እስራኤል በምሥራቅ ኢየሩሳሌም በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ ትምህርት ቤቶችን ዘጋች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የታጠቁ የእስራኤል የደህንነት ኃይሎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፍልስጤማውያን ስደተኞች የሚደገፉ ሦስት ትምህርት ቤቶችን እስራኤል በኃይል በያዘችው ምሥራቅ እየሩሳሌም መዝጋታቸው ተገለፀ።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተማሪዎች ሐሙስ ዕለት ጠዋት ትምህርት እንደጀመሩ የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች ካስወጧቸው በኋላ ወደ ሹአፋት የመጠለያ ጣብያ እንዲሄዱ ተደርገዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ የእስራኤል ባለሰልጣናት ሕጸናት ትምህርት የማግኘት መሰረታዊ መብታቸውን እየነፈጉ ነው በማለት "የዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ መናቅ" ነው ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።
እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ለፍልስጤማውያን ስደተኞችን ያገደቸው በጥር ወር ሲሆን በኤጀንሲው ሃማስ ሰርጎ ገብቷል ስትል ትከስሳለች።
ኤጀንሲው በበኩሉ የቀረበበትን ውንጀላ አስተባብሎ ገለልተኛ መሆኑን ገልጿል።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት የእስራኤል መከላከያ በትምሀርት ቤቱ አካባቢ መሰባሰቡን ተከትሎ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሳቸውን የለበሱ ሴት ተማሪዎች ሹአፋት በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውጪ ተሰብስበው ሲተቃቀፉ ይታያል።
በትምሀርት ቤቱ ግድፈግዳ ላይ የተለጠፈው መዘጋቱን የሚገልጸው ማስታወቅያ "ትምህርታዊ ተቋም ከፍቶ ወይንም መምህራንንም ሆነ ሌሎች ሠራተኞችም ቀጥሮ መስራት የተከለከለ ነው። እንዲሁም ተማሪዎችን መዝግቦ ወይንም ወደዚህ ተቋም ተማሪዎች እንዲገቡ ማድረግ የተከለከለ ነው" ይላል።
ኤጀንሲው እድሜያቸው ከስድስት እስከ 15 ዓመት የሆነ ከ550 ተማሪዎች በላይ ተማሪዎች እንደነበሩት እና አንድ ሠራተኛው በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል።
በእስራኤል በቁጥጥር ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ የሚገኘው ትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር "የመማር እድላቸውን ላጡት ታዳጊ ልጆቹ ድርጊቱ የሚያስጨንቅ ነበር" ብለዋል።
ኤጀንሲው በምሥራቅ ኢየሩሳሌም በሚገኙ ሦስት ትምህርት ቤቶች የእስራኤል ፖሊስ መሰማራቱን እና ተማሪዎቹን ወደ ቤታቸው እንዲልኩ ማስገደዳቸውን ተናግሯል።
"ወደ ትምሀርተ ቤቶቹ በኃይል ገብቶ እንዲዘጉ ማስገደድ ዓለም አቀፍ ሕግን ሆን ብሎ መናቅ ነው"ሲሉ ፊሊፔ ላዛራኒ በኤክስ ገጻቸውለይ ለጥፈዋል።
"ትምህርት ቤቶቹ ሊጣሱ የማይገባቸው የተባበሩት መንግሥታት ቅጥር ግቢዎች ናቸው"
አክለውም "ባለፈው ወር እንዲዘጋ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የእስራኤል ባለሰልጣናት የፍልስጤማውያን ሕጻናት የመማር መሰረታዊ መብትን ነፍገዋል" ብለዋል።
"የኤጀንሲው ትምህርት ቤቶች የቀጣዩን ትውልድ ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል አገልግሎት መስጠታቸውን መቀጠል አለባቸው"
በእስራኤል ቁጥጥር ስር ያልሆነውን ከፊል ዌስት ባንክን የሚያስተዳደርረው የፍልስጤም አስተዳደር የእስራኤል እርምጃ "የሕጻናትን የመማር መብት የሚጋፋ ነው" ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።
በኢየሩሳሌም የሚገኘው የብሪቴን ቆንጽላ ዩኬ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድስ፣ ቱርክ እና ጃፓን በተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ስር ያሉት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን እንደሚቃመሙ በመግለጽ "ከተማሪዎቹ፣ ወላጆቻቸው እና መምህራኑ" ጎን እንቆማለን ብሏል።
"የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤማውያን ስደተኞች ኤጀንሲ በምስራቅ ኢየሩሳሌም፣ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ በተሰጠው ሰልጣን በ1950 የተቋቋመ ነው። እስራኤል በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ እርዳታ ሕግ ሕጻናት ትምህርት ላይ ለሚሰሩ ተቋማት ተገቢ የሆነ የስራ ሁኔታ እንዲኖር የማመቻቸት ግዴታ አለባት" ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የእስራኤል ፓርላማ በአገሪቱ ባለስልጣናት እና በኤጀንሲው መካከል ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖር ከልክለዋል፤ ኤጀንሲው በእስራኤል ግዛት ውስጥ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎችም አግዷል።
እስራኤል ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን በቁጥጥሯ ስር ያስገባችው እአአ በ1967 በተካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት ነው።
ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን በ1980 ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሯ ስር ያስገባችው እስራኤል ሙሉ ከተማውን እንደ ዋና ከተማዋ ትቆጥራለች።
ይህንን የእስራኤል መንግሥት እርምጃ የተለያዩ የዓለም መንግሥታት ማኅበረሰብ አባላት እውቅና አልሰጡትም።
ፍልስጤማውያን ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ወደፊት ለሚመሰርቱት ነጻ ግዛት እንደ ዋና ከተማ ይመለከቱታል።
በአሁኑ ወቅት በግምት 230,000 እስራኤላውያን ሰፋሪዎች እና 390,000 ፍልስጤማውያንም በአካባቢው ይኖራሉ።
በርካታ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት እስራኤል በምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና በተለያዩ የዌስት ባንክ አካባቢዎች ያካሄደችው ሰፈራዎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ሕገወጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።












