አምነስቲ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ከእስር እንዲፈታ የሚጠይቅ ዘመቻ ጀመረ

ታትሟል

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚጻፍ ደብዳቤ ከአራት ወራት በፊት የታሰረው ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ከእስር እንዲፈታ የሚጠይቅ ዘመቻ ጀመረ።

“የኢትዮ ኒውስ” የዩትዩብ መገናኛ ብዙኃን መሥራች የሆነው በላይ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው ከአራት ወራት በፊት ኅዳር 3/2016 ዓ.ም. ነበር።

በላይ ማናዬ በቁጥጥር ሥራ ከዋለ ወራት ቢቆጠሩም ፍርድ ቤት አልቀረበም እንዲሁም ስለታሰረበት ምክንያት ያልተገለጸ ሲሆን ምርመራ አልተደረገበትም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የበላይ ማናዬ የታሰረው፤ “በአማራ ክልል ያለውን ግጭት አስመልክቶ በሠራው ዘገባ ነው ተብሎ ቢታመንም የታሰረበት ምክንያት አልተገለጸለትም” ብሏል።

የጋዜጠኛው በላይ ማናዬ ባለቤት በላይነሽ ንጋቱ ወደ አዋሽ አርባ ከተወሰደ በኋላ በአካል እንዳላገኘችው ለቢቢሲ ተናግራለች።

በላይነሽ “ሦስት ወር አልፎታል በአካልም አላገኘሁትም፤ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ አንዳለም አላውቅም” ብላለች።

አራት ኪሎ ከሚገኘው ቢሮው ወደ መኖሪያ ቤቱ በማቅናት ላይ እያለ ሲቪል እና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች መያዙን ባለቤቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በላይ ማናዬ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ያሉትን 25 ቀናት ያሳለፈው ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደነበር በላይነሽ ገልጻለች።

ከኅዳር 28/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በአፋር ክልል ወደ ሚገኘው የአዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከል ተዘዋውሯል።

በላይ ማናዬ ወደ አዋሽ አርባ ከተዘዋወወረ በኋላ ባሉት ሦስር ወራት ግንኙታቸው በስልክ ብቻ መወሰኑን ባለቤቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ግጭት ምላሽ “ሌሎች ሰባት ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ አስሮ ጥቂቶችንም ከእስር ፈትቷል” ሲል አክሏል።

አምነስቲ ዘመቻውን አስመልክቶ በድረ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት፤ “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ካሰሯቸው ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙትን በላይ ማናዬን እና ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መፍታት አለባቸው” ሲል አሳስቧል።

የመብት ተቆርቋሪው አክሎም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ፕሬሱን እና ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን ተጠቅመውበታል” ሲል ከሷል።

አምንስቲ የአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ በአውሎ ንፋስ በተመታበት ወቅት በላይ ማናዬን ጭምሮ በሌሎች ታሳሪዎች ላይ ጉዳት ቢደርስባቸውም፣ በላይ ለደረሰበት ጉዳት የህክምና እርዳታ ሳያገኝ ቀርቷል ብሏል።

የጋዜጠኛው ባለቤት በላይነሽ ንጋቱም በተመሳሳይ ከአውሎ ንፋሱ አደጋ ሦስት ቀናት በኋላ በስልክ እንዳገኘችው ገልጻ በጊዜው “ህክምና አላገኘንም” ማለቱን ለቢቢሲ ተናግራለች።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ባስጀመረው ዘመቻ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚጻፈውን ደብዳቤ ቅጂ ረቂቅ በድረ ገጹ ላይ አጋርቷል።

ተቋሙ ሰዎች በድረ ገጹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጋራውን የደብዳቤ ቅጂ ወይም በራሳቸው ቃላት የጻፉትን ድብዳቤ ተጠቅመው ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ ጠይቋል።