በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 92 ደረሰ

በዓለማችን ላይ ቢሊየኖች የኮቪድ-19ን እንቅስቃሴ ለመግታት ቤት ዘግተው ተቀምጠዋል። የዚህን ቫይረስ የስርጭት ሽክርክሪት ለመስበር ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ራስዎን ሰዎች ከሚበዙበት ስፍራ ማራቅ ነው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን ደጋግሞ በሳሙናና በውሃ መታጠብ ደግሞ ሌላው መከላከያ ነው። እናንተም ጤና እኛም ደህና ሆነን እንድንውል እየተመኘን ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ የቀጥታ ዘገባችንን ይከታተሉ ግብዣችን ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጠ/ሚንስትሩ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እያገለገሉ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችም ስጦታ አበረከቱ

    @TakeleUma

    የፎቶው ባለመብት, @TakeleUma

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በኤካ ኮተቤ ሆስፒተሰል ተገኝተው በተቋሙ እያገለገሉ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችም የተለያዩ ስጦታዎችን ማበርከታቸው ተነገረ።

    ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማም፤ ከጠቅላይ ሚንትሩ እና ከቀዳማዊት እመቤት ጋር የፋሲካ በዓለን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ቦታዎችን ተዟዙረን ስጦታዎችን አበርክተናል ብለዋል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    በተመሳሳይ መሪዎቹ የአረጋውያንን ቤት ማደስ መርሀ ግብርን ያስጀመሩበት እማሆይ አዱኛ መኖሪያ ቤትና የአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት በመገኘትም የበዓል ስጦታዎችን አበርክተዋል ሲል ፋና ዘግቧል።

    • በተጨማሪም አፍንጮ በር አካባቢ ሚገኝ የህፃናት ማሳደጊያ ተገኝተው የፋሲካ በዓል ስጦታ ማበርከታቸውን ተዘግቧል።
  2. ሰበር, በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 7 ሰዎች መካከል የ14 ዓመት ታዳጊ ትገኛለች

    Addis Ababa Bole Airport

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ተረጋግጦ ይፋ ከተደረጉት ሰባት ሰዎች መካከል አንዲት የ14 ዓመት ታዳጊ እንደመትገኝበት ተገለጸ።

    ከሰባቱ ሰዎች ውስጥ ከታዳጊዋ በስተቀር ሁሉም የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ የነበራቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ታዳጊዋ ምናልባት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳላት ለማወቅ በመጣረት ላይ ነው ተብሏል።

    ቀሪዎቹ ስድስት ሰዎች ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ እንደሆነም ተነግሯል።

    የወረርሽኙ ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰባቱ ሰዎች መካከል አምስቱ ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ሴቶች ናቸው። በእድሜም ትንሿ 14 ዓመት እንዲሁም ትልቁ 76 ዓመት እንደሆኑ የወጣው ዝርዝር ያመለክታል።

    በየዕለቱየሚደረገውንየኮሮናቫይረስምርመራውጤትንተከትሎየጤናጥበቃሚኒስቴርዛሬባወጣውመግለጫተጨማሪሰባትሰዎችላይቫይረሱመገኘቱን አመልክቷል፤ ይህ አሃዝም ከዕለት ዕለት በተለያየ መጠን እየጨመረ ይገኛል።

    በዚህም ሳቢያ ባለፈው ከአንድ ወር ባለይ ባለው ጊዜ በዚትዮጵያ ውስጥ በምርመራ ቫይረሱእንዳለባቸው የተረጋገጡትን ሰዎች ቁጥርወደ 92 ከፍአድርጎታል።

    ይህ አሃዝ የተገኘውም ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት በኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታው ምርመራ ከተደረገላቸው 400 ሰዎች መካከል እንደሆነ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

  3. ኮሮናቫይረስ፡ ሊቢያ 10 ቀናት የሚዘልቅ ሰዓት እላፊ አወጀች

    Libya

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው የሊቢያ መንግሥት ለ10 ቀናት የሚቆይ የ24 ሰዓታት ሰዓት ዕላፊ አውጃለሁ አለ።

    ይህ ማለት የተመድ እውቅና ያለው መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ስፍራዎች ዜጎች ለመጪዎቹ 10 ቀናት መንቀሳቀስ አይችሉም ማለት ነው።

