የሃውስ ኦፍ ካርድስ ተዋናይ ኬቨን ስፔሲ በወሲብ ጥቃት ተከሰሰ

ኬቨን ስፔሲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

 ሀውስ ኦፍ ካርድስ በተሰኘው ተከታታይ ፊልም ላይ ፍራንክ አንደርውድ በሚል ገፀ ባህርይ የሚታወቀው ታዋቂው አሜሪካዊ ተዋናይ ኬቨን ስፔሲ ሶስት ወንዶች ላይ በተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች መከሰሱን የሜትሮፖሊታን ፖሊስ አረጋግጧል።

የ62 አመቱ ተዋናይ በአራት ወሲባዊ ጥቃቶችም በዛሬው ዕለት በእንግሊዙ ዌስት ሚኒስትር ፍርድ ቤት ይቀርባል።

ክሱ በሜትሮፖሊታን ፖሊስ የተሰበሰበውን ማስረጃ ግምገማ ተከትሎ ነው።

የአሁኑ ክስም በአውሮፓውያኑ 2005 በለንደን በአንድ ወንድ ላይ ሁለት ጊዜ ወሲባዊ ጥቃቶችን አድርሷል የሚል ክስን አካቷል።

በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2008 በለንደን በአሁኑ ወቅት በ30ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወንድ ላይ ያለፈቃዱ ወሲባዊ ተግባር ፈፅሞበታል በሚል ወንጀል ተከሷል።

ሌላኛው ክስ በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በ30ዎቹ እድሜ ላይ የሚገኝ ግለሰብ ላይ በአውሮፓውያኑ 2013 ግላስተርሻየር ከተማ ውስጥ የመድፈር ወንጀል ፈፅሟል የሚል ነው።

ተዋናዩ ከዚህ ቀደም ቢሆን ለሚቀርብበት ክስ በፈቃደኝነት መልስ ለመስጠት በዩናይትድ ኪንግድም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተናግሯል።

አሜሪካን ቢውቲ በሚለው ፊልሙ ዝነኝነት ያተረፈው ተዋናዩ ባለፈው ወር ጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ በተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቀርቦ ንፁህነቱን እንደሚያረጋግጥ ተናግሯል።

ኬቨን ስፔሲ የሁለት ጊዜ የኦስካር አሸናፊ ሲሆን እንደ ሰቨን፣ ኤልኤ ኮንፊደንሻንል፣ ቤቢ ድራይቨር እንዲሁም በኔትፍሊክስ ተከታታይ ፊልም ሃውስ ኦፍ ካርድስ ባሉ ፊልሞች ላይ ተውኗል።

በኔትፍሊክስ በሚተላለፈው ተከታታይ ፊልም ከስድስተኛው ክፍል ቀድሞ ከመገደሉ በፊት ፍራንክ አንደርውድ የተሰኘው ገፀባህርይ በሴረኛነቱ የሚታወቅ ሲሆን ጋዜጠኛንና ፖለቲከኛን ገድሏል።

በሆሊውድ ውስጥ በይፋ አግባብ ያልሆነ ተግባራትን በመፈጸም ክስ ከቀረበባቸው ጥቂት ተዋናዮች መካከል ስፔሲ አንዱ ሲሆን በተመሳሳይም ሃርቬይ ዊንስተን ላይ የቀረበቡት ክሶች ይታወሳሉ።

የሃርቬይ ክስን ተከትሎ 'ሚቱ' የተሰኘ ከፍተኛ የጸረ ጸታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ መነሳቱ ይታወሳል። ሃርቬይ የቀረበበትን ክሶች ተከትሎ ኔት ፍሌክስም ሆነ ፊልሙን የሚሰራው ስቱዲዮ ከፊልሙ ስክሪፕት ላይ ያለው የመሪ ተዋናይነት በሌላ እንዲተካ ድርሰቱ እንዲቀየር አድርገዋል።