በኢየሩሳሌም የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሬት ሽያጭ የፈጠረው ቁጣ

በኢየሩሳሌም የአርመኖች ይዞታ
ታትሟል

ጥንታዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ በተለያዩ ዕምነቶች ዘንድ ቅድስት ስፍራ ተደርጋ ነው የምትቆጠረው።

በክርስትና፣ በእስልምና እና በአይሁድ እምነት ተከታዮች በምድር ካሉ ቅዱስ ቦታዎች መካከል ዋነኛዋ ተደርጋ የምትታየው ኢየሩሳሌም የግጭትም ማዕከል ናት።

ለበርካታ ዓመታትም የእስራኤል መንግሥት እና ፍልስጤማውያን መፋለማቸውን ቀጥለዋል።

ይህች ጥንታዊ ከተማ የአርመን፣ የግብፅ፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ገዳማት እና አብያተ ክርስትያናትንም ይዛለች።

ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አገር ክርስትናን ብሔራዊ ሃይማኖት አድርጋ የተቀበለችው አርሜኒያ፣ ኢየሩሳሌምን ማዕከል ያደረገችው ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው።

አርመኖች በክርስትና ዕምነት ቅዱስ ስፍራ የሚባሉ ቦታዎችን ኢየሩሳሌም ውስጥ ይዘዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢየሩሳሌምም 2 ሺህ ያህል አርመኖች ይኖራሉ።

በአሁኑ ወቅት ግን የአርመኖች በኢየሩሳሌም የመኖር ሁኔታ ስጋት ላይ ወድቋል።

የራሳቸው የቤተክርስቲያን አባቶች የአርመኖች የመሬት ይዞታዎችን ለሽያጭ ማቅረባቸው ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሯል።

አርመኖችንም በከፍተኛ ሁኔታ አስቆጥቷል። በአሁኑ ወቅት በርካቶች ቁጣቸውን ለመግለጽ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህ የአርመኖች እየተንቀለቀለ ያለ ቁጣ ፓትርያርኩ እንዲደበቁ አደርጓቸዋል።

ከእሳቸው በተጨማሪም ምንም ስህተት አልተሰራም ብለው የካዱ እና በርካቶች ያወገዟቸው ሌላ ካህንም የማኅበረሰቡን ቁጣ ፈርተው ወደ አሜሪካ ተሰደዋል።

“ሁኔታው እንቆቅልሽ ሆኖብናል። ማለቴ ምን እንደተፈጠረ፣ መቼ እንደሆነ እና እንዴትስ እንዲህ ሊሆን ቻለ? የሚለውን ለማወቅ እየሞከርን ነው” ሲሉ የማኅበረሰቡ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሃጎፕ ዲጄርናዚያን ያስረዳሉ።

ምንድን ነው የተከሰተው? የአርመኖች የመሬት ይዞታ ከሆነው 25 በመቶው ምስጢራዊ በሆነ የሊዝ ውል ተሽጧል።

ለ99 ዓመት የተፈረመው ይህ የሊዝ ውል አንድ አይሁዳዊ አውስትራሊያዊንም የመሬት ባለቤት አድርጎታል።

የተሸጠው መሬት ትልቅ የመኪና ማቆሚያ ቦታንም ያካትታል። ይህ ስፍራ በጥንታዊቷ ከተማ ካሉት ጥቂት ክፍት ቦታዎች አንዱ ነው። በርካታ አርመኖችም ይህንን ስፍራ ለወጣቱ ትውልድ በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሪያ ቤት ለመገንባትም አስበውት የነበረ ነው።

ይህንን ምስጢራዊ ውል የተመለከቱት ሃጎፕ እና ሌሎች እንደሚናገሩት አምስት የአርመን ቤተሰቦችን የያዘ እና በኦቶማን ዘመን የተሰራ ህንጻ፣ ሬስቶራንት፣ ሱቆች እንዲሁም የኦርቶዶክስ እምነት መንፈሳዊ ትምህርት ቤትንም ይሸፍናል።

በርካቶች መሬቱ በዚህ መንገድ ተሸንሽኖ መሸጡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የአርመን ማኅበረሰብ አባላtእ ህልውናን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው።

ከዚያም አልፎ የታሪክንም ሁነት ያላገናዘበ ነው ይላሉ።

“ለ700 ዓመታት የኖርንበት ታሪካዊ መሬት ነው። በአንድ ፊርማ ይህንን መሬት ማጣት በባህላችን፣ በየዕለቱ ሕይወታችን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል። ከዚያም በላይ የኢየሩሳሌምንም ገጽታ ይለውጣል። የታሪካዊቷ ኢየሩሳሌምን መዋቅር እንዲሁም ዕይታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነው” ይላሉ ሃጎፕ።

የአርመን ካህናት

የኢየሩሳሌምን ገጽታ የሚቀይረው ስምምነት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢየሩሳሌም በፋሲካ በዓል ትደምቃለች።

በተለይም በሚያዝያ ወር ላይ በሚውለው የኦርቶዶክስ የፋሲካ በዓል።

ከወትሮው በተለየ በዘንድሮው ግን አርመኖች ፋሲካን ያከበሩት በስጋት ተሞልተው ነው።

‘መሬታቸው የመነጠቁ’ ዜናም የተሰማበት ወቅት ነው።

የአርመኑ ፓትርያርክ ኑርሃን ማኑግያን መሬቱን ፈርመው እንደሰጡ ቢያምኑም፣ ለእሳቸው ይሰሩ በነበሩ በአካባቢው ቄስ “ተታልያለሁ” ይላሉ።

ቄሱ ከካህንነት ሥልጣናቸው እንዲሻሩም ተደረገ። ከአርመኖች መኖሪያ ስፍራ ሲባረሩም በእስራኤል ፖሊስ ጥበቃ ታጅበው ሲሆን፣ ነዋሪዎቹም በቁጣ “ከሃዲ” እያሉ እየጠሯቸው ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በርካታ አርመኖች ሳምንታዊ ተቃውሞ እያደረጉ ይገኛሉ። እጅ ለእጅ ተያይዘውም፣ አገራዊ መዝሙሮችን በመዘመርም ተቃውሟቸውን ፓትርያርኩ ካሉበት ገዳም መስኮት ስር ሆነው ያሰማሉ። ፓትርያርኩ ከገዳማቸው ሲወጡ አይሰማም ተደብቀውም ነው ያሉት።

አርመኖቹም ፓትርያርኩን የመሬት ውሉን እንዲሰርዙ እየጠየቁ ይገኛሉ።

በጽንፈኛ አይሁዶች የሚፈጸሙ በኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመሩ ይገኛሉ። እናም አሁን የተደረገው የመሬት ሽያጭ በስፍራው በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ራስን የመጉዳት ተግባር አድርገው ይመለከቱታል። ውሉ በክርስትና ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው የሚሉም አልታጡም።

“የከተማዋ ገጽታ፣ ሁኔታዋ፣ ታሪኳ እየተቀየረ ነው” ትላለች በጥንታዊቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆነችው አርዳ።

በተለይም በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ የታየው ለውጥ ጽንፈኛ የሃይማኖት ብሔርተኞችን የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል ትላለች።

“በጎዳና ላይ የሚራመዱ ካህናት ላይ ሰፋሪዎች መትፋት ጀምረዋል። በከተማው ውስጥ የገና ዛፎችን ማየት እንደማይፈልጉ ይናገራሉ። የክርስቲያን ምግብ ቤቶች ያለ ምክንያት ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። ነገሮች ወደ ሆነ አቅጣጫ እየሄዱ ነው” ትላለች።

እስራኤል ጥንታዊቷ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን በኃይል የተቆጣጠረችው በአውሮፓውያኑ 1967 ነው።

በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትም በዮርዳኖስ ቁጥጥር ስር የነበረችውን ኢየሩሳሌምን በመውረር ወደ ግዛቷ ቀላቀለች። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ግዛቲቱ የእስራኤል ናት የሚል እውቅና አልሰጠም።

ከዚያ ወዲህ ባሉት አስርት ዓመታትም ከተማዋ ግጭት እና ጦርነት የማያጣት ሆናለች። ፍልስጥኤማውያን ግዛታችንን በወረራ እና በኃይል ተነጠቅን ሲሉ፣ እስራኤል በበኩሏ ታሪካዊ ይዞታዬ ነው ትላለች። የእየሩሳሌም መሬቶች ይዞታም ውዝግብ አያጣውም።

የአርመኖች ሰፈር (አርመኒያን ኳርተር) የክርስቲያኖች መግቢያ በሆነው ጃፋ ጌት አካባቢ ይገኛል።

እዚህ አካባቢ በፍልስጤማውያን የሚተዳደሩ ሁለት ታሪካዊ ሆቴሎች ለሁለት የውጭ ኩባንያዎች ተሸጡ።

ጽንፈኛ እና አክራሪ የአይሁድ ሰፋሪዎች ቡድኖች ሁለቱን ኩባንያዎች በሽፋንነት በመጠቀም ነበር ሆቴሎቹን የገዟቸው።

የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይህ ስምምነት እንዲሰረዝ ለሁለት አስርት ዓመታት በፍርድ ቤት ስትሟገት ቆይታለች።

ሆኖም ቤተ ክርስቲያኗ በፍርድ ቤት መሸነፏን ተከትሎ ሰፋሪዎች ባለፈው ዓመት ወደ አንደኛው ሆቴል ገብተዋል።

የአርመን ሽማግሌዎች እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ሰፋሪዎች የአርመኖችን መሬት ለመግዛት ተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀርቡ እንደነበር ነው። ሰፋሪዎቹ ዋነኛ ዓላማቸው በምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁዶችን ቁጥር መጨመር ነው።

የአርመኖች ሰፈር የሚገኘው የአይሁድ ሰፋሪዎች በሚኖሩበት አካባቢም በመሆኑ ስፍራውን በጣም ተፈላጊ ያደርገዋል።

ሆኖም የጃፋ ጌት ንብረቶችን የገዙት የአይሁድ ሰፋሪዎች ቡድን ቃለ አቀባይ አሁን ስለተደረገው የአርመኖች መሬት ሽያጭ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አርመኖች

የአርመን ፓትርያርክ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል

የክህነት ማዕረጋቸው ተገፏል እንዲሁም ተወግዘው ተባረዋል ከተባሉት ካህን ባሬት ዬሬትሲያን መሬቱን በሊዝ የገዙት ዳኒ ሮትማን ወይም በአንዳንድ ሰነዶች ላይ ዳንኤል ሩቢንስታይን ተብለው የተጠሩት ግለሰብ ከዚህ የአርመኖች መሬት ጀርባ ፓለቲካዊ አላማ አላቸው መባሉን አጣጥለውታል።

ነገር ግን የፍልስጥኤም ክርስቲያን መሪዎች የመሬቱ ሽያጭ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው ይላሉ።

“ኢየሩሳሌምን በተመለከተ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን የሚያዳክም ነው” በማለት የቅድስት አገር ብሔራዊ የክርስቲያን ጥምረት ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ዲሊያኒ ይናገራሉ።

“በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ይህ በኃይል የተያዘ [የተወረረ] መሬት ነው። መሬቱም ድርድር እና ውይይት የሚያስፈልገው ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነት ሽያጮች በፍልስጥኤም ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ይዞታ ላይ ያሉ ሕገወጥ ሰፋሪዎችን የሚያጠናክር ነው” ይላሉ።

በተጨማሪም የኢየሩሳሌምን “ብዝኃነት” ክፉኛ እንደሚጎዳም ያምናሉ።

የአርመን ቤተ ክርስቲያን ድርጊት አርመኖችን ብቻ አይደለም ያስቆጣው።

የፍልስጥኤም ፕሬዝዳንት፣ የኢየሩሳሌም የክርስቲያን ቅዱሳን ስፍራዎች ጠባቂ የሆኑት የዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ 2ኛ ለአርመን ፓትርያርክ ያላቸውን እውቅና አንስተዋል።

ይህም የእውቅና መነፈግ በክብረ በዓላት ላይ መገኘት እና ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን በተመለከተ ተወካይ ሆነው በመገኘት ሁኔታዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖን የሚያሳርፍ ነው።

የቅድስት ሃገር ብሔራዊ የክርስቲያን ጥምረት ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ዲሊያኒ
የምስሉ መግለጫ, የቅድስት አገር ብሔራዊ የክርስቲያን ጥምረት ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ዲሊያኒ

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአርመን ፓትርያርክ ያደረጉትን የመሬት ሽያጭ ስምምነት እንደሚያውቅ ገልጿል።

ነገር ግን ሚኒስቴሩ ስምምነቱ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምክንያት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅዱስ ጀምስ ገዳም ቅጥር ግቢ ውስጥ የተካሄደው ውይይት ከአርመኖች ህልውና ጋር የተያያዘ ነው።

ታሪካዊው ገዳም በአውሮፓውያኑ 1948 የተከሰተው የአረብ እና የእስራኤል ጦርነት ለአርመኖች መሸሸጊያ ስፍራ ሆኖ አገልግሏል። ስፍራው ትምህርት ቤት፣ ቤተ መጻህፍት፣ የእግር ኳስ ሜዳ እና ሌሎችንም የያዘ ትልቅ ገዳም ነው።

በአሁኑ ወቅት በአርመን ኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ቀሳውስቱ እና ነዋሪዎች መካከል የነበረው ግንኙነት ሻክሯል። ከሰሞኑም ማኅበረሰቡ ከዓለም አቀፍ የአርመን የሕግ ባለሙያዎች ጋር ጉዳዩ እንዴት መያዝ እንዳበት ተወያይተዋል።

አርመናዊው ጋሮ ሳንድሮኒ በሴራሚክስ ሱቁ አቅራቢያ ጎድጓዳ ሳህን በጌጣጌጥ እያሸበረቀ ነበር። ከሰሞኑም መጻኢው የአርመኖች ሁኔታ ስጋት ፈጥሮበት ሃሳብ ገብቶታል።

ከመቶ ዓመት በፊት የቱርኮች የዘር ማጥፋትን ሸሽተው ከመጡ ቤተሰቦችም ነው የተወለደው። ኢየሩሳሌምም ሲመጡ ድንቅ የሆነውን የአርመን ሸክላ ሥራንም ይዘው ነበር። ጋሮ አርመኖች ታዋቂ የሆኑበትን የሸክላ ሥራንም አስቀጥሏል።

አርመኖች መንፈሳዊ አገራችን ናት በሚሏት በዚህች ቅድስት ከተማ መሬት ለመግዛት ገንዘብ ያዋጡ እንደነበር ታሪክን ይጠቅሳል። እናም የአርመን ቤተ ክርስቲያን ይህን መሬት የመሸጥ መብት የላትም ይላል።

“የሚያበሳጨንም ጉዳይ ነው። ይህ መሬት የአርመናውያን ሕዝብ ነው። መሬቱ በኢየሩሳሌም ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት የአርመን ፓትርያርክ ንብረት አይደለም” ብሏል።

“ፓትርያርኩ ይህንን መሬት መጠበቅ እና መንከባከብ ነው የነበረባቸው” ሲልም ያስረዳል።