    ሬውተርስ በትሪፖሊ የሚገኙ የመንግሥት ባለስልጣናትን በመጥቀስ እንደዘገበው ከሆነ ሰዓት እላፊው ከነገ የፊታችን አርብ ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል።

    ሊቢያ በተመድ እውቅና በተሰጠው መንግሥት እና በጀነራል ሃፍታር በሚመራው ጦር መካከል ያለው ውጊያ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አስቸጋሪ አድርጎታል።

    ከጥቂት ቀናት በፊት እንኳ በትሪፖሊ የኮሮናቫይረስ ህመምተኞችን ያክም የነበረ ሆስፒታል በተደጋጋሚ በሚደርስበት የቦምብ ጥቃት ለመዘጋት ተገዷል።

    መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው መንግሥት ለጥቃቱ የጀነራል ሃፍታር መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

    ሊቢያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ 48 ሰዎች ይገኙባታል። 1 ሰው ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሞቷል።

  4. ቻይናውያን ሀኪሞች ወደ ኢትዮጵያ እየሄዱ ነው ተባለ

    ጭንብል ያደረጉ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቻይናውያን ዶክተሮች ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ እና ቡርኪና ፋሶ እያቀኑ ነው ተባለ።

    ሀኪሞቹ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ወደ ሁለቱ አገራት እንደሚሄዱ የቻይና ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ 'ቻይና ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትወርክ ሪፖርትስ' አሳውቋል።

    ምን ያህል ሀኪሞች ወደ ኢትዮጵያ እና ቡርኪና ፋሶ እየሄዱ እንደሆነ ግን የተባለ ነገር የለም።

    ዶክተሮቹ ከሲቹዋን እና ከቲአንጂን ግዛቶች የተውጣጡ ናቸው ተብሏል።

    የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር እንዳለው የህክምና ባለሙያዎቹ ወደ ሁለቱ አገራት ጉዞ የጀመሩት ሀሙስ ዕለት ነው።

    የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጃን እንደተናገሩት፤ ሀኪሞቹ ልምዳቸውን ያካፍላሉ፤ ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ የቴክኒክ እገዛም ያደርጋሉ።

  5. የግብጽ ዶክተሮች የመከላከያ እቃዎች እንዳያጥረን እንሰጋለን አሉ

    በግብጽ የኮሮናቫይረስን በመዋጋት ላይ የሚገኙት የጤና ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት እራሳቸውን ለመከላከል የሚረዱ መገልገያ ቁሳቁሶች እጥረት ሊያጋጥማቸው ይችላል።

    ስጋታቸውን ለመንግስት ቢያቀርቡም ተገቢውን ትኩረት እንዳላገኙ ገልጸዋል።

    ነገር ግን የአገሪቱ መንግስት የመከላከያ እቃዎቹ በበቂ ሁኔታ አቅርቦት አለ ያለ ሲሆን በአንድ ለይቶ ማቆያ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰራ ዶክተርም የህክምና ባለሙያዎች እንደውም ትርፍ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል እየወሰዱ ነው ብሏል።

    እስካሁን በግብጽ 178 ሰዎች በቫይረሱ ሕይታቸው ሲያልፍ በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙት ደግሞ 13 በመቶ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች ናቸው።

  6. ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት ድርጅት ሥራው በትክክል ምንድነው? አገሮችንስ የማዘዝ ሥልጣን አለው?

    ዶ/ር ቴድሮስ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅትን ኮንነዋል። ሁለተኛ ገንዘብ አንሰጠውም ብለዋል። እንደ ትራምፕ አስተያየት ድርጅቱ አፍቃሪ-ቻይና ሆኗል፤ ኃላፊነቱንም በአግባቡ አልተወጣም።

    ለመሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊነት ምንድነው? አገራትን ይህን አድርጉ፣ ያን አታድርጉ ብሎ የማዘዝስ ሥልጣንስ አለው?

    ማማከር እንጂ ማዘዝ አይችልም።

    ስዊዘርላንድ ከ50 በላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሉባት። ከነዚህ ውስጥ ሲሶው በጄኔቫ ነው የሚገኙት።

    የዓለም ጤና ድርጅት ገና ወደ ቅጥር ሲገባ አረንጓዴና ማራኪ ነው። በየትኛው የግቢው ክፍል ማጨስ አይፈቀድም።

    ወደ እንግዳ መቀበያው አዳራሽ ሲዘልቁ የሚያገኙት ብን ብን የሚሉ ባንዲራዎችን ነው፤ ለዓይን ይማርካሉ።

    ከኮርኒሱ ቁልቁል የሚወርዱት 194 ባንዲራዎችን ነፋስ ያወዛውዛቸዋል። ከነዚህ መሀል የአሜሪካ ባንዲራ የመውረጃው ጊዜ ተቃርቦ ይሆናል።

  7. በጋና የሬሳ ማቆያዎች እየተጨናነቁ ነው ተባለ

    የሬሳ ሳጥን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    መንግስት የተለመደው አይነት የቀብር ስነ ስርአት እንዳይሄድ መከልከሉን ተከትሎ በጋና የሚገኙ ዜጎች የሟቾችን አስክሬን ወደ ማቆያዎች እየወሰዱ ነው።

    በዚህም ምክንያት የሬሳ ማቆያዎቹ ከአቅማቸው በላይ መጨናነቃቸው ነው የተነገረው።

    አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ የሟቾችን ሬሳ እገዳው እስከሚነሳም ድረስ ቢሆን አቆይተን ተገቢውን የቀብር ስነ ስርአት እንፈጽማለን ብለዋል።

    የሬሳ ማቆያ ማዕከላት ሰራተኞች እስከዛሬ ድረስ እንደዚህ አይነት መጨናነቅ አይተው እንደማያውቁ ለአገር ውስጥ መገናኛዎች ገልጸዋል።

    በዋና ከተማዋ አክራ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ኃላፊ እንደገለጹት ከዚህ በኋላ ሬሳዎችን መቀበል ሊያቆሙ ነው።

  8. ኮሮናቫይረስ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው የአውሮፓ እግር ኳስ

    ኔይማር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሁኑ ሰአት ተቋርጦ የሚገኘው የአውሮፓ እግር ኳስ ከዚህ በኋላ በዝግ ስታዲየሞች እንዲደሚካሄድ ግልጽ ቢሆንም መቼ የሚለው ጥያቄ ግን ምላሽ አላገኘም።

    ይህንን ያለው በአውሮፓ የሚገኙ ሊጎችን የሚወክለው ማህበር ነው።

    የማህበሩ ምክትል ኃላፊ አልቤርቶ ኮሎምቦ እንዳሉት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተቋረጠው የአውሮፓ ሊግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል።

    ‘’አብዛኛዎቹ የማህበሩ አባል ሊጎች በተለይም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እንዲጀመሩ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ነገር ግን እንደ ቤልጂየም ያሉ ጥቂት አገራት ከነጭራሹ የዘንድሮው ውድድር እንዲሰረዝ ሀሳብ አቅርበዋል’’ ብለዋል።

  9. "እናቴን በእናቶች ቀን በኮሮናቫይረስ አጣሁ"

    የቀብር ስፍራ

    የፎቶው ባለመብት, ISMAIL MONEER

    የእናቶች ቀን ሳምንታት ሲቀሩት አያ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) ለእናቷ ስጦታ እያፈላለገች ነበር።

    የ33 ዓመቷ አያ ለእናቷ ስጦታ ስትፈልግ፤እናቷን በእናቶች ቀን እንደምታጣ ፈጽሞ አልገመተችም ነበር።

    የአያ እናት ግብፅ ውስጥ ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው የመጀመሪያዎቹ አስር ሰዎች አንዷነበሩ።

    በግብጽ እስካሁን 2,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 160ው ሞተዋል።

    የአያ እናት ለሳምንት ያህል ተዳክመው ነበር።ነገር ግን በነበሩበት ሁኔታ ሕይወታቸው ያልፋል ብላ አላሰበችም።

    መሞታቸውን ስትሰማ ራሷን ስታለች።

    "ወንድሜ እየተሻላት ነው ብሎኝ ነበር። ድና ለልደቷ ወደ ቤት እንደምትመለስ ተስፋ አድርገን ነበር። የእናቶች ቀንና ልደቷን አጣምረን ልናከብርላት አስበን ነበር። ወንድሜ መሞቷን ሲነግረኝ ውሸትህን ነው አልኩት" ትላለች።

  10. በደቡብ ኮሪያ የተካሄደውን ምርጫ ገዢው ፓርቲ አሸነፈ

    ደቡብ ኮሪያ ምርጫ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ይህ ምርጫ እንደ ሌላው ጊዜ አይነት አይደለም።

    የኮሮና ወረርሽኝ ደቡብ ኮሪያውያን ድምጻቸውን ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያ ከመሄድ አላገዳቸውም።

    በምርጫ ጣቢያዎች ሰዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ድምጽ ሰጥቷል ተብሏል።

    የምርጫው ውጤትም የፕሬዝደንት ሙን ጂ ፓርቲ ማሸነፉን አመላክቷል።

    ከቻይና በመቀጠል ኮሮናቫይረስ መጀመሪያ ተሸጋግሮ የነበረው ወደ ደቡብ ኮሪያ ነበር። ይሁን እንጂ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ቫይረሱ ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ሥር አውሎታል።

  11. በአውስትራሊያ ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ አይከፈቱ የሚለው ውዝግብ አስነስቷል

    ተማሪዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ስራ ይጀምሩ የሚል አቋም ይዘዋል።

    ነገር ግን ትምህርት ቤቶች ላይ ስልጣን ያላቸው ግዛቶች በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ አልተቀበሉትም።

    ሁሉም ግዛቶች በተለይም የቪክቶሪያ ግዛት መማሪያ ክፍሎች ሙሉ ሆነው ትምህርትን ማስቀጠል አደጋ አለው ብለዋል።

    በአሁኑ ሰአት ትምህርት ቤቶች ክፍት ቢሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይልኩም ግዛቶቹ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ ሁኔታ ያበሳጫቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ልጀቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ሄደው በአስተማሪ እንዲማሩ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

    በፍርሀትና በግራ መጋባት ውስጥ የሚገኙት ወላጆች ደግሞ የማንን ትዕዛዝ መቀበል እንዳለባቸው ጨንቋቸዋል።

  12. ፒዛ የሚያደርሰው ግለሰብ በኮቪድ መያዙን ተከትሎ ከ70 በላይ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ገቡ

    በሕንድ ፒዛ የሚያደርሰው ግለሰብ በኮቪድ-19 መያዙ መረጋጋጡትን ተከትሎ ከ70 በላይ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉ ተነገረ።

    በሕንዷ ዴልሂ ከተማ የፒዛ ትዕዛዞችን ከምግብ ቤቶች ወደ መኖሪያ ቤቶች በማድረስ የሚተዳደረው ሰው በኮሮና መያዙ ከታወቀ በኋላ ከእርሱ ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ 72 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል።

    የሕንዱ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ከተደረጉት መካከል ማናቸውም ምርመራ አልተደረገላቸውም።

    "ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ። ምርመራ የሚደረግላቸው የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ከሆነ ነው" ብለዋል አንድ የጤና ኃላፊ።

  13. በርካታ ኬንያውያን ከለይቶ ማቆያ ሊያመልጡ ሞከሩ

    የኬንያታ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በአስርታት የሚቆጠሩ ኬንያውያን መንግስት ካዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ለማምለት መሞከራቸው ተሰምቷል። ምክንያታቸው ደግሞ በማዕከሉ ውስጥ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑ ነው።

    ኬንያ ድንበሮቿን ከመዝጋቷ በፊት ወደ አገሪቱ የገቡ ሰዎች በለይቶ ማቆያዎች ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል።

    ነገር ግን መንግስት ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ ቢጨርሱም ለተጨማሪ ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።

    "ከዚህ በኋላ ወደ ማዕከሉ የመመለስ ፍላጎት የለንም። አንደኛ ሳይንሱ ለሚያዛቸው ቀናት ያክል በለይቶ ማቆያው ቆይተናል፤ ሁለተኛ ከዚህ በላይ ለመንግስት መክፈል አንችልም‘’ ብሏል በኬንያታ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያለው ሲሞን ሙጋምቢ።

    "ሁለት ጊዜ ተመርምረን ውጤታችን ቫይረሱ እንደሌለብን ቢያሳይም በለይቶ ማቆያው እንደንቆይ ተደርገናል። ሁሉንም ወጪ ምንሸፍነው ደግሞ እኛ ነን።"

  14. "የምናውቀው ሰው እስኪሞት መጠበቅ የለብንም" ዶ/ር ፅዮን ፍሬው

    ዶ/ር ፅዮን ፍሬው

    የፎቶው ባለመብት, @DRTSION/TWITTER

    የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ፅዮን ፍሬው

    የድንገተኛ ክፍል እና የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስቷ ዶ/ር ፅዮን ፍሬው የጤና ጥበቃ አማካሪ ናቸው።

    በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በሆነባት የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ የሚሠሩት ዶ/ር ፅዮን የኮሮናቫይረስ ይዟቸው እንዳገገሙ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

    ስለ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል እየወሰደች ስላለችው እርምጃ ዶ/ር ፅዮንን ከጥቂት ሳምንታት በፊት አነጋግረናቸው ነበር።

    በተለይም በአሁን ወቅት “መዘናጋት ትክክል አይደለም” ሲሉ ዶክተሯ ይናገራሉ። “የምናውቀው ሰው እስኪሞት መጠበቅ የለብንም፤ ቁጥሩ 40 ሺህ ወይም 60 ሺህ እስኪደርስ መጠበቅ የለብንም። በጣም የምወደው ሰው ከዚህ በሽታ ሊሞት ይችላል ብለን ማሰብ አለብን” በማለትም ዶ/ር ፅዮን ያክላሉ።

  15. አሰቃቂው የኢራን አስክሬን ማቆያ ክፍል ገጽታ

    በኮሮናቫይረስ ለሞተ ሰው በኢራን ቀብር ሲፈጸም

    የፎቶው ባለመብት, MEHR NEWS AGENCY

    የምስሉ መግለጫ, በኮሮናቫይረስ ለሞተ ሰው በኢራን ቀብር ሲፈጸም

    አንድ በስፋት እየተሰራጨ ያለ ቪድዮ በኢራን በመንግሥት የአስክሬን ማቆያ ክፍል ውስጥ የተቀረጸ ነው። በቪድዮው ላይ ሠራተኞች በበርካታ አስክሬኖች ተከበው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ይታያል።

    ገሚሱ አስክሬን በነጭ ጨርቅ ተጠቅልሏል። ሌላው በጥቁር ላስቲክ ተከቷል።

    ቪድዮውን እየቀረጸ ያለው ሰው በነጭ ጨርቅ የተጠቀለሉት ዛሬ ጠዋት "የተሠሩ" ናቸው ይላል።

    ከዛ ደሞ በጥቁር ላስቲክ የተጠቀለሉ አስክሬኖችን እያሳየ "እነዚህ ደግሞ ቀብራቸው ከመፈጸሙ በፊት ገና ለቀብር ዝግጁ የሚደረጉ ናቸው" ሲል ይናገራል።

  16. በዉሃን ከተማ የሚገኙ ጥንዶች ለመጋባት እየተጣደፉ ነው

    ጥንዶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮናቫይረስ መጀመሪያው የተጠቃችው የቻይናዋ ዉሃን ከተማ የሚኖሩ ጥንዶች በመንግስት ቢሮዎች እውቅና ለማግኘት እየተመዘገቡ ነው። በርካቶችም ወደ ፎቶ ስቱዲዮዎች በመሄድ የሰርግ ፎቶዎች እየተነሱ ይገኛሉ።

    ለ11 ሳምንታት ከእንቅስቃሴ ታግደው የነበሩት ጥንዶች ጥድፊያ ከተማዋ ወደ ቀደመው ሁኔታዋ እንደተመለሰች ማሳያ ነው ተብሏል።

    ልክ መጋቢት 30 ቀን ላይ ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ያሳወቀችው ዉሃን በአሁኑ ሰአት በርካታ ሰዎች በመንድ ይታዩባታል።

    ጥንዶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ጥንዶችም ለወራት ተራዝሞባቸው የነበረውን የሰርግ ስነ-ስርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን ደፋ ቀና እያሉ ነው።

    ‘’ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የሰርግ ፎቶ የሚነሱ ጥንዶች ቁጥር በጣም ከፍ ቢልም በቀን ሁለት ወይም ሶስት ብቻ ነው የምናስተናግደው’’ ብሏል አንድ ቢቢሲ ያነጋገረው የፎቶ ስቱዲዮ ባለቤት።

  17. ትራምፕ ቫይረሱ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበትን ጊዜ አልፏል አሉ

    Trump

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድ ትራምፕ ቫይረሱ በአሜሪካ ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት ጣሪያን ማለፉን እና አንዳንድ ግዛቶች በዚህ ወር መከፈት እንደሚጀምሩ ተናገሩ።

    ትራምፕ ቫይረሱን በማስመልከት በዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ ላይ፤ ከአሜሪካ ግዛት አስተዳዳሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ግዛቶቹ ስለሚከፈቱበት ሁኔታ ዛሬ ምሽት መግለጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

    "አሃዞች እንደሚያሳዩት በመላው አገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው" በማለት ትራምፕ ተናግረዋል።

    አሜሪካ 638,000 ዜጎቿ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ30,800 በላይ ነው።

    ከሌሎች አገራት በላይ በአሜሪካ በቫይረሱ የሞቱ እና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ለምን ከፍ አለ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬዝደንቱ ሲመልሱ፤ "እንዳንድ አገራት የሚያወጡትን አሃዝ የሚያምን አለ?" በማለት የቻይናን ስም ጠቅሰዋል።

    ትራምፕ ጨምረውም ቫይረሱ በቻይዋ ዉሃን ከተማ ሳይሆን ከዉሃን ላብራቶሪ ነው የወጣው ስለሚባለው ያልተረጋገጠ ሪፖርት አሜሪካ ትመለከተዋለች ብለዋል።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በቤጂንግ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በዉሃን በሚገኙ ሁለት ላብራቶሪዎች የደህንነት ጉዳይ ያሳስበናል ሲል ሪፖርት ስለማድረጉ ዘግበዋል።

  18. በኮሮናቫይረስ የሞተችው ነፍሰ ጡር ነርስ ልጅ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል

    አርግዬዋ

    የፎቶው ባለመብት, Other

    እንግሊዝ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወቷ ካለፈ አንዲት ነፍሰ ጡር ነርስ ልጇ በሰላም እንዲወጣ መደረጉ ተሰምቷል።

    የ28 ዓመቷ አርግዬዋ አግያፖንግ በሉተን እና ደንስቴብል ሆስፒታል ለአምስት ዓመታት የሰራች ሲሆን ሕይወቷም ያለፈው በዚሁ ሆስፒታል ነው።

    አርግዬዋ ከአስር ቀናት በፊት ነበር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሆስፒታል የገባቸው።

    የሆስፒታሉ ኃላፊ ዳቪድ ካርተር አርግዬዋ በጣም ተወዳጅና ታማኝ ነርስ ነበረች ብለዋል። የተወለደው ልጅ ወንድ ይሁን ሴት ባይጠቅሱም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ግን ተናግረዋል።

    የአርግዬዋ ባለቤትም ቫይረሱ የተገኘበት ሲሆን በአሁኑ ሰአት በቤት ውስጥ እራሱን ከሌሎች አግልሎ ይገኛል።

  19. ውድ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች እንደም አደራችሁ?

    Addis Ababa

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ዘገባችን ከቫይረሱ ስርጭት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በፍጥነት እናደርሳችኋለን።

    ዛሬ ፀሎተ ሐሙስ ነው። መንግሥትና የሃይማኖት አባቶች የሚሰጡትን የጥንቃቄ መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጋችሁን አትዘንጉ።

    የትናንት ዘገባችንን ከታች መመልከት ትችላላችሁ።

  20. የዛሬውን ጨርሰናል፤ ነገ እንመለሳለን

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች፤ ለዛሬ ያልነውን አጠናቀናል። ነገ በሌሎች የአገር ውስጥና የውጪ ዘገባዎች እንመለሳለን።

    ራሳችሁን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አትዘንጉ።

    መልካም ምሽት!