ እስከያዝነው ወር መጨረሻ ድረስ ሙሉ እንቅስቃሴ የተከለከለ ሲሆን ከ95 ሺ በላይ ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

    በዓለማችን ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ከወሰዱ አገራት አንዷ መሆን በቻለችው ደቡብ አፍሪካ ከቤት ውጪ አካላዊ እንቅስቃሴ እንኳን ማድረግ አይቻልም።

    የአልኮል መጠጦች አይሸጡም፣ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ከቤት መውጣትም ክልክል ነው።

  14. የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ህዝባቸው ስለኮቪድ-19 እንዲፀልይ ጠየቁ

    በታንዛንያ በቤተ እምነቶች መሰባሰብ አልተከለከለም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የአገራቸውን ሕዝቦች ስለኮሮናቫይረስ ለሶስት ቀን ፀሎት እንዲያደርጉ ጠየቁ።

    ፕሬዝዳንቱ ለህዝባቸው ጥሪ ያቀረቡት በትዊተር ገጻቸው በኩል ሲሆን የፀሎት ስነስርዓቱ በአብያተክርስትያናት ይካሄድ ወይንም ምዕመናን በያሉበት ይፀልዩ የታወቀ ነገር የለም።

    ፕሬዝዳንቱ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆኑ በትዊተራቸው ላይ “የአገሬ ሕዝብ ሆይ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከአርብ እስከ እሁድ ድረስ፣ ወደ ፈጣሪ ከዚህ ወረርሽኝ እንዲያድነን እንድትፀልዩ እጠይቃለሁ፤ ሁላችንም በየእምነታችን እንፀልይ፤ ይሰማናል” ብለዋል።

    በታንዛኒያ በሃይማኖት ስፍራዎች መሰባሰብ አልተከለከለም።

    ነገርግ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

    በታንዛኒያ እስከዛሬዋ እለት ድረስ 94 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አራት ሰዎች ሲሞቱ 11 ደግሞ አገግመዋል።

  15. ቻይና በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን አልደበኩም አለች

    ቻይና በኮሮናቫይረስ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ቀንሳ ሪፖርት አድርጋለች መባሉን አጣጣለች።

    በቫይረሱ የሞቱም ሆነ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ቀንሰን ሪፖርት አላደረግንም ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባዩ።

    ቻይና በዉሃን በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በ50 በመቶ ከፍ ማደረጓ ይታወሳል። በዚህም በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በ1290 ከፍ ብሏል።

    ቃል አቀባዩ ዛሆ ሊጂዓን የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር ማስተካከያ ማድረግ ዓለም አቀፋዊ የስታትስቲክ አሰራር ነው ስለማለታቸው ሬውተርስ ዘግቧል።

  16. "ያስጨነቀኝ ከእኔ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ጤንነት ነበር" የኮሮናቫይረስ ታማሚዋ ከባህር ዳር

  17. ቱኒዚያ የፀጥታ አስከባሪ አካላትን ኮሮና ሊያስይዙ አሲረዋል ያለቻቸውን በቁጥጥር ስር አዋለች

    ቱኒዚያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚል በዜጎቿ ላይ የጣለችው የእንቅስቃሴ ገደብ ከሳምንት በኋላ ያበቃል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቱኒዚያ አገር ውስጥ ሚኒስቴር የጸጥታና ደህንነት ሰራተኞችን ኮሮናቫይረስ ሊያስይዙ ነበር ያላቸውን ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

    በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሁለት ሰዎች መካከል አንዱ የእስላማዊ ቡድን አባል ነው ተብሏል።

    ግለሰቡ በቅርቡ ከእስር ቤት የወጣ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የፖሊስና የደህንነት አባላት ላይ ሄደው እንዲያስሉ አበረታቷል ሲል ከስሶታል።

    ሚኒስቴሩ ሌላኛው ግለሰብ ሆን ብሎ እየዞረ ሲያስል ነበር በሚል ለሚኖርበት አካባቢ ፖሊስ ጣብያ ሪፖርት መደረጉን ጨምሮ አስታውቋል።

    ግለሰቡ ከዚህ ቀደምም በክትትል ላይ የነበረ ነው የተባለ ሲሆን ኮሮናቫይረስ አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ገና በምርመራ ላይ ያለ ነው።

    ቱኒዚያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚል በዜጎቿ ላይ የጣለችው የእንቅስቃሴ ገደብ ከሳምንት በኋላ ያበቃል።

  18. በባህር ዳር ከተማ የተደረገ የበዓል ገበያ ቅኝት

    የበዓል ገበያ በባህር ዳር

    የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ በሆነቸው ባህር ዳር ያለውን የፋሲካ በዓል የገበያ ሁኔታ ለመቃኘት የቢቢሲ ሪፖርተር በከተማዋ የተለያዩ የገበያ ቦታዎች ተዘዋውሯል።

    በባህር ዳር ለሁለት ሳምንት ያህል በሰውም ሆነ በተሽከርካሪ እንቅስቀሴ ላይ የተጣለው እገዳ ከተነሳ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑ ነው።

    ከእገዳው በፊት ከነበረው በተሻለ ብዙ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ለብሰው ይንቀሳቀሳሉ። በታክሲዎችም ሆነ በባጃጆች የሚጫነው የሰው ቁጥር በግማሽ ቀንሷል።

    በዋናው የገበያ ቦታ እንደዚህ ቀደሙ የሰው ቁጥር በብዛት ባይኖርም የበዓል ግብይቱ ግን ሞቅ ብሏል።

    በተለይ ለበዓል የሚሆኑ ነገሮች የሚሸጡበት አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነው። ዶሮ፣ እንቁላል፣ በግ እና ቅቤ መሸጫዎች ደግሞ ብዙ ሰዎች የተገኙበት ነው።

    በዋናው ገበያ እንደዚህ ቀደሙ መግቢያ መውጫዎቹ ላይ የነበሩ ነጋዴዎች ወደ ገበያው መሃል እንዲገቡ ተደርጓል።

    ነጋዴዎቹ በሚቀመጡበት መካከል ለመንቀሳቀስ የሚያስችል መንገድ ቢኖርም ነጋዴዎቹ እርስ በርስ ተጣብቀው በሚባል ደረጃ ነው የተቀመጡት።

    በከተማዋ የፊት እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያደረጉ ሰዎች ቁጥር ከፍ ቢልም በተለይ ነጋዴዎች ይህንን ሲያደርጉ ብዙም አይስተዋልም።

    የበዓል ገበያ በባህርዳር

    በተለይም አነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ እና ቁጭ ብለው በሚነግዱ ሰዎችና ቆመው በሚገዙት መካከል የመጠበቅ ነገር ብዙም ስለማይታይ የትንፋሽ ልውውጥ የመኖር ዕድሉ ከፍ ይላል።

    አንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች የያዙትን ዕቃ ሸጠው ከመጨረሳቸው የተነሳ መደርደሪያቸው ባዶ ሆኖ ይታያል።

    ነጋዴዎቹም ሰዉ የሚገዛውን ነገር ማወቅ ባለመቻላቸው መያዝ ያለባቸውን ዕቃ እንዳያውቁ እና ከአዲስ አበባ የሚጫንላቸው ዕቃ መቀነሱን በስፍራው ለተገኘው የቢቢሲ ሪፖርተር ነግረውታል።

    በከተማው የመንገድ ላይ ንግድ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለው ትርምስ እንደዚህ ቀደሙ ባይሆንም አሁንም ንግዱ ከመቀጠሉም በላይ ጥንቃቄ የጎደለው ጭምር ነው።

    የጀበና ቡና የሚሸጡ ሴቶች በገበያ ቦታዎቹ በብዛት ያሉ ሲሆን ቡናዎቹን የሚሸጡባቸው ሲኒዎችን ብዙዎች ስለሚጋሩት በንጽህናው ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል።

    የክልሉ መንግሥት የገበያ ቦታዎች ቁጥርን በማስፋት ጥግግቱን በመበተን የበግ፣ የፍየል፣ የከብትና ዶሮ አነስተኛ ገበያ በማመቻቸት፣ የቤት ለቤት አቅርቦት ላይ እየሠራ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

    በሁሉም የገበያ ስፍራዎች የሚደረገው ግብይት ላይ የሚስተዋለው ሌላ የጋራ ጉዳይ የወረቀት ገንዘብ ልውውጡ አሁንም ከፍተኛ መሆኑ ነው።

    የበዓል ገበያ በባህርዳር
  19. የአዛውንቶቹ ብርቱ ተጋድሎ በዩናይትድ ኪንግደም

    ማርጋሬት ፔይን

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ቤታቸውን ዘግተው ከተቀመጡ ሳምንታት አልፏቸዋል።

    ነገር ግን እግራቸው ቤት ቢሰበሰብም ልባቸው በቫይረሱ የታመሙትን ለማከም ላይ ታች የሚሉ ዜጎች ጋር የሆነ ሰዎች አልጠፉም።

    ለምሳሌ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተሳተፉትና እድሜያቸው የመቶን ጣሪያ ሊነካ ስንዝር ቀናት የቀራቸው ካፒቴን ሙር በቤታቸው ጓሮ ምርኩዛቸውን ተደግፈው መቶ ዙር ለመሮጥ መወሰናቸው የዜጎችን ልብና ቀልብ ሰርቆ ነበር።

    የእድሜ ባለፀጋው ካፒቴን በዚህ ተግባራቸው የ800 ሺህ ዎችን ቀልብና ኪስ ገዝተዋል። 17 ሚሊየን ፓውንድም ሰብስበው ለድጋፍ ይሁን ብለው አስረክበዋል።

    አሁን ደግሞ የ90 ዓመቷ ማርጋሬት ፔይን ከስኮትላንድ 282 ደረጃዎችን ለመውጣት ወስነው ምርኩዛቸውን አንስተዋል።

    ይህ ደረጃ 731 ሜትሮች የተገመተ ሲሆን ተራራ የመውጣት ያህል ነው ተብሏል።

    ይህንን ደረጃ ወጥቶ ለመጨረስ ሁለት ወር ይፈጅብኛል ብለው የገመቱት ወይዘሮዋ እሁድ ዕለት ጀምረው 10ሺህ ፓውንድ ማሰባሰብ ችለዋል።

    ወ/ሮዋ የተሰበሰበው ገንዘብ ለጤና ባለሞያዎች እርዳታ እንደሚውል ተናግረዋል።

  20. አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅትን መደገፍ ካቆመች አፍሪካ ያሰጋታል

    አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጀት የምታደርገውን ድጋፍ ካቆመች በአፍሪካ የሚሰሩ የተለያዩ የመከላከል ስራዎች አደጋ ይገጥማቸዋል ተባለ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጀት የምታደርገውን ድጋፍ ካቆመች በአፍሪካ የሚሰሩ የተለያዩ የመከላከል ስራዎች አደጋ ይገጥማቸዋል ተባለ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ ካቋረጡ በአፍሪካ የሚካሄዱ ፖሊዮን የማጥፋት ዘመቻዎች፣ የፀረ ኤች አይ ቪ ና የወባ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዱ ተገለፀ።

    የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ የበላይ ኃላፊ ማትሲዲሶ ሞዬቲ አሜሪካ የፕሬዝዳንትን ውሳኔ ዳግም እንድታጤነው ጠይቀዋል።

    የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን በኮንግረስ በኩል መጽደቅ አለበት።

    አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ድጋፍ አድራጊ ስትሆን በአሁኑ ወቅት ለሁለት ዓመት 151 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር።

    ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት 50 ሚሊየን ዶላሩን የተቀበለ ሲሆን ነገር ግን የትራምፕ ድጋፍ የማቋረጥ ውሳኔ በአህጉሪቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ይጎዳዋል ተብሏል።

    ከሚጎዱት ፕሮግራሞች መካከል አንዱ በተለያዩ አገራት የሚካሄዱ የመከላከል ስራዎች ናቸው።

    በአፍሪካ አሁንም 12 አገራት የፖሊዮ ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን ፖሊዮን ከአፍሪካ ለማጥፋትም በአህጉር ደረጃ እየተሰራ ነው።

    የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ከሚያካሄደው ስራ መካከል ደካማ የሆነውን የጤና ስርዓት መሆኑ ይታወቃል።

    የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 300 ሚሊየን ዶላር በጅቶ ነበር።

    በአፍሪካ በአሁኑ ሰዓት ወደ 18 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።