አንጀሊና ጆሊ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን አምባሳደርነቷን በፈቃዷ ለቀቀች

አንጀሊና ጆሊ በስደተኞች ጉዳይ አምባሳደርነት ለ20 ዓመታት ሰርታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አንጀሊና ጆሊ በስደተኞች ጉዳይ አምባሳደርነት ለ20 ዓመታት ሰርታለች
ታትሟል

ታዋቂዋ አሜሪካዊት የፊልም ተዋናይ አንጀሊና ጆሊ ለ20 ዓመታት ካገለገለችበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የአምባሳደርነት ሚናዋ በፈቃዷ መልቀቋን አስታወቀች።

የ47 ዓመቷ ጆሊ “በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በማቅረብ የተባበሩት መንግሥታት የበርካቶችን ሕይወት የታደገ ሥራ አከናውኗል ብዬ አምናሁ” ብላለች።

ጨምራም ከመንግሥታቱ ድርጅት ሚናዋ ከለቀቀች በኋላ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንደምትሰማራ “በግጭቶች ክፉኛ የተጠቁ ሰዎች ድምጽ በደንብ እንዲሰማ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር እሰራለሁ” በማለት ተናግራለች።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን እንዳለው አንጀሊና ጆሊ ከፍ ያለ ተጽእኖን መፍጠር ከቻሉ የስደተኞች መብት አቅንቃኞች መካከል አንዷ ናት ሲል አድናቆቱን ገልጿል።

የሆሊዉድ ኮከብ ተዋናይ የሆነችው ጆሊ በኢንስታግራም ገጿ ላይ “ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ጋር ለ20 ዓመታት ከሰራሁ በኋላ ዛሬ ቦታዬን ለቅቄያለሁ። ስደተኞች በዓለም ላይ የማደንቃቸው ሰዎች ናቸው፣ ቀሪ ሕይወቴን በሙሉም ከእነሱ ጋር ለማስራት ሰጥቻለሁ” ብላለች።

ነገር ግን አንጀሊና ጆሊ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ስታከናውን የቆየችው ሥራ ካቆመች በኋላ ከየትኞቹ ድርጅቶች ጋር በቀጣይ ለመስራት እንዳቀደች የሰጠችው ዝርዝር መረጃ የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ላይ ጆሊ “ሰፋ ባለ የሰብአዊ እርዳታ እና የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ እንደምተሰማራ” ገልጿል።

መግለጫው “ጆሊ ስደተኞች የሚያልፉበትን የስቃይ ታሪክ ለመመልከት እና ተስፋ እንዲሁም ጽናታቸውን በአካል ተገኝታ ለመመልከት ከ60 በላይ ተልዕኮዎችን ካለድካም ከኮሚሽኑ ጋር አከናውናለች” ሲል አስተዋጽኦዋን ዘክሯል።

ሚስተር ኤንድ ሚስ ስሚዝ እና ላራ ክሮፍት፡ ቶምብ ሬይደር የተባሉትን ጨምሮ በበርካታ በዓለም ዙሪያ ዝናን ባተረፉ ፊልሞች ላይ የተወነችው ጆሊ፣ ከመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር መሥራት የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 2001 ነበር። በማስከተልም በ2013 የኮሚሽኒ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን አስካሁን አገለግላለች።

ከኮሚሽኑ ጋር ስትሰራ የቆየችው አንጀሊና ጆሊ ባለፉት ወራት በጦርነት ውስጥ በሚገኙት ዩክሬን፣ የመን እና ቡርኪናፋሶ ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን አግኝታለች።