በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 92 ደረሰ

በዓለማችን ላይ ቢሊየኖች የኮቪድ-19ን እንቅስቃሴ ለመግታት ቤት ዘግተው ተቀምጠዋል። የዚህን ቫይረስ የስርጭት ሽክርክሪት ለመስበር ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ራስዎን ሰዎች ከሚበዙበት ስፍራ ማራቅ ነው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን ደጋግሞ በሳሙናና በውሃ መታጠብ ደግሞ ሌላው መከላከያ ነው። እናንተም ጤና እኛም ደህና ሆነን እንድንውል እየተመኘን ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ የቀጥታ ዘገባችንን ይከታተሉ ግብዣችን ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የናይሮቢ ከተማ ገዢ ለድሆች መጠጥ አቀርባለሁ አሉ

    ማይክ ሶንኮ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ላልቻሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ጋር አብሮ መጠጥ ሊያቀርብ እንደሆነ የከተማዋ ገዢ መናገራቸው መነጋገሪያ አድርጓቸዋል።

    አገረ ገዢው ማይክ ሶንኮ ይህንን የተናገሩት ማክሰኞ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነበር።

    ሶንኮ "አነስተኛ ጠርሙስ ሄነሲ [የኮኛክ መጠጥ ዓይነት ነው] በምግብ እድላው ላይ ጨምረን ለሕዝባችን እናቀርባለን" ማለታቸው ተሰምቷል።

    የከተማዋ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በዚህ የአገረ ገዢው ንግግር ሲሳለቁ ተስተውሏል።

    አገረ ገዢው አክለውም "በዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ በሌሎች የጤና ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አልኮል ኮሮናቫይረስንም ሆነ ሌሎች ቫይረሱችን ይገላል" ብለዋል።

    በአገሪቱ በሚሰራጨው ሲትዝን ቲቪ የአገረ ገዢው አስተያየት ተደምጧል።

    የመዲናዋ ናይሮቢ ገዢ በተናገሩት ነገር ደግሞ በርካታ ኬንያዊያን በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ እየተሳለቁበት ነው።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  2. ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በዋስ እንዲፈታ ፍርድቤት ወሰነ

    የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ተጠርጥሮ የታሰረውን ጋዜጠኛ ያየሰው በገንዘብ ዋስ እንዲፈታ መወሰኑን ጠበቃው ታደለ ገብረመድህን ለቢቢሲ ገለፁ።

    ጠበቃው እንዳሉት፣ ጋዜጠኛው ላይ የቀረበው ክስ “ሃሰተኛ መረጃን ማሰራጨት” የሚል ሲሆን እስካሁን ለ 3 ግዜ ችሎት ቀርቧል።

    ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያያዘ ሐሰተኛ መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ አሰራጭቷል በሚል ነበር ከሦስት ሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለው።

    በዛሬው የችሎት ውሎ፣ መርማሪ ፖሊስ 7 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበለው አቶ ታደለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

    ዛሬ የአራዳ ምድብ ችሎት በ25 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈታ መወሰኑ ተገልጿል።

    ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሲፒጄ፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኛውን ‘ካለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ’ ሲል ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

  3. ያለንክኪ እጅ የሚያስታጥበው ፈጠራ

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ያለ እጅ ንክኪ እጅ የሚያስታጥበው የፈጠራ ውጤት

    ኢዘዲን ካሚል ይባላል ። የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነው። እስካሁን ከትምህርት ሰዓት ውጭ 30 የፈጠራ ሥራዎችን ጨምሮ 7 የሚሆኑ የአንድሮይድ መተግበሪያዎችንም እንደሰራ ይናገራል።

    ከፈጠራ ሥራዎቹ ውስጥ ለ13ቱ የፈጠራ ሥራዎቹ ከ'ሴቭ አይዲያስ ኢንተርናሽናል' የባለቤትነት መብት እንዳገኘ ገልፆልናል።

    የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ደግሞ ከጓደኛው ጋር በመሆን ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ሁለት የፈጠራ ሥራዎችን ሰርቷል። አንደኛው ያለ እጅ ንክኪ እጅን መታጠብ የሚያስችል የፈጠራ ውጤት ነው።

  4. ዚምባብዌ ለ33 ሺህ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ልታደርግ ነው

    በዚምብብዌ እስካሁን ድረስ 18 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ዚምባብዌ በዚህ ወር መጨረሻ ቢያንስ 33 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎቿ የኮቪድ-19 ምርመራ ለማድረግ ማቀዷን አስታወቀች።

    የአገሪቷ ጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት ብቻ 665 ሰዎች መመርመሩን አስታውቋል።

    በዚምባብዌ እስካሁን ድረስ 18 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውም አስታውቋል።

    የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ኒክ ማንግዋና እንዳሉት እስካሁን ድረስ 167 መመርመሪያ መሳሪያዎች ያሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለመግዛት መታዘዙን አስታውቀዋል።

    መንግሥት ምርመራ ለማድረግ ያሰበው የጉንፋን ምልክት የሚታይቸው፣ የሳምባ ምች ታማሚዎችን፣ ትኩሳት ያለባቸውን፣ በእድሜ የገፉትን፣ የቤት መቀመጡ ታውጆ በነበረበት ወቅት ሲሰሩ የነበሩትን፣ የጤና ባለሙያዎችንና የመንግሥት ሰራተኞችን ነው።

    ዚምባብዌ በከፊል ተጥሎ የቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ እሁድ ዕለት ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል።

  5. ኬንያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የማያደርጉ ዜጓቿን ማሰር ልትጀምር ነው

    የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ነው ብሎ ካስታወቀ ቆይቷል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኬንያ ፖሊስ ኃላፊ ከዛሬ ጀምሮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የማያደርጉ ዜጎችን ማሰር እንደሚጀምር አስታወቁ።

    ኬንያውያን የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ነበር።

    ይህ ውሳኔ እስካሁን ድረስ አስገዳጅ ያልነበረ ሲሆን ከአሁን በኋላ ግን ማንኛውም ኬንያዊ ሰዎች በተሰበሰቡበት ስፍራ ሲንቀሳቀስ ማድረግ ይጠበቅበታል ተብሏል።

    ኢንስፔክተር ጄነራል ሂላሪ ሙቲያምቢ እንዳሉት ዜጎች የአፍና አፍንጫ እንዲገዙ በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

    የኬንያ ጤና ሚንስትር ማንኛውም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረገ ግለሰብ 20ሺህ ሽልንግ (188 ዶላር ገደማ) እንደሚቀጣ አስታውቆ ነበር።

    የሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚሰሩ ረዳቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛው ውድ በመሆኑ መንግሥት እንዲያቀርብላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር።

    ጤና ሚንስትር ዜጎች እንዴት መሸፈኛውን ማድረግና ማውለቅ እንዳለባቸው እያስተማረ ይገኛል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ያለባቸው ግለሰቦች የህክምና ባለሙያዎችና የኮቪድ-19 ሕሙማንን የሚንከባከቡ ግለሰቦች መሆናቸውን ሲመክር ቆይቷል።

  6. የ99 ዓመቱ ሽማግሌ 4 ሚሊዮን ፓውንድ ሰበሰቡ

    ሽማግሌው ቶም ሙር

    ሽማግሌው አቶ ቶም ሙር ነው የሚባሉት፤ ሻምበል ናቸው። የሚኖሩት በቤድፎርድሻያር አካባቢ ነው። ከቤታቸው ጓሮ በሚገኝ ሜዳ 100 ዙር ለመሮጥና እና በዚያ መንገድ በሚገኝ ትኩረት ለጤና ባለሞያዎች የሚሆን የእርዳታ ገንዘብ ለማሰባሰብ አሰቡ።

    ባለፈው ሐሙስ መቶ ዙር እሮጣለሁ ብለው ተነስተው ለአዛውንቶች በተሰራ ድጋፍ ምርኩዝ ይህንኑ አሳክተዋል፤ እየተራመዱም ቢሆን።

    በዚህ ያልረኩት ሽማግሌው ሌላ 100 ዙር ሩጫ አደርጋለሁ ብለዋል።

    የብሔራዊ ጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ቻሪቲስ ቱጌዘር የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ሽማግሌው ያሰባሰቡት ገንዘብ ተቀብሎ ለሚመለከተው ያደርሳል።

    ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የሽማግሌውን በጎ ተግባር "አርአያነት ያለውና የሚያነቃቃ" ብሎታል።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ 170ሺ ሰዎች በሽማግሌው ተግባር ልባቸው ተነክቶ ገንዘብ በኢንተርኔት ያዋጡ ሲሆን ይህ ዘገባ እስኪታተም ድረስም መጠኑ 4 ሚሊዮን የእንግሊዝ ስተርሊን ፓውንድ ደርሷል።

  7. ከኮቪድ-19 ያገገሙት የአዳማ ነዋሪ

    አዳማ

    አቶ ዳግማይ በቀለ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ናቸው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት መጋቢት 18/2012 ዓ.ም ነበር በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ጤና ጥበቃ ያስታወቀው።

    እኚህ የ61 ዓመት አዛውንት አዲስ አበባ በሚገኘው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው በአሁን ጊዜ ከቫይረሱ በማገገማቸው አዳማ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰዋል።

    የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳግማይ፣ ቫይረሱ እንዴት ሊይዛቸው እንደቻለ እንደማያውቁ ይናገራሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ ምልክቶችን በማየታቸው ራሳቸውን ለመለየት ስለፈለጉ ከቤተሰባቸው ርቀው ሆቴል ተከራይተው መቀመጣቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል። ተጨማሪ ለማንበብ

  8. ከኮሮና ተጠንቀቁ ባለ ህይወቱን ያጣው ወጣት

    ወራቤ ከተማ

    የፎቶው ባለመብት, ወራቤ ከተማ አተስዳደር

    በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በተለምዶ ዋሽንግተን በሚባለው አካባቢ ከትናንት በስቲያ አንድ ግለሰብ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚመከሩት ጥንቃቄዎች መካከል አንዱ የሆነው ርቀት መጠበቅን መምከሩ ለሕይወቱ ማለፍ ምክንያት ሆኗል።

    በአንድ ሻይ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው ሟች አራት ደንበኞች ተጠጋግተው መቀመጣቸውን ተመልከቶ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ መንገሩን ተከትሎ በተፈጠረ ግብግብ ሕይወቱ ልታልፍ እንደቻለች የስልጤ ዞን የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃለፊ የሆኑት አቶ ሙዲን ሙኒር ለቢቢሲ ገልፀዋል።

  9. በኢትዮጵያ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አርማ

    የፎቶው ባለመብት, Ministry of Health

    የምስሉ መግለጫ, የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አርማ

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ዛሬ በሦስት ጨምሮ 85 መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    አዲስ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠው ሦስቱም ሰዎች ወንዶች ሲሆኑ፤ አንደኛው ከአሜሪካ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ ሲሆን ሁለቱ ግን የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ቢሆንም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው እንደሆኑ ተገልጿል።

    ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ በ431 ሰዎች ናሙና ላይ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    እስካሁን ድረስ በአገሪቱ በአጠቃላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 4988 ሲሆን በሽታው የተገኘባቸው ሰማንያ አምስት ሰዎች ናቸው።

    ከተያዙት ውስጥ የህክምና ድጋፍ አግኝተው ማገገማቸው የተነገረው 15 ሰዎች ሲሆኑ እስካሁን ድረስ በበሽታው ሦስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

  10. ቢል ጌትስና ባለቤታቸው ሚሊንዳ የትራምፕን ውሳኔ አጣጣሉ

    የማይክሮሶፍት መስራች የሆኑት ቢልጌትስና ባለቤታቸው ሚሊንዳ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚያደርጉትን መዋጮ ለማቋረጥ መወሰናቸው " አደገኛ" ነው ሲሉ አውግዘውታል።

    "ዓለም የጤና ድርጅቱን ከምን ጊዜውም በላይ ይፈልገዋል" ብለዋል።

    የጥንዶቹ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ጌትስ ፋውንዴሽን የዓለም ጤና ድርጀት ትልቁ ለጋሽ ተቋም ነው።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  11. በደቡብ አፍሪካ ማረሚያ ቤቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ተሰግቷል

    በደቡብ አፍሪካ ማረሚያ ቤቶች የኮቪድ-19 ምርመራ እየተደረገ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በደቡብ አፍሪካ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እየተደረገ ነው

    በደቡብ አፍሪካ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ታራሚዎች ቁጥር በሁለት ቀናት ብቻ 49 ደረሰ።

    የደቡብ አፍሪካ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እንዳለው ከሆነ በኢስት ሎንዶን ማረሚያ ቤት ብቻ በኮቪድ-19 የተያዙ ታራሚዎች ቁጥር 53 ደርሷል።

    በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ታራሚዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የማረሚያ ቤቶቹ ሠራተኞችም መታመማቸው ተነግሯል።

    እስከሁን ድረስ 23 የማረሚያ ቤቶቹ ሰራተኞች መታመማቸው የተገለፀ ሲሆን የመጀመሪያው ታማሚ ከ10 ቀን በፊት ቀብር ላይ የተገኘ ሠራተኛ እንደነበር ይፋ ሆኗል።

    ከሁለት ቀን በኋላ ሌላ የማረሚያ ቤቱ ሠራተኛ በቫይረሱ መያዙ እንደታወቀ በአጠቃላይ ታራሚዎችና ሰራተኞች ላይ ምርመራ መደረጉ ተነግሯል።

    የማረሚያ ቤቱ ቃል አቀባይ እንዳሉት ማረሚያ ቤቱ ፀረ ተዋህሲያን የተረጨ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ የተያዙና የታመሙትን ጤና እየተከታተሉ ነው።

    ታራሚዎቹ የጤና ሁኔታቸው ከተባባሰ በሚል የሚታከሙባቸው ሆስፒታሎችና የሚጓጓዙባቸው አንቡላንሶች በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

  12. የተባበሩት መንግሥታት ትራምፕን በመቃወም ከአለም ጤና ድርጅት ጎን ነኝ አለ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአለም ጤና ድርጅትን ከመተቸት በተጨማሪ የገንዘብ መዋጮን አቆማለሁ በሚሉበት ሰአት የተባበሩት መንግሥታት ከድርጅቱ ጎን ነኝ፤ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ውሳኔም እቃወማለሁ ብሏል

    በተለይም ፕሬዚዳንት ትራምፕ አገራቸው ለድርጅቱ ታደርገው የነበረውን የአባልነት የገንዘብ መዋጮን አቆማለሁ ማለታቸው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለውታል። በአሁኑ ወቅት የገንዘብ መዋጮ እቀንሳለሁ ማለትም ተገቢም እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

    "ወቅቱ የአንድነት እንዲሁም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ተባብሮ ቫይረሱን የሚታገልበትና፤ ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ ለመቀነስ መረባረብ የሚያስፈልግበት ሰአት ነው" በማለት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአለም አቀፉን ጤና ድርጅት የቫይረሱን መዛመት ሚስጥራዊ በማድረግ፣ ለወረርሽኙም የሰጠው ምላሽ የዘገየ እንዲሁም ቻይናን ማዕከል ያደረገ በማለት አውግዘዋል። አገሪቷም ለድርጅቱ የምትሰጠውን እርዳታም እንድታቋርጥ ወስኛለሁ ብለዋል።

    አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ግን በድርጅቱ ላይ እየተሰጠ ያለውን ትችት አይቀበሉትም " የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ወረርሽኙ ከተነሳበት ሰአት ጀምሮ ለአገራትና ማህበረሰቡ ድጋፍ በመስጠት እየተጋፈጠ ነው። በተለይም ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች ስልጠናዎችን፣ መመሪያዎችን እንዲሁም ህይወት አድን የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችንና አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል" ብለዋል።

    "የአለም ጤና ድርጅት ሊደገፍ ይገባል። አለም ከኮሮና ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለማሸነፍ የድርጅቱ ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። ይህ የፀና እምነቴ ነው" በማለት አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

  13. ኮሮናቫይረስ፡ ቤት ጥቃት የበዛበት ሲሆን ወደየት ይሸሻል?

    በፍቅር ጓደኛዋ የተገደለችው የ27 አመቷ ሎሬና ኳራንታ

    የፎቶው ባለመብት, LORENA QUARANTA

    የምስሉ መግለጫ, በፍቅር ጓደኛዋ የተገደለችው የ27 አመቷ ሎሬና ኳራንታ

    በስፔኗ ግዛት አልማሶራ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ተደርጎ እንዲውለበለብና የሶስት ቀናት ሐዘን ታውጇል። ምናልባት ስፔን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በኮሮና ቫይረስ ከመሞቱ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ሁኔታው እንደሱ አይደለም የብዙዎችን ልብ የሰበረው የካሪናን አሟሟት ለማሰብ ነው።

    ካሪና ከሁለት ልጆቿ ፊት ለፊት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው በባለቤቷ አማካኝነት ነው። ከገደላትም በኋላ እጁን ለፖሊስ የሰጠ ሲሆን ወንጀሉንም ተናዟል።

    ከኮሮና በፊት ቢሆን ሰው ተሰባስቦ የ35 አመት እድሜ ያላትን ጎረቤታቸውን ይዘክሯት ነበር። አሁን ግን በኮሮና ምክንያት ቤታቸው የዋሉ ግለሰቦች ግን በርቀት በሃዘን አስበዋታል።

    ደወልም ተደወለ፣ ልብ የሚሰረስር ሙዚቃም በኦርኬስትራ ታጅቦ ቀረበ፤ የአካባቢው ህዝብ መውጣት ባይችልም በመስኮታቸው እንዲሁም የቻሉት ደግሞ ወደ በረንዳቸው ወጣ ብለው በፀሎት አስበዋታል።

    አገራት የኮሮና መዛመትን ለመቆጣጠር ቤት የመቀመጥ ውሳኔ ማሳለፈቸውን ተከትሎ ሴቶች ከጥቃት አድራሾቻቸው ጋር በአንድ ቤት እንዲቆለፉ፣ እርዳታ ከሚለግሷቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት አለመኖር እንዲሁም ማምለጥ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

    ልጆችም ትምህርት ቤት ስለማይሄዱና ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ ስለሚያሳልፉ የነዚህ ጥቃቶች ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፤ ለማይሽር ስነልቦናዊ ጉዳቶችም እየተጋለጡ ነው።

    ካሪና በስፔን ውስጥ በዚህ አመት ብቻ በትዳር አጋሮቻቸው ወይም በቀድሞ አጋሮቻቸው ከተገደሉ ሴቶች መካከል 17ኛዋ ናት። ኮሮናን ለመከላከል ውሳኔዎች ከተላለፉ በኋላ በትዳር አጋሯ የተገደለችው የመጀመሪያ ሴት ሆናለች።

    እንደ ስፔን ጣልያንም በኮሮና ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ ናት። ከመቶ በላይ ዶክተሮች ኮሮናን ሲያክሙ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    የ27 አመቷ ሎሬና ኳራንታ ዶክተር ለመሆን የቀራት ጥቂት ጊዜ ነበር፤ ህይወቷ በአጭር ባይቀጭ። እንደ ሌሎች ዶክተሮች በኮሮና አይደለም የሞተችው የፍቅር ጓደኛዋ መግደሉንም ለፖሊስ ተናዟል።

    አስከሬኗም ወደተወለደችበት ሲሲሊ ፋቫራ ከተማ ሲመለስም ብዙዎች በበረንዳቸው ላይ ነጭ አንሶላ ሰቅለው በኃዘን ተቀብለዋታል።

    የነጩ አንሶላ ምልክትም ከንቲባ አና አልባ ይገልፁታል " የመንፈሷን ፅዳት እንዲሁም ለዘመናት ህልሟ የነበረው ዶክተር ስትሆን የምትለብሰውን ነጭ መለዮ ልብስ የሚያመላክት ነው።"

  14. ቻይና ዓለምን ጉድ ካሰኙት ሆስፒታሎች አንዱን ዘጋች

    ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቻይና የኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ለማከምና ለይቶ ለማቆየት በአስር ቀናት ውስጥ ሁለት ትልልቅ ሆስፒታሎችን ገንብታ ነበር።

    ከሁለቱ ሆስፒታሎች አንዱ የሆነው ‘ተንደር ጎድ ማውንቴን’ የተባለውና በዉሃን የሚገኘው ሆስፒታል መዘጋቱ ተገልጿል።

    በውስጡ የነበሩ የመጨረሻዎቹ ታማሚዎችም የመጨረሻ ክትትል ለማድረግ ወደሌላ ሆስፒታል ተዘዋውረዋል።

    ሆስፒታሉ የተገነባው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን በጊዜያዊነት ለማከም ሲሆን በአስር ቀናት ውስጥ መጠናቀቁ ደግሞ ዓለምን ጉድ አሰኝቶ ነበር።

    በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም የዚህን ሆስፒታል ግንባታ በቀጥታ ሲከታተሉ ነበር።

    ይህም ሆስፒታል እስከሚዘጋበት ሰአት ድረስ 2000 የሚሆኑ ታማሚዎችን አስተናግዷል።

  15. በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከ125ሺህ ሰዎች በላይ ሞተዋል

    የሟቾች አስከሬን ሲነሳ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ በዓለማችን ላይ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

    ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ደግሞ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 126 ሺህ 539 ደርሷል።

    ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በአሜሪካ ሲሆን ይህም 25,992 ነው ተብሏል።

    ጣልያን (21,067)፣ ስፔን(18,255)፣ ፈረንሳይ (15,729) እና ዩናይትድ ኪንግደም (12,107) በቅደም ተከተል ሟቾች ተመዝግቦባቸዋል።

    ቻይና አስቀድሞ ቫይረሱ የተገኘባት አገር ብትሆንም የሞቱት ሰዎች ቁጥር ግን 3,345 ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

  16. በኮሮና ዘመን ፍቅረኛዬ ናፈቀችኝ ብሎ ሾልኮ የወጣው አውስትራሊያዊ ዘብጥያ ወረደ

    አውስትራሊያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የ35 ዓመቱ አውስትራሊያዊ ፐርት የሚገኘው ማደሪያውን ዘግቶ፣ የመንግሥትን ትዕዛዝ አክብሮ መቀመጥ ጀምሮ ነበር።

    አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ ለመከላከል ማህበራዊም አካላዊም ርቀታችሁን ጠብቁ ብላ 14 ቀን የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።

    እሱም ይህንኑ አምኖ ካረፈበት ሆቴል ቢቀመጥም አላስቻለውም፤ በሆቴሉ የእሳት አደጋ መውጫ በኩል ሹልክ ብሎ በመውጣት ታክሲ ተሳፍሮ አይንሽን ላየው እየመጣሁ ነው ቢልም ፖሊስ አንተ ስትሾልክ የሚሾልክ ቫይረስ ቢኖርስ ሲል ዘብጥያ ወርውሮታል።

    ጉዳዩን ያዩት ዳኛ “ እጅጉን ሲበዛ ራስ ወዳድ” በማለት ስድስት ወር እንዲታሰር ቢፈርዱበትም፤ አምስቱን የቅጣት ወር ግን አንስተውለታል።

    አውስትራሊያ ጥብቅ ነው የተባለውን የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለች ሲሆን ቤት ውስጥ የመቀመጥ ትዕዛዙን ተላልፈው የተገኙ በርካቶች ዜጎቿን ቅጣታቸውን ተከናንበዋል።

  17. ዴንማርክ የአፀደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ከፈተች

    ትምህርት ቤት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ዴንማርክ ከዛሬ ጀምሮ የአፀደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መክፈት ጀምራለች።

    አገሪቱ ቀስ በቀስም አስተላልፋቸው የነበሩ ክልከላዎችን እንደምታላላ ይጠበቃል።

    በአዲሱ የትምህርት ቤት ሕግ መሰረት ህጻናት ከሌላ ጊዜው በተለየ ተራረቀው ይቀመጣሉ፤ ንጽህናቸውን እንዲጠብቁም ከባድ ክትትል ደረግባቸዋል።

    ከተቻለም ተማሪዎች ከመማሪያ ክፍል ውጪ ሆነው እንዲማሩ ይደረጋል ተብሏል።

    እስካሁን ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን የሚከለክለው እገዳ ያልተነሳ ሲሆን በሆስፒታል ያሉ ታማሚዎች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን መንግስት አስታውቋል።

    በዴንማርክ 6700 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 300 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  18. የተቀደደ ከመጣፍ ወደ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማዘጋጀት

    ልብስ ሰፊዋ

    በባንኮክ ጎዳናዎች አንዱ ጥግ የሚገኘው ይህ የልብስ ስፌት ሱቅ አሁን ሥራውን ቀይሯል።

    እንደ ቀድሞ የተቀደደ ስፉልኝ፣ የረዘመ አሳጥሩልኝ አልያም ወገብ አጥበብቡልኝ የሚባልበት ጊዜ አይደለም። አፌን የምሸፍንበት እራፊ ጨርቅ ስፉልኝ ግን የዘመኑ የልብስ ሰፊዎች የገበያ አኪር ነው።

    ልብስ ሰፊዋ ሳናንቲፓክ ሜፖን-ንጋም ትባላለች። የበፊቱ ትዕዛዝ ሁሉ ጠፍቷል ስትል ከሁለትና ሶስት ወር በፊት የነበራት ገበያ ዳመና ያየው ጉም መሆኑን ትናገራለች።

    አሁን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ፈላጊ ብቻ ነው ያለው። መጀመሪያ የጤናዬን ያሉ ታይላንዳውያን ትዕዛዙን ያዥጎደጉዱታል።

    እስካሁን 5,000 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን አምርታለች። ዋጋውም ቢሆን አገር ጎብኚ ይበዛባት ለነበረችው ታይላንድ ነዋሪ ብዙ አይደለም ተብሏል። በዚህ ስራ በጠፋበት ወቅትም ሀያ ሰዎች ያህል ቀጥራ እንደምታሰራ ትናገራለች።

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ
  19. አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት የማዋጣውን ገንዘብ አቋርጫለሁ አለች

    የዓለም ጤና ድርጅት

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ የሰጠው ምላሽ ቀርፋፋ ነው፤ በአካሄዱም ቻይናን ማዕከል አድርጓል ላሉት የዓለም ጤና ድርጅት አገራቸው የምታበረክተውን የገንዘብ መዋጮ እዲቋረጥ አዘዙ።

    ይህም ማለት አሜሪካ ለድርጅቱ በየዓመቱ ለድርጅቱ ትሰጥ የነበረው ገንዘብ እንዲቆም የሚያደርግ ነው ተብሏል።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የትራምፕን ውሳኔ "ጊዜውን ያላገናዘበ እርምጃ" ሲሉ ተችተውታል።

    ዶናልድ ትራምፕ ከሳምንታት በፊት ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመሩትን መሥሪያ ቤት ክፉኛ ሲወቅሱ ነበር። በየዓመቱ የሚሰጡትን መዋጮ ለማጤን እንደሚገደዱም መጠቆማቸው ይታወሳል።

  20. አይስላንድ ኮቪድ-19 መከላከል እንደምን ተሳካላት

    አይስላንድ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    በምድራችን የሰሜን ዋልታ ጫፍ ላይ የምትገኘው የአይስላንድ ደሴት የኮሮናቫይረስን መስፋፋት ለመከላከል ከዓለማችን አገራት የተለየ እርምጃን እየወሰደች ነው።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከአገር አገር እየተዛመተ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመያዝ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በየዕለቱ ሕይወታቸውን እያጡ ባለበት በዚህ ወቅት አይስላንድ የተለየች ሆናለች።

    ኖርዲክ በሚባለው አካባቢ የምትገኘው አይስላንድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በግዛቷ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ለመቆጣጣር እንደቻለች ተመስክሮላታል።

    ባለፉት ሁለት ወራት በሚሆን ጊዜ ውስጥ 1500 በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያገኘች ሲሆን አራት ሰዎች ብቻ በበሽታው ለሞት ተዳርገዋል።