ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስፔን ክሮሺያን በመርታት የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ዋንጫን አነሳች
ክሮሺያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ዋንጫ ለማንሳት የነበራት ሕልም በስፔን መክኗል።
በሮተርዳም የተካሄደው የፍፃሜ ፍልሚያ ከ120 ደቂቃዎች በኋላ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሄድ ግድ ሆኗል።
ዳኒ ካርቫሃል ለስፔን የማሸነፊያዋን ጎል በማስቆጠር ብሔራዊ ቡድኑ ዋንጫ እንዲያነሳ አግዟል።
የስፔን ብሔራዊ ቡድን በፈረንጆቹ 2012 የአውሮፓ ዋንጫን ካሸነፈ በኋላ ያነሳው የመጀመሪያው ዋንጫ ነው።
የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠው ሮድሪ ጨዋታው ከባድ እንደነበር ጠቅሶ በድሉ እጅግ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።
ሮድሪ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ሶስት ዋንጫ ካነሳ ድፍን ወር ሳይሞላው ነው ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የኔሽንስ ሊግ ዋንጫ ባለቤት መሆን የቻለው።
ተጫዋቹ ይህ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን ትልቅ መነቃቃት እንደሚሆን ተስፋ አለው።
የረሚ ፒኖ፣ ጋቪ እና አንሱ ፋቲን የመሳሰሉ ወጣት ተጫዋቾች በአዲሱ የስፔን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተዋል።
ስፔን ከፈረንሳይ ቀጥሎ የዓለም ዋንጫ፣ የአውሮፓ ዋንጫና የኔሽንስ ሊግ ዋንጫ ማንሳት የቻለች ሁለተኛዋ የአውሮፓ ቡድን ሆናለች።
ስፔን ባለፈው የዓለም ዋንጫ ወደ መጨረሻው 16 ደርሳ በፍፁም ቅጣት ምት በሞሮኮ ተረትታ መውደቋ አይዘነጋም።
በሌላ በኩል ለሃገሩ ዋንጫ ለማምጣት ብዙ የጣረው ሞድሪች ሳይሳካለት ቀርቷል።
በ2018 የዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ደርሶ የተሸነፈው፤ በ2022 ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የክሮሺይ ብሔራዊ የመጀመሪያ ዋንጫውን ለማንሳት ጫፍ ደርሶ ነበር።
በሮተርዳም በነበረው ፍልሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ የክሮሺያ ደጋፊዎች ለብሔራዊ ቡድናቸው ድጋፍ ሲሰጡ አምሽተዋል።
166 ጊዜ ለሃገሩ የተሰለፍው ሉካ ሞድሪች አስደናቂ የእግር ኳስ ሕይወቱን የሚያጠናቅቅበት መልካም አጋጣሚ ነበር።
ይህ ጫና ይመስላል ክሮሺያዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ብለው ነው ጨዋታውን የጀመሩት።
ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ግማሽ ሰዓት ሲያመራ ክሮሺያ ስፔን ላይ ጫና ማሳደር ተያያዘች። ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች በጨዋታ ጎል ማስቆጠር ተሳናቸው።
በመለያ ፍፁም ቅጣት ስፔን 5-4 በማሸነፍ የውድድሩ አውራ ሆና አጠናቃለች።
የ37 ዓመቱ ሞድሪች ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ይቀጥላል ወይስ ጫማ ይሰቅላል የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።
ተጫዋቹ በሚቀጥለው ዓመት መገባደጃ ጀርመን በምታዘጋጀው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ሊሳተፍ ይችላል የሚል ግምት አለ።