እስራኤል ዜጎችን ጨምሮ የጥቃት አድራሽ ቤተሰቦችን ከሀገሯ የሚያስወጣ ሕግ አፀደቀች

የእስራኤል ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤል ፓርላማ ዜጎችን ጨምሮ በሽብርተኝነት ወንጀል የተፈረደባቸው ሰዎች ቤተሰቦችን መንግሥት ከሀገር እንዲያባርር የሚያስችል ሕግ አፅድቋል።

አከራካሪ የተባለው ሕግ ሊኩድ በተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ፓርቲ የቀረበ ነው። የሽብር ድርጊት የፈፀሙ አሊያም የደገፉ ሰዎች ወላጆች፣ እህትና ወንድሞች እንዲሁም ልጆች ከእስራኤል እንዲባረሩ ይደረጋል።

የእስራኤል ሰብዓዊ መብት ድርጅት አዲሱ ሕግ ሕገ-መንግሥታ አይደለም ብሏል።

አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አዲሱ ሕግ የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ፍልስጤማዊያን ላይ ያነጣጠረ ነው ሲሉ ትችታቸውን አሰምተዋል።

አዲሱ ሕግ እንደሚለው ስለሽብር ጥቃት መረጃ ያላቸው አሊያም ለፖሊስ አቤቱታ ያላቀረቡ ወይም “ለሽብር ድርጊት ድጋፋቸውን የገለፁ እና ግንኙነት ያላቸው” ሰዎች ቤተሰቦች ከሀገር ይባረራሉ።

በተጨማሪም “የሽብር ድርጊት እና ሽብርተኛ ቡድንን ያደነቁ አሊያም ድጋፋቸውን በለተያዩ መንገዶች የገለፁ” ከሀገር እንዲወጡ ሊደረግ ይችላል።

እኒህን ሰዎች ከሀገር የማስወጣት ኃላፊነት የተጣለበት የእስራኤል የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ነው።

ክርክር እየተደረገበት ሳለ አንዳንድ የፓርላማ አባላት ሕጉ አይሁዳዊ እስራኤላዊያን ላይ ልንጠቀመው አይገባም የሚል ሐሳብ ማንሳታቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል በድረ-ገፁ አስነብቧል።

“የይጋል አሚር ቤተሰቦች ወደየትም አይባረሩም” ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባሉ ሜራቭ ሚካኤሊ ተናግረዋል። ይጋል አማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ይትዣክ ራቢን ገዳይ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሚኪ ሌቪ ደግሞ በወጣትነታቸው ሽብርተኛ ቡድኖችን የደገፉ አይሁዳዊ እስራኤላዊያንንስ “ታባርራላችሁ ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

እስራኤላዊው የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ዳሊያ ሻይንድሊን አዲሱ ሕግ ለፍልስጤማዊያን እና ለአረብ እስራኤላዊያን የወጣ ስለመሆኑ “ምንም ጥርጥር የለውም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የእስራኤል ዜግነት ያለው አይሁድ በዚህ ሕግ ሳቢያ ከሀገር ይባረራል የሚል ግምት የለኝም” ይላሉ።

“እርግጥ ነው ይህ ሕጉ ውስጥ አልተካተተም። ነገር ግን እንዴት ነው ተግባራዊ የሚደረገው የሚለው ወሳኝ ነው። አይሁዳዊያን ፍልስጤማዊያን ላይ የሚፈፅሙት ጥፋት “የሽብር ድርጊት” ተብሎ ሲጠራ እኔ በፍፁም ሰምቼ አላውቅም።”

ከእስራኤል ሕዝብ 20 በመቶው የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ፍልስጤማዊያን ናቸው።

ባለፈው ወር አንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ መግጨቱ አይዘነጋም። የእስራኤል ፖሊስ ግለሰቡ የእስራኤል ዜግነት ያለው ፍልስጤማዊ ነው ብሎ ነበር።

በርካታ አረብ እስራኤላዊያን በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው ለሐማስ ያላቸውን ድጋፍ በመግለፃቸው ምክንያት ፍርድ ተፈርዶበቸዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴሩም ሆነ የአቃቤ ሕግ ቢሮ አዲሱ ሕግ እንዴት ነው ተግባራዊ የሚደረገው የሚለው ላይ ስጋት እንዳላቸው ግልፀዋል። አዲሱ ሕግ ተቃውሞ ሊገጥመውና ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል ይጠበቃል።

የእስራኤል ዲሞክራቲክ ተቋም አጥኚ የሆኑት ኢራን ሻሚር-ቦረር ሕጉ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያመራ ከሆነ ውድቅ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው ይላሉ።

ከእስራኤል የሚባረሩት ቤተሰቦች ወደ ጋዛ አሊያም “እንደ ሁኔታው ወደ ተመቻቹ መዳረሻዎች ያቀናሉ” ተብሏል።

ከእስራኤል ወታደሮች በቀር ማንኛውም የእስራኤል ዜጋ ወደ ጋዛ መግባት አይፈቀድለትም።

እስካሁን 100 ገደማ እስራኤላዊያን በሐማስ ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት። ከእነዚህ መካከል 60 ገደማው በሕይወት እንዳሉ ይገመታል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ዜግነታቸውን የማይነጠቁ ሲሆን ነገር ግን ከ7 እስከ 15 ዓመታት ድረስ ወደ እስራኤል ተመልሰው እንዲመጡ አይፈቀድላቸውም።

የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ደግሞ ከ10 እስከ 20 ዓመታት ወደ እስራኤል እንዳይገቡ ሊታገዱ ይችላሉ።

ከሀገር ከሚያስወጣው ሕግ በተጨማሪ በሽብር ጥቃት አማካይነት የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑት ታዳጊዎችን ለሕግ የሚያቀርብ ጊዜያዊ መመሪያ ፀድቋል።