ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጎንሳሎ ራሞስ ወደ ዩናይትድ፤ ቪክተር ኦሲምሄን ወደ ቼልሲ?
ማንቸስትር ዩናይትድ የቤንፊካውን ፖርቹጋላዊ አጥቂ ለማስፈረም እየተንደረደረ ነው ሲል ጎል ዘግቧል።
የ21 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የፊት መስመር ተጫዋች ጎንሳሎ ራሞስን ማስፈረም የሚፈልግ ክለብ ቢያንስ 120 ሚሊዮን ዩሮ ለቤንፊካ ማቅረብ ይኖርበታል።
የ18 ዓመቱ አጥቂ ኢቫን ፈርጉሰን ከማንቸስተር ዩናይትድ የሚመጣለትን የፊርማ ጥያቄ ውድቅ ያደርጋል ሲል ሰን አስነብቧል።
የሪፐብሊክ አየርላንድ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ወጣቱ አጥቂ ለብራይተን የሚጫወት ሲሆን አሁን ባለበት ቤት መቆየቱ እንደሚጠቅመው ተናግሯል።
ፈርጉሰን ለማንቸስተር ዩናይትድ ልዩ ፍቅር እንዳለው በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።
የዴቪድ ዴ ሂያን ምትክ እያሰሰ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ የብሬንተፈርዱን ስፔናዊ በረኛ ዴቪድ ራያን ማስፈረም እንደሚሻ ጊቭ ሚ ስፖርት ፅፏል።
የ27 ዓመቱ ዴቪድ ራያ የ32 ዓመቱ ዴቪድ ዴ ሂያ ምትክ ይሆናል ተብሎ ተጠብቋል።
ደቡብ ኮሪያዊው የናፖሊ ተከላካይ ኪም ሚን-ጄ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ስሙ ቢያያዝም እሱ ግን ትኩረቱ ከጣሊያኑ ክለብ ጋር መሆኑን ሜይል አስነብቧል።
ቼልሲ፤ ለናፖሊው ናይጄሪያዊ አጥቂ ቪክተር ኦሲምሄን 100 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ዝግጁ ነው ይላል የፉትቦል ኢንሳይደር ዘገባ።
ሰማያዊዎቹ፤ የ31 ዓመቱን ፈረንሳዊ አማካይ ንጎሎ ካንቴ ውል በሁለት ዓመት ለማራዘም መዘጋጀታቸውን የዝውውር ወሬዎች አውራው ፋብሪዚዮ ሮማኖ ገልጧል።
የቀድሞው የቼልሲ አሠልጣኝ የነበሩት ጀርመናዊው ቶማስ ቱኽል እንግሊዛዊውን አሠልጣኝ አንተኒ ባሪ ወደ ባየርን ሙኒክ ለመውሰድ መመኮራቸው ሰማያዊዎቹን አስከፍቷል የሚል ዘገባ ያወጣው ደግሞ ቴሌግራፍ ነው።
ፉትቦል ኢንሳይደር፤ አርሰናል ኢኳዶራዊውን አማካይ ሞይሰስ ካይሴዶ በሚቀጥለው ክረምት ለማስፈረም ይሻል ሲል ፅፏል።
መድፈኞቹ ባለፈው የጥር ወር የዝውውር መስኮት የ21 ዓመቱ ካይሴዶን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
አስተን ቪላ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ እና ብራይተን፤ አሌክስ ኦክስሌድ-ቻምበርሌይንን ለማስፈረም እየተፎካከሩ ነው።
ሜይል እንደዘገበው ቻምበርሌይን ከሊቨርፑል ጋር ያለው ውል በሚቀጥለው ክረምት ይጠናቀቃል።
ስፖርት የተሰኘው ደረ-ገፅ እንደፃፈው የማንቸስተር ሲቲው አማካይ ኢካይ ጉንዶጋን ባርሴሎናን መቀላቀል ይፈልጋል።
የ32 ዓመቱ ጀርመናዊ በሚቀጥለው ክረምት ከሲቲ ጋር የገባው ውል ሲጠናቀቅ ወደ ካታሎኑ ክለብ ማቅናት እንደሚሻ ተሰምቷል።
ቼልሲና አርሰናል የቤልጂዬሙን አማካይ አማዶ ኦናና ለማስፈረም እንደሚሹ ፊቻየስ የተሰኘው የስፔን ጋዜጣ ዘግቧል።
የ21 ዓመቱ አማካይ ኦናና በመጀመሪያው ዓመት የኤቨርተን ቆይታው ብዙዎችን ያስደመመ ብቃት እያሳየ ይገኛል።