ፔሎሲ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በኮንግረስ ከዴሞክራቶች መሪነታቸው እንደሚነሱ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዴሞክራቶችን ሲመሩ የቆዩት አንጋፋዋ ፖለቲከኛ ናንሲ ፔሎሲ ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ አስታወቁ።
የ82 ዓመቷ ፔሎስ በኮንግረሱ ተሰሚነት ያላቸው የዴሞክራት ፓርቲ አባል ከመሆናቸውም በላይ በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታሪክ የመጀመሪያዋ አፈ ጉባኤ ናቸው።
ፔሎሲ ካሊፎርኒያ ዲስትሪክን ወክለው በምክር ቤት አባልነታቸው የሚቀጥሉ ይሆናል።
የፔሎሲ ውሳኔ የተሰማው ሪፓብሊካኖች በአጋማሽ ምርጫ በሕዝብ ተካዮች ምክር ቤት የበላይነትን መያዛቸው ከተሰማ በኋላ ነው።
ሪፓብሊካኑ ኬቪን ማካርቲ በፓርቲያቸው የምክር ቤቱ ዕጩ ሆነው በመመረጣቸው ፔሎሲን የመተካት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል።
ፔሎሲ በቀጣይ ወር በምክር ቤቱ የዴሞክራቶች መሪ ሆነው ለመምረጥ እንደማይወዳደሩ ተናግረዋል።
“በምክር ቤት ዴሞክራቶችን የሚመራ የአዲስ ትውልድ ሰዓት ደርሷል” ብለዋል ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ባቀረቡት መግለጫ።
ፔሎሲ እስከ አውሮፓውያኑ 2023 መጀመሪያ ድረስ አፈ ጉባኤ ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ በአዲስ የኮንግረስ አባላት ሲተካ ፔሎስ እአአ በ1987 የተረከቡትን ስልጣን ያስረክባሉ።
የኒው ዮርክ ኮንግረስ አባል ሃኪም ጄፍሪስ በምክር ቤቱ የዴሞክራት መሪ ሆነው ሊመረጡ ይችላሉ የተባለ ሲሆንም ይህም ዴሞክራቶችን በምክር ቤት በመምራት የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊ ያደርጋቸዋል።
በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ከምክትል ፕሬዝዳንት ቀጥሎ ተተኪ ፕሬዝዳንት እንደሚሆን በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ተመልክቷል።
የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ አንቶኒ ዙርከር ፔሎሲ አፈጉባኤ ሳሉ የተቀማጭ ፕሬዝዳንት አጀንዳዎችን በማጠናከር ወይም ውድቅ እንዲሆኑ በማድረግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ነበሩ ይላል።
አንቶኒ እንደሚለው ፔሎሲ ብቁ መሆናቸው የተመሰከረላቸው መሪ ሆነው በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ይሰፍራል። በምክር ቤት ቆይታቸው ፔሎሲ በተለይ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመን ጎልተው ወጥተው ነበር።












