ምዕመናን ለምን በኮሮናቫይረስ ዘመን በቤተክርስቲያንና መስጊድ ውስጥ ካልተሰባሰብን ይላሉ?

አሜሪካ ውስጥ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በፋሲካ ወቅት ክፍት ክፍት ነበሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ውስጥ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በፋሲካ ወቅት ክፍት ክፍት ነበሩ
ታትሟል

በበርካታ አገራት አማኞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት በቤተ ዕምነቶች ተሰብስበው ጸሎትና ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችን እንዳይፈጽሙ ተከልክለዋል። ነግር ግን ይህ ሁሉም ቦታ እየተከበረ ያለ አይደለም።

በተባበሩ መንግሥታት ድርጅት የእምነት ነጻነት ተሟጋች ዶክትር አህመድ ሻሂድ መንግሥታት አንዳንድ የእምነት መለገጫዎችን ለምዕመኑ ጤና ሲሉ ሊሽሯቸው ግድ ይላል፤ ይህም የዓለም አቀፍ ሕግ ድጋፍ አለው ይላሉ።

ዶ/ር አሕመድ በተለይ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ የእምነት አባቶች ምዕመኖቻቸው ርቀታቸውን እንዲጠብቁ የማበረታታትና የማሳመን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ጨምረው እንደሚሉትም የዕምነት ተቋማት ምዕመናን የማኅበረሰቡን ጤና ከሚያቃውሱ ተግባራት እንዲጠበቁ የማሳመን የሕግ ባይሆንም የሞራል ግዴታ አለባቸው።

አምላክን እንጂ ኮረናቫይረስን አንፈራም

ምንም እንኳ በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን የፈረንጆቹን ፋሲካ በቤተ ክርስቲያን ሳይሰባሰብ ቢያከብርም በአሜሪካ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ግን ይህ አልሆነም።

የሉዊዚያና ፓስተር ቶኒ ስፔል እንደሚለው እርሱ በሚመራው የተበርናክል ቤተክርስቲያን በሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ተገኝተዋል። በሉዊዚያና ከ50 ሰዎች በላይ በአንድ ቦታ እንዳይሰባሰቡ ተከልኳል። ይህን ክልከላ ጥሰው ነው ምዕመናኑ የተገኙት።

ወደ ፓኪስታን ስናመራ በዚያ ከ5 ሰው በላይ ለጸሎት እንዳይሰባሰብ ቢባልም አብዛኛዎቹ የሙስሊም ሼኾች ይህንን መመሪያ ሲጥሱ ተስተውለዋል።

ፓኪስታን አሁን አንዳንድ መመሪያዎችን ማላላት ጀምራለች። ይህን ተከትሎ አንዳንድ የሐይማኖት አባቶች መጪውን የረመዳን ጾምን በማስመልከት ተሰባስቦ መጸለይ ይፈቀድ እያሉ ነው።

ፓኪስታን ውስጥ አንዳንዶች ለጸሎት ወደ መስጊዶች ሄደው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፓኪስታን ውስጥ አንዳንዶች ለጸሎት ወደ መስጊዶች ሄደው ነበር

ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን ነገሩን ከአገሪቱ የሐይማኖት አባቶች ጋር እመክርበታለሁ ታገሱኝ ብለዋል።

በፓኪስታን በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች መካከል ቀላል ቁጥር የማይባሉት ከመካ መዲና ጉብኝት ተመላሾች ናቸው። ሌሎች ደግሞ ተብሊግ አልጃምአት የሚባሉ የሰበካ (ዳእዋ) ጉባኤ አባላት ናቸው።

እነዚህ የተብሊግ አልጃምአት ጉባኤ አባላት በፓኪስታን ብቻ ሳይሆን በህንድ፣ በኢንዶኒዢያ እና በማሌዢያም ተህዋሲው እንዲስፋፋ ምክንያት ሆነዋል።

በደቡብ ኮሪያ በሺህ የሚቆጠሩ የተህዋሲው ተጠቂዎች ከሺንሾንጂ ቤተክርስቲያን የተያያዙ ናቸው። ይህ ምስጢራዊ መንፈሳዊ የክርስቲያ ቡድን ለኮቪድ-19 መስፋፋት ዋናውን ቦታ ይይዛል።

ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ የዚህ ቤተክርስቲያን አባላት ለመመርመር ፍቃደኛ አለመሆናቸው ነው። አባላቱም በይፋ እንዲታወቁ አይሹም። በዚህ ምስጢራዊነቱ ክንያትም አማኞቹ ቫይረሱን እንዳስፋፉት ይነገራል።

የዚህ ለየት ያለ የክርስቲያን ቡድን አባላት አመራሮች ለሆነው ነገር መንግሥትንና የደቡብ ኮሪያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ሳይንቲስቶችና የሕክምና ባለሞያዎች በቂ ርቀት ሳይጠብቁ መቆየትና በአንድ አካባቢ መሰባሰብ ለበሽታው የመጋለጥ እድልን ሰፊ እንደሚያደርገው ደጋግመው ቢናገሩም በርካታ አማኞች ግን መስማት አልቻሉም። ለምን?

ኮሮና
Banner

ጸሎት እንደ አየርና ምግብ

ማቴው ሽሚዝ የካቶሊክ ክርስቲያን ነው። በአሜሪካ ፔኒሲልቪኒያ ይኖራል። በዚያ አብሮ ማምለክ ተከልክሏል።

ሽሚዝ እንደሚለው ጸሎት እጅግ መሠረታዊ ነገር ነው፤ ለምን በግሮሰሪ ርቀት ጠብቆ መስተናገድ እንደሚቻለው ቤተክርስቲያንም ውስጥ ይሄ ሊሆን እንዳልቻለ አይገባውም።

"መንግሥት በግሮሰሪ ርቀታችሁን ጠብቃችሁ ተስተናገዱ፤ ቤተክርስቲያን ግን ርቀታችሁን ጠብቃችሁም ቢሆን አታምልኩ ማለቱ ምን ያህል ከእምነት ይልቅ ለንግድ ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጥ ማሳያ ነው" ይላል።

ከአምላክ ጋር በየትም ቦታ ሆኖ መገናኘት አይቻልም ወይ? የግድ በርከት ብሎ በቤተ ክርስቲያን መሰባሰብ ለምን? ለሚለው ጥያቄ ሽሚዝ ሲመልስ፡-

"ባል ወይም ሚስት አብረው በአካል እንዲገናኙ ሲሹ በተናጥል ራሳቸውን ችለው መቆም አይችሉም ማለት አይደለም፤ ወይም ደካማነታቸውን አይደለም የሚያሳየው፤ ፍቅራቸውን እንጂ፤ አምላክም ጋር መቅረብ እንደዚያው ነው።"

መንግሥትን እንደ ፀረ ሐይማኖት የማየት አባዜ

ባስቲያን ሩጀንስ የደች የአእምሮ ጤና ባለሞያ ነው፤ ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው ሃይማኖትና አአምሮን በተመለከተ ነው።

እሱ እንደሚለው ሰዎች መንግሥታቸውን የሚያዩበት መንገድ ትዕዛዙን ለመቀበል ያላቸውን ዝግጁነት ይወስናል።

ለምሳሌ በአሜሪካ ሕዝቡ መንግሥትን በጥርጣሬ ነው የሚመለከተው፤ መንግሥት የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ለመከተል ችግር የሚሆንባቸው መጀመሪያውኑም መንግሥትን በጥርጣሬ ስለሚመለከቱት ነው ይላል።

ይህም ማለት ይላል ሩትጀንስ . . . የሕክምና ባለሞያዎች ሳይቀሩ መሰባሰብ አደጋ አለው ሲሉ ቢመክሩም የመንግሥት ሰዎች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ሕዝቡ እነሱን በቀላሉ ለማመን ይቸገራል።

እንዲህ ዓይነት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለ አለመተማመን ግን እዚህ በኔዘርላንድስ አታይም፤ ስለዚህ ሕዝቡ በቤተ እምነት አትሰባሰብ ሲባል ቶሎ ይቀበላል።

የታንዛኒያው ፕሬዝዳንትጆን ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ሰዎች ተሰብስበው ከማምለክ መከልከል የለባቸውም ይላሉ

የእመነት አባቶችን ለምን አንሰማቸውም?

አንዳንድ አገራት ከሕዝቡ ይልቅ መሪዎቹ ችግር ፈጣሪዎች ናቸው።

ለምሳሌ በታንዛኒያ ፕሬዝዳንቱ ጆን ማጉፉሊ ሕዝቡ ወደ መስጊድና ቤተክርስቲያን ያለ ምንም ስጋት እንዲሄድ መክረዋል። ማጉፉሊ በኬሚስትሪ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው።

በአንድ የቤተክርስቲያን ጉባኤ ላይ ጆን ማጉፉሊ ሲናገሩ "ኮሮናቫይረስ ሰይጣን ነው፤ በእየሱስ ክርስቶስ በሚያምን ልብና ሰውነት ውስጥ ሊኖር አይቻለውም፤ ወዲያውኑ ይቃጠላል። ስለዚህ እምነታችንን እናጠንክር" ሲሉ ለምዕመናን ንግግር አድርገዋል።

አሁን ታንዛኒያ ውስጥ እንቅስቃሴዎች ዝግ ባይሆኑም ትምህርት ቤቶችና የሰዎች ስብስብ ግን ክልክል ነው። በታንዛኒያ ውስጥ ሰሞኑን በአንድ ቀን ብቻ 28 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ሼክ ሐሰን ሳይድ ሺዘንጋ የታንዛኒያ ተቀዳሚ ሙፍቲህ ናቸው።

እርሳቸውም ከፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ሀሳብ ጋር ይስማማሉ።

"አንድ ሰው ቤቱ የሚሰግደው ሶላት በመስጂድ በደቦ ሲፈጽመው 27 እጥፍ ምንዳ ያገኝበታል" ይላሉ። ስለዚህ አሉ ሙፍቲሁ ሼኽ ሐሰን፤ በዚህ በቫይረሱ ወቅትም ቢሆን ፈጣሪ በሽታውን እንዲይዝልን በመስጊድ እየተሰባሰብን ልንለማመነው ግድ ይላል።

ሙፍቲሁ በታንዛኒያ መስጊዶች ይዘጉ የሚል ውሳኔ ከተላለፈ እርሳቸው የሚመሩት የታንዛኒያ ብሔራዊ ሙስሊም ምክር ቤት ቅሬታውን ለሚመለከተው ከመግለጽ እንማይቆጠብ አረጋግጠዋል።

ይህ ሲባል ጥንቃቄ እርቋቸዋል ማለት አይደለም። ሼክ ሐሰን እንደሚሉት ወደ መስጊድ የሚመጡ ምዕመናን የራሳቸውን መስገጃ ይዘው እንዲመጡ አድርገናል፤ የጸሎት ሰዓቱም እንዲያጥር፣ አማኞች ቶሎ ቶሎ እጃቸውን እንዲታጠቡም ያደረግነው በሽታውን ለመከላከል ነው ይላሉ።

ይህ እርምጃ ግን ለኅብረተሰብ ጤና ባለሞያዎች በቂ አይደለም። ሰዎች ተሰባሰቡ ማለት በሽታውን የመለዋወጥ እድላቸው ከፍ አለ ማለት ነው።

ታንዛኒያ ውስጥ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በአንዱ የተዘጋጀ የእጅ መታጠቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታንዛኒያ ውስጥ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ

የሐይማኖት ነጻነት በኮሮናቫይረስ ምክንያት እየተጣሰ ይሆን?

አንዳንዶች ምዕመናን እምነታቸውን እንዳይፈጽሙ ሊከለከሉ አይገባም፤ በዚህ ወቅትም ቢሆን ሲሉ ይከራከራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእምነት ነጻነት ተሟጋች አህመድ ሻሂድ ግን በዚህ አይስማሙም።

አንድ ሰው የማምለክ መብቱ ሌሎችን ከመጉዳት መለስ ባለው ክልል የሚወሰን ነው፤ ስለዚህ ሐይማኖታዊ መብቴ ነው ማለት ይህንን ገደብ ካለመረዳት የሚመጣ ነው ይላል።

አንድ ሰው ሐይማኖቴ ያዘኛል ብሎ ሌሎች ላይ ጉዳት ማድረስ አይችልም፤ በዚህ ወቅት ተሰባስቤ ላምልክ ማለት በኅብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ማድረስ ነው። ይህ መብት አይደለም።