የሩሲያ ጥቃቶች 10 ሚሊዮን ዩክሬናውያንን ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አቆራረጠ

ሩሲያ ባካሄደቻቸው አዲስ የሚሳኤል ጥቃቶች መሠረተ ልማት ላይ ከደረሰወ ጉዳት በተጨማሪ 7 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል። 

የፎቶው ባለመብት, KYRYLO TYMOSHENKO/TELEGRAM

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ ባካሄደቻቸው አዲስ የሚሳኤል ጥቃቶች መሠረተ ልማት ላይ ከደረሰወ ጉዳት በተጨማሪ 7 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል። 
ታትሟል

ፕሬዝደንት ቭሎድሚየር ዜሌንስኪ በአዲስ መልክ የተጀመሩት የሰሞኑ የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃቶች 10 ሚሊዮን የዩክሬን ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲቋረጥባቸው ማድረጉን ተናገሩ።

“የኃይል አቅርቦቱን ወደነበረበት ለመመለስ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው” ብለዋል ዜለንስኪ በዕለታዊ መግለጫቸው።

ሩሲያ ባካሄደቻቸው አዲስ የሚሳኤል ጥቃቶች መሠረተ ልማት ላይ ከደረሰወ ጉዳት በተጨማሪ 7 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል። 

ዜሌንስኪ የዩክሬን አየር መከላከያ ስድስት ተምዝግዛጊ ሚሳኤሎችን እና አምስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ መጣሉን ጨምረው ተናግረዋል። 

የዩክሬን ጦር መኮንኖች እንዳሉት ከሆነ ተመትተው የወደቁት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ኢራን ሠራሽ ናቸው።

ትናንት ሐሙስ ኅዳር 8/2015 ዓ.ም. ሩሲያ በርካታ የኃይል ተቋማትን እና የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎችን በሚሳኤል ደብድባለች።

ሰባቱ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉት ዛፖሪዢያ ከተማ አቅራቢያ የመኖሪያ አፓርተመንታቸው በሚሳኤል ከተመታ በኋላ መሆኑን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

በምስራቅ ዩክሬን የሚገኝ የጋዝ ማምረቻ እና በዲኒፕሮ የሚገኝ የሚሳኤል ፋብሪካ የአዲሱ ዙር የሩሲያ ዒላማዎች መሆናቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በስፋት ከተቋረጠባቸው መካከል መዲናዋ ኪዬቭ፣ በምዕራብ ዩክሬን የምትገኘው ቪንያዲያ እና ኦዴሳ ከተሞች እንደሚገኙበት ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬም በድጋሚ አገሮች የአገሪቱን የአየር ክልል ጥበቃ ላይ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዜሌንስኪ አሁንም ሩሲያ ሰላም አትፈልግም ያሉ ሲሆን የሞስኮ ፍላጎት “በተቻለ አቅም ሁሉ ሕመም እና ስቃይ ማምጣት ብቻ ነው” ብለዋል።

ሞስኮ በበኩሏ ዩክሬን ለድርድር ለመቀመጥ ፍላጎት የላትም በማለት አዲስ የከፈተቻቸውን ጥቃቶች ምክንያታዊ ለማድረግ ሞክራለች።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩክሬን ጎረቤት በሆነችው ፖላንድ ሁለት ሚሳኤሎች መውደቃቸውን ተከትሎ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋትን ተፈጥሮ ነበር።

ዜሌንስኪ ከሁሉም ቀድመው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል በሆነችው ፖላንድ ላይ ሚሳኤል የተኮሰችው ሩሲያ ነች ያሉ ቢሆንም ዘግይቶ ግን ሚሳኤሎቹ የተተኮሱት በዩክሬን አየር ኃይል ነው ተብሏል